Google search engine

“እኔ ከኢትዮጵያ ተጨዋቾች የምለየው የተጨዋች ጓደኛና ግሩፕ ስለሌለኝ ነው”ምንያህል ተሾመ

በተለይ ለሊግ ስፖርት

በአለምሠገድ ሰይፉ

እንዝርት ነው ይሉታል በኳስ ክህሎቱና ጨዋታ አዋቂነቱ፤ ከኢትዮጵያ ቡና የቢ ቡድን ተነስቶ በሃገሪቱ ካሉት ታላላቅ ክለቦች ጋር በመሰለፍ ዋንጫ ለማንሳት የታደለው ምን ያህል ተሾመ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ክለብ አልባ ሆኖ ለመቀመጥ ተገዷል፡፡  “ እኛ ተጨዋቾች መብታችንን ለማስከበር ጥግ ድረስ መሄድ አለብን” የሚለው ይኸው ተጨዋች እስከሁን ክለብ ያልያዘበትን ምስጢርም አጫውቶናል፤ ልበ ሙሉው ምን ያህል ተሾመ “አዎ! ኳስ መጫወት እችላለሁ፡፡ ችሎታም አለኝ” ሲል ይናገራል፡፡ “እኔ በችሎታዬ እንጂ ግሩፕ አደራጅቼ ክለብ መያዝ ፈፅሞ አልሻም” የሚለው ምን ያህል ለዛሬው የሊግ ስፖርት ጋዜጣና የዌብሳይት ተከታታዮቻችን ጣፋጭ የሆነ ቆይታ አድርጓል፤ (በነገራችን ላይ አዲሱ የዌብሳይት ገፃችንን ለማስተዋወቅ ያህል WWW.leaguesport.net መሆኑን በአክብሮት እንገልፃለን)

ሊግ፡- በአሁኑ ጊዜ ምንያህል ከስፖርቱ አካባቢ የጠፋበት ምክንያት ምንድነው ?

ምንያህል፡- ዋናው ነጥብ ከወልድያ ስፖርት ክለብ ጋር ክርክር ላይ ስለነበርኩኝ ነው፡፡

ሊግ፡- ክርክር ስትል…?

ምንያህል፡- መልቀቂያ ስላልወሰድኩና የሁለት ወር ደመወዝ እነርሱ ጋር ይቀረኝ ስለነበር ወደሌላ ክለብ መዛወር አልቻልኩም፡፡ ከዚህ ባሻገር በአሁኑ ጊዜ በሃገሪቱ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር እና ከቤተሰብም መራቅ ስላልፈለግኩ ከአዲስ አበባ ወጥቼ መጫወት ምርጫዬ አልነበረም፡፡

ሊግ፡-  ለምን?

ምንያህል፡- ያው ሁሉን ነገር የምታየው ነው፤ በተለያዩ ክልሎች እየተፈጠረ ያለው ብጥብጥ ተረጋግተህ ኳስ ለመጫወት የሚመች አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ስታየው የኳሱ መንፈስ እየተለወጠ በመሄዱ ክለብ ይዞ ለመጫወት ዘግይቻለሁ፡፡

ሊግ፡- ከወልድያ ጋር ያለው አለመግባባት አሁንስ መፍትሄ አግኝቷል?

ምንያህል፡- አዎ፡፡ ሁሉም ነገር በሚገባ መፍትሄ አግኝቷል፡፡ መልቀቅቂያዬንና የሁለት ወር  ደመወዜንም ወስጃለሁ፡፡ ያው አንተም እንደምታውቀው የኢትዮጵያ ተጨዋቾች መብታቸውን በማስከበር ረገድ ችግር አለባቸው፡፡ እኔ ግን የፉትቦል ፌዴሬሽኑን ህግና መመሪያ በሚገባ ስለማውቅ ተካስሼ መልቀቂያውንም ደመወዜንም ተቀብያለሁ፡፡

ሊግ፡- ካለክለብ መቀመጡ ትንሽ አይከብድም?

