በመሸሻ ወልዴ
ቅዱስ ጊዮርጊስ በሳምንቱ መጨረሻ ከተጋጣሚው ተሽሎ እና ጥሩ ሆኖ በዋለበት የሜዳው ላይ ጨዋታ ሲዳማ ቡናን ተፋልሞ 6-2 አሸንፏል፤ ይህ ውጤትም ክለቡን ወደ መሪነት ደረጃው ላይ ያመጣው ስለሆነም የቡድኑን ተጨዋቾች እና ደጋፊውን ጮቤ ሊያስረግጠውም ችሏል፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን ሲረታ አብዛኛው የቡድኑ ተጨዋቾች ጥሩ እንቅስቃሴን ያሳዩ ሲሆን በተለይ ደግሞ የቡድኑ የፊት መስመር ተጨዋቾች አቤል ያለው እና ጌታነህ ከበደ የነበራቸው ጥምረትም ጥሩ ከመሆኑ አንፃር ሁለት ሁለት የድል ግቦችም ሊያስቆጥሩ መቻላቸው ከፍተኛ አድናቆት እንዲቸራቸውም አድርጓቸዋል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ሲዳማ ቡናን ባሸነፈበት ጨዋታ በሜዳ ላይ ስለነበረው እንቅስቃሴ፣ ቡድናቸው የመሪነት ስፍራውን ስለመቆናጠጡ፣ በቡድናቸው ዙሪያ እና በራሱ የግል ብቃት እና ሌሎችን ተጨማሪ ጥያቄ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አቅርቦለት በሚከተለው መልኩ ምላሹን ሰጥቷል፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን በሰፊ ግብ ልዩነት አሸንፎ በመሪነት ላይ ተቀምጧል፤ እነሱን በእዚህን ያህል የግብ ልዩነት እናሸንፋለን ብላችሁ ጠብቃችሁ ነበር?
አቤል፡- በፍፁም፤ ብዙ ጎል እናስቆጥራለን ብለን ባናስብም ጨዋታውን በድል አድራጊነት እንደምናጠናቅቅ ግን በጣም እርግጠኞች ነበርን፤ ከሲዳማ ቡና ጋር በነበረን ጨዋታ እኛ ጠብቀን የነበረው እነሱ ወልዋሎ አዲግራት ላይ 5 ጎል አስቆጥረው ከመምጣታቸው አኳያ በጨዋታው እንደሚፈትኑን እንጂ በርካታ ግቦችን አስቆጥረንባቸው እንደምናሸንፋቸው አልነበረም፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን በሰፋ የጎል ልዩነት ለማሸነፍ የቻለበት ጠንካራ እና ጥሩ ጎኑ ምንድን ነበር?
አቤል፡- በመጀመሪያ ሁላችንም ለጨዋታው ወደ ሜዳ የገባነው በከፍተኛ ወኔና የአሸናፊነት መንፈስ ነበር፤ አስቀድመንም ባቀድነው መሰረት ሶስቱን የባለፉት ሶስት ተከታታይ የሜዳችን ላይ ጨዋታዎችን የግድ ማሸነፍ አለብን በሚል ስሜት ስለመጣንና ያለንንም ነገር አውጥተን ስለተጫወትን ከፈጣሪ እርዳታ ጋር በመጨረሻ አሸናፊ ልንሆን ችለናል፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉ መሪ ሆኗል፤ በዚህ ጉዞው ይቀጥላል? ሻምፒዮናስ ይሆናል?
አቤል፡- አዎን፤ ለዚህ ምንም ጥያቄ የለውም፤ ምክንያቱም አሁን ላይ በአንደኛ ደረጃ መቀመጣችን ጊዜ የሚፈጅ እንደሆነ እንጂ መሪ እንደምንሆን አስቀድመንም እናውቀው ነበርና ጉዞአችን አሁንም ቢሆን ይቀጥላል፤ በእዚህ ስፍራ ላይ ስንሆን ደግሞ ሁሉም ቡድኖች እኛን የሚፈሩበት ሁኔታም ስላለ የመሪነት ግስጋሴያችን አሁንም ሆነ ወደፊት አብሮን ይኖራል፤ መሪ ሆነንም ሻምፒዮና የምንሆነው እኛው ነን፡፡
ሊግ፡- ሲዳማ ቡናን በረታችሁበት ጨዋታ ሁለት ጎሎችን አስቆጥረሃል፤ ሁለት የግብ ኳሶችንም አቀብለሃል፤ ቀኑ ለአንተ ልዩ ነበር ማለት ይቻላል?
