Google search engine

“ከቅ/ጊዮርጊስ በሚኖረንና ጥሩ ፉክክር በሚደረግበት ጨዋታ እነሱን አሸንፈን የነጥብ ልዩነቱን እናሰፋዋለን” አሚን ነስሩ /መቐለ 70 እንደርታ/

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/

ለመቐለ 70 እንደርታእግር ኳስ ክለብ የተከላካይ ስፍራ ላይ በመሰለፍ አበረታች እና ስኬታማ ብቃቱን በየጨዋታዎቹ ላይ እያሳየ የሚገኘው ወጣቱ ተጨዋች አሚን ነስሩ የአዲስ አበባ ስታድየም ላይ የፊታችን ማክሰኞ ክለባቸው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ላለበት ጨዋታ በሚገባ መዘጋጀታቸውን እና ግጥሚያውን ለማሸነፍም ወደ ስፍራው እንደሚመጡ አስተያየቱን ለሊግ ስፖርት ጋዜጣሰጥቷል፡፡
መቐለ 70 እንደርታ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎው ላይ በሜዳውም ሆነ ከሜዳው ውጪ ባስመዘገባቸው ውጤቶች የአሁን ሰዓት ላይ ሊጉን ተከታዮቹን ፋሲል ከነማን እና ሲዳማ ቡናን በ8 ነጥብ ልዩነት በመብለት እየመራ ሲሆን የቡድኑ ግብ አዳኝ አማኑኤል ገብረ ሚካሄልም የሊጉን የኮከብ ግብ አግቢነት በመምራት ላይ ይገኛል፡፡
የመቐለ 70 እንደርታ ክለብ የሊጉ ጨዋታዎች ሊጠናቀቁ የ9 ሳምንታት ግጥሚያዎች በቀሩበት የአሁን ሰዓት በሜዳው አራት እና ከሜዳው ውጪ አምስት ግጥሚያዎች የቀሩት ሲሆን የአሰልጣኝ ገብረ መድህን ኃይሌው ቡድን የዘንድሮውን የሊግ ዋንጫ ለማንሳት ከፍተኛ እድሉም አለውና ቀሪ ጨዋታዎቹ በጉጉት እየተጠበቀም ይገኛል፡፡
የመቐለ 70 እንደርታ ክለብየሊግ ተሳትፎው ላይ እያስመዘገበ ስለሚገኘው ስኬታማ ውጤት፤ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አዳማ ከተማን ስላሸነፈበት ጨዋታ እና የፊታችን ማክሰኞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ስለሚያደርጉት ወሳኝና ተጠባቂ ጨዋታ ለቡድኑ በቋሚ ተሰላፊነት ከሚጫወቱ ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነውን አሚን ነስሩን ጠይቀነው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የመቐለ 70 እንደርታየፕሪምየር ሊግ ስኬታማ ጉዞ እና የውጤታማነት ሚስጥር
“መቐለ 70 እንደርታን በሊጉ ተሳትፎ ውጤታማ እያደረገው ያለው የተለየ ሚስጥር ምንም የለም፤ ክለባችን ለስኬት እየበቃ የሚገኘው ጠንካራ ህብረት እና አንድነትም ስላለን ነው፤ ከዛ ውጪም አሰልጣኛችን ገ/መድህን ኃይሌ ለእኛ የሚሰጠን ስልጠናና ለሁሉም ተጨዋቾችም ያለው አመለካከት እኩል ሰለሆነም ይሄ ተደማምሮ ቡድናችንን ለውጤታማነት አብቅቶታል፡፡”