ምንያህል፡- በዚህ ሰአት መጫወት እየቻልኩ መጫወት አለመቻሌ እንደሰው በመጠኑም ቢሆን ሞራሌ እንዲነካ ያደርገዋል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የግዴታ መጫወት አለብኝ ብዬ እሳት ውስጥ መግባት አልፈለግኩም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጵያ ኳስ በጣም እየከበደ ነው የሄደው፡፡

ሊግ፡- አንተ ልምድ ያለህ ተጨዋች ከመሆንህ አንፃር ከወልድያ ጋር መለያየትህን ተከትሎ ክለቦች ጥሪ አላደረጉልህም?

ምንያህል፡- በመጀመሪያ ጥሪ ያቀረበልኝ የመቀሌ ስፖርት ክለብ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ ከዚህ ሳልርቅ አዲስ አበባ ላይ ነው መጫወት የፈለግኩት፡፡ በመሆኑም ከመቀሌ ቀርቦልኝ የነበረውን ጥሪ ችላ ብያለሁ፡፡ በዚህ ረገድ ለተፈጠረው ክፍተት የራሴው ጥፋት ነው፡፡ እንደምታውቀው ደግሞ የአዲስ አበባ ቡድኖች ሶስት ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ለቅዱስ ጊዮርጊስና ለኢትዮጵያ ቡና ከአሁን ቀደም የተጫወትኩ በመሆኑ ተመልሶ እነርሱ ጋር የመግባት ፍላጎቱ የለኝም፡፡ እናም አንድ የሚቀረው መከላከያ ነው፡፡ ይህ ክለብ ደግሞ የራሱን ስኳድ ቀደም ብሎ የያዘ በመሆኑና እንደተጨዋች ገፍቶ ሄዶ መጠየቅ ትንሽ ስለሚከብድ በዛ የተነሳ ክለብ ሳልይዝ ለመቆየት ተገድጃለሁ፡፡

ሊግ፡- በተጠበቀው መልኩ ክለቦች ለአንተ የዝውውር ጥያቄ አለማቅረባቸው ከአቅም መውረድ ጋር ሊያያዝ ይችላል?

ምንያህል፡- በፍፁም! እንደዛ አላስብም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እውነታ እኮ አንድ አሰልጣኝ ከወደደህ አሊያም ለእርሱ አጨዋወት ከተመቸህ ክለብ ትይዛለህ፡፡ በተረፈ ስለእኔ አቋም መውረድና ከፍ ማለቱን ለመናገር እኔ ስጫወት ማየት አለበት፡፡ ከእዚህ በተረፈ ዝም ብለህ በመተዋወቅ ብቻ የምትሰራ ከሆነ አደጋ አለው፡፡ በተረፈ የእኔ አቋም በፊትም የምታውቀውና ምንም አይነት የመዋዥቅ ነገር የሌለበት ነው፡፡

ሊግ፡- የክለቦቹ ዝምታ ከበዛ ያለክለብ መቀመጥህ ነዋ?

ምንያህል፡- እንደዛ እንኳን አይሆንም፡፡ ሁሉም ስኳዴን አሟልቼ እየተጫወትኩ ነዉ እያሉ ነው፡፡ በዛ ላይ ምርጥ የተባሉት ቲሞችም ወርደዋል፡፡ ከዚህ አንፃር በሁለተኛው ዙር ላይ መጫወት የምችልበት ሁኔታ አለ፡፡ ለፌዴሬሽኑ ባስገባሁት ደብዳቤና በተሰጠኝ ምላሽም በማንኛውም ጊዜ መጫወት እንደምችል ስለተፈቀደልኝ በቅርቡ የማርፍበትን ክለብ በጋራ የምናየው ይሆናል፡፡

ሊግ፡- ቀደም ብለህ እንደተናገርከው ለአዲስ አበባ ክለቦች የመጫወትህ ተስፋ በሩ ዝግ በመሆኑ አሁንስ ክልሎችን ማማተር አልጀመርክም?

ምንያህል፡- የጀመርኩትና እየጨረስኩ ያለው ክለብ አለ፡፡ ማነው ብለህ ግን ብትጠይቀኝ አልነግርህም (ቃለ-ምልልሱ የተሰራው ሃሙስ ነው) በዚህ አጭር ሁለትና ሶስት ቀናት ውስጥ የሚያልቅ ክለብ ስላለ ሄጄ መጫወቴ አይቀርም፡፡ እኔ ግን ሁሌም የሚያሳስበኝ ነገር ቦታው ላይ ያለው ሰላም የተረጋጋ መሆኑ ላይ ነው፡፡ ወልድያ ላይ ካየሁት ፈተና አንፃር ድጋሚ የዚህ አይነት ነገር እንዲገጥመኝ ፈፅሞ አልሻም፡፡ ነገር ግን ክለብ ገብቼ እንደምጫወት ጥርጥር እንዳይገባችሁ፡፡

ሊግ፡- ወልድያ በነበርክበት ጊዜ ገጥሞኛል የምትለው አስቸጋሪ ሁኔታ የቱ ነው?

ምንያህል፡- የጎላ ችግር መፈጠሩን ለመናገር የግዴታ እኔ ላይ ብቻ እስኪደርስ መጠበቅ አይኖርብኝም፡፡ በእነ ብሩክና በአሰልጣኝ ዘማሪያም ላይ የደረሰው ችግር በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ከዚህ አልፎ ተርፎም ዳኛው ላይ የደረሰው ችግር የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በጣም የሚገርመው ነገር እዛ በነበረው ብጥብጥ ላይ እኔ አልነበርኩም፤ ነገር ግን የቅጣቱ ደብዳቤ ሲመጣ “ፀብን በማነሳሳት” ይላል፡፡ እኔ አዲስ አበባ ሆኜ እንዴት ነው ፀብ የማነሳሳው? ይህ ነገር ፈፅሞ ሞራል የሚነካ ድርጊት ነው፡፡ በፀቡ ላይ ተሳትፌ ቢሆን እሺ እኔ እዚህ አዲስ አበባ ተቀምጪ የመጣው የስም ዝርዝር ላይ እኔም መካተቴ ከፍተኛ የሆነ የሞራል ውድቀት ነው የፈጠረብኝ፡፡

ሊግ፡- በእግር ኳስ ህይወትህ የእኔን ትክክለኛ ብቃት ተረድቷል የምትለው አሰልጣኝ ማነው?

ምንያህል፡- ጥሩ ጊዜያትን አሳልፌአለሁ፡፡ ቡና በነበርኩበት ጊዜ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ፣ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ደግሞ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እንዲሁም ደደቢትም ነፍሱን ይማረውና በንጉሴ ደስታና ቅዱስ ጊዮርጊስም በነበርኩበት ወቅት ጣፋጭ የሚባል ጊዜያቶችን አሳልፈያሁ፡፡ ከዚህ አንፃር አንዱን ነጥዬ እገሌ ነው ለማለት እቸገራለሁ፡፡ ከላይ የጠቀስኩኳቸው አሰልጣኞች የእኔን አቅም ከነባህሪዬ ተረድተው ስላሰለጠኑኝ ላቅ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡   

ሊግ፡- የውጭ አሰልጣኞችንስ እንዴት አየሃቸው?

ምንያህል፡- እንደምሳሌነት ቅዱስ ጊዮርጊስን ባነሳ እዚህ ክለብ ስትጫወት የሚመጡት አብዛኛዎቹ የውጪ አገር አሰልጣኞች የሚፈልጉት የሚያቀርቡትን ታክቲክ እንድትተገብርላቸው ነው፡፡ እነርሱ ከእኛ አሰልጣኞች የሚለዩት የሚፈልጉትን ታክቲክ በማስተግበር ላይ ነው እንጂ የአንተን አቅምና ችሎታ በመለወጡ ላይ ብዙም አይጨነቁም፡፡ ከዚህ አንፃር ከውጪ አገር አሰልጣኞች ብዙም የተለየ ነገር አግኝቻለሁ ለማለት አልደፍርም፡፡

ሊግ፡- ምን ያህል ለራሱ ከፍተኛ ግምት ይሰጣል፤ ጉረኛ ነው፤ እኔ እችላለሁ ይላል ይሉሃል እውነት ነው?

