የኢትዮጵያ ቡናው ስኬታማ የመሀል ሜዳ ተጨዋች ታፈሰ ሰለሞን ቡድናቸው ነገ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ በማሸነፍ ወደ አፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የሚያልፉበትን ዕድል እንደሚያሰፉት ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ አስተያየቱን ሰጥቷል፤ ለኢትዮጵያ ቡና ለመጪዎቹ አራት ዓመታት ለመጫወት ፊርማውን ያኖረው ታፈሰ ሰለሞን በኢትዮጵያ ቡና የተጨዋችነት ዘመን ቆይታውም ደስተኛ መሆኑንም ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ቡና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮናውን ፋሲል ከነማን በመከተል በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ከሀድያ ሆሳዕናና ከአዳማ ከነማ ጋር በሚያደርጋቸው ሁለት ጨዋታዎች የዓመቱን የውድድር ዘመን ያጠናቅቃል፤ ነገ ከሀድያ ጋር የሚያደርገው ጨዋታም ወሳኝ መሆኑን ተከትሎም የቡድኑ ተጨዋቾች ግጥሚያውን በጉጉት እየተጠባበቁት ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናውን ታፈሰ ሰለሞን በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ ተሳትፎአቸው ዙሪያና ነገ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ስለሚያደርጉት ጨዋታ እንደዚሁም ሌሎችን ጥያቄዎች አንስተንለት ተጨዋቹ ምላሽን ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና ከሀድያ ሆሳዕና የሚያደርገው ጨዋታ ወደ ኮንፌዴሬሽን ካፑ ለማለፍ ዕድሉን የሚወስንበት ነው፤ ስለ ጨዋታው ምን ትላለህ?
ታፈሰ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ያለፉት ጥቂት ግጥሚያዎቻችን ላይ ተከታታይ ነጥቦችን ጥለን ነበር፤ ከዛ መነሻነትም ከሲዳማ ቡና ጋር የነበረንን የሰሞኑን ጨዋታ ለማሸነፍ ከፍተኛ ፍላጎትን አሳድረን ወደ ሜዳ ብንገባም ውጤቱ ሊሳካልን አልቻለም፤ ነገ እሁድ ግን ከሀድያ ሆሳዕና ጋር የሚኖረን ጨዋታ ቡድናችንን ወደ ኮንፌዴሬሽን ካፑ ሊያሳልፈው የሚችልና በወሳኝነቱም አቻ የማይገኝለት ፍልሚያ ስለሆነ ለእዚህ ጨዋታ እንደሌላው ጊዜ ግጥሚያዎቻችን ሁሉ በሚገባ ተዘጋጅተንበታል፡፡
ሊግ፡- ከሀድያ ሆሳዕና የምታደርጉት ጨዋታ እናንተ የሁለተኛ ደረጃ ውጤታችሁን ለማስከበር ለእነሱ ደግሞ የሁለተኛ ደረጃን ለመያዝ የሚያስችላቸው ከመሆኑ አኳያ ጨዋታው ስጋት አይሆንባችሁም?
ታፈሰ፡- ሀድያ ሆሳዕና ብዙም የሚያስፈራን ቡድን አይደለም፤ በአንደኛው ዙር ላይ ተመልክተናችኋል፤ ጫና አላሳደሩብንም፤ በመከላከሉ ላይ አተኩረው ነው ሲጫወቱ የነበሩት በነገው ጨዋታም ከእዚህ የሚዘል እንቅስቃሴው ስለማይኖራቸው ለእኛ በምንም መልኩ ስጋት አይሆኑብንም፤ እናሸንፋችኋለንም፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና ባለፉት ተከታታይ ግጥሚያዎቹ ማሸነፍ ሳይችል ቀርቶ ነጥቦችን እየጣለ ነው፤ የእዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው ትላለህ?
