Google search engine

“ከሳይንሳዊ ስልጠና እንውጣ ማለት ኤች አይ ቪ በሽታ በፌጦ ይድናል ብሎ ራስን እንደማሞኘት ነው” አቶ አሳየኝ ጥላሁን (በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን ስፖርትና ባህል ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት)

በአለምሰገድ ሰይፉ

ጥርስ የነቀለበትን ሙያ የተሰናበተው
በ1981 ዓ/ም ነው፤ ከእርምጃችን የጀመረው
የኳስ ክህሎት በኦሜድላ፣ ራስ ሆቴል፣ኢትኮባና
ባንኮች ክለብ የተጫወተው አሳየኸኝ ጥላሁን
ከምንም በላይ በ1978 ኦሜድላ እያለ ከነ
ተስፋዬ ፈጠነ ጋር አብሮ የተጫወተበትን ጊዜ
ትውስታ መቼም አይዘነጋውም፡፡
ያኔ በቀይ ወጥ ለክለባቸው ደም የሚለግሱ
ተጨዋቾችን ከዛሬዎቹ የመቶና የሁለት መቶ
ሺህ ወርሃዊ ደመወዝተኞች ጋር ማነፃፀር
ከባድ ነው ይላል፡፡ ከለውጡ በፊት በ1981
ከሃገር ወጥቶ ከ27 አመታት በላይ በስዊድን
ሃገር የሚገኘው ይኸው ጥበበኛ ተጨዋች
ዛሬም ድረስ ከስፖርቱ አልራቀም፡፡ በተለያያ
ጊዜ በርካታ ስልጠናዎችን በመውሰድ
በኖርዌይ የቢ ላይሰንስ ያገኘው አሳየኸኝ
አሁን ደግሞ በአውሮፓ የኢትዮጵያውን
ባህልና ስፖርት ፌዴሬሽንን በፕሬዝዳንትነት
እያገለገለ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው
አጭር የእረፍት ጊዜ ቆይታው ከሊግ ጋዜጣ
ማኔጂንግ ኤዲተር አለምሰገድ ሰይፉ ጋር
አጭር ቆይታ አድርጎ ወደሃገሩ ተመልሷል፡፡
ሊግ፡- በአውሮፓ የሚገኘው
የኢትዮጵያውያን ባህልና ስፖርት ፌዴሬሽን
እንዴት ተመሰረተ?
አቶ አሳየኸኝ፡- እውነቱን ለመናገር
እኔ የዚህ ፌዴሬሽን መስራች አይደለሁም፡
፡ በኖርዌይ የምንኖር ኮሚኒቲዎች ትንሽ
ስለነበርን የማህበሩ ምስረታ ላይ የእኔ ተሳትፎ
አልነበረም፤ ነገር ግን በወቅቱ ከኖርዌይ፣
ስዊዘርላንድና ከፊንላንድ የተውጣጣ
ስካንዴኔቭያን የሚባል ቡድን ስለነበረን በዚህ
ክለብ አማካይነት ተሳትፎ እናደርግ ነበር፡፡
ከዚህ በተረፈ ይህ ሃሳብ የተጠነሰሰው ቀድሞ
የብሄራዊ ቡድናችን ተጨዋቾች በነበሩት በእነ
ግርማ ሳህሌ አማካይነት ነው፡፡ አላማውም
በአውሮፓ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን በስፖርቱ
አማካይነት ማገናኘትና ማቀራረብ ነው፡፡
ሊግ፡- ፌዴሬሽኑ ከተመሰረተ ምን ያህል
ጊዜ አስቆጠረ? የውድድሩ ፎርማትስ ምን
ይመስላል?
