Google search engine

“ከቅ/ጊዮርጊስ የሚኖረንን ጨዋታ ማን ያሸንፋል ብሎ ለመናገር ከባድ ይመስለኛል” በረከት ደስታ /ፋሲል ከነማ/

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ነገም በወሳኝ ግጥሚያዎች ይቀጥላል፤ ነገ ከሚከናወኑት ፍልሚያዎች መካከልም የውድድሩ መሪ ቅ/ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ ጋር ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት ተጠብቋል፤ ይህን ግጥሚያ በተመለከተ እና ከቡድናቸው አቋም ጋር በተያያዘ ዘንድሮ ጥሩ የውድድር ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው በረከት ደስታ ከሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር ቆይታን አድርጎ የሰጠን ምላሽ የሚከተለውን ይመስላል፡፡

ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስን ነገ እሁድ ትፋለማላችሁ፤ ይህን ጨዋታ በምን መልኩ ትጠብቀዋለህ?

በረከት፡- ይህ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር የሚደረግበት ነው፤ ግጥሚያውን የሚያሸንፈው ክለብ እኛ ከሆንን ለዋንጫው ባለቤትነት የሚኖረን ተስፋ የለመለመ ይሆንልናል፤ እነሱ ካሸነፉ ደግሞ በቅርቡ የምንከተላቸው እኛ ስለሆንን ሻምፒዮንነታቸውን የበለጠ የሚያረጋግጡበት ይሆናል፡፡

ሊግ፡- የእሁዱን ጨዋታ ማን በበላይነት ያጠናቅቃል?

በረከት፡- በአሁን ሰዓት ላይ እነሱ በጥሩ ብቃት ላይ ከመሆናቸው አኳያ ይህን ግጥሚያ ይሄኛው ቡድን ያሸንፋል ብሎ ለመናገር ከባድ ይመስለኛል፤ ሁሉም ነገር እሁድ በሚደረገው ግጥሚያ የሚደረግም ይሆናል፡፡

ሊግ፡- ፋሲል ከነማ ተከታታይ ድሎችን እያስመዘገበ ይገኛል፤ የእዚህ የውጤት ሚስጥር ምንድን ነው?

በረከት፡- ባለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ ነበርን፤ ዘንድሮ ግን በፈለግነው ስኬት ልንጓዝ ስላልቻልንና በእዛም የቁጭት ስሜት ሊፈጠርብን ስለቻልን ከእዛ በመነሳት ነው ጥሩ ውጤትን እያስመዘገብን የምንገኘው፡፡

ሊግ፡- ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር በሚኖራችሁ የዘንድሮ ፉክክር ነጥብ አጥባችሁ የውድድር ዘመኑን ታጠናቅቃላችሁ ወይንስ በሰፋ ልዩነት? ሻምፒዮና ካልሆናችሁስ…..

በረከት፡- ሻምፒዮና ካልሆንማ ሁለተኛ ሆነን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ላይ የምንሳተፍ ይሆናል፤ ከእዛ ውጪ ከእነሱ ጋር ስላለን ልዩነት ደግሞ መናገር የምፈልገው ሻምፒዮና ባንሆን እንኳን  ነጥቡን አጥበን ብንጨርስ በጣም ደስ ይለኛል፡፡

ሊግ፡- ስኬታማ የውድድር ጊዜን እያሳለፍክ ይገኛል፤ የውድድር ዓመቱ ለአንተ ምርጥ ነው ማለት ይቻላል?

በረከት፡- አዎን፤ በሁሉም ነገር ጥሩ ጊዜን ነው እያሳለፍኩ ያለሁት፤ ባሳለፍነው ዓመት ለእኔ እንደዘንድሮ ቡድኑን በጥሩ መልኩ አላገለገልኩትም ነበር፤ አሁን ግን በምፈልገው መልኩ በመጫወት ልክሰው ችያለሁ፡፡

ሊግ፡- አቡበከር ናስር ዓምና የውድድሩ ድምቀት ነበር፤ ዘንድሮ ደግሞ ብዙዎቹ ተጨዋቾች ለአንተ ምስክርነታቸውን እየሰጡ ነው የሚገኘው፤ በእዚህ ዙሪያ ምን የምትለው ነገር አለ?

በረከት፡- የእግር ኳስ ተጨዋች የሚለየው በሜዳ ላይ ነው፤ ይሄንን አቋሜንም ኳስ እስከማቆምበት ደረጃም ማስቀጠል ነው የምፈልገው፤ ስለ አቋሜም ብዙ ሰዎች እንድለወጥ ከመፈለግ የሚነግሩኝ ነገር አለና ጠንክሬ በመስራቴም ነው ብዙዎች ስለ እኔ ምስክርነታቸውን እየሰጡ የሚገኘው፡፡

ሊግ፡- የዘንድሮ አስቆጪ ጨዋታችሁ የትኛው ነው?

በረከት፡- አራቱም የተሸነፍንባቸው ጨዋታዎች አስቆጪ ናቸው፤ ከሐዋሳ እና ከወልቂጤ ከተማ ጋር በተለይ የጣልናቸው ነጥቦች ይበልጥ ያስቆጫሉ፡፡

ሊግ፡- ጣፋጩ ድላችሁስ?

በረከት፡- ከመከላከያ ጋር ተጫውተን ያሸነፍንበትና ባህርዳርንም ድል ያደረግንበት ግጥሚያ ለእኛ ምርጥ የሚባል ነው፡፡

ሊግ፡- ለፋሲል ከነማ ጎሎችን ከማስቆጠርህ ጋር በተያያዘ ምን የምትለው ነገር አለ?

በረከት፡- አምስት ጎሎችን እስካሁን አስቆጥሬያለሁ፤ ሰባት ደግሞ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ለማቀበል ችያለሁ፤ አምና ሶስት ግቦችን ነበር ለማስቆጠር የቻልኩት፤ ጎል ከማስቆጠር ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ጊዜ የምደርስበት እድሎች ቢኖሩም አሁንም ተጨማሪ ግቦችን የማስቆጠር ችግሮቼ ሊቀረፉ አልቻሉም፤ ይህን ችግሬን ቀርፌ ወደፊት ግን ብዙ ጎሎች ማስቆጠሬ አይቀሬ ነው፡፡

ሊግ፡- የአምናው ሻምፒዮና በእዚህ የነጥብ ልዩነት ከመበለጡ ጋር በተያያዘ ምን ትላለህ?

በረከት፡- የሊጉ ውድድር ለብሔራዊ ቡድን ዝግጅት እና በሌላ ጉዳዮች በሚቋረጥበት ሰዓት ነው ብዙ ጊዜ የእኛ ቡድን ነጥብ ጥሎ የሚበለጠው፤ አንድ አንዴም እድለኛ ካለመሆን ጋር ተያይዞ ውጤት የምናጣበት ጊዜም አለ፤ ወደ ሜዳ ስንገባ በውስጣችን ጥሩ የመጫወት ፍላጎት ይኖረንና ያን ግን ተግባራዊ አናደርገውም፡፡

ሊግ፡- በመጨረሻ….?

በረከት፡- አሁን ላይ ሻምፒዮና የሚሆንውን ቡድን መወሰን ስለማይቻል የሊጉ ውድድር እስኪጠናቀቅ ድረስ መሪውን ቅ/ጊዮርጊስ እንፋለመዋለን፤ሻምፒዮና ከሆንን ድሉ ለእኛ በጣም ጣፋጭ ነው የሚሆንልን፤ ሊጉን ካላሸነፍንም ሁለተኛ ወጥተን ኢትዮጵያን በመወከል ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ እናልፋለን፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P