አቤል፡- በጣም እንጂ፤ ለአንድ ተጨዋች ጎል ማግባት እንደዚሁም ደግሞ ለቡድኑም ጓደኞቹ ኳስ ማቀበል የተለየ የደስታ ስሜትን ነው የሚፈጥርለትና ሲዳማ ቡናን በተፋለምንበት ጨዋታ የእኔ በጨዋታው ላይ ጥሩ ሆኖ መዋል፣ ጎል ማግባት እና የግብ ኳስ ማቀበል መቻሌ ቀኑን በተለየ መልኩ እንድመለከተው አድርጎኛል፤ ከሲዳማ ቡና ጋር ስንጫወት ደግሞ ከዚህ ቀደምም የቀናኝ እና ሀትሪክ የሰራሁበት አጋጣሚውም ስለነበር የእሁዱ ጨዋታ ያንን ፍልሚያ እንዳስታውስም ጭምር አድርጎኛል፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባልተለመደ እና ባልተጠበቀ መልኩ የሊጉን ዋንጫ አጥቷል፤ ይሄንን ዋንጫ የማጣት የቅርብ ጊዜ ረሃቡን ዘንድሮ የምታስታግሱለት ይመስልሃል?
አቤል፡- በሚገባ! እንደዛም ለመሆን ነው በዚህ ዓመት ቆርጠን የተነሳነው፤ ስለዚህም የእዚህ አመት የሊጉ ዋንጫ ወደ ቀድሞው እና ድል ወደለመደበት ክለቡ እና ቤቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጥታ ያመራል፡፡
ሊግ፡- የቅዱስ ጊዮርጊሱ ጌታነህ ከበደ በሰሞኑ በተለይ ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበራችሁ የሸገር ደርቢ ጨዋታ ላይ ስሜታዊ በመሆን ጭምር አንተን ጨምሮ ሲናገር ተስተውሏል፤ ያን ዕለት ምንድን ነበር ሲላችሁ የነበረው?
አቤል፡- የእውነት ነው፤ ያን ዕለት ጌታነህ ለቡድኑ ሲል እንጂ ሌላ ከምን ነገር አኳያ አይደለም አንዳንድ ነገሮችን ሲናገር የነበረው፤ እሱ ወደ ኋላ መሸሽ ሳይሆን ወደፊት ማጥቃት እንዳለብንም ነበር በተደጋጋሚ ጊዜ ሲናገር የነበረው፤ ሁሉም ተጨዋችም ያንን ካወቀ በኋላ ነው በጥሩ ስሜት ላይ ሆኖ በመጫወት እና ያለውንም ነገር በማውጣት ቡድኑን ለድል እንዲበቃ ያደረገውና ሁላችንም ጌታነህ የሚናገረውን ነገር በክፋት እንዳልሆነ ስለምናውቅ የእሱ አነሳሽነት በጣም ጠቅሞናል፤ እኔ ደግሞ ጌታነህን ከበፊት ጀምሮም አውቀዋለሁና ያንን ያህል የከፋ ነገርንም አይናገርም፡፡
ሊግ፡- ከጎሎች ርቆ የነበረው ጌታነህ ከበደ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ጎሎችን ማስቆጠር ጀምሯል…..?
አቤል፡- ይሄ እኮ የታወቀ ነው፤ እሱ ጎል ማግባት ከጀመረ እንደማያቆምም ነው የምናውቀው፡፡ በዚህ ደግሞ እኔም ሆንኩ የቡድናችን ተጨዋቾች ከጎኑ ሆነንም እንረዳዋለን፡፡ ከሲዳማ ቡና ጋር በነበረን ጨዋታም ጎል እንዲያስቆጥር የረዳሁት የእሱን ምርጥ ተጨዋችነት ስለማውቅም ነውና ይሄ የምንወደው አጥቂ ወደ ጎል አግቢነቱ በመመለሱ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡
ሊግ፡- ለቅዱስ ጊዮርጊስ በመጫወት እና ጎሎችን በማስቆጠር ጥሩ ስምና ዝናን እያተረፍክ ነው፤ ከዚህ ብቃትህ አንፃር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ ትሆናለህ?
