Google search engine

“ከሊጉ መውረዳችን አሳዛኝ ነው፤ ወደ ፕሪምየር ሊጉም ዳግም እንመለሳለን” ምንተስኖት ከበደ /መከላከያ/

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/


የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዛሬ ቅ/ጊዮርጊስ ከመከላከያ ባህር ዳር ከተማ ከወልቂጤ ከተማ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀመራል
የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን በገቢ ለማጠናከር ከዛ ውጪ ደግሞ ተወዳዳሪ ቡድኖች የራሳቸውን አቋም እንዲለኩበት ታስቦ የሚዘጋጀው ዓመታዊው የሲቲ ካፕ ዋንጫ ዘንድሮም ለ14ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ይኸው ውድድር ከዛሬ አንስቶም በድምቀት ይከናወናል፤ የሲቲ ካፑ ዋንጫ ሊጀመር የነበረው ባለፈው ሳምንት ቢሆንም በሀገሪቱ ከሚታየው የፀጥታ ችግር አኳያ ውድድሩ ለዛሬ ሊተላለፍ ችሏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዛሬ በይፋ ሲጀመርም የመጀመሪያ ተጋጣሚ ሆነው የሚቀርቡት ቡድኖች የምድብ አንድ ተፎካካሪ ክለቦች የሆኑት ተጋባዦቹ ባህር ዳር ከተማና ወልቂጤ ከተማ ሲሆኑ ጨዋታቸውንም ከ8 ሰዓት አንስቶ ያደርጋሉ፤ በቅዱስ ጊዮርጊስና በመከላከያ ክለቦች መካከል የሚካሄደው ሌላው የእዚህ ምድብ ተጠባቂ ጨዋታም ከቀኑ 10 ሰዓት አንስቶ ይከናወናል፡፡
የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫ የሌላው ምድብ ጨዋታም ነገ የሚቀጥል ሲሆን ከምድብ ሁለት በ8 ሰዓት ኢትዬ-ኤሌክትሪክ ከተጋባዡ ክለብ ወልዋሎ አዲግራት ጋር በ8 ሰዓት ጨዋታውን ሲያደርግ በ10 ሰዓት ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና ከሌላው ተጋባዥ ቡድን ሰበታ ከተማ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ የሚጠበቅ ሆኗል፡፡
የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ የዘንድሮ ውድድር ከፀጥታም ሆነ ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ውድድሩ በሰላም ተጀምሮ በሰላም የሚጠናቀቅበትን ነገር በሜዳ ላይ ለማሳየት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከየክለቦቹ የደጋፊ አስተባባሪዎች ጋር የቅድመ ዝግጅትን ውይይት ያደረጉ ሲሆን የእዚህ ዓመት ውድድርም በጥሩ መልኩ እንዲጠናቀቅም ሁሉም የስፖርት አፍቃሪም የየራሱን ድርሻ እንዲወጣም መልዕክት ሊተላለፍ ችሏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ /ሲቲ/ ካፕ ዋንጫን ጅማሬ በማስመልከት ከተሳታፊ ክለባት አንድ አንድ ተጨዋቾች ጋር ቡድናቸው በሚያደርገው ጨዋታ ዙሪያና ስለ ዘንድሮ አጠቃላይ የውድድር ዘመን የዝግጅት ጊዜ ቆይታቸው ያናገርናቸው ሲሆን ተጨዋቾቹም የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፤ ተከታተሏቸው፡፡

