“ፋሲል ከነማን ለስኬት እያበቃሁ የሚገኘው የራሱ ጥንካሬ እንጂ የሌላ ቡድኖች ድክመት አይደለም”
“ከራሴ ክብር ይልቅ ቡድኔን አስቀድሜ ነው በመጫወት ላይ የምገኘው”
“እኛ ዋልያዎች ለአፍሪካ ዋንጫው ስናልፍ የማላውቀው አይነት የደስታ ስሜት ተፈጥሮብኛል፤ ካሜሮን ላይም ክስተት ቡድን እንዲኖረን እፈልጋለሁኝ”
ሀብታሙ ተከስተ /ፋሲል ከነማ/
#በመሸሻ_ወልዴ
ፋሲል ከነማ ሊጠናቀቅ የ6 ሳምንታት በቀሩበት ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ላይ ዋንጫውን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማንሳት እየተንደረደረ ሲሆን ይህን ድል እውን ሲያደርግም አራተኛው የክልል ቡድን ይሆናል፤ የአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ቡድን ይህ ቡድን እልሙን በራሱ እድል ላይ ተወስኖ ሊያሳካም ካሉት ግጥሚያዎች ውስጥ የትናንቱን ጨዋታ ውጤቱን ሳይጨምር ከዚህ በኋላ አንድ ወይንም ደግሞ ሁለት ግጥሚያን ማሸነፍም ብቻ በቂ ይሆንለታል፡፡
ፋሲል ከነማ በዘንድሮ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው ጠንካራ ቡድንን በመገንባት በስኬታማነት ግስጋሴው የቀጠለ ሲሆን የቡድኑን የውድድር ዘመን ቆይታውንና ስለ ራሱ አቋም እንደዚሁም ደግሞ የዋልያዎቹን ለአፍሪካ ዋንጫ ከማለፍ ጋር በተያያዘ እና የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ለማንሳት ስለመቃረባቸው ከቡድኑና ከዋልያዎቹ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ሀብታሙ ተከስተ /ጎላ/ ጋር ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ቆይታን አድርጎ ተጨዋቹ ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ ምላሽን ሰጥቷል፡፡
ሊግ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን በ12 ነጥብ እየመራችሁ ይገኛል፤ ይሄን ልዩነት በእዚህ ሰዓት ጠብቀኸው ነበር?
ሀብታሙ፡- በፍፁም፤ የእዚህ ውድድር ዘመን ሲጀመር የእኛ እቅድ የነበረው ዋንጫውን ስለማንሳት ብቻ እንጂ በእዚህ ሰዓት ላይ ተከታዮቻችንን በእዚህን ያህል የነጥብ ልዩነት ስለመብለጥ ፈፅሞ ያሰብነው ነገር አልነበረም፤ ይሄ ልዩነት ያልተጠበቀም ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ክለባችን ባለፉት የውድድር ዘመናት ጠንካራ ቡድንን ፈጥሮ ለሁለት ጊዜያት ያህል አንዱን እስከ ፍፃሜ ድረስ በመጓዝ ሌላውን ደግሞ በኮቪድ የተነሳ ሊጉን እየመራን የውድድር ዘመኑ በመቋረጡ በቁጭት ስሜት ውስጥ ሆነን ኳሱን በመጫወታችን ነው ግስጋሴያችን እያማረልን የሚገኘው፡፡
ሊግ፡- ለፋሲል ከነማ ከሜዳ ላይ ብቃት አንፃር የውድድር ዘመኑ በጣም ምርጥ ነው ማለት ይቻላል?
ሀብታሙ፡- አዎን፤ ለእኛ ሊጉ ሲጀመር ብቻ ነው አዲስ አበባ ላይ በነበረን ጨዋታ ትንሽ ደከም ብለን የነበረው እንጂ እንደ አጠቃላይ ሌሎች የጨዋታ ተሳትፎአችን ከተመለከትነው ቡድናችን በሁሉም መልኩ ጠንካራ እና በጣምም ደስ የሚል ነበር፤ ፋሲል የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎው ላይ ጎሎችን የሚያገባ፣ እምብዛም ጎልን የማያስተናግድ እንደውም የማይቆጠርበት ማለት ይቻላል በዛ መልኩ በመጓዝ ነው ጥንካሬውንና ምርጥ ቡድንነቱንም እያሳየን ያለው፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ ቤትኪንጉን በሰፊ ነጥብ እየመራ የሚገኘው በራሱ ጥንካሬ ብቻ ነው?