ታፈሰ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ነጥቦችን መጣል እንደምክንያት ከምጠቅሰው ውስጥ የመጀመሪያው ድሬዳዋ ከተማ ላይ ካደረግነው ጨዋታ ጀምሮ እኛ ለምንፈልገው እንቅስቃሴ የሜዳዎች ለእንቅስቃሴ አመቺ አለመሆንና ጭቃነቱም የጎዳን ስለሆነ ነጥቦችን ልንጥል ችለናል፤ ሌላው በእግር ኳስ የሚያጋጥም ጥቃቅን ስህተትም አለና ያም ነጥብን አሳጥቶናል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር ለክለባችሁ 27 ጎሎችን አስቆጥሮ ከአራት ዓመት በፊት በጌታነህ ከበደ ተይዞ የነበረውን የፕሪምየር ሊጉን የከፍተኛ ኮከብ ግብ አግቢነትን ሪከርድ ሊሰብር ችሏል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን አልክ?
ታፈሰ፡- ወጣቱ ተጨዋቻችን አቡኪ ይህን ሪከርድ ሊሰብር እንደሚችል ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ በመቶ ፐርሰንት የራስ መተማመን ስሜት ለብዙዎች ተናግሬ ነበር፤ ከጊዜያቶች በኋላም አንተም ቃለ-ምልልስን አድርገክልኝ ይህን ሀሳቤን ደግሜውም ነበር፤ በመሀል በአንድ አንድ ጨዋታዎች ላይ ጎል ሳያገባ ሲቀር ከፍቶኝ የነበረ ቢሆንም በሰሞኑ ጨዋታዎች ላይ ደግሞ ይሄ የሊጉ ምርጥ ተጨዋች የእውነት የተናገርኩትን ሀሳቤን በተግባር ላይ በማዋልና የሀገሪቱን ሪከርድም ሊሰብር በመቻሉ የተሰማኝ የደስታ ስሜት ከፍተኛ ነበር፤ አቡበከር የሀገሪቱ ድንቅ ተጨዋች ነው ከእዚህ በኋላም ይሄ ተጨዋች በቀሪዎቹ ሁለት ግጥሚያዎች ላይ ሁለት ግቦችን በማከልም ሊጉን በ29 ጎል የሚያጠናቅቅም ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- አቡበከር አሁን የያዘው ሪከርድ የሚሰበር ይመስልሃል?
ታፈሰ፡- እርግጠኛ ነኝ፤ በራሱ ካልሆነ በስተቀር በማንም አይሰበርም፡፡
ሊግ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የተወሰኑ ጨዋታዎች ቢቀሩትም ፋሲል ከነማ ሻምፒዮና ሆኖበታል፤ ድሉ ይገባዋል?
ታፈሰ፡- በሚገባ ነዋ! አንድ ሰሞን ላይ ከፋሲል ከነማ ይልቅ የቅዱስ ጊዮርጊስ አካሄድና አመጣጥ ያስፈራል ብዬ አስተያየቴን ሰጥቼ ነበር፤ በኋላ ላይ ነገሮች ተቀይረው ግን ፋሲል አስፈሪና ከእኛ ውጪ በማንም ሳይሸነፍ የመጣ ቡድን ሆኖ የቤትኪንጉ ባለድል ሆኗል፤ ፋሲል የውድድሩ ሻምፒዮና የሆነው ከሁሉም ቡድኖች የተሻለ ስለሆነም ነውና ድሉ ይገባዋል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በቅርቡ የደመወዝ ቅጣትን ካስተላለፈባቸው ተጨዋቾች መካከል አንዱ አንተ ነበርክ፤ በምን ነበር የተቀጣችሁት? ስለቅጣቱስ ምን አልክ?
ታፈሰ፡- የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እኔን ጨምሮ አራት ለምንደርስ የቡድኑ ተጨዋቾች ላይ በቅርቡ የደመወዝ ቅጣትን ሊያስተላልፍብን የቻለው ከቅ/ጊዮርጊስ ተጨዋቾች ጋር ታይታችኋል ተብለን ነው፤ እኛ ግን በወሬና በአሉባልታ ካልሆነ በስተቀር በፍፁም ከእነሱ ተጨዋቾች ጋር አልነበርንም፤ ይህን ተከትሎ የተጣለብንን ቅጣትንም በፍፁም አሜን ብዬም አልተቀበልኩትም፤ ለዛም ብለን በተቀጣንበት ጉዳይም ዙሪያ ለክለባችን በአካል በመገኘትም ሆነ በፅሁፍ ቅሬታንም አቅርበናል፤ እስካሁን ድረስ ምንም አልተባልንም፤ በቀጣይነት የሚመጣውን ነገርም እየተጠባበቅንም ነው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡናን የዘንድሮ አቋም እንደ አጠቃላይ በምን መልኩ አገኘከው?