ምንያህል፡- (ሳቅ…) እንዴ! እችላለሁ የማይል ተጨዋች እስቲ ማነው? ሲጀመር አንድ ተጨዋች ችሎታ ስላለው እኮ ነው ክለብ የሚገባው፡፡ አልችልም ብዬ ወደ ሜዳ ከገባው ቀድሜ በስነ-ልቦና ተሸንፌያለሁ ማለት ነው፡፡ እግር ኳስ በተፈጥሮው በራስህ የዳበረ ኮንፊደንስ እንዲኖርህ ያስገድዳል፡፡ እችላለሁ ብለህ ማውራት ብቻ ሳይሆን መቻልህን ሜዳ ላይ በተግባር ማሳየት  መቻል ይጠበቅብሃል፡፡

ሊግ፡- ካሉት የአገራችን ተጨዋቾች ጋር ራስህን እንዴት ታነፃፅረዋለህ?

ምንያህል፡- እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነው የምጫወተው፡፡ ማንኛውም ተጨዋች ለብሄራዊ ቡድን ተሰልፎ የሚጫወተው ስለቻለ ነው፡፡ ያ ልጅ ባይችል ኖሮ የአገሩን ባንዲራ ለብሶ አይጫወትም ነበር፡፡

ሊግ፡- ምን ያህል የቀድሞ ብቃቱን እያሳየ አይደለም የሚል ቅሬታ ይቀርብብሃል፤ ይሄን ጥያቄ እንዴት ትመልሳለህ?

ምንያህል፡- በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ በነበረኝ የመጨረሻው አመት ቆይታዬ ግማሹ ደጋፊ ገብቼ እንድጫወት ይፈልጋል፤ የተቀረው ደግሞ አይፈልግም፤ ሲጀመር በዛን ወቅት የተቀመጥኩት በጉዳት ምክንያት ነው፡፡ ለአራትና አምስት ወራት ያህል በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ለመራቅ ተገድጃለሁ፤ እኔን ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ተጨዋቾች የሚለየኝ ነገር ካመመኝ አመመኝ ነው እንጂ ከህመሜ ሳላገግም መጫወት አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም እዚህ ሃገር ያሉ ክለቦች ሁሉ ጉልበትህን መጠቀም ነው የሚፈልጉት፡፡ ከነጉዳትህም ቢሆን ገብተህ እንድታገለግላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ጉዳትህን ደብቀህ ተጫወትክ ማለት ደግሞ የከፋ ጉዳት ማምጣት ነው፡፡ ዘንድሮ ልብ ብለህ ከሆነ ድጋፍ ራሱ በግሩፕ ሆኗል፡፡ ይህ ደግሞ ለስፖርቱ አደጋ ነው፡፡

ሊግ፡-  ባህሪህ እንዴት ይገለፃል?

ምንያህል፡- እኔ ከኢትዮጵያ ተጨዋቾች ለየት የሚያደርገኝ ነገር ኳስ ተጨዋች ጓደኛ የለኝም፡፡ አሊያም ግሩፕ ይዤ አልንቀሳቀስም፡፡ በእኔ የጨዋታ የህይወት ዘመን ያለህን የተጨዋች ጓደኛ ጥራልኝ ብትለኝ በጣም የምቀርበው በሃይሉ አሰፋን (ቱሳ) ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ከማንም ጋር የምገናኝበት ሁኔታ የለም፡፡ ከቱሳ ጋርም ቢሆን አጋጣሚ ወደኛ ሰፈር ሲመጣ ነው የምንገናኘው፡፡ ከዚህ በተረፈ ከሰፈር ወጥቼ ከተጨዋቾች ጋር የምገናኝበት ሁኔታ የለም፡፡ ያ ደግሞ እኔን ጎደቶኛል፡፡ ወደድክም ጠላህም እግር ኳሱ አካባቢ ግሩፕ ተፈጥሮአል፡፡ ሁሉም የየራሱ ግሩፕ አለው፡፡ እኔ ግን የዚህ አይነት ህይወት የለኝም፡፡ ከስራዬ በኋላ በጣም የምወዳቸው ቤተሰቦችና ልጆች አሉኝ ወደዛ ነው የምሄደው፡፡ ይህን ስልህ ሌላው ቤተሰብ የለውም እያልኩ አይደለም፤ ሆኖም ግን እነርሱ የሚገናኙበት ፓርት አላቸው፡፡ እኔ ደግሞ እንደዛ አልፈልግም፡፡ ተጨዋቾች ካላቸው  ግሩፕ በተጨማሪ በሌላ በኩል ደግሞ ከደጋፊውም ጋር በቅርበት ይገናኛሉ፡፡ እኔ ደግሞ የዚህ አይነቱን ህይወት አልፈልገውም፡፡