አቶ አሳየኸኝ፡- እስካሁን 16 አመታትን
ተጉዘናል፡፡ ዘንድሮ በስዊዘርላንድ የሚዘጋጀው
ውድድር ለ17ኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው፡፡ ምንም
እንኳን የፕሮግራሙ አላማ ባህልና ስፖርት
የሚባል ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ
እየተደረገ ያለው የእግር ኳስ ውድድሩ ነው፡፡
በአንደኛና ሁለተኛ ዲቪዝዮን የተከፈለ ሲሆን
የህፃናትም ውድድር ይገኝበታል፡፡ በአንደኛ
ዲቪዝዮን ሃያ ቡድኖች የሚሳተፉ ሲሆን
በሁለተኛ ዲቪዝዮን ደግሞ አስር ቡድኖች
አሉ፡፡ በውጪ ሃገር ከሚገኙት በተጨማሪ
ከኢትዮጵያ ሁለት ቡድኖች በእንግድነት
ተጋብዘው በውድድሩ ላይ ይሳተፋሉ፡፡
ባለፉት ሁለት አመታት ከኢትዮጵያ
ኢትዮ-አበበ ቢቂላ ቡድን የተሳተፈ ሲሆን
አምና ደግሞ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና
ተጨዋቾች ቡድን በአውሮፓ በተካሄደው
አመታዊ ውድድር ላይ ተሳትፏል፡፡ ከዚህ
በተረፈ ዘንድሮ በስዊዘርላንድ ለሚደረገው
17ኛው ውድድር የቀድሞ ተጨዋቾች ሆነው
እንደ ክለብ ራሳቸውን ያደራጁና በአካዳሚ
ደረጃ የሚገኙ ቡድኖች እንድንጋብዛቸው
አመልክተዋል፡፡ እናም ይህ ጥያቄ እንዴት
ምላሽ ያገኛል? የሚለውን ነገር ጠቅላላ
ጉባኤው ተሰብስቦ የሚወስነው ይሆናል፡
፡ ለጊዜው ግን በየአመቱ ሁለት ቡድኖች
ከኢትዮጵያ እንዲሳተፉና አንድ ቡድን ደግሞ
ከሁለት ጊዜ በላይ መሳተፍ አይችልም
በሚለው አሰራራችን እየተጓዝን ነው፡፡
ይሄን ያደረግንበት ምክንያት ሁሉም እድል
እንዲያገኙ በማሰብ ነው፡፡
ከምንም በላይ ደግሞ ፌዴሬሽናችን
ኢትዮጵያ ለሚገኙ ቡድኖች የተሳትፎ
ግብዣ ሲያደርግ የተለያዩ መስፈርቶችን
በማስቀመጥ ነው፡፡ ከምንም በላይ ባሉበት
አካባቢ ማህበራዊ ሃላፊነትን መወጣት
የሚለው ቅድሚያ የሚሰጠው አካሄድ ነው፡፡
ይህም ማለት አካዳሚዎችን ማቋቋም፣ ሜዳ
መስራትና ታዳጊዎች ስፖርቱን ሊያዘወትሩ
የሚችሉበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት
የሚለው ነጥብ በድርቡ ይሰመርበታል፡፡
ሊግ፡- አሜሪካ ያለው ፌዴሬሽን በየአመቱ
በሚያዘጋጀው ውድድር ላይ ለኢትዮጵያ
ስፖርት ውለታ የፈፀሙ ግለሰቦችን
በእንግድነት ይጋብዛል፡፡ የእናንተስ ፌዴሬሽን
የዚህ አይነት አሰራርን ይከተላል?
አቶ አሳኸየኝ፡- በዚህ ረገድ አሜሪካ ያለው
ፌዴሬሽን በምስረታም ሆነ በልምድ ቀደምቶች
ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር እኛም እንደፌዴሬሽን
ከእነርሱ የምንወስደው ተሞክሮ ይኖራል፡፡
ከዚህ መነሻነትም ከአሁን ቀደም ለሃገራቸው
ስፖርት ትልቅ ውለታ ፅፈው ማለፍ የቻሉ
ግለሰቦችን በየአመቱ እየጋበዝን በፕሮግራሙ
ላይ እንዲታደሙ እያደረግን ነው፡፡ ወደፊትም
ይህ አሰራር የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም
እነዚህ ግለሰቦች ለሃገሪቱ ስፖርት የላቀ
ሚና ተጫውተው ሳለ በቀጣይ ህይወታቸው
ምንም ሳይገኙ ያላቸውን ሰጥተው እያለፉ፣
አብዛኛዎቹ ደግሞ አሉ ከሚባሉት በታች
ሆነው የሚገኙ ስላሉ ይሄን አጋጣሚ
እየተጠቀምን ለአዲሱ ትውልድ ማስተዋወቅና
ማስታወስ መቻል የታሪክ ሃላፊነት አለብን
ብለን እናስባለን፡፡
ከስፖርቱ በተጓዳኝ የእኛ ኢትዮጵያዊያን
ባህልና አስተዳደግ መረዳዳትና መተጋገዝን
የሚጠይቅ በመሆኑ እንደ ፌዴሬሽን በተቻለን
አቅም ኢትዮጵያ ውስጥ ወድቀውና አስታዋሽ
አጥተው ህይወታቸው እጅግ ፈታኝ ሁኔታ
ላይ ይገኝ የነበሩ ተጨዋቾን በዚሁ ፌዴሬሽን
አማካይነት እገዛ አድርገናል፡፡ ይህም ማለት
ቢያንስ የማይራቡበት፣ የማይራቆቱበትና
ታመው የሚታከሙበትን ሁኔታ በማመቻቸት
ረገድ ፌዴሬሽኑ የሚቻለውን ነገር ሁሉ
አድርጓል፡፡
ሊግ፡- በየአመቱ ከሃገር ሃገር ተጉዞ
ውድድሮችን ማካሄድ ትንሽ አያስቸግርም?