የአዳማ ከተማ ጋር ስለነበራቸው እና ድል ስላደረጉበት ያለፈው ሳምንት ጨዋታ
“የአዳማ ከተማን የተፋለምንበት የሜዳችን ላይ ጨዋታ ጥሩ እና ጠንካራ ፉክክር የተደረገበት ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ግጥሚያውን እኛ እስከመጨረሻው ሰአት ድረስ ታግለንና በልጠን ስለተጫወትንበት የጨዋታው አሸናፊ ለመሆን ችለናል፤ ባገኘነው የድል ውጤትም በጣም ተደስተናል”፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን ማክሰኞ ስለሚገጥሙበት ተጠባቂ ጨዋታ እና ስለሚመዘገበው ውጤት
“የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ጋር የሚኖረን የማክሰኞው ጨዋታ ውጤቱ ለሁለታችንም ወሳኝ እና በጣም አስፈላጊያችን ስለሆነ በሜዳ ላይ ጥሩ ፉክክር ይደረግበታል፤ ለእዚህ ጨዋታም በደንብ በመዘጋጀታችን ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር የሚኖረንን ጨዋታ አሸንፈን ከእነሱ ጋር ያለንን የነጥብ ልዩነት እናሰፋዋለን”፡፡
ቅ/ጊዮርጊስን ከሜዳቸው ውጪ አዲስ አበባ ላይ ስለመፋለማቸው
“ቅዱስ ጊዮርጊስንማክሰኞ አዲስ አበባ ላይ የምንፋለም መሆኑ ለእኛ ምንም የሚፈጥርብን ችግርም ሆነ ተፅዕኖ የለም፤ የአዲስ አበባ ሜዳ ለእኛ የጨዋታ እንቅስቃሴ ጥሩ ነውና በዚ በኩል የሚያሰጋን ነገር የለም”፡፡
ለመቐለ 70 እንደርታ የፋሲል ከነማ እና የሲዳማ ቡና እያሸነፉ መምጣታቸው ስጋት ይሆንበታል?
“በፍፁም፤ የመቐሌ 70 እንደርታን ክለብ ከስር ከስር እየተከተሉት ያሉት ፋሲል ከነማ እና ሲዳማ ቡና እንደ እኛ ሁሉ ግጥሚያቸውን ማሸነፍ መቻላቸው እኛን የሚያስፈራንም ሆነ የሚያሰጋን ነገር አይኖርም፤ ምክንያቱም እነሱ የሚያሸንፉትንም ጨዋታ እኛም እያሸነፍን ነው፤ በቀጣዩ ጊዜ ደግሞ ሁለቱም ቡድኖች እንደ እኛ ሁሉከሜዳቸው ውጪ ከበድ ያለ ጨዋታዎች አሏቸው እና የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እድላችንን የምንወስነው ራሳችን ነንና የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ሰፊ እድሉ አለን”፡፡
የፕሪምየር ሊጉ ላይ ለመቐለ 70 እንደርታ እየሰጠ ስላለው ግልጋሎት እና ስለ ወቅታዊ አቋሙ
“መቐለ 70 እንደርታን ውጤታማ ለማድረግ አቅሜና ጉልበቴ በሚፈቅደው ሁሉ ጠንክሬ በመስራት የአሁን ሰአት ላይ ለክለቤ ጥሩ ግልጋሎትን እየሰጠሁ ነው የምገኘው፤ የወቅታዊ አቋሜን በሚመለከት በጥሩ ሁኔታም ላይ ነው የምገኘው እና እነዚህን ሁሉ እንዳሳካ አሰልጣኜ ገ/መድህን ኃይሌ የሚሰጠኝ ስልጠናን በአግባቡ እየተከታተልኩኝ መሆኔ እና ሁሌም ለመለወጥ የምተጋም ተጨዋች ስለሆንኩ ይህ ሊጠቅመኝ ችሏል”፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን መቐለ 70 እንደርታ ያነሳል? ወይንስ ሌላ ክለብ ያነሳል?
“የዘንድሮውን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ መቐለ 70 እንደርታ እንጂ በፍፁም ሌላ ክለብ አያነሳም፤ ለእዚህም ሻምፒዮናነት እንዲረዳን ከተከታዮቻችን ክለቦች ጋር ያለንን የነጥብ ልዩነት ማራቃችን እና ሻምፒዮና ለመሆንም በራሳችን እድል የምንወሰን መሆኑም ይረዳናልና የእዚህ ዓመት የዋንጫ ማረፊያው መቐለ 70 እንደርታ ይሆናል”፡፡

የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎችን በተመለከተ
“የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎች ለቡድናቸው ያላቸው ፍቅር እና ስለሚሰጡት ድጋፍ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ ለስኬታማነታችንም የእነሱ ድጋፍ በጣም ጠቅሞናል፤ ለቡድኑ ከሚሰጡት ድጋፍ ባሻገርም እያንዳንዱን ተጨዋቾች የሚያበረታቱበት መንገድም ሊያስደንቃቸው ይገባል”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P