ሊግ፡- ይህ ነገር ጎድቶኛል ብለህ ካሰብክ በቀጣይነት ባህሪህን ለመቀየር ታስባለህ?

ምንያህል፡- በፍፁም አልቀይርም፤ በዚህ አይነት ህይወት ውስጥ ነው የምቀጥለው፡፡ ይህን በማድረጌ ምንም ያጣሁት ነገር የለም፤ ህይወቴ የተሟላ ነው፡፡ ግዴታ ከኳስ ተጨዋቾች ጋር ዝምድና ፍጠር የሚል ህግ የለም፤ ሜዳና ትሬኒንግ ላይ ትገናኛለህ በቃ ያልቃል፡፡ በተረፈ ማህበራዊ ህይወት አስገድዶህ ልትገናኝ ትችላለህ፡፡ ከዛ ውጪ ሁሌ እየተገናኘህ ላይፍ ይከብዳል፡፡ እዚህ ያንተን ትልቅ ሃላፊነት የሚጠብቁ ልጆች አሉ፡፡ ለእነርሱ በቂ ጊዜ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ እኔም እንደዛ ባለማድረጌ ያን ያህል ተጎድቻለሁ ብዬ አላስብም፡፡

ሊግ፡- ምንያህል ያለውን ጥሩ ችሎታ መደበቅ ባይቻልም አብዝቶ መዝናናትን ያዘወትራል ስለሚባለውስ ነገር?

ምን ያህል፡- መዝናናት ስትል ምን አይነት መዝናናት ነው? መሸታና ጭፈራ ቤት ከሆነ ፈፅሞ እንዳታስበው የእኔን ምስክርነት ተወውና፤ ምንያህልን እዚህ ቦታ አይተነዋል የሚል ሰው ካለ በጣም ይገርመኛል፡፡ ትዳር ከመሰረትኩ አምስት አመት ሆኖኛል፡፡ እናም ትዳር መስርቶና ልጅ አፍርቶ መዝናናት በእጅጉ ይከብዳል፡፡ ልዝናና በምችልበት ሰአት ወይ ከባለቤቴ ጋር አሊያም ከጓደኞቼ ጋር ልዝናና እችላለሁ፡፡ ሆኖም ግን በእርግጠኝነት የምነግርህ እኔ የመሸታ ቤት ህይወት ፈፅሞ የለኝም፡፡

ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ እያለህ ቅጣት ተጥሎብህ ከቢ ቡድን ጋር እንድትሰራ የተገደድክበት ሁኔታ ነበር፤ ምክንያቱ ምንድነው?