ታፈሰ፡- ቤትኪንጉ ሲጀመር ቡድናችን ሻምፒዮና እስከመሆን ይደርሳል ብዬ ተናግሬ ነበር፤ ልክ ወደ ድሬዳዋ ለጨዋታ ስንጓዝ ግን የሜዳው ጭቃ መሆንና አሰልጣኛችን ካሳዬ አራጌ ለሚፈልገው የአጨዋወት ታክቲክም ይህ ሜዳ ምቹ ባለመሆኑ ነገሮች ሊበላሹብንና አብረውን ሊሄዱም ስላልቻሉ የጠበቅነውን ውጤት ሳናገኝ ቀርተናል፤ እንደዛም ሆኖ ግን ቡና በእዚህ ዓመት ላይ በስኳዱ ከያዛቸው ወጣት ተጨዋቾች አኳያና እየተከተለ ከሚገኘው የጨዋታ እንቅስቃሴም የተነሳ ወጣት ተጨዋቾቻችን ታክቲኩን ገና በመላመድ ላይም ስለሆኑ የያዝነውን አቋም በጥሩ ሁኔታ ነው የምገልፀው፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት ለመጫወት በቅርቡ ፊርማህን አኑረሃል፤ ከዚህ ውሳኔ ላይ እንዴት ልትደርስ ቻልክ?
ታፈሰ፡- ኢትዮጵያ ቡና በሁሉም መልኩ ስለተመቸኝ ነዋ! ቡና በእግር ኳስ ህይወቴ ተጫውቼ ካሳለፍኩባቸው ክለቦች በቀዳሚነት ኳስን ደስ ብሎኝ የተጫወትኩበት ቡድን ነው፤ የሚከተለው አጨዋወት በጣም የተመቸኝ ነው፤ በዛ ላይ የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የአጨዋወት ፍልስፍና የኳስ ችሎታህን በጣም የሚያሳድግልክ ስለሆነና እሱ ያለው ስብህናም የሚገዛክ ስለሆነ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ታሳቢ አድርጌ ነው ለክለቡ ለተጨማሪ ዓመታቶች በመቆየት ለመጫወት የወሰንኩት፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአጠቃላይ የጨዋታ ድምር ውጤት በቅርቡ ለአፍሪካ ዋንጫው አልፏል፤ አንተም ከመጨረሻው ጨዋታ በጉዳት ወጣህ እንጂ የቡድኑ አባል ነበርክ፤ ይሄን ተከትሎ ሰሞኑን ለቡድኑ ተጨዋቾች ሽልማት ተሰጥቷል፤ ከዚህ መነሻነትም እናንተም መሸለም ነበረባችሁም የሚል ነገርንም እየሰማን ይገኛልና፤ በጉዳዩ ዙሪያ ምን አልክ?
ታፈሰ፡- በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱና የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስብስብ ውስጥ እኔ በተጨዋችነት የነበርኩበት ቢሆንም ከፋሲል ከነማ ጋር በነበረን ግጥሚያ ላይ ጉዳትን በማስተናገዴ እመሜን ለወጌሻችን በማሳወቅና ለአሰልጣኜም ውበቱ እንዲነግርልኝ በማድረግ ከኮትዲቯሩ ግጥሚያ ውጪ ልሆን ችዬ ነበር፤ ይሄን ተከትሎም ዋልያዎቹ ለአፍሪካ ዋንጫው ሲያልፉ በጣም ነበር የተደሰትኩት፤ ለማለፋችንም የብዙ ተጨዋቾችና ቀደም ሲል የነበረው አሰልጣኝም አስተዋፅኦ አለበት፤ ለብሔራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች የተሰጠው ሽልማት ላይ በተመለከተ ብዙ ሰው እየደወለ እናንተም እኮ የእዚህ ሽልማት ተቋዳሽ መሆን አለባችሁ እያሉ ቢያናግሩንም እኔ ግን በዚህ ዙሪያ ምንም ነገርን አልልም፡፡
ሊግ፡- የዋልያዎቹን ስብስብ ዳግም መቀላቀል አላሰኘህም?