አቤል፡- አሁን ላይ ያንን ፈፅሞ አላስብም፤ ስለራሴም ስምና ዝናም ብዙ አልጨነቅም፤ እኔን ሁሌም የሚበልጥብኝም ከራሴ ዝናና ክብር ይልቅ የቡድኔ ሻምፒዮናነት ነውና አሁን ላይ ቅድሚያ ለዛ እየሰጠሁ ጊዜውን እየተጠባበቅኩ ነው የምገኘው፡፡
ሊግ፡- እንደ እግር ኳስ ተጨዋችነትህ የመጨረሻ ግብህና የአንተ ድርሻህ የት ነው የሚሆነው?
አቤል፡- የእግር ኳስን ስጫወት በዚህ ሃገር ላይ ብቻ ተወስኜ መቅረትን ፈፅሞ አልፈልግም፤ እንደማንኛውም ተጨዋች ከሃገር ወጥቶ በፕሮፌሽናል ደረጃ መጫወት የእኔ ህልምና እቅድ ስለሆነ ያንን ማሳካት እፈልጋለሁኝ፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉን ቀጣይ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ወደ ክልል ወጥቶ ይጫወታል፤ ከዚህ አንፃር ምን ውጤት የምታስመዘግቡ ይመስልሃል?
አቤል፡- ለዚህ ምንም ጥያቄ የለውም፤ የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ለሚፈልግ ቡድን እንዲህ ያሉ ጨዋታዎችን ማሸነፍ መቻል ለሻምፒዮናነት ይረዳዋልና ወደ ወልዋሎም ሆነ ወደ ጎንደር በመጓዝ የምናደርጋቸውን ጨዋታዎች በአሸናፊነት እንወጣቸዋለን፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ ቡድን ሊያርመው እና ሊያስተካክለው የሚገባ ነገር ምንድነው?
አቤል፡- በዋናነት ሁላችንም እንደ ቡድን ስንከላከል የትኩረት ማጣት ችግር ነበረብን፤ እንዘናጋለንም፤ አሁን ግን ይሄ ችግር ቀስ በቀስ እየተቀረፈ መጥቷልና ይሄ እኛን በጣም የሚጠቅመን ነው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን ስትጫወት ምን አይነት የጨዋታ ታክቲክ ይመችሃል?
አቤል፡- ሁሉም አሰልጣኝ የየራሱ አጨዋወት ቢኖረውም ለእኔ ግን ሁሌም የሚመቸኝ ብዙ ጎል የምናስቆጥርበት እና በተደጋጋሚ ጊዜም ቶሎ ቶሎ ጎል ጋር የምንደርስበትም አጨዋወትን ነው፡፡
ሊግ፡- ከባህር ማዶ ክለቦች የማን ደጋፊ ነህ?
አቤል፡- የማንቸስተር ዩናይትድ፡፡
ሊግ፡- ሊቨርፑል የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ከበርካታ ዓመታቶች በኋላ ሊያነሳ ተቃርቧል…..?
አቤል፡- የእዚህ ዘመን ዋንጫ ለሊቨርፑሎች የሚገባቸው ቢሆንም፤ ለእኔ ግን እንደ ማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊነቴ ዋንጫውን ማንሳታቸው ፈፅሞ አይመቸኝም፡፡
ሊግ፡- የቡድንህ አጋር እና ጓደኛህ ጌታነህ እኮ የሊቨርፑል ደጋፊ ነው፤ ለእሱ እንኳን ስትል…?
አቤል፡- አሁንም በድጋሚ የምልህ የሊቨርፑል ዋንጫ ማንሳት ለእኔ አይመቸኝም ነው፤ ከእሱ ማለትም ከጌታነህ ጋር እኮ በዚህ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ ጊዜም እያወራን ነው፤ የእሱ ቡድን እያስመዘገበ ካለው ከፍተኛ ውጤት አኳያ እየተዝናናብኝ እና እያበሸቀኝም ነውና እሱን ዘንድሮ ፈፅሞ አልቻልኩትምም፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ….?
አቤል፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች እንደ 12ኛ ተጨዋች ሁሌም ቢሆን ምርጥ ድጋፋችሁን እየሰጣችሁን ነው፤ ይሄ ድጋፋችሁም ወደፊት ይቀጥል፤ አሁን ላይ ሲዳማ ቡናን በጥሩ ጨዋታ ካሸነፍን በኋላ በመሪነት ደረጃ ላይ ልንቀመጥ በመቻላችን ለሁላችሁም የቡድኔ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎቻችን እንኳን ደስ አላችሁ ማለትን እፈልጋለው፡፡