ምንያህል፡- ችግሩ የተፈጠረው ወልድያ ላይ ስንጫወት ነው፤ በወቅቱ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ይመራ የነበረው ብራዚላዊው ዶ ሳንቶስ የሚባለው ነው፡፡ 35ኛው ደቂቃ ላይ ተነስ አለኝ፡፡ አሟሙቄም ሊያስገባኝ አልቻለም፡፡ ቡድናችን ደግሞ ጨዋታውን 3ለ0 እየመራ ነበር፡፡ እናም ግጥሚያው ሊጠናቀቅ ሶስት ደቂቃ ሲቀረው ግባ አለኝ፡፡ እኔም ፈቃደኛ አልሆንኩም፡፡ እንደባለሙያ እሱ ትክክል ቢሆንም እኔ ግን ያን ያህል ሰአት አሟሙቀህ ሞራልህ ወድቆና በዛ ላይ ቲምህ በሰፊ ውጤት እየመራ መግባቱ ጥቅም እንደሌለው ስለገባኝ መግባት እንደማልፈልግ ነገርኩት፡፡ ከዛ በሚቀጥለው ትሬኒንግ ላይ ስመጣ ዶ ሳንቶስ “አግጄሀለሁ” አለኝ፤ ወደ ቢሮም ስሄድ ተቀጥተሃል አሉኝና  ከቢ ቡድን ጋር ሰርቼ ዳግም ወደ ዋናው ቡድን ተመልሻለሁ፡፡

ሊግ፡- ዳግም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስና ቡና የመመለሱ አጋጣሚ ቢፈጠር የት ትገባለህ?

ምንያህል፡- ምን አለ መሰለህ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁና አስቸጋሪው ነገር አንድ ክለብ ተጫውተህ በድጋሚ ስትመለስ በጣም ተጨብጭቦልህ ከወጣህ በሚቀጥለው ትንሽ ስህተት ብትሰራ ስድብ አሊያም ትችት አለው፡፡ ይሄን የማላደርገው ትችትን ላለመቋቋም ሳይሆን በቃ በነበርኩበት ክለብ አንድ ጥሩ ነገር ከሰራህ ታሪክ ሆኖ ነው መቅረት ያለበት፡፡ እናም ወደነበርኩበት ክለቦች ከመመለስ ይልቅ በአዲስ ክለብ ሌላ አዲስ ታሪክ ነው መስራት የምፈልገው፡፡ እናም አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስም ሆነ ወደ ኢትዮጵያ ቡና በድጋሚ የመመለሱ ፍላጎት የለኝም፡፡        

ሊግ፡- በሊጉ ላይና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ከመጫወትህ አንፃር አንዳንዶች የምንያህል የኳስ ዘመን አብቅቷል ኳስ ማቆም አለበት የሚል አስተያየት ይሰነዝራሉ በዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ?

ምንያህል፡- ደጋፊው የመሰለውንና ያመነበትን ነገር የመወሰን መብት አለው፡፡ አሁን ባለው የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የእኔ በጣም ሰኒየር የሆኑ ተጨዋቾች አሁን ድረስ  በፕሪምየር ሊጉ ላይ እየተጫወቱ ነው፤ እናም እነዚህ ታላላቆቼ እያሉ እኔ ኳስ አቆማለሁ የሚል ግምት ፈፅም የለኝም፡፡ ሰው የፈለገውን መወሰን ይችላል፡፡ ወደኋላ መለስ ብለህ ካሰብክ ግን የእኔ ታላላቆች ፕሪምየር ሊግ ላይ ሲጫወቱ እኔ ቢ እንኳን መጫወት ባልጀመርኩበት ሁኔታ አሁን ድረስ እነርሱ ፕሪምየር ሊግ እየተጫወቱ ሳለ እኔ ጫማዬን የምሰቅልበት አንዳችም ምክንያት አይኖርም፡፡

ሊና፡- በአሁኑ ሰአት የተጨዋቾች ወርሃዊ ክፍያ ጣራ እየነካ ነው ይሄን እውነት ተከትሎ ሁለት የተለያዩ ሃሳቦች ይስተናገዳሉ፡፡ አንተስ እንደተጨዋች በዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ?

