ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በፋሲል ከነማ ሻምፒዮናነት ከተጠናቀቀ በኋላ ለሐዋሳ ከተማ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ጥሩ እንቅስቃሴ በማሳየት የተጫወተውን መስፍን ታፈሰን የሊግ ስፖርት ጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ አናግሮታል።
የሐዋሳ ከተማ ውስጥ የተወለደው መስፍን በቤተሰቡ ከሚገኙት ልጆች ውስጥ ብቸኛው ወንድ ልጅ ሲሆን ሶስት እህቶች አሉት። የቤቱ ኳስ ተጨዋችም ስፖርተኛም እሱ ብቻ ነው። እናቱ በልጅነቱ ዕድሜ ወፍራም መሆኑን በማየት ቹንኬ ብለው ባወጡለት ስያሜ የሚጠራው ይህ ተጨዋች ወደፊት ትልቅ ደረጃ ላይ ይደርሳል ተብሎ እየተጠበቀ ሲሆን ከእሱ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንድታነቡት በሚከተለው መልኩ ጋብዘነዎታል።
ሊግ፦ እግር ኳስ ተጨዋች የመሆን እልምን ሰንቀህ ነው ኳስ መጫወት የጀመርከው?
መስፍን፦ አይደለም፤ ልጅ እያለው ኳስን ለስሜት ነበር ስጫወት የነበርኩት። ትንሽ ካደግኩኝ በኋላ ግን የኳሱ ጥቅም ስለገባኝና ጥሩ ደረጃም ላይ መድረስን ስላለምኩ ኳስ ተጨዋች ሆንኩኝ።
ሊግ፦ የእግር ኳስ ተጨዋች ባትሆን ኖሮስ በምን ሙያ ላይ እናገኝህ ነበር?
መስፍን፦ ሰፈራችን የንግድና የገበያ ቦታ ስለነበር ነጋዴ ነበር የምሆነው።
ሊግ፦ የአንተ የትውልድና የእድገት ቦታ ምን በመባል ይታወቃል?
መስፍን፦ ሐዋሳ ጣውላ /ቀበሌ 02/ ሰፈር ነው የሚባለው።
ሊግ፦ በተወለድክበት ሰፈር ከአንተ ውጪ ሌሎች የሚታወቁ ተጨዋቾችስ ወጥተዋል?
መስፍን፦ አዎን፤ ለምሳሌ ያህል እስከ ብሄራዊ ቡድን ደረጃ ተመርጦ የነበረውና በተለያዩ ክለቦች ውስጥ የተጫወተው ዘነበ ከበደ /አዩካ/ በዋናነት ይጠቀሳል። ሌላው ሀላላ አለ።
ሊግ፦ የእግር ኳስን መጫወት ስትጀምር ከባህር ማዶና ከሀገር ውስጥ የትኞቹን ተጨዋቾች ተምሳሌት አደረግክ?
መስፍን፦ በሀገር ውስጥ ደረጃ እነ አዳነ ግርማን፣ ሳላህዲን ሰይድና ጌታነህ ከበደን በመመልከት ስላደግኩ እነሱን ነው ሞዴሎቼ ያደረግኳቸው። ከውጪዎቹ ደግሞ ሊዮኔል ሜሲን በጣም የምወደው ቢሆንም እሱን ካለው ድንቅ ብቃት አኳያ ተምሳሌት ማድረግ በጣም ነው ከባድ የሆነብኝና ከማድነቅ በዘለለ ሌላ ነገር ውስጥ አልገባውም።
ሊግ፦ ከባህርማዶ ክለቦች የማን ደጋፊ ነህ?
መስፍን፦ የአርሰናልና የባርሴሎና ደጋፊ ነኝ። ሁለቱም ጥሩ ኳስን ስለሚጫወቱም ነበር ደጋፊያቸው ልሆን የቻልኩት።
ሊግ፦ የእግር ኳስን በፕሮጀክትና በክለብ ደረጃ ተጫውተህ እያሳለፍክ ነውና በአንድ ጨዋታ በርካታ ግቦችን ያስቆጠርክበትን ጊዜ ታስታውሳለህ?
መስፍን፦ አዎን! ኳስን መጫወት የጀመርኩት በፕሮጀክት ደረጃ ነው። ከዛም በሐዋሳ ከተማ የተተኪው ቡድን ውስጥ ከተጫወትኩ በኋላ በአሁን ሰዓት ላይ ደግሞ ካለፉት ሶስት ዓመታት ጀምሮ በዋናው ቡድን ውስጥ እየተጫወትኩኝ እገኛለው። በእነዚህ የኳስ ጊዜ ቆይታዎቼም በአንድ ጨዋታ ሁለትና ሶስት ግቦችን ያስቆጠርኩባቸው ጊዜያቶች ቢኖሩም በእኔ ስር የተመዘገበው ብዙ ግብ ግን በአንድ ወቅት ሙሉጌታ ምህረት አቋቁሞት በነበረው ዛማ የፕሮጀክት ቡድን ውስጥ ኳስን ስጫወትና ተጋጣሚያችንንም 18-2 ስናሸንፍ ቡድኑ ምርጥ ነበርና በአንድ ጨዋታ 9 ግቦችን ያስቆጠርኩበት ነው ከፍተኛው።
ሊግ፦ የሐዋሳ ከተማ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ ተሳትፎው ተጠናቋል፤ አጠቃላይ የውድድር ቆይታችሁን በምን መልኩ ትገልፀዋለህ?
መስፍን፦ የውድድር ተሳትፎአችንን እንደ ቡድን ሳየው ከበፊቱ የተሻለ ነው። ከቅርብ ዓመታቶች ወዲህ ላለመውረድ ይጫወት የነበረውን ቡድን እስከ 5ኛና 6ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ በማድረግ ላይ ስለሆንን ይሄ ጥሩ የለውጥ ማሳያ ነውና በጣም ደስ ይላል። ሌላው ይሄ ወጤት የተገኘውም ቡድኑ በአብዛኛው የተገነባው በወጣቶች ላይ ተሰርቶ ስለሆነም ይሄ ቡድን ይበልጥ ሲጠናከር የመጪው ዓመት ላይ አስፈሪ ቡድንም ይሆናል።
ሊግ፦ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫውን ፋሲል ከነማ አንስቶታል፤ ይገባዋል? እናንተስ ለምን ለማንሳት አልቻላችሁም?
መስፍን፦ ፋሲል ከነማማ ስለሚገባው ነው የሊጉን ዋንጫ ያነሳው። እነሱ ከመጀመሪያው ጨዋታቸው አንስቶ ነው ያላቸውን ጥሩ ነገር ስላስቀጠሉት ሊጉ ገና አራት ጨዋታ በቀረው ወቅት የውድድሩ ሻምፒዮና የሆኑት። እኛን በተመለከተ ከመሪው ቡድን ጋር በነጥብ ባልራቅንበት ወቅት ለሻምፒዮናነት ለመጫወት እያሰብን ነበር የዋንጫውን ባለቤትነት ፋሲል ካረጋገጠ በኋላ ግን እስከ ሁለተኛ ደረጃ የሚያደርሰንን ውጤት ለማስመዝገብ ነበር ስንጫወት የቆየነውሀ። ያም ሆኖ ግን በአንድ አንድ ሁኔታዎች ነው ፈጣሪ ሊልልን ስላልቻለ ጥሩ በሚባል ደረጃ የዘንድሮ ውድድራችንን ልናጠናቅቅ የቻልነው።
ሊግ፦ ለሐዋሳ ከተማ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ካጠናቀቀበት ደረጃ ወደ ላይ ከፍ እንዳይል ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ የምትጠቅሰው አለ?
መስፍን፦ አዎን፤ ብዙውን ጊዜ ነጥቦችን እንጥል የነበርነው በደረጃ ሰንጠረዡ እታች ካሉና እንደ እነ አዳማ ከነማ ከሚገኙም ወራጅ ቡድኖች ጋር ስንጫወት ሽንፈትን እናስተናግድም ስለነበር ነው። ከአዳማ ጋር ስንጫወት በሁለቱም ዙሮች ተሸንፈን ውጤትን አጥተናል። እነዚህ ሁኔታዎች ናቸው እኛን በደረጃው ሰንጠረዥ ወደ ላይ ከፍ እንዳንል ያደረጉን።
ሊግ፦ ሐዋሳ ከተማ ከዘንድሮ ቡድኑ ምን ምን ነገሮች ተምሮ ይመጣል?
መስፍን፦ የነበሩብንን ክፍተቶች አውቀናቸዋል። እነዚህም በስራ የሚመጡ ናቸው። በያዝነው ስብስብ ላይ ተጠናክረን መጥተን የመጪው ዓመት ላይ ስኬታማ ቡድን እንደሚኖረን አምናለው።
ሊግ፦ በቤትኪንግ እንደ ግልስ ምን አይነት የውድድር ዘመንን አሳለፍክ?
መስፍን፦ በጣም ደስ የሚል ጊዜን ነው ያሳለፍኩት። በአጠቃላይ ሰባት ጨዋታዎች አራቱን ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ሶስቱን ደግሞ በጉዳት ለቡድኔ ሳልሰለፍ በመቅረት 10 ያህል ግቦችን ማስቆጠሬ በጥሩ ብቃት ላይ እንደምገኝ ስላሳወቀኝ ይህ ለእኔ ደስታን ፈጥሮልኛል።
ሊግ፦ ለሐዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ዓመት ላይ 8 ከዛም 5 ዘንድሮ ደግሞ 10 ግቦችን አስቆጠርክ። ይሄ የግብ ቁጥር በመጪው ዓመት ይጨምራል?
መስፍን፦ አዎን። ያለዚያማ እድገቱ አይኖረኝም። በተጨዋችነት ዘመኔ በርካታ ጎሎችን ማስቆጠር እልሜ ነው። ከክለብ ባሻገር ለብሄራዊ ቡድንም ሁለት ጎሎችን ከጅማሬዬ ለማስቆጠርም በቅቻለውና ይህ ጎል ማስቆጠሬ የሚቀጥል ነው።
ሊግ፦ በቤትኪንጉ ዘንድሮ የአንተ ምርጡ ተጨዋች?
መስፍን፦ የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስርና የባህርዳር ከተማው ፍፁም ዓለሙ ናቸው። አቡበከር በተለይ የሀገሪቱን የግብ ሪከርድንም ሰብሯልና የልፋቱን አግኝቷል። ይህን ስመለከት ማንም ከለፋ የፍሬውን ያገኛል።
ሊግ፦ አሁን የሊግ ውድድሩ ተጠናቋል። ምን እያደረግክ ነው?
መስፍን፦ በእረፍት ላይ እገኛለው። አህምሮዬን ትንሽ ፈታና ዘና ካደረግኩ በኋላ ደግሞ ለመጪው ዘመን ውድድር ራሴን ማዘጋጀት እጀምራለው።
ሊግ፦ ከእግር ኳስ ጨዋታ በኋላ ብዙውን ጊዜ የት ነበር የምታሳልፈው?
መስፍን፦ ቤቴ ነው። አልፎ አልፎ ደግሞ አካባቢያችን ሀይቅ ሰፈር ስለሆነ እዛ ቁጭ ብዬም ጥሩ አየርን በመቀበል ሁኔታዎችን እቃኛለው።
ሊግ፦ የዓሳ ወይንስ የጥሬ ስጋ አድናቂ ነህ?
መስፍን፦ ሁለቱንም አልምርም። በቅድሚያ ግን ጥሬ ስጋን አስቀድማለው።
ሊግ፦ በእግር ኳስ ምርጡ ጎልህ የቷ ናት?
መስፍን፦ በሲዳማ ቡና ላይ ዘንድሮ ያስቆጠርኳት። በጣም ታምራለች።
ሊግ፦ በእግር ኳስ ችሎታህ ማሻሻል ያለብህ?
መስፍን፦ ብዙም አይደለም። ችግሬ ጥቂት ስለሆነ ያን ክፍተቴን አሻሽዬ እመጣለው።
ሊግ፦ ለፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ሙከራ ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ አምርተህ ነበር?
መስፍን፦ አዎን። እዛ ስጓዝና ሙከራን ሳደርግ ዋንኛዬ ዓላማ ካደረጉት ውስጥ ወደ ስፔን ለሚገኙ ቡድኖች ተጨዋቾችን የሚመለምሉ ሰዎች ይመጣሉ ስለተባልኩና ወደዛም ችሎታዬን አሳይቼ ለማምራት ነበር። ያ ተሳክቶልኝ ግብ እስከማስቆጠር ደረጃ ብደርስም ሰዎቹ ስላልመጡ ወደ ሀገሬ ልመለስ ቻልኩ።
ሊግ፦ በሐዋሳ ከተማ ከሚገኙት ተጨዋቾች ውስጥ የትኞቹ ተጨዋቾች ናቸው እናንተን የሚያዝኗኗችሁ?
መስፍን፦ እከሌ እከሌ የምትለው ተጨዋች የለም። ሁሉም ናቸው በጋራ ሳቅና ደስታን የሚፈጥሩልን።
ሊግ፦ ቀጣይ ምኞትህ?
መስፍን፦ ለሀገሬ ብሄራዊ ቡድን ተመርጦ መጫወት። ሀገሬን ለታላቅ የውድድር መድረክ ማብቃትና ፕሮፌሽናል ተጨዋች ሆኜም ስሟን ማስጠራት የእኔ ዋንኛ እልሞች ናቸው።
ሊግ፦ ቆይታችንን እናጠቃል?
መስፍን፦ ለዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ መገኘቴ ፈጣሪዬን ከዛ በመቀጠል ደግሞ ቤተሰቦቼን በተለይም ደግሞ አባቴንና አሰልጥነውኝ ያለፉትን ሁሉ ከልብ ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ።