Google search engine

“ከምጫወትበት ክለብ ጋር ሻምፒዮና እስካልሆንኩኝ ድረስ ውጤታማ ተጨዋች ነኝ ብዬ አላስብም” አንተነህ ተስፋዬ

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች አንተነህ ተስፋዬ በአሁኑ ሰአት የድሬዳዋ ከተማ ክለብን በመልቀቅ በዚህ ሰዓት ክለብ አልባ የሆነ ተጨዋች ሲሆን በቅርቡ ግን አዲሱን ቡድኑን ይፋ ያደርጋል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጨዋችነት ቆይታው ላይ ለአርባምንጭ ከተማ፣ ለሲዳማ ቡናና ለድሬዳዋ ከተማ ክለቦች የተጫወተው ይኸው ተጨዋች በእዚህ ሰአት ክለብ አልባ ሊሆን የቻለው ለመከላከያ በፕሪምየር ሊጉ ለመጫወት ፊርማውን ካኖረ በኋላ መከላከያ የከፍተኛው ሊግ እንጂ የፕሪምየር ሊጉ ተወዳዳሪ አይደለም የሚል መረጃ ከእግር ኳስ ፌዴሬሽን በመስማቱ ውሉን አስቀድዶ ነው ቡድኑን ሊለቅ የቻለው፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለቻን የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታው ሩዋንዳን ለመግጠም ወደ ኪጋሊ ከማምራቱ በፊት አንተነህን ስለብሄራዊ ቡድናችንና ከራሱ የእግር ኳስ ተጨዋችነት ህይወት ጋር አያይዘን ጥያቄዎችን ያቀረብንለት ሲሆን ተጨዋቹም ምላሹን እንደሚከተለው ሰጥቶናል፡፡

ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከመመረጥህ ባሻገር የተጫወትክባቸውም አጋጣሚዎች አሉ፤ እነዛን ስሜቶች በምን መልኩ ነው የምትገልፃቸው?
አንተነህ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተመራጭ ተጨዋች ሆነህ ሃገርህን አገልግላት፤ ጥቀማት የሚል ጥሪው በተደጋጋሚ ሲደርስህ ሁሌም ነው ደስ የሚልህ፤ እኔም እነዛን እድሎች ያገኘው ተጨዋች በመሆኔ አሁንም ድረስ በውስጤ ጥሩ ስሜት ነው እየተሰማኝ የሚገኘው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተመራጭ ተጨዋች በማትሆንበት ጊዜ እና የቡድኑም አባል ሆነህ የመሰለፍ እድሉን በማታገኝበት ሰዓት ያለህስ ስሜት ምንድነው የሚመስለው?
አንተነህ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች በሚኖረው በማናቸውም ሰአት ለሃገሬ የመመረጥ እድሉን ባላገኝም ባልሰለፍም በእኔ ውስጥ የሚፈጠር የቁጭት ስሜት ፈፅሞ የለም፤ ምክንያቱም ወደ ብሄራዊ ቡድን የሚመጡ አሰልጣኞችም ሆኑ የኮቺንግ ስታፎች በእኔ ብቃት ላይ እምነት ከሌላቸው አለመምረጣቸው ተገቢ ነው ብዬ ስለማምን፤ ለብሔራዊ ቡድን ከተመረጥኩ እሰየው ብዬ እቀበላለሁ፤ ካልተመረጥኩ ደግሞ መጪውን ጊዜ ለመመረጥ እጠብቃለሁ ማለት ነውና እንዲህ ያሉ ነገሮች ብዙ ጊዜ ስላላጋጠሙኝ ሁኔታዎቹን ሁሉ እንደ አመጣጡ የምቀበል አይነት ተጨዋች ነኝ፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተደጋጋሚ ሸንፈቶችን እያስተናገደ ነው፤ ህዝቡም እየተቃወማችሁ ነው፤ ምን ይሻላል?
አንተነህ፡- አዎ፤ ሽንፈቱ ተደጋግሟል፤ በሽንፈቱም ህዝቡም ሆነ እኛ የቡድኑ ተጨዋቾች በጣም ተናደናል፤ ስንሸነፍም ህዝቡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተቀውሞናል፤የህዝቡ መቃወም ደግሞ ተገቢ እና ልክም ነው፤ ለውጥ የሚመጣው መቃወም ሲኖርና ከዛ ተነስተን ማስተካከልም ስንችል ነው፤ በቀጣዩ ጊዜ የቡድናችንን የውጤታማነት ጉዞ የተሻለ ለማድረግ ጥሩ ነገርን ሰርተን በመምጣት የስፖርት አፍቃሪውን ማስደሰት እና ከሜዳ የራቀውንም ደጋፊ መመለስ ይጠበቅብናል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሐራዊ ቡድን የአሁን ላይ ሽንፈት ምክንያቱ ምንድነው ትላለህ?
አንተነህ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በተደጋጋሚ ጨዋታዎች ሽንፈትን እያስተናገደ ያለበት ዋነኛ ምክንያት በአዲስ ኮች ለመመራት መቻሉ አሰልጣኙም የራሱን የሆነ አዲስ አጨዋወት ቡድኑ ውስጥ ለመፍጠር እያደረገ ያለውን ጥረት እኛ ተጨዋቾች በፍጥነት ልንተገብር ስላልቻልን ነው፤ እንዲህ ያሉ የውጤት ማጣቶች ደግሞ አይደለም በእኛ ሃገር ትልቅ የሚባሉ አሰልጣኞችም ወደ አውሮፓ ሲመጡና ሲያሰለጥኑ የሚያጋጥማቸው ነውና እኛም ጋር ይሄ ደርሷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በእዚህን ወቅት ላይ በተለይ ኳስ ይዞ ለመጫወት ሙከራን ቢያደርግም ከፍተኛ ጎል የማስቆጠር ችግር አለበት ይሄ አዲስ ከሚከተለው አጨዋወት አንፃርም ውጤቱን አሳጥቶታል፡፡ ስለዚህ ቡድኑ በአጨዋወት ደረጃ በደንብ ሲግባባና ሲዋሃድ የተሻለ ነገርን የማያመጣበት አንዳችም ምክንያትም የለም ብዬም ነው የማስበው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ለአርባምንጭ ከተማ፣ ለሲዳማ ቡና እና ለድሬዳዋ ከተማ ለመጫወት ችለሃል፤ በእነዚህ ቡድኖች ቆይታህ ደስተኛ ነበርክ?
አንተነህ፡- አዎን፤ በተለይ ደግሞ በሲዳማ ቡና፤ ምክንያቱም እዛ እያለሁ ለሻምፒዮናነት እስከመፎካከርም ደርሰናልና፡፡
ሊግ፡- ባሳለፍከው የእግር ኳስ ህይወት ውጤታማ ተጨዋች ነኝ ብለህ ታስባለህ?
አንተነህ፡- በፍፁም፤ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጨዋቾች ቆይታዬ ላይ የነበርኩባቸው ክለቦች ውስጥ እንደግል ጥሩ ጊዜን ለማሳለፍ ብችልም ከእነርሱ ጋር ሻምፒዮና እስካልሆንኩ ድረስ ውጤታማ ተጨዋች ነኝ ብዬ አላስብም፡፡ አንድ ተጨዋች ውጤታማ ነው የሚባለው የግድ የዋንጫ ክብሮችን ሲያገኝ ነውና በቀጣዩ ጊዜ ይሄንን ለማሳካት ነው ጥረቴን የማደርገው፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳሱ ቆይታህ ምን አስደስቶሃል? ምንስ አስከፍቶሃል?
አንተነህ፡- የሚያስደስተኝ የተሻለ ነገርን ስንሰራና ባለድል መሆን ስንችል ነው፤ የሚከፋኝ ደግሞ ውጤትን ስናጣ ነው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ ላይ የትኞቹን ተጨዋቾች ታደንቃለህ?