ምንያህል፡- እንደተጨዋች ስለጠየቅከኝ እኔም እንደዚህ እንዲከፈለኝ እፈልጋለሁ፡፡ በሌላ አንፃር ህዝቡ ይሄን ክፍያ የሚቃወመው ለተጨዋቾች የሚከፈለው ወርሃዊ ክፍያና ኳሱ እኩል ባለመሄዳቸው ነው፡፡ የተወሰነ ጊዜ እግር ኳሳችን በጣም ተሟሙቆ ነበር፡፡ አሁን ያለው ክፍያ  በዛን ጊዜ ቢሆን በጣም ጥሩ ነበር፡፡ በጣም የሚገርምህ ነገር ያኔ ለብሄራዊ ቡድን ተመርጬ ወደናይጄሪያ ተጉዘን ስንጫወት የእኔ ወርሃዊ ደመወዝ 1700 ብር ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ጣራው 250 ሺህ ብር ደርሷል፡፡ እውነት ለመናገር ክፍያውና ኳሱ በጣም ተራርቀዋል፡፡
ሊግ፡- ብዙ ጊዜ ምንያህል ታክቲካል ዲሲፕሊንድ አይደለም እያሉ ጨዋታ ላይ ግን ያሰልፉሃል፤ እውነት አንተ የተሰጠህን ታክቲካል ዲሲፕሊን የመተግበር ችግር አለብህ?

ምንያህል፡- እውነት ለመናገር ታክቲካል ዲሲፕሊን ይባላል እንጂ ስለታክቲክና ቴክኒክ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም እውቀት የለንም፡፡ እስቲ አንተ ንገረኝ የትኛው የአገራችን አሰልጣኝ ነው እየተመራ ታክቲክ ቀይሮ በመግባት ውጤት ቀልብሶ የሚያውቀው? እኔ በተፈጥሮዬ ስጫወት ፕሌይ ሜከር ብሆን እንኳን ሁኔታዎች ከፈቀዱ ኳስ ላስጥል እወጣለሁ፡፡ ይሄን የተመለከተ ሰው ምን ያህል  ታክቲካል ዲሲፕሊንድ አይደለም ሊልህ ይችላል፡፡ በእኔ እምነት ከሚገባብህ ኳሱን ብታድነው ይሻልሃል፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለፅኩልህ ሲጀመር ታክቲክና ቴክኒክ የሚባለው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም አልተለመደም፡፡ ቶም ሴንትፌት በነበረ ጊዜ እንኳን በታክቲክ ነበር የምንጫወተው፡፡ አስር አስር ሜትር ይሰጠናል እሱን ሸፍነህ ትጫወታለህ በተረፈ ታክቲክና ቴክኒክ የሚባሉ ነገር ኢትዮጵያ ላይ ትንሽ ችግር አለ፡፡

ሊግ፡- በኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ ምን አፈራህ?

ምፀን ያህል፡- እጅግ በጣም ብዙ የሚወደኝን ደጋፊ አፍርቻለሁ፡፡ ብቻ ምን አጣሁ ልበልህ? በሄድክበት ቦታ ሁሉ የሰዎች ፍቅርን ታያለህ፡፡ አሁን ድረስ ሰዎች ሲያገኙኝ ለብሄራዊ ቡድን አትጫወትም እንዴ? እያሉ ይጠይቁኛል፡፡ ከዚህ አንፃር በዚህ ስፖርት ብዙ ነገር አትርፌያለሁ፡፡

ሊግ፡-  ከነቀድሞው ብቃትህ የምናይበት ጊዜ ቅርብ ይሆናል?

ምንያህል፡-፡ ሰው ስለሆንኩ እንዲህ ነው ብዬ ልገልፅልህ አልችልም፡፡ ነገር ግን በድርድር መልክ የጀመርኩት ክለብ አለ፡፡ ሁሉ ነገር በዚህ ሳምንት ተጠናቆ ክለቡን እንደምቀላቀል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በርካታ የብሄራዊ ሊግ ክለቦች ጥያቄ አቅርበውልኝ ነበር፡፡ ሆኖም እኔ ብሄራዊ ሊግ መጫወት ስለማልፈልግ ነው ጥያቄውን በአዎንታዊነት ያልተቀበልኩት፡፡ ምክንያቱም አሁን የእኔ ደረጃ ፕሪምየር ሊግ ላይ ነው፡፡

ሊግ፡-  ለበርካታ አመታት በፕሪምየር ሊጉ እንደመጫወትህ መጠን የኮከብ ተጨዋችነት ክብርን ማግኘት አልቻልክም፤ በተለይ በ2003 ዓ.ም ለዚህ ክብር ተቃርበህ ሽልማቱን  ባለማግኘትህ ምን ተሰማህ?

