Google search engine

“ከመቐለ ጋር የሚኖረን ጨዋታ ውጤቱ ከእነሱ ይልቅ ለእኛ በጣም አስፈላጊያችን ስለሆነ እናሸንፋቸዋለን” የኢትዮጵያ ቡናው ጠንካራ የተከላካይ ስፍራው ተጨዋች አህመድ ረሺድ /ሺሪላ/

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/


በነገው ዕለት ክለባቸው ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ የሚመዘገበው ውጤት ለእነሱ በጣም አስፈላጊያቸው እንደሆነና ጨዋታውንም እንደሚያሸንፉ አስተያየቱን ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ መሸሻ ወልዴ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል፡፡
ሊግ ስፖርት ጋዜጣ ከአህመድ ረሺድ ጋር ሌሎችንም ጉዳዮች በማንሳት ጥያቄዎችን ያቀረበችለት ሲሆን ተጨዋቹም የሚከተሉትን ምላሾች ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፡፡


ሊግ፡- 1440ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በሳምንቱ መጀመሪያ ይከበራል፤ ፆሙ እንዴት ነበር?
አህመድ፡- በመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ ለሚከበረው የኢድ አልፈጥር በዓል እስካሁን ስንፆም የነበረው ፆም በጣም ጥሩ የነበረ ሲሆን ይህም ፆም በገደብ ደረጃ ዕድሜያቸው ከ7 ዓመት አንስቶ ያሉትን የእምነቱን ተከታዮች እንዲፆሙም የሚያደርግ ስለሆነ አሁን ላይ ፆሙን በሰላም ልናጠናቅቅ ከጫፍ ደርሰናል፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ተጨዋች ከመሆንህ አንፃር የኢድ አልፈጥር ፆሙ እንዴት ነበር?
አህመድ፡- ፆመኛ ሆነህ እግር ኳስ መጫወት በጣም ቢከብድም በእምነትህ ጠንካራ ከሆንክ ግን ፆሙ ሁሌም ብርታት ነው የሚሆንህና እኔም ምንም ነገር ሳይከብደኝ ነው እስካሁን ድረስ እየፆምኩ ኳሱን እየተጫወትኩኝ የምገኘው፡፡
ሊግ፡- የኢድ አልፈጥር በዓልን አስመልክተህ እንኳን አደረሳችሁ ማለት የምትፈልገው?
አህመድ፡- ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1440ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ በዓሉም የሰላምና የደስታ ይሁንላችሁ እላለው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በዘንድሮው የፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎ ውጤታማ መሆን አልቻለም፤ ከዚህ በኋላ ምን ማድረግን ያስባል?
አህመድ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዓመቱ የውድድር መክፈቻ ላይ ሲጀመር የእኛ ቡድን ዋንኛው እቅድ የነበረው ሻምፒዮና ለመሆን ነበር፤ ያም ሆኖ ግን በተለያዩ ምክንያቶችና በራሳችን ችግሮች ውጤቱ ሳይሳካልን ቀርቷል፤ እየተመዘገበው ያለው ውጤትና ያለንበት ደረጃም ለቡድናችን ፈፅሞ የማይመጥነው ነውና ቢቻል እንኳን ይሄን ውጤት በተወሰነ መልኩ ልናሻሽለው የግድ ይለናል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡናን ውጤት እናሻሽለው ስትል የት ድረስ በመጓዝ ነው?
አህመድ፡- አሁን የምንገኝበት ደረጃ በርካታ ክለቦች ወደተከማችሁበት የወራጅ ቀጠናው አካባቢ ነው፤ ይሄ ስፍራም ለእኛ ፈፅሞ ስለማይገባን የዘንድሮውን ውድድር ቢያንስ በቀሪዎቹ ጨዋታዎች እስከ 5ኛ ያለውን ስፍራ ይዘን ለማጠናቀቅ ነው ጥረትን የምናደርገው፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና እንዲህ ያሉ ውጤቶች ብዙም ተቀባይነት የላቸውም፤ ከዚህ ተነስታችሁ ሌላ ያሰባችሁት ነገር አለ?
አህመድ፡- አዎን፤ ይገባኛል፤ ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ከዋንጫ በስተቀር ሌሎች የሚመዘገቡ ውጤቶች ብዙም ተቀባይነት የላቸውም፤ ዘንድሮም ይህን የሊግ ዋንጫ እናነሳለን ብለን አልተሳካልንም፤ ከዚህ በኋላ አሁን ላይ እኛ እያሰብን የምንገኘው ቢያንስ የጥሎ ማለፉን ዋንጫ እንኳን አንስተን ደጋፊውን ማስደሰት እንዳለብን ነው፡፡ ይሄን ዋንጫ ለማንሳት ደግሞ አሁን ባለንበት ሁኔታ መቀጠል የለብንምና በዚህ ላይ ወደ ጥሩ ስነ-ልቦና በመምጣት ዋንጫውን ማንሳት የግድ ይለናል፡፡
ሊግ፡- የመቐለ 70 እንደርታን የምትፋለሙበት የሊጉ ጨዋታ ነገ በአዲስ አበባ ስታድየም ይካሄዳል፤ ለጨዋታው በምን መልኩ ነው የተዘጋጃችሁት? ምን ውጤትስ ትጠብቃለህ?
አህመድ፡- ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር የሚኖረን የእሁዱ ጨዋታ እንደሌሎች ግጥሚያዎች ሁሉ የምንጠብቀው ነው፤ ለእነሱ ብለንም የተለየ ዝግጅትን አላደረግንም፤ የሁለታችን የእርስ በርስ ጨዋታም ውጤቱ እነሱ ለዋንጫው ፉክክር ከመጫወታቸው አንፃር እኛ ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው አካባቢ በፍጥነት ለመራቅ የምናደርገው ስለሆነ ጥሩ ፉክክር የሚደረግበትም ነው፤ የዚህ ጨዋታ ውጤትም ከመቐለ ይልቅ ለእኛ በጣም አስፈላጊያችንም ስለሆነ መቐለ 70 እንደርታዎችን እናሸንፋችኋለን፡፡
ሊግ፡- ለመቐለ 70 እንደርታም እኮ ውጤቱ በጣም አስፈላጊያቸው ነው….?
አህመድ፡- ይሄን ሳላውቅ ቀርቼ አይደለም፤ የእሁዱ ጨዋታ ውጤት ከእነሱ በተሻለ ለእኛ በጣም ያስፈልገናል ያልኩት የቡድናችን የነጥብ ቁጥር ከዋንጫው ፉክክር ይልቅ ለወራጆቹ በጣም ቅርብ በመሆኑና ይሄን ጨዋታ ማሸነፍ መቻል ደግሞ ቡድናችንን ለቀጣዮቹ ጨዋታዎችም በስነ-ልቦናው ደረጃ በጣም ከፍ የሚያደርገው ስለሆነም ነው ስለቡድናችን ለቀረበልኝ ጥያቄ ምላሼን የሰጠሁት፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፉክክርንን እንዴት ተመለከትከው? በአንተ እይታስ ማን የተሻለ ቡድን ነው?
አህመድ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ጨዋታዎች በሜዳ ላይ ውጤትን ለማምጣት ከሚታየው ሁኔታዎች አንፃር ስመለከተው የክልሎች የበላይነት የታየበት እንጂ ጠንካራ ፉክክር የተደረገበት ነው ብዬ ለመናገር አልደፍርም፤ ከዛ ይልቅ በአብዛኛው እኔ ያየሁት የቱም ቡድን ክልል ሄዶ ማሸነፍ እንደማይችል እና ግጥሚያዎቹ ሁሉ ስጋት ሲሆኑበት መመልከት ነው፤ በጨዋታውም ስንት አገባለው ሳይሆን ስንት ሊገባብኝ ይችል ይሆን በሚልም ተጨንቆ የሚጫወት መሆኑን ታዝቤያለው፤ እንዲህ ባለ ሁኔታም ዋንጫውን ለማንሳትም ክለቦች አንገት ለአንገትም ሲያያዙ አይቼ አላውቅምና በሜዳ ላይ ካለው ፉክክር አንፃር የዘንድሮ ውድድር ጠንካራ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ያም ሆኖ ግን በዘንድሮ የውድድር ዘመን ቆይታ ለእኔ በሜዳ ላይ የኳስ ፍሰት እንቅስቃሴውም ሆነ በውጤታማነቱ የተሻለ ቡድን ብዬ አድናቆት የምሰጠው ክለብ ፋሲል ከነማን ነው፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
አህመድ፡- የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ላይ እያስመዘገበው ያለው ውጤት ክለቡን የማይመጥነው እንደሆነ ሁሉም ይስማማበታል፤ ይሄ ውጤት በእኔ የተጨዋችነት ዘመን ይመዘገባል ብዬም አላሰብኩም ነበር፤ መሆን መቻሉ ግን ጥሩ ያልሆነ ስሜት እንዲሰማኝ አድርጓል፤ ለደጋፊዎቻችን ጥሩ ነገር ሰርተን ልናስደስታቸው ተዘጋጅተን ነበር፤ ግን ሳይሳካልን ቀረ፤ በኳስ ይሄ ያጋጥማል፤ ለደጋፊው የሚገባውን አልሰጠነውም፤ በውጤት ብናስከፋውም ሁሌም ግን ከጎናችን ናቸው፤ ስለዚህም ለእነሱ ልዩ ምስጋናና ክብር በመስጠት በቀሪዎቹ ጨዋታዎቻችን ላይ እንደዚሁም ደግሞ በጥሎ ማለፉ ጨዋታ ውጤታማ ሆነን ልንክሰው ነው የሚገባን፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P