አቶ አሳየኸኝ፡- እውነት ነው ይሄን መሰል
ውድድር ማካሄድ ቀላል አይደለም፡፡ አውሮፓ
ደግሞ በባህል፣ በአየር ፀባይና በአኗኗርም
ከሃገር ሃገር በጣም ይለያያል፡፡ በመሆኑም
በየአመቱ ሃገር ለሃገር እየዞሩ ይሄን ውድድር
ለማካሄድ ትልቅ ተግዳሮቶች አሉብን፡፡ የእኛ
ከአሜሪካን የሚለየው እዛ የሚደረገውን
ውድድር የሚያዘጋጀውና ቦታ የሚመርጠው
ፌዴሬሽኑ ነው፤ እኛ ግን የእነርሱን ያህል
ለማድረግ አቅማችን ያን ያህል አልጎለበተም፡
፡ አንድን ውድድር ለማካሄድ በጣም ብዙ
ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ፌዴሬሽናችን
ፋይናንሽያሊ ምንም የሌለው ተቋም ነው፡
፡ እናም በራሳችን አቅም ውድድሩን ማካሄድ
ስለማንችል እስከ 2016 ዓ/ም ድረስ ሃገራት
ናቸው ውድድሩን ሲያዘጋጁ የነበረው፡፡ ከዚያ
በኋላ በነበረው ሁኔታ ፌዴሬሽኑ በሁለት
እግሩ መቆም ስላለበትና ኢኮኖሚካሊም
ጡንቻውን ማፈርጠም ስለሚኖርበት
ፌዴሬሽኑ ማዘጋጀት አለበት በሚል በጠቅላላ
ጉባኤ ላይ የተወሰነ በመሆኑ ወደዛ ለመጓዝ
ተሞክሯል፡፡
እንደ መነሻነትም ባለፈው አመት
በሆላንድ በተዘጋጀው ውድድር ላይ
አዲሱን አሰራር ለመፈተሽ ተሞክሮ ነበር፡
፡ ነገር ግን ሂደቱ አዲስ ከመሆኑ አንፃር
እንዲሁም በሀገሪቱ የነበረው የፀጥታ ጉዳይና
ያልተጠበቀው የወጪ ብዛት ትልቅ ጫና
በመፍጠሩ ፌዴሬሽኑ የዛን አመት ውድድር
በኪሳራ እንዲፈፅም ተገዷል፡፡ ይህ ሁኔታም
ኦዲት ተደርጎ ለጠቅላላ ጉባኤው ሪፖርት
ቀርቧል፡፡ በ2017 ዓ/ም ደግሞ ውድድራችንን
ጣልያን ሮም ላይ አካሄደን ነበር፤ ይህም
ተሳትፎ ልክ እንደሆላንዱ ውጤታማ ሳይሆን
የቀረና የወጪ ዝርዝሩም በኦዲት እየተፈተሸ
ሲሆን ጉዳዩም ወዴት ያምራ? የሚለው ነገር
በጠቅላላ ጉባኤው የሚወሰን ይሆናል፡፡
ምክንያቱም የፌዴሬሽኑ ገንዘብ በአግባቡ
ኦዲት አልተደረገም፤ በወቅቱ ይህ ውድድር
የተዘጋጀው ፌዴሬሽኑ ኢትዮ-ኢታሊ ከሚባል
ቡድን ጋር በመተባበር ነበር፤ ሆኖም በመሃል
አለመግባባትና ችግር ተፈጥሮ ስለነበር
ወጪውና ገቢው ተጣርቶ እንደተቋም ማወቅ
የሚገባው ነገር አልታወቀም፡፡ ይህ ጉዳይ
ወደፊት ወይ በህግ አሊያም በኢትዮጵያውያን
ባህል የሚፈታ ይሆናል፡፡
ሊግ፡- በዚህ ምክንያት ፌዴሬሽኑ
የመሰንጠቅ አደጋ ገጥሞት ነበር የሚባለው
ነገር ምን ያህል እውነት ነው?