ምንያህል፡- ብዙ ጊዜ እንደተለመደው ኮከብ ተጨዋች የሚመረጠው የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ካነሳው ክለብ ነው፡፡ በዛን አመት ከክለቤ ጋር ዋንጫ ከማንሳቴም ባሻገር ለብሄራዊ ቡድንም ጥሩ አስተዋፅኦ በማድረጌ ልመረጥ ይገባ ነበር፡፡ ሆኖም በወቅቱ የኮከብነት ማዕረግን ያገኘው አዳነ ግርማ ነው፤ አወዳዳሪው አካል ራሱ ባወጣው መስፈርት እርሱን መርጧል፡፡ እንደ እኔ እምነት ግን ዋንጫ ያነሳ ቡድን እያለ የኮከብነት ምርጫው ሻምፒዮን ካልሆነው ቡድን መሆኑ ተገቢ አይደለም እላለሁ፡፡

ሊግ፡- ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረግከውን ዝውውር ተከትሎ ከቡና ደጋፊዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ይገጥምህ ነበር፡፡ እንደውም “ሚስቴ ወኪሌ” እያሉም ያበሽቁ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ የአንተ ስሜት እንዴት ይገለፃል?

ምንያህል፡- ኢትዮጵያ ቡናን ለቅቄ ደደቢትና ቅዱስ ጊዮርጊስ እየተጫወትኩ ባለሁበት ጊዜ ስድብና ሌሎች ነገሮችን አስተናግጃለሁ፡፡ እኔ ግን ሁሌም የማስበው በጥሩ ሁኔታ ያሳለፍኩትን ጊዜ ነው፤ ኢትዮጵያ ቡና ከቢ ጀምሮ ተጫውቼ ወደ ዋናው ቡድን አድጌ በክለቡ ውስጥ ጥሩ የሚባል ጊዜ አሳልፌያለሁ፡፡ ከዛ በተረፈ እነርሱ የፈለጉትን ነገር ማለት ይችላሉ፡፡ እኔ ግን በጥሩ ሁኔታ ላሳለፍኩበት ክለብ ደጋፊዎች መልስ መስጠት ስለማልፈልግ ነው ሲሰድቡኝ ዝም የምለው፡፡

ሊግ፡- ስቴድየም የሚባለውን ነገር ባለቤትህ ስትሰማና እቤት ስትገናኙ ምን ትልሃለች?

ምንያህል፡- ምንም አይገረማትም፡፡ እሷ እንደውም እንደዛ የሚሉት ስለሚወዱህ ነው ትለኛለች፤ አንዳንዴም የእርሷ ስም ስቴድየም መነሳቱ ዘና ያደርጋታል፡፡

ሊግ፡- ለመሰናበቻ አንድ እድል ሰጥቼሃለሁ?

ምንያህል፡- አሁን እዚህ ላይ ሆኜ እንድበረታታ ከጎኔ በመሆንም ሁለንተናዊ ድጋፍ የሚሰጡኝ ሰዎች አሉ፡፡ እውነት ለመናገር በዘንድሮው የውድድር ዘመን ሊጉ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ስቴድየም ገብቼ አላውቅም፡፡ በተለይ የሻለ ጤና ስፖርት ክለብ አባላት ሁሌም ከጎኔ እንደቆሙ ነው፡፡ በጣም ብዙ የሆኑ ስማቸውን ብጠራ ጋዜጣውን ሊሞላው ስለሚችል በጅምላ ላቅ ያለ ምስጋናን ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ከሻላ ጤና ስፖርት አባላት በተጨማሪ በዙሪያዬ ያሉ ጓደኞቼን ሁሌም  በፅናት እንድቆም ስለሚያበረታቱኝ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡

 

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P