አንተነህ፡- የቅርብ ጓደኛዬን ቢያድግልኝ ኤልያስንና ደጉ ደበበን ነው የማደንቀው፤ ሁለቱም ለእኔ በቦታዬ ከመጫወታቸው ባሻገር ከፍተኛ መነሳሳትን የፈጠሩልኝ ተጨዋቾች በመሆናቸው ቀዳሚ ምርጫዎቼ ሆነዋል፡፡
ሊግ፡- የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ላይ የማን ደጋፊ ነህ? ቡድኑ ሲያሸንፍ እና ሲሸነፍ ምን አይነት ስሜት አለህ?
አንተነህ፡- የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ ነኝ፤ ቡድኑ ሲያሸንፍ ደስ ይለኛል፡፡ ሲሸነፍ ደግሞ እንደሌላው እንደሚናደድ አይነት ደጋፊዎች አይደለሁም፤ በዛ ውስጥም የለሁበትም፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሩዋንዳን ነገ እሁድ ይፋለማል፤ ምን ውጤትን ትጠብቃለህ?
አንተነህ፡- የሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን ጋር የሚኖረን የነገው ጨዋታ ለእኛ አንድ እና አንድ እድላችን የሚሆነው ማሸነፍ ብቻ ነውና ይሄን ለማሳካት ነው ወደ ስፍራው ያመራነው፤ ከኡጋንዳ ጋር በነበረን የአቋም መለኪያ ጨዋታ ቡድናችን ቢሸነፍም ጥሩ ቅርፅን የያዘ ቡድን መሆኑን አሳይቷል፡፡ ስለዚህ ነገ ጥሩ ውጤትን ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ከእኛ ጠብቁ፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ቆይታህ አንተን ያስቸገረህ አጥቂ አለ?
አንተነህ፡- ከአጥቂዎች ማንም እኔን ያስቸገረኝ የለም፤ ምክንያቱም ታግዬም ሆነ ሳልታገል ኳስን በቀላሉ የምወስድባቸው ተጨዋች ስለሆንኩ፡፡
ሊግ፡- እንደ እግር ኳስ ተጨዋችነትህ የትኛው ምግብ የአንተ ቀዳሚ ምርጫህ ነው?
አንተነህ፡- ፓስታ ነዋ! በጣምም ነው የምወደው፡፡
ሊግ፡- ከደቡብ ክልል ተወላጅነትህ አኳያ ጥሬ ስጋንስ እንዴት ዘለልከው?
አንተነህ፡- ጥሬ ስጋን ለመብላት ሰዎች አስገድደውኝ ካልወሰድኩኝ በስተቀር እዛ ላይ ብዙም አይደለሁም፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጨዋቾችነት ቆይታህ ላይ እነማንን በተቃራኒነት ስትገጥም ደስ ይልሃል?
አንተነህ፡- የሃገሪቱ ትላልቅ ቡድኖችን ስንገጥም፤ ያኔ ጥሩም ስሜት ነው የሚሰማኝ፡፡
ሊግ፡- ከሜዳ በቀይ ካርድ ወጥተህ ታውቃለህ?
አንተነህ፡- በፍፁም፤ በጣም ጥቂት ቢጫ ካርዶችን ግን ማየቴን አስታውሳለሁ፡፡
ሊግ፡- አንተነህ እንዴት ትገለፃለህ?
አንተነህ፡- ስለ እኔ ሌላ ሰው ቢያወራ በጣም ደስ ይለኛል፤ ራስህ ተናገር ከተባልኩ ደግሞ በጣም ዝምተኛ ሰው ነኝ፡፡ ሰው ከቀረበኝ እቀርባለሁ ሰውንም መንካት አልፈልግም፡፡ እንዲነኩኝም አልፈልግም፡፡ ከዛ ውጪ ሰው ሲያስቀይመኝ የማለፍ አይነት ባህሪም አለኝ፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳሱ ላይ ማሻሻል የምትፈልገው?
አንተነህ፡- የእግር ኳስ ተጨዋችነት ብቃቴ ላይ ማሻሻል የምፈልገው ኳስ በእኛ ቡድን የተከላካይ ስፍራ ተጨዋቾች ቁጥጥር ስር ሲውል ቡድናችን እንዲያጠቃ ከመፈለግ ኳስን ወደፊት ገፍቼ እንድጫወት ነው፤ ይሄን አሰልጣኞች ስለነገሩኝ አሻሽላለሁኝ፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P