አቶ አሳየኸኝ፡- አዎ እውነት ነው፡
፡ በወቅቱ ፌዴሬሽናችን ለሁለት የመከፈል
አደጋ ገጥሞት ነበር፡፡ ነገር ግን በቦርዱ
አባላት ታታሪነትና እንደዚሁም በቀድሞው
አመራር ተባባሪነት ከመበታተን አደጋ ተርፈን
ባለፈው ጊዜ በነበረው ጠቅላላ ጉባኤ አዲሱ
አመራር ተመርጦ እንቅስቃሴ ላይ እንገኛለን፡
፡ የዚህ አዲስ አመራር ተቀዳሚ እንቅስቃሴም
ተቋሙን የማዘመንና ከጄኔሬሽኑ ጋር የሚሄድ
ተጠያቂነት ያለው አሰራርን ማመቻቸት ነው፡
፡ ከዚህ በተረፈ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ
ያለው ነባራዊ ሁኔታ ስለተቀየረ መስራት
የሚቻልበት አጋጣሚ ተፈጥሮልናል፡፡ ከአሁን
በፊት በነበረው አካሄድ ልዩነቶች፣ የፖለቲካና
የሃይማኖት አስተሳሰቦች ስፖርቱ ላይ ያጠላሉ፡
፡ ሁሉም ወገን ስፖርቱን ወደሚፈልገው
አቅጣጫ ለመጎተት ስለሚፈልግ ሂደቱ
ትንሽ ፈታኝ ነበር፡፡ አሁን ግን ሁኔታዎች
በመለወጣቸው ያሰብነውን ለማሳካት
እንዲቻለን የቀረፅናቸው ፕሮፖዛሎች ስላሉ
ለጠቅላላ ጉባኤው ቀርበው አዎንታዊ ምላሽ
ሲያገኝ ወደተግባር የምንገባ ይሆናል፡፡
ሊግ፡- ከዚህ አንፃር ዘንድሮ በስዊዘርላንድ
የሚካሄደው አመታዊ ውድድር በተሻለ ሁኔታ
ይጠናቀቃል የሚል እምነት አላችሁ?
አቶ አሳየኸኝ፡- ከስድስት ወር በፊት
ስቱትጋርት ላይ ተፈጥሮ የነበረው ችግር
ሰው ሰራሽ ችግሮች ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታ
ደግሞ ህብረተሰቡን በጣም ጎድቶታል፡
፡ ከምንም በላይ ከተለያዩ አገራት የመጡት
ሰዎች በተፈጠረው ሁኔታ በእጅጉ አዝነዋል፡
፡ ምንም እንኳን ውድድሩ የተካሄደ ቢሆንም
ፕሮግራሙን በሚመጥን ሁኔታ የተደረገ
አልነበረም፡፡ ቀደም ሲል ከአዘጋጁ ሀገር ጋር
የውድድር ሰነድ የነበረን ቢሆንም በገቡት ቃል
መሰረት ተግባራዊ መሆን ባለመቻሉ ጥሩ
ሊባል የማይችል ስሜት ተፈጥሮ አልፏል፡
፡ በመሆነም ከዚህ አካሄድ ተምረንና ጥንቃቄ
በመውሰድ የቀጣዩን አመት ውድድር በስኬት
ለማጠናቀቅ አቅደናል፡፡
እኔም ወደዚህ ከመምጣቴ በፊት
በነበረው ስብሰባ በዙሪክና አካባቢዋ
ከሚኖሩ ሰዎች መካከል ለውድድሩ አዘጋ
ጅነት ንዑስ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ሁሉ
ንም ኢትዮጵያዊ የሚያቅፍና ማንንም በሀይ
ማኖትም ሆነ በአመለካከት የማያገል ውድድር
ለማሰናዳት ይቻል ዘንድ ኮሚቴው በንቃት
እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ ፌዴሬሽናችን
ከኢትዮ-ዙሪክ ጋር በመሆን ሌት ተቀን
እየሰራን ሲሆን በዚህም ባለፈው ጊዜ ያዘነውን
ህዝብ ለመካስ እየተዘጋጀን ነው፡፡
ሊግ፡- ውድድሩ የሚካሄድበት ቀን መቼ
ነው?
አቶ አሳየኸኝ፡- ከጁላይ 31 እስከ ኦገስት
3 ይደረጋል፡፡
ሊግ፡- በአውሮፓ የሚገኘው ፌዴሬሽን
በየአመቱ ከሚያካሂደው ውድድር ጎን ለጎን
ለሃገሪቱ ተተኪ የሚሆኑ ስፖርተኞችን
ለማፍራት እየሰራ የሚገኘው ነገር አለ?
አቶ አሳየኸኝ፡- ቀደም ብዬ ያነሳሁልህ
ይህንኑ ነው፡፡ ሲጀመር ይህ ፌዴሬሽን
የተመሰረተው ስፖርቱን አስታኮ
ኢትዮጵያዊያን እንዲሰባሰቡ ለማስቻል ነው፡
፡ ህገ-ደንባችንንም ገልጠህ ካየኸው ራዕይም
አልነበረውም፡፡ አሁን ግን ይህ አካሄድ
እንዲቀየር እንፈልጋለን፤ ከጊዜው ጋር አብሮ
መጓዝ የሚቻለው ደግሞ አንተ ቀደም ብለህ
ያነሳኸውን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ስንችል
ነው፡፡
አውሮፓ ውስጥ እንደመኖራችን መጠን
የተሻለ ፋሲሊቲና ዘመናዊ ስልጠና ለማግኘት
የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች ስለሚኖሩ እዚህ
ያለ ኢትዮጵያዊ እዛ ሄዶ ማግኘት፣ አልያም
እዛ ያለው እዚህ መጥቶ ማገዝ የሚችልበትን
መንገድ መፍጠር አለብን፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ
በውጭ ሀገር የሚኖሩና አቅምና ችሎታ
ያላቸው ህፃናቶችን ወደአገራቸው መጥተው
በየእድሜያቸው እርከን መሳተፍ የሚችሉበትን
ሁኔታ ለማመቻቸት ይቻል ዘንድ ወደፊት
ሃሳቡ ለጠቅላላ ጉባኤው ቀርቦ የሚፀድቅና
መሆን የሚገባው ነው ብለን እናምናለን፡፡
አንተ እድሉ ገጥሞህ ውድድሩ ላይ
አልተገኘህም ይሆናል እንጂ ያለውን ታለንት
ብታይ በጣም የሚገርም ነው፡፡ ለንፅፅር
ያህልም እዚህ በመጣሁበት አጋጣሚ
አንድ ሶስት ጨዋታዎችን ለማየት እድል
አግኝቻለሁ፡፡ እናም የሁለቱን ውድድር
በሙያተኛ እይታ ስመዝናቸው እዛ አውሮፓ
ውስጥ የሚደረገው ውድድር በጣም ጠንካራና
ለተለያዩ ክለቦች የሚጫወቱ ልጆች ያሉበት
ነው፡፡
ከዚህ መነሻነትም ባለፈው ጊዜ ከብሄራዊ
ቡድኑ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ጋር
ተቀጣጥረን ተገናኝተን ነበር፡፡ ከብሄራዊ ቡድን
አንስቶ በየእድሜ ካታጎሪያቸው ማገልገል
የሚችሉ ተጨዋቾች ስላሉ ፌዴሬሽናችን
ይህን ሁኔታ ለማመቻቸት ሃሳብ ያቀርብን
ሲሆን የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝም ሃሳባችንን
በመደገፍ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው
በቀጣይነት እንዴት መስራት እንደሚቻል
ወደፊት በሁለታችንም በኩል በትኩረት
የሚሰራበት ይሆናል፡፡
ሊግ፡- ለበርካታ አመታት በተጨዋችነት
እንደማሳለፍህ መጠን በአሁኑ ጊዜ
ያለውን የአገራችንን የኳስ ሁኔታ እንዴት
ገመገምከው?
አቶ አሳየኸኝ፡- (ፈገግታ) በዚህ ዙሪያ
በጥልቀት ለማውራት ትንሽ ከባድ ነው፡፡ የ
ምሰጠው አስተያየትም ሊያቀያይም ይችላል፡፡
ሊግ፡- እንዲህ ብሎ ነገር የለም
የሚሰማህን ሁሉ በነፃነት ተናገር?
አቶ አሳየኸኝ፡- እንግዲህ የሁሉም
ሰው አመለካከት ይለያያል፤ እንደጉራ
ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ሆነህ በመወለድህ ብቻ
የምታገኘው ክህሎት አለ፤ እናም የሃገራችን
ተጨዋቾች ታለንት አላቸው፡፡ ነገር ግን ይህ
ታለንት በአግባቡና ከጊዜው ጋር አብሮ ሄዷል
ወይ? ብለህ ስታስብ አዎ! ብዬ ለመናገር
አልደፍርም፡፡ ከዚህ ውጪ ሁሉም ያለበትን
ዘመን በማሰብ የእኛ ጊዜ ይሻላል ሊል ይችላል፡
፡ ነገር ግን እንደሙያተኛ ብትጠይቀኝ አሁን
ካለው ስታንዳርድ፣ ከጎረቤት ሃገሮች አቅምና
ከወቅታዊ የአለም ፉትቦል አንፃር የእኛ በእጅጉ
ወደኋላ የቀረ ነው፤ ሌላው በዚህ ስፖርት ደስ
ያለኝ ነገር ተጨዋቾችና አሰልጣኞች በከፍተኛ
ደረጃ እየተጠቀሙ መሆናቸው ነው፡፡
ሊግ፡- ግን ይገባቸዋል ትላለህ?
አቶ አሳየኸኝ፡- ማግኘታቸው ጥሩ
ቢሆንም እነርሱ ከሚጠቀሙበት ነገር አንፃር
ስፖርታችን የዛን ያህል ተለውጧል ብዬ
ለመናገር አልደፍርም፡፡ በንፅፅር ካየኸው
ደግሞ ሁለቱ እጅግ በተራራቀ መንገድ
ነው የተጓዙት፤ ብሩ ተቆልሏል፤ እግር
ኳሱ ግን የለም፡፡ ይህ ማለት በእኛ ጊዜ
እንደነበረው ዘመን ተጨዋቹ ምንም ሳያገኝ
ቀጣይ ህይወቱ ይመሰቃቀል ማለቴ ሳይሆን
በአሁን ሰአት ሃገራችን ካለችበት ደካማ
የኢኮኖሚ አቅም አንፃር ስታየው ክፍያው
ትንሽ የተጋነነ ይመስላል፡፡ ይህም ሆኖ ግን
ተጨዋቾቹ ለምን ብቃታቸው ከፍ አይልም?
ብዬ እነርሱን መውቀስ አልፈልግም፡፡
ምክንያቱም ተጨዋቾቹ ያልተሰጣቸውን ነገር
ከየት ያምጡ? ቀደም ብዬ እንደገለፅኩልህ
ተጨዋቾቹ ኳሱን መያዝ ይችሉበታል፡፡ ነገር
ግን ከዚያ ወዴት ነው የሚሄደው? ምንስ ነው
የሚደረገው? የሚለው ነገር በዘመናዊ ስልጠና
መገራት መቻል አለበት፡፡
እዚህ አገር አካዳሚ የሚባሉትን
የተወሰኑትን ተዟዙሬ አይቻለሁ፤ ነገር ግን
ስም ብቻ ነው እንጂ አካዳሚነቱን የሚመጥን
ነገር የለም፡፡ በሌላ አንፃር ለዚህ ስፖርት ተብሎ
በየአመቱ ከፍተኛ የሆነ በጀት ከመንግስትም
ሆነ ከሃገር ይባክናል፡፡ ግን ለውጡ ዜሮ
ከመሆኑ አንፃር ይህ ስፖርት ባለቤት ያጣ
መድረክ ሆኗል ብዬ ነው ያሰብኩት፡፡
ከዚህ በላይ ኳሱ ዜሮ በሆነበት ሁኔታ
በዲሲፕሊን ግድፈት ደጋፊዎች ፅንፍ
ለይተው የዚህ አይነት አምባጓሮ መፍጠሩ
በጣም የሚያሳፍር ነው፡፡
ሊግ፡- ስልጠናን በተመለከተ ሁለት
መንተ ሃሳቦች እየተሰነዘሩ ይገኛል፤
እንደሙያተኛ አንተ በዚህ በኩል ምን ትላለህ?
አቶ አሳየኸኝ፡- በጣም በተደጋጋሚ
ጊዜ የሰማሁትና እጅግ አስልቺ፣ እንዲሁም
ለለውጡ አንዳችም ፋይዳ የሌለው ነገር
እንደሆነ ነው የሚገባኝ፡፡ የስልጠና አሰጣጡን
በተመለከተ ሁለት አይነት አስተሳሰቦች እንዳሉ
ሰምቻለሁ፤ እኔ ይሄን ነገር ስሰማ ድሮ ልጅ
ሆነን የሚነገረንን ተረት ነው የማስታውሰው፡
፡ “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ይባላል፡፡
መጀመሪያ ያለብንን ችግር እንወቅ፤ ከዛ ወዴት
እንሂድ? የሚለው ነገር ይከተላል፡፡ አንድ
ማወቅ ያለብን እውነታ ደግሞ ማናችንም
ከሳይንሳዊ አስተሳሰብ መውጣት አይቻለንም፡
፡ በሌላ አማርኛ ከሳይንሳዊ ስልጠና እንውጣ
ማለት ለኤች አይ ቪ በሽታ ፌጦ መድሃኒት
ነው እያሉ ራስን እንደማሞኘት ነው፡፡
ምክንያቱም ስፖርቱ በራሱ
የሚጠይቃቸው አምስት ነገሮች አሉ፡፡ እናም
ከእነዚህ ሳይንሳዊ ተሞክሮዎች ውጪ ሌላ
ግኝት ካለ ለሳይንቲስቶች አቅርቦ እነርሱ
ይከራከሩበት፡፡ እኛም ይሄን ሂደት ወደተግባር
ለውጠን ለአለም እናበርክት፡፡ ከዚህ ውጩ
በሌለና በተግባር ባልታየ ነገር ላይ ጊዜ
ማባከን ለፉትቦላችን የሚፈይደው አንዳችም
ነገር የለም፤ ስፖርቱ የሚመራው በደመ-ነፍስ
መሆን የለበትም፡፡ ከአሁን በፊት ስፖርተኛ
ስለነበርክ ብቻ ስፖርቱን በብቃት ትመራለህ
ማለት አይደለም፡፡ ከዛ ባለፈ ስፖርት
ማኔጅመንት መማር አለብህ፤ ስልጠናን
በተመለከተም ከዚህ በፊት ኳስ ስለተጫወተ
ብቻ አሰልጣኝ መሆን የለበትም፡፡ እርግጥ ነው
በስፖርቱ ማለፍ መቻል ሊያግዝህ ይችላል፡፡
አሁን እንዳየሁት ኢትዮጵያ ውስጥ
እየተሰጠ ያለው ስልጠና ስኬል ላይ ብቻ
ያተኮረ በመሆኑ ነው ችግር የተፈጠረው፡
፡ ሰው መቅረፁ ላይ ግን ሁሉ ነገር ዝግ
በመሆኑ እድገትና ለውጡ ከድጡ ወደማጡ
እየሆነ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በስነ ምግባር
ደረጃ የሚሰጠው ትምህርት ደካማ በመሆኑ
ተጨዋቾች ራሳቸው ቀይ ካርድ ከማየታቸው
ባሻገር ሜዳ ላይ በሚያሳዩት ያልተገባ
ድርጊት ለደጋፊዎች ረብሻ መቀስቀስ አይነተኛ
ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡ በመሆንም የተለየ
ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት የሚገባው ነጥብ
ላይ ሙያተኞች አይናቸውን ገልጠው ሊሰሩ
ይገባል ባይ ነኝ፡፡
ሊግ፡- ለነበረን ቆይታ በሊግ ስፖርት
ጋዜጣ አንባቢያን ስም አመሰግናለሁ?
አቶ አሳየኸኝ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P