“ከሁሉም ቡድኖች ኳሱን ይዞ በመጫወት እኛ የተሻልን ነን”
“ቤትኪንጉን በየከተማው ከ1-3 አጠናቀን በመጨረሻም ሻምፒዮና እንሆንበታለን”
ፈቱዲን ጀማል /ባህርዳር ከተማ/
በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎው ጥሩ ውጤትን በማስመዝገብ ላይ ለሚገኘውና በደረጃው ፉክክር ውስጥም ከሚገኙት ክለቦች መካከል አንዱ ለሆነው የባህርዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ በተከላካይ ስፍራ ላይ በመጫወት የሚታወቀው ፈቱዲን ጀማል የእዚህ ዓመት እቅዳቸው በየከተማው ላይ የሚካሄዱትን ውድድሮች ከ1-3 ባለው ደረጃ ውስጥ በማጠናቀቅ መጨረሻ ላይ ግጥሚያዎቹ ባህርዳር ከተማ ላይ የሚደረግበት እድል ሳላለ ቡድናቸው የውድድሩ ሻምፒዮና እንደሚሆን ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የሐዋሳ ከተማ ቆይታቸው ሊጉን በመሪው ፋሲል ከነማ በአራት ነጥብ ብቻ በመበለጥ በአራተኛ ደረጃ ላይ ሆነው ያጠናቀቁትና አሁን ላይ ደግሞ በድሬዳዋ ከተማ ላይ የሚደረገውን ውድድር ትናንት ከሲዳማ ቡና ጋር በነበራቸው ጨዋታ ተሳትፎአቸውን የጀመሩት ባህርዳሮች በድሬዳዋ ከተማ ቆይታቸው ከሐዋሳ ከተማ በተሻለ ጥሩ ውጤት እንደሚገጥማቸውም እየተናገሩ ይገኛል፡፡
ባህርዳር ከተማ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ እስካሁን ስላደረጋቸው ጨዋታዎች እና ስለ ቀጣዩ የውድድር ዘመን ጉዞአቸው እንደዚሁም ደግሞ ስለ ራሱና ስለ ካሜሮኑ የአፍሪካ ዋንጫ የብሄራዊ ቡድናችን ተሳትፎና ስለ አጠቃላይ የእስካሁኑ ውድድሩ አነጋግረነው ተከታዩን ምላሽ በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በሐዋሳ ከተማ ላይ ስለነበራቸው የውድድር ተሳትፎ
“የሐዋሳ ከተማ ላይ በነበረው ቆይታችን ምንም እንኳን ሜዳው ለጨዋታ ባይመችም እንደተከተልነው አዲስ የጨዋታ ታክቲክ ጥሩ ጎን ነበረን፤ ከአዳማ ከተማ ጋር በመጨረሻው ግጥሚያ ስንጫወት ውጤቱ ተበላሸብን እንጂ በሊጉ የደረጃው ሰንጠረዥ ሁለተኛ ስፍራ ላይ ለመቀመጥም እንችል ነበር”፡፡
በውድድሩ ላይ የእነሱን ቡድን አቋም ከሌሎቹ ጋር ሲያነፃፅር
“ከሁሉም ቡድኖች ኳሱን ይዘን በመጫወትም ሆነ በሁሉም ነገር እኛ የተሻልን ነበርን፤ ይህንንም በቀጣይነት የምናስቀጥለው ይሆናል”፡፡
በድሬዳዋ ከተማ ለሚኖራቸው የውድድር ተሳትፎ ራሳቸውን ስላዘጋጁበት መንገድ
“ወደ ድሬዳዋ የተጓዝነው በሐዋሳ ከተማ ላይ ከነበረን የውድድር ቆይታችን ልንማር የምንችልበትን ነገር ላይ ሰርተን በመምጣት ነው፤ ሐዋሳ ላይ የአጨራረስ ችግር ነበረብን፤ እሱን ልምምድ ላይ በደንብ ሰርተንበት መጥተናል፤ በየጨዋታውም ትኩረት ያደረገ ቡድን ውጤቱን ለማሻሻልም የሚከብድ ነገር ስለሌለ በቀጣይነት ሁሉም ነገር ተስተካክሎልን ከመጣ ካለፈው በጣም የተሻለ ቡድን ይኖረናል”፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ምን ውጤትን ለማምጣት እንዳቀዱ
“የውድድር ዘመኑ እቅዳችን በየከተማው የሚካሄዱትን ግጥሚያዎች በውጤት በማጠናቀቅ ከ1-3 ባለው ደረጃ ውስጥ ሆኖ መጨረስ ነው፤ በሐዋሳው ተሳትፎአችን አራተኛ ሆነን ነበር የጨረስነው፤ ከእዚህ በኋላ በሚኖሩን ውድድሮች ግን ከ1-3 ባለው የውጤት ደረጃ በማጠናቀቅ የመጨረሻዎቹ ግጥሚያዎች ላይ ደግሞ ባህርዳር ላይ የሚደረግበት እድሉ ስላለ ሊጉን በሻምፒዮናነት እንደምናጠናቅቅ ነው”፡፡
ባህርዳር ከተማ ካለው ወቅታዊ አቋም አኳያ በእርግጠኝነት ሻምፒዮና ይሆን እንደሆነ