መከላከያ ከፕሪምየር ሊጉ ስለመውረዱ እና አሁን ላይ እያደረጉት ስላሉት የፕሪ ሲዝን ዝግጅት
“በመጀመሪያ የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ የሃገሪቱ ትልቅ ቡድን ሆኖና ይሄን ክለብም ለትልቅ ደረጃ ላይ እናበቃዋለን ብለን ተዘጋጅተን በመጨረሻ ያልጠበቅነውንና ቡድኑን የማይመጥን ወደታችኛው ዲቪዝዮን እንዲወርድ ያስቻለውን ውጤት በማስመዝገባችን በጣም ነው ያዘንነው፤ ስለፕሪ ሲዝን ዝግጅታችን በተመለከተ በቅድሚያ ዘንድሮ መውረድ የለም በሚልና የፕሪምየር ሊግም ተወዳዳሪ ናችሁ ተብሎ ስለተነገረን ለእዛ ነበር በጥሩ ሞራልና ፍላጎት ስንዘጋጅ የነበረው፤ በመሃል ግን ትንሽ ውዥንብሮች መጡና በታችኛው ሊግ ነው የምትጫወቱት ስንባል የሞራል ውድቀት ደርሶብን ነበር ስንለማመድ የነበረው አሁን ላይ ደግሞ በተቃራኒው ቁርጣችንን ስናውቅ ሞራላችንን ገንብተን በመምጣት ነው ጠንካራ የሚባለውን ዝግጅታችንን እየሰራን የምንገኘው”፡፡
መከላከያ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ነው ወደታችኛው ሊግ ሊወርድ የቻለው፤ ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ዳግም የምትመልሱት ይመስልሃል?
“አዎን፤ ይህን የምነግርህ እርግጠኛ ሆኜም ነው፤ የቡድናችን ሁሉም ተጨዋች ክለቡ በመውረዱ በከፍተኛ የቁጭት ስሜት ላይ ይገኛል፤ መከላከያ አሁን ላይ እየተዘጋጀ የሚገኘው ቡድኑን ለፕሪምየር ሊጉ ሊያሳልፉ የሚችሉ የተጨዋቾችን ስብስብ ይዞ ነው፤ ከዛ ውጪም በቡድኑ የቀረነው ብዙ ነባር ተጨዋቾችም ስላሉ የፕሪምየር ሊጉን የምንቀላቀል ይሆናል”፡፡
መከላከያ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ስለሚያደርግው የውድድር ተሳትፎ እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ስለሚያደርጉት የመክፈቻ ጨዋታ
“የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ የእዚህ አመት ላይ በታችኛው ሊግ ለመወዳደር ይዘጋጅ እንጂ እላይ በነበርንበት ሰአት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በተደጋጋሚም ሆነ ሁሌም ነው ጠንካራ ፉክክርን ያደርግ የነበረው፤ በውጤት ደረጃም ቢሆን በመሸናነፉ ላይ ቡድናችን እጅ የማይሰጥ ስለሆነ የሚቀራረብ እንጂ የሚራራቅ አይደለምና የዛሬውን ጨዋታ ለማድረግ ወደሜዳ የምንገባው እነሱን ለማሸነፍ ነው”፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ተሳትፎአችን በተመለከተም ይሄ ውድድር ለእኛ በጣሙን ነው የሚጠቅመን፡፡ ወቅታዊ አቋማችንን በሚገባ እንመለከትበታለን፤ የታችኛው ሊግ ውድድር ላይ በምን መልኩ መቅረብ እንደሚገባንም የሚያስመለክተን ጨዋታም ስለሚሆን በውድድሩ ላይ ጥሩ ውጤት ልናመጣ ዝግጁ ነን”፡፡
የመከላከያ የተጨዋቾች ስብስብን በተመለከተ
“የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ከፕሪምየር ሊግ አይወርድም የሚል ውሳኔ ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ ቡድናችን እስከ ብሄራዊ ቡድን ደረጃ የደረሱ ተጨዋቾችን በማሰባሰብ እና ጥሩ ብቃት ያላቸውንም ልጆች በማስቀረት ጥሩ ቡድንን ለመገንባት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኝ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ውሳኔው ተሽሮ እታች ነው የምትጫወቱት ሲባል የተወሰኑ ተጨዋቾች ለቀቁብን፤ ያም ሆኖ ግን የበፊቱ ቡድን ላይ የተሻሉ የሚባሉ ተጨዋቾችን ስላመጣንና ውል ያለባቸው ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾችም አሁን ላይ ስላሉን ስብስባችንን በተመለከተ ለምንወዳደርበት ሊግ በጣም የሚመጥን እና የተሻለ የሚባል ቡድንም ነው ያለን”፡፡
የመከላከያ ክለብ ውስጥ በቀጣይነት ምን ለመስራት እንደተዘጋጀና ስለቀጣይ ጊዜ የኳስ ህይወቱ
“የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ከሊጉ ለመውረዱ ሁላችንም የቡድናችን ተጨዋቾች በጣሙን ተጠያቂነት ያለብን በመሆኑ ያ የቁጭት ስሜት በእያንዳንዳችን ውስጥ ሊፈጠርብን ችሏል፡፡ የመከላከያ መውረድ ሁላችንንም የታሪክ ተጠያቂ ያደረገን በመሆኑም ያን ቁስል አሽረን ክለቡን ዳግም የፕሪምየር ሊጉ ተወዳዳሪ ለማድረግ ተዘጋጅተናል፤ እኔም እንደቡድኑ ተጨዋችነቴ የሚቻለኝን ጥሩ ግልጋሎት ለማበርከት ዝግጁ ሆኛለሁ”፡፡
የመከላከያ ክለብ በስኳዱ ይዞት ከነበረው የተጨዋቾች ስብስብና ካሳካቸው ሌሎች ድሎች አኳያ ከሊጉ መውረድ ነበረበት
“በፍፁም፤ ግን እግር ኳስ ሆነና ወረድን፤ ከፕሪምየር ሊጉ ለመውረዳችን ዋነኛ ምክንያቶች ብዬ የምጠቅሳቸው በጣሙን የምንዘናጋ እና ቸልተኛ በመሆናችን ነው፤ የእግር ኳስ ጨዋታ ዛሬ ነገ የምትለው ነገር አይደለም፤ የየእለቱን ጨዋታ ማሸነፍ ይኖርብሃልና ይሄን ነው ማለት የምፈልገው”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: