“የዋንጫ ርሃቤን በሲዳማ ቡና ማሳካት እፈልጋለሁ”
“አዲስ አበባን ከአንድ ግብ በላይ አስቆጥረን ማሸነፍ ነበረብን”
ሙሉዓለም መስፍን /ሲዳማ ቡና/
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመኑ መጀመሪያ ለክለቡ ሲዳማ ቡና በቋሚነት የመሰለፍ ዕድል አልነበረውም፤ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ብለን ለሙሉዓለም መስፍን /ዴኮም/ ጥያቄ አቀረብንለት ተጨዋቹ ሲመልስም “ከእዚህ ቀደም ተጫውቼ ላሳለፍኩበት እና በድጋሚም ከዓመታት በኋላ ፊርማዬን ላኖርኩበት የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ የውድድር ዘመኑ መጀመሪያ ላይ ተሰልፌ ልጫወት ያልቻልኩት ከሰውነት ኪሎ መጨመር ጋር በተያያዘ እና ማች ፊትነሴም በምፈልገው ሁኔታ ላይ ስላልነበር ነው፤ ይሄን ተከትሎም በእኔ ቦታ ላይ የሚጫወተውም ተጨዋች ጉዳት ከሜዳ አራቀው እንጂ በጥሩ ብቃት ላይ ሆኖ ክለባችንን ያገለግል ስለነበር በእዛ መልኩም ነው ለመጫወት ያልቻልኩት፤ በኋላ ላይ ግን የብርሃኑ አሻሞ መጎዳት እኔን ተክቼው እንድጫወት ስላደረገኝ አሁን ላይ ቡድናችንን አቅሜ በሚችለው መጠን እያገለገልኩት ነው የምገኘው”፡፡ በሚል ሙሉዓለም መስፍን ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቆይታ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የደቡብ ክልል ተወካዩ ሲዳማ ቡና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ጅማሬ በውጤት ማጣት ሲዳክር የነበረ ክለብ ሲሆን በኋላ ላይ ደግሞ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ መሻሻሎችን በማሳየት አሁን ላይ በመሪነት ደረጃ ወደሚገኙት ክለቦች ሊቃረብ ችሏል፤ ሲዳማ ቡና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው የ14ኛ ሳምንት ጨዋታውን ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር አድርጎ ሀብታሙ ገዘኸኝ ባስቆጠረው ብቸኛ የድል ግብ 1-0 ያሸነፈ ሲሆን ይህም ውጤት ወደ አራተኛ ደረጃ ከፍ እንዲል አድርጎታል፤ ከክለቡ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎና ከራሱ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ሙሉዓለም መስፍንን አናግሮት የሚከተለውን መልስ ተጨዋቹ ለጋዜጣው ሰጥቷል፤ ቃለ-ምልልሱም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፡፡
ሊግ፡- አዲስ አበባ ከተማን አሸንፋችሁ በደረጃው ሰንጠረዥ ወደ ላይ ከፍ ብላችኋል፤ ድል ስላደረጋችሁበት ጨዋታ ምን ትላለህ?
ሙሉዓለም፡- የሁለታችን ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ከረር እና ከፍ ብሎ ከነበረው ፀሐይ አኳያ ግጥሚያው የተቀዛቀዘ ነበር፤ እንደ ሌላው ጊዜም ጨዋታውን በፈጣን መልኩም አልተጫወትንም፤ ፈዘን ነበር፤ በሁለተኛው አጋማሽ ላይ ግን ይህን ጨዋታ የግድ ማሸነፍ አለብን በሚል ተነጋግረን ወደሜዳ ስለገባንና ማሸነፍ ደግሞ ወደመሪዎቹ ቡድኖችም በነጥብ ስለሚያቃርበንም ተደጋጋሚ የጎል ዕድሎችን በመፍጠርና ከእነዛ ውስጥም አንዷን ስለተጠቀምንም ግጥሚያውን በድል አድራጊነት ልንወጣ ችለናል፤ በአሸናፊነታችንም በጣም ተደስተናል፡፡
ሊግ፡- በዕለቱ ስለነበረው ተጋጣሚያችሁ አዲስ አበባ ከተማ ምን አልክ?
ሙሉዓለም፡- ከእነሱ ጋር በነበረን ጨዋታ የአየሩ ሞቃታማነትም ሊሆን ይችላል በእንቀስቃሴ ደረጃ ትንሽ ወረድ ብለው ነው ያገኘዋቸው፤ ጫና ሊፈጥሩም አልቻሉም፤ ባለፈው ግጥሚያቸው በሰፊ ግብ ሲያሸንፉ ብዙ ነገር ጠብቀንባቸው ነበር፤ ከእኛ ጋር ሲጫወቱ ሳይ ግን የዘንድሮ አጠቃላይ ውድድሩ ላይ ወጥነትና ተገማች ነገርን አታይምና ይህንን ነው በእነሱ ላይም የተመለከትኩት፡፡
ሊግ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የተጎናፀፋችሁት የድል ውጤት ለእናንተ የሚገባችሁ ነው?
ሙሉዓለም፡- በጣም እንጂ፤ ከፈጠርናቸው የግብ ዕድሎች አኳያም ውጤቱ ሲያንሰንም ነው፤ ከአንድ ግብ በላይም አስቆጥረን ማሸነፍም ነበረብን፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ አሁን አሁን ሲዳማ ቡና በለውጥ አብዮት ላይ ይገኛል፤ የእዚሁ ሚስጥር ምን ይሆን?
ሙሉዓለም፡- በሐዋሳ ከተማ በነበረን የዘጠኝ ሳምንታት የውድድር ቆይታችን ቡድናችን 9 ግጥሚያዎችን አድርጎ 11 ነጥብን ነበር ያስመዘገበው፤ አሁን ወደ ድሬዳዋ ስናመራ ደግሞ ነጥብ በመያዝም ሆነ ሜዳ ላይ ባለን የጨዋታ እንቅስቃሴ መቀናጀቱ ላይ ጥሩ የሆነ የራስ መተማመን ስላለን በ5 ጨዋታ አበረታች የሚባል ጥሩ ውጤትን እያስመዘገብን ይገኛል፤ ከእዚህ በኋላም በሚኖሩን ጨዋታዎች ላይ በተለይም ሁለተኛው ዙር ላይ በአንድ አንድ ቦታዎች ላይ ክፍተቶች ስላሉብን እነዛን ሞልተን ምርጥ ቡድን እንዳለን የምናስመለክት ይሆናል፡፡
ሊግ፡- ሲዳማ ቡና በዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎው ምን ውጤትን ለማምጣት አልሞ ነው የተነሳው? አሁን ላይስ….?
ሙሉዓለም፡- የውድድር ዘመኑ ጅማሬ ላይ እንደሚታወቀው የቡድናችን አሰልጣኝ የሆነው ገብረመድህን ሀይሌ ከእዚህ ቀደም ዋንጫ የማንሳት ልምዱ ስላለውና ክለባችንም እሱን አስቀድሞ ሲያስፈርመውም ስለ እሱ በደንብ አድርጎ ጠንቅቆ አውቆም ዋንጫ የማንሳት ዕቅድንም ይዞ ስለሆነ በዛ ሁኔታ ላይ ነው እልማችንን ለማሳካት ወደ ውድድሩ የገባነው፤ ያ ባይሳካ እንኳን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ላይ ቡድናችን የግድ መሳተፍ አለበት የሚልንም እቅድ ነድፈናልና ሌላኛው አማራጫችን እሱ ነው፤ ከዛ ውጪ ግን በሊጉ ተሳትፎ ሶስተኛ ወጣህም