“አዎ! በውድድሩ ላይ እንደታየነው ብዙ ጠንካራ ጎን ነው ያለን፤ ከዛም በመነሳት እልማችንን እናሳካዋለን”፡፡
ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ፋሲል ከነማ እየመራ ከመሆኑ አንፃር ሻምፒዮና ስለመሆን ሀሳባቸው
“ሻምፒዮና ለምን አንሆንም? ፋሲል ሊጉን ይምራ እንጂ በነጥብ እኛን ብዙ አልራቁንም፤ ብዙ ቡድኖችም በነጥብ አልተራራቁም፤ ከአንድ ጨዋታ ያልበለጠ የነጥብ ልዩነትም ነው በብዙዎቹ ቡድኖች መካከልም ያለን በዛ ላይ ፋሲል ከነማንም የምታገኝበት እድሉም ስላለ ሻምፒዮና በመሆኑ ላይ ብዙም ስጋቱ የለንም”፡፡
በዘንድሮው የውድድር ዘመን ክለባቸው ስለያዘው የተጨዋቾች ስብስብ
“በቤትኪንጉ ዘንድሮ የያዝነው የተጨዋቾች ስብስብ በአብዛኛው የአምናዎቹን ነው፤ የተወሰነ ተጨዋቾችንም ብቻ ነው የጨመርነው፤ ጥሩ ስብስብም ነው ያለን፤ በውጤት ደረጃ ከአቀድነው አንፃርና በሐዋሳ ከተማ እንደነበረን የውድድር ቆይታችን ቡድናችንን ስመለከተው ምንም ነገር ይከብደናል ብዬም አላስብም”፡፡
ስለ ቡድናቸው አሰልጣኝ
“ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ አይደለም ወደ እኛ ክለብ መጥቶ ከዛ በፊትም ባሳለጠነው የብሔራዊ ቡድን ላይም ሆነ ሰበታ ከተማን በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በያዘበት ወቅት ከአጨዋወት ቅርፅና ታክቲክ እንደዚሁም ደግሞ በሌሎችም ነገሮች ላይ ብዙ ነገሮችን እየቀየረ ያለ ምርጥ አሰልጣኝ ነው፤ እሱ የሚይዘው ቡድን ሁሌም ኳስ እንዲጫወት ይፈልጋል፤ ከኳሱ ውጪም በክፍል ውስጥ የሚሰጥህ ትምህርት በብዙ ነገሮች እንድትቀየርም ያደርግሃል፤ ወደ እኛም ቡድን ከመጣ በኋላ እያንዳንዱ ተጨዋች ኳሱን ይዘህ እንድትጫወት ይፈቅድልሃል፤ ከዛ ውጪም ተጨዋቾችን የሚይዝበትና ወደ አንድ የሚያመጣበትም መንገድ የተለየ ስለሆነ ይሄ ሁኔታ እሱን ለየት እንዲል ያደርገዋል”፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የሐዋሳ ከተማ ቆይታቸው ያስደሰታቸውና ያስከፋቸው ጨዋታ
“በጣም ያስደሰተኝ ግጥሚያ በጨዋታው ላይ ጥሩ ከነበሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች ጋር ያደረግነውና በባከነ ሰዓት ላይ ጎል አስቆጥረን ያሸነፍንበትን ነው፤ የተከፋንበት ጨዋታ ደግሞ ከአዳማ ከተማ ጋር በነበረን ጨዋታችን ላይ በመጀመሪያው አጋማሽ እንደ ቡድን ጥሩ ስላልነበርንና በሁለተኛው አጋማሽ ላይ ደግሞ ጥሩ ብንሆንም የተመራንበትን ውጤት ለመቀየር አለመቻላችንና ያልጠበቅነውን አይነት ሽንፈትም ስለደረሰብን ያ ግጥሚያ ያስቆጨኛል”፡፡
ቤትኪንጉን እስካሁን እንዴት እንደተመለከተው
“የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን የእስካሁን ጨዋታዎች እንዳየሁት ሁለት ግጥሚያን ስታሸንፍ ወደ ላይ የመምጣት ነገር ስላለ ይሄ ቡድን ሻምፒዮና ይሆናል፤ ይሄ ቡድን ደግሞ ይወርዳል ብለህ የምትናገርበት ሁኔታ ላይ አይደለም የምንገኘው፤ አብዛኛው ቡድኖች ተመጣጣኝ እና ጠንካራ አቋም ነው ያላቸው፤ በውጤት በኩልም አንገት ለአንገት ተያይዘው ይገኛል፤ ስለ ውድድሩ ብዙ ለማለትም የሁለተኛው ዙርን መጠበቅ የበለጠ ግድ ይላል”፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ጎልቶ የተመለከተው ተጨዋች
“የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር አምና እንዳሳየው አቋም አይነት ባይሆንም ያለፉትን የዘጠኝ ሳምንታት ጨዋታዎችን ስመለከት የፋሲል ከነማው በረከት ደስታ እስካሁን ጥሩ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል፤ ሊጉ ገና ከመሆኑ አንፃር በቀጣይ በርካታ ጨዋታዎች ላይ ደግሞ ሌሎችንም ጥሩና ጎልተው የሚወጡ ተጨዋቾችን የምንመለከት ይመስለኛል”፡፡
በባህርዳር ከተማ ውስጥ እያሳለፈ ስላለው የቡድኑ ቆይታ
“ወደ አንድ አዲስ ቡድን ውስጥ ስትገባ መላመዶች እስኪኖሩ ድረስ በጣም ልትቸገር ይችል ይሆናል፤ እኔን ግን ይህ ከባድ ነገር በባህርዳር ከተማ ቡድን ውስጥ ገጥሞኛል ብዬ አላስብም፤ ምክንያቱም የክለቡ ኳስ ይዞ የመንቀሳቀስ አጨዋወት ምንም እንኳን ከሜዳ ጥሩ አለመሆን ጋር ቢያስቸግርም ታክቲኩ ከእኔ ጋር አብሮ የሚሄድ ሆኖ ስላገኘሁት ነው”፡፡
ስለ አፍሪካ ዋንጫ የዋልያዎቹ ተሳትፎ
“በካሜሮን አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለውን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎን እንደተመለከትኩት ዋልያዎቹ በመጀመሪያው የኬፕቨርዴ ግጥሚያቸው ላይ ውጤቱ ተበላሸባቸው እንጂ በጥሩ ሶስተኝነት ወደ ተከታዩ ዙር ማለፍ ይችሉ ነበር፤ ኬፕቨርዴ በጨዋታው የተለየች ቡድን አልነበረችም፤ እኛ ወደ ቀጣዩ ዙር እንዳናልፍ በግጥሚያው አንድ ተጨዋች በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቱና በጎዶሎ ልጅ መጫወታችን ጎድቶናል፤ ከካሜሮን ጋር በነበረን ጨዋታ ላይ ደግሞ በመጀመሪያው አጋማሽ እኛ ጥሩ ነበርን፤ ጎል ማስቆጠርም ችለናል፤ ኳስን ከበረኛ አንስተን ፖሰስ አድርገን ለመጫወት እንሞክርም ነበር፤ ወደ እነሱ ሜዳ የገባንበትም ሁኔታ ነበር፤ በሁለተኛው አጋማሽ ላይ ግን የቡድኑ አሰልጣኝ የራሱ የሆነ የአጨዋወት እቅድ ቢኖረውም እኔ አንድ ተጨዋች ያን አጋማሽ በሁለት ስኪመር ተጨዋቾች ብንጠቀም ኖሮ የከፋ ሁኔታ አይገጥመንም ብዬ ነው የማስበው፤ በጨዋታው ሆኖም ግን እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ላይ በሄድንበት የጨዋታ ቴምቦ ልንንቀሳቀስ ስላልቻልንና የእነሱን የጨዋታ ቴምቦም እኛ ልንቆጣጠር ስላልቻልን ለሽንፈት ልንበቃ ችለናል፤ ለውጤት ማጣቱ የአሰልጣኝም የተጨዋችም ችግር አለ፤ ይሄን መቀበልም የግድ ይላል፤ በሶስተኛው የቡርኪናፋሶ ጨዋታ ላይ ደግሞ በእንቅስቃሴ ደረጃ እኛ ጥሩ ነበርን፤ ኳስን ይዘንም ተጫውተናል፤ ያም ሆኖ ግን ያመከነው የጎል እድል አለ፤ በእግር ኳስ ማሸነፍ ፣ መሸነፍና አቻ መውጣት ያለ ቢሆንም ቡድናችን ከእዚህ ውድድር ብዙ ነገርን ተምሯልና አሁን ለእኛ የሚበጀን በአፍሪካ ዋንጫው ላይ እንደከዚህ በፊቱ ረጅም ዓመት መጠበቅ ሳይኖርብን በየሁለት ዓመቱ መካፈል እንዳለብን ነው”፡፡
በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ለእሱ የቱ ሀገር ምርጡ እንደሆነ
“ጨዋታዎቹን እንደተከታተልኩት ምርጡ የውድድር ሀገር ሞሮኮ ነው፤ እነሱ ዋንጫውን የማንሳት እድሉም አላቸው፤ ሌላው ናይጄሪያዎችም ጥሩ ቢሆኑም አሁን ግን ከውድድሩ ሊሰናበቱ ችለዋል”፡፡
በአፍሪካ ዋንጫው ምርጡ ተጨዋችስ
“እንደ ቡድን ሞሮኮን ጥሩ እንዳልኩት ሁሉ በክለብ ደረጃ ደግሞ ለፒ. ኤስ ጂ የሚጫወተው አክራፍ ሀኪሚ ልክ እንደ መሐመድ ሳላና ሳዲዬ ማኔ ሁሉ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ይገኛልና እሱን ጭምር ነው ጥሩና ምርጡ ተጨዋች የምለው”፡፡