ታፈሰ፡- እንዴት አያሰኘኝም፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተጨዋችነት ዘመኔ ቀደም ሲሉ በነበሩት ብሔራዊ ቡድኖች ላይ ደስተኛ አልነበርኩም፤ ምክንያቱም ያኔ ተጨዋቾች ይመረጡ የነበሩት በስምና ዝና ጭምር ነበርና፤ አሁን ግን አሰልጣኝ አብርሃምና ውበቱ አባተ ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ ተጨዋቾች የሚመረጡት በወቅታዊ ችሎታ ስለሆነ ደስተኛ ሆኜ ነው ስጫወት የነበርኩትና የአሁኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈውን ቡድን ዳግም መቀላቀል በጣም እያጓጓኝ ነው፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዘንድሮ ጥሩ ብቃትህን አሳይተሃል?
ታፈሰ፡- አዎን፤ በጉዳትና በሜዳዎች ለጨዋታ ምቹ አለመሆን አንድአንዴ ሙሉ አቋሜን ለክለቤ ባላሳይም ጥሩ ነበርኩኝ፡፡
ሊግ፡- ታፈሰ ሰለሞን ራሱን አለመጠበቁ በአንድአንድ ወሳኝ የቡድኑ ጨዋታዎች ላይ ለቡድኑ ጥሩ እንዳይንቀሳቀስ አድርጎታል እየተባለ ነው?
ታፈሰ፡- በዚህ ዙሪያ እኔ ማንንም አልሰማም፤ የተባለው አሉባልታ ስለሆነም አልቀበለውም፤ አንድአንዴ ደስ የማይሉ ነገሮችን ትሰማለህ ወደ ሐዋሳ ከመጣን በኋላ የእኔና የዊሊያም ሰለሞንን ስም በማጥፋት ብዙ ሲባል ነበር፤ ኢትዮጵያ ቡናን ከሚጎዱት ነገሮች ውስጥ እንዲህ ያሉ አሉባልታ ወሬዎች ናቸው፤ አንድአንድ ደጋፊዎች ትክክለኛ እና ተገቢ ያልሆኑ ነገሮችን ወደ ክለቡ በማምጣት ስህተትን እየሰሩም ይገኛሉና ይሄን ቡድኑ ሊያውቀው ይገባል፡፡
ሊግ፡- አሰልጣኛችሁን ካሳዬ አራጌን በማስመልከትስ ምን ትላለህ?
ታፈሰ፡- ስለ እሱ ተወርቶ አያልቅም፤ ካሳዬ አራጌ ለሊጉ ከ15 ዓመታት ቆይታ በኋላ እንደገና አዲስ ሆኖ የመጣ አሰልጣኝ ነው፤ በዛ ላይ ደግሞ አዲስ የጨዋታ ፍልስፍናንም በቡድኑ ውስጥ እንዲተገበር እያደረገ ያለ፤ ይህን የጨዋታ ፍልስፍናን በተመለከተም አሁን በያዛቸውና ብዙም በማይታወቁ ተጨዋቾች ማንም አሰልጣኝ ሊያደርገው የማይችልም ነው፤ ተጨዋቾቹን ራሱ ነው ያመጣቸው፤ የእሱ እንቅስቃሴ ተጨዋች ይፈልጋል፤ ይህ በሆነበት ሁኔታ ብዙ ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾች ሳያስፈርም ቡድኑን በእዚህ የሁለተኛ ደረጃ ላይ ሊያስቀምጠው በመቻሉና ወደ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ለማለፍም ክለቡ እየተንደረደረም መሆኑን ስታይ አሰልጣኙን እንድታመሰግነውም ያደርግሃል፡፡
ሊግ፡- እናጠቃል?
ታፈሰ፡- ኢትዮጵያ ቡናን አሁን በያዘው የጨዋታ ፍልስፍና በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ላይ ማየት በጣም አጓጉቶኛል፤ ይህን እልም ለማሳካትም የነገው ጨዋታ ወሳኝ ነውና ለግጥሚያው ዝግጁ ነን፤ ከዛ ውጪ ፈጣሪ ይርዳንም ነው የምለው፡፡