ሀብታሙ፡- አዎን፤ እንደዛ ባይሆንማ ሊጉን አንመራም ነበር፤ ምክንያቱም የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎአችን ላይ ከእኛ ስር ያሉት ክለቦች ኢትዮጵያ ቡና፣ ቅ/ጊዮርጊስ እና ባህርዳር ከተማን የመሳሰሉት ቡድኖች በጣም ጠንካራ እና የሚገርሙ ቡድኖች ስለነበሩም ነው፤ ስለዚህም ፋሲል ሊጉን የመራው በራሱ ጥንካሬ እንጂ አንድአንዶች እንደሚሉት በሌሎቹ ድክመት አይደለም፤ ይሄ ስለሆነም እኛን ፈጣሪ ስለረዳንና ጠንካራ ስለሆንንም ነው በመሪነት ማማው ላይ ልንቀመጥ የቻልነው፡፡
ሊግ፡- ሊጉን በ12 የነጥብ ልዩነት ከመምራታችሁ እና ከቀሪ ጨዋታዎቻችሁ አኳያ ሻምፒዮናነታችሁን አላወጃችሁም?
ሀብታሙ፡- በሂሳብ ስሌት ገና ነው፤ 6 ጨዋታም ይቀረናል፤ ሻምፒዮና ለመሆንም ቀሪ ግጥሚያዎቻችንን ቢያንስ ሁለቱን እና ሶስቱን ማሸነፍ ስላለብን ያኔ ሁሉም ነገርም ይረጋገጣል፡፡
ሊግ፡- የውድድር ዘመኑን ለፋሲል ከነማም ለብሔራዊ ቡድንም በመጫወት ጥሩ ጊዜን እያሳለፍክ ይገኛል፤ ከዚህ በመነሳት የዘንድሮ የኮከብ ተጨዋችነት ሽልማት ወደ እኔ ያመራል እያልክ ነው?
ሀብታሙ፡- ሌሎች ሲሉ ሰማው እንጂ እኔ መች አልኩና፤ በውድድር ዘመኑ ጥሩ እንቅስቃሴን እያደረግኩኝ እንደሆነ ከደጋፊዎቻችን ጀምሮ ከሌሎች አካላቶች ጥሩ ነገርን እየሰማውኝ ነው የሚገኘው፤ የውድድር ዘመኑ ኮከብ ተጨዋች ተብዬ ብሸለም ደግሞ በጣምም ነው ደስ የሚለኝ፤ ያም ሆኖ ግን እኔ በአሁን ሰዓት እያሰብኩ ያለሁት ከራሴ ክብር እና ዝና ይልቅ ቡድኔን አስቀድሜ ስለመጫወት ነው የማስበው፤ ፋሲል ዘንድሮ በጣም ጥሩና ምርጥ ተጨዋቾች አሉት፤ ኮከብ ተጨዋች ተብሎ ለመመረጥም ብዙዎቻችን እድሉም አለንና እኔም ቡድኑን ለውጤት ሊያበቃው የሚችለውን ነገር በማስቀደም ኮከብ ተጨዋች ለመባልም ጥረትን አደርጋለውኝ፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ ሻምፒዮና ሆኖ አንተ ኮከብ ተጨዋች ተብለህ ባትመረጥ ይከፋሃል?
ሀብታሙ፡- ኸረ አይከፋኝም፤ ከላይ ሀሳቤን እንደገለፅኩት የእኛ ቡድን ብዙዎቹ ተጨዋቾች ዘንድሮ ምርጥ የውድድር ጊዜን ስላሳለፉ ኮከብ ተጨዋች የመባል እድሉ አላቸው፤ ያንም አውቃለው፤ ስለዚህም ከሁሉም በፊት የሚቀድመው የቡድናችን ሻምፒዮናነት እንጂ የእኔ ክብር ስላልሆነ በጣም የምደሰተው በክለባችን ሻምፒዮናነት ነው፡፡
ሊግ፡- ለፋሲል ከነማም ለብሄራዊ ቡድንም በቋሚነት ተሰልፈህ እየተጫወትክ ነው የምትገኘው፤ ይሄን እድል ከማግኘትህ ጋር አያይዘህ ምን ትላለህ ?
ሀብታሙ፡- በፋሲል ከነማ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ በቋሚነት ተሰልፌ መጫወት ስጀምር የአሁኑ የመጀመሪያዬ ጊዜ አይደለም፤ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጊዜም ለቡድኑ ተሰልፌ እጫወት ነበር፤ ዓምና ግን ከአቋም መውረድ ጋር በተያያዘ ሳይሆን ተደራራቢ የጤና ችግር ስላጋጠመኝ ብቻ ተቀይሬ የገባሁባቸው ጨዋታዎች ነበሩና በአብዛኛው ለቡድኑ እየተጫወትኩ ያለሁት ብቃቱ ስላለኝ ነው፤ ይሄን እድል ያገኘሁትም ሁሌም ጠንክሬ ስለምሰራና በአሰልጣኙ ስለታመነብኝም ነው፤ ለብሔራዊ ቡድን እየተጫወትኩ ያለሁትም የአሰልጣኙን ታክቲክ በሜዳ ላይ ተግብሬ ስለምወጣም ነውና በዛ ለቡድኑ በቋሚነት ተሰልፌም ለመጫወት በቅቻለሁ፡፡
ሊግ፡- እንደ አንድ እግር ኳስ ተጨዋች ምን ይጎድለኛል ብለህ ታስባለህ?
ሀብታሙ፡- የእግር ኳስ ተጨዋች ስትሆን ሁሌም ቢሆን አቋምህ ሙሉ አይሆንምና ከችሎታዬ ጋር በተያያዘ የሚቀረኝ ነገር አለ፤ ከእነዛ ውስጥም አንዱ የአየር ላይ ኳስ የጋራ ሽሚያ ላይ አምሳ አምሳ በሆነ መልኩ ኳስን ከባላጋራዬ በተሻለ መልኩ መጠቀም እንዳለብኝ አውቄያለውና በየቀኑ በእዛ አጨዋወት ውስጥ አንድአንድ ነገሮችን እየሰራው በመምጣት ክፍተቴን ለማረም እየጣርኩ ነው የሚገኘው፤ ሌላው ደግሞ ለእኔ ያልታየ ለአሰልጣኜ ደግሞ የሚታይ ችግር ስለሚኖርም እሱ ከሚነግረኝ ነገር ተነስቼም ችሎታዬን ለማሻሻል በቀጣይነትም ጠንክሬ እሰራለሁኝ፡፡
ሊግ፡- ለፋሲል ከነማ ዘንድሮ በምን ያህል ጨዋታዎች ላይ ተጫወትክ?
ሀብታሙ፡- ከሁለት ጨዋታዎች ውጪ ሁሉም ላይ አለው፤ ያልተሰለፍኩት ከወላይታ ድቻ ጋር በነበረን የአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታ ላይና ባህርዳር ላይ በ5 ቢጫ ካርድ ያልተጫወትኩበት ነው፡፡
ሊግ፡- አሰልጣኝ ስዩም ከበደና የቡድናችሁን የተጨዋቾች ስብስብ በምን መልኩ ነው የምትገልፃቸው?
ሀብታሙ፡- ስለ ስዩም በተደጋጋሚ ጊዜ ብዙ ብዬአለው፤ እሱ እንደ አሰልጣኝ ብቻ ሳይሆን አባታችንም ነው፤ ያለን ግንኙነትም የልጅና አባትም ነው፤ የሚወደድ አሰልጣኝም ነው፤ በእሱ ስልጠናና የታክቲክ አተገባበርም በችሎታዬ ላይ ከፍተኛ ለውጥን እንዳመጣም ያደረገኝ ነው፤ ስለ ስዩም ይህን ካልኩ የቡድናችንን ተጨዋቾች በተመለከተ ደግሞ እኔ ከእነሱ ጋር በመጫወቴ ዕድለኛ ነኝ፤ የቡድን አጋሮቼ በኳሱ ጥሩ ኳሊቲ ያላቸው እና ወደ ውጪም በመውጣት በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት መጫወት የሚችሉ ናቸው፤ እንደ ግል ሳይሆን እንደ ቡድንም ነው እንድንጫወት የሚያደርጉን፤ ከልምምድ አንስቶ ወደሜዳ ስንገባ ለቡድናችን ውጤት ስንል ብዙ ነገርን ልንባባል እንችል ይሆናል፤ በኋላ ላይ ግን ይቅርታ ተባብለንና እንደ ቤተሰብም ሆነን ነው ያለንን ግንኙነታችንን የምናጠናክረውና በእዚህ ውስጥ እየተጓዙ ላሉት ተጨዋቾችም ሆነ አሰልጣኛችን ከፍተኛ ምስጋና ነው ያለኝ፡፡
ሊግ፡- በፋሲል ከነማ ክለብ ውስጥ ከጨዋታ በኋላ መልበሻ ክፍሉን የሚያደምቁት ተጨዋቾች እነማን ናቸው?
ሀብታሙ፡- የመጀመሪያው ተጠቃሽ ተጨዋች ሽመክት ጉግሳ ነው፤ እሱ በሜዳ ላይም ሆነ ከሜዳ ውጪ ለቡድናችን ወሳኙ ሰው ነው፤ ሌላው ቀጥዬ የምጠራው ተጨዋች ደግሞ ሀምሳሉ ጥላሁን /ሳኛ/ ነው፡፡ እነሱ ቡድኑን ውጤት እንዲያመጣ ከማነቃቃት በተጨማሪ ደስታን የሚፈጥሩልን ተጨዋቾችም ስለሆኑ ይለዩብኛል፡፡
ሊግ፡- ዋልያዎቹን ለካሜሮኑ የአፍሪካ ዋንጫ ካሳለፉት እና በሜዳ ላይም በቋሚ ተሰላፊነት ከተጫወቱት ተጨዋቾች መካከል አንዱ ሆነሃል፤ የእዛን ዕለት የነበረ ስሜት ምን ይመስላል…ከዚህ በፊትስ ሀገራችን ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ባለፈችበት ጊዜስ የነበርክበት ሁኔታስ ምን ይመስላል?
ሀብታሙ፡- ዋልያዎቹ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ባለፉበት ጊዜ እኔ የነበርኩበት ሁኔታ ያኔ ኳስን በሰፈር ውስጥ ነበር የምጫወተውና በዲ.ኤስ.ቲቪ ተመልክቼ ነው ሰዉ ሁሉ ለአፍሪካ ዋንጫው በማለፋችን ሲጨፍር እኔም ከጨፋሪዎቹ መካከል አንዱ ሆኜ ደስታዬን ልገልፀው የቻልኩት፤ አሁን ደግሞ ፈጣሪን ይመስገነውና በተመልካችነት ዘመን ያየሁትን ደስታ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋና ይባስ ብሎ ደግሞ የቡድኑ አንዱ ተጨዋች እና ቋሚም ተሰላፊ ሆኜ ይህን ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍን ድል ስለተጎናፀፍኩኝ እኔን የተሰማኝ የደስታ ስሜት ፈፅሞ የማላውቀው አይነት ነበር፤ ከዚህ በፊት እንደዚህ ያለ የደስታ ስሜት አጋጥሞኝና ተሰምቶኝም አያውቅም፤ ለእዚህ አፍሪካ ዋንጫ ማለፋችንንም ሁላችንም አጥብቀን የፈለግነውም ሀገራችን በብዙ ነገሮች ማለትም ከፖለቲካው ጋር በተያያዘ በእርስ በርስ እልቂትና በሌሎችም ነገሮች ላይ በጥሩ ሁኔታ ላይ የማትገኝ በመሆኑና በኳስ የሚደሰተው ህዝብ ደግሞ ብዙ በመሆኑም ለውድድሩ እንዳለፍን በሀገር ውስጥ ስለነበረው ስሜትና ወደዚህም ከመጣን በኋላም ደስታችንን በአዲስ አበባ ዋናዋና መንገዶች ላይ በመኪና እየዞርን ስንገልፅ ህዝቡ ላይ የተመለከትነው ነገር በጣም ደስ ይል ስለነበር ለዚህ ክብር ላበቃን ፈጣሪያችን ምስጋና አለኝ፡፡
ሊግ፡- ወደ ካሜሮን በመጓዝ በአፍሪካ ዋንጫው ላይ እንሳተፋለን፤ ከውድድሩ ምን ውጤትን ትጠብቃለህ?
ሀብታሙ፡- በአሁን ሰዓት ከእኛ ተሳትፎ ብቻ ሳይሆን ውጤት እንደሚጠበቅ ብናውቅም ጥሩ ነገርን ሰርተን ሀገራችንን ለማኩራት የምንችልበትን ነገር ልንፈጥር ይገባል፤ በካሜሮን ጉዞአችንም የእኛ የቅድሚያ ዋንኛው ዓላማ ሊሆን የሚገባውም የቶርናመንቱ ክስተትና ምርጥ ቡድንም መባል ነውና ይሄን ከጓደኞቼ ጋር የምናሳከውም ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- ወደ ትዳር ዓለሙ አመራህ?
ሀብታሙ፡- ሀይ! አሁን ገና ነኝ፤ ስለዛም እያሰብኩኝ አይደለሁም፤ ከቤተሰብ ጋርም ነው እየኖርኩ ያለሁትና ትዳር የፈጣሪ ፈቃድ ስለሆነም ያኔ ጊዜው ሲደርስ የምፈፅመው ነው የሚሆነው፡፡
ሊግ፡- ወደ ማጠቃለሉ ብናመራና አንድ ነገርን ብትል?
ሀብታሙ፡- እሺ፤ በቅድሚያ በኳሱ ከሁሉም በላይ ለእዚህ ደረጃ እንድበቃ ያደረገችኝን የጌታዬ እናትን ድንግል ማሪያምን ማመስገን እፈልጋለው፤ እሷ ሁሉንም ነገርም ነው ያደረገችልኝ ሲቀጥል ቤተሰቦቼን፣ እንደዚሁም ደግሞ ልጅ ሆኜ ያሰለጠነኝን ተገኝ እቁባይን እንደዚሁም ደግሞ እስካሁን ድረስ አሰልጥነውኝ ያለፉትንና የሰፈሬን ብልኮ አካባቢ ጓደኞቼንና የፋሲል ከነማ ደጋፊዎችንና የቡድን አጋር ጓደኞቼን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡
https://t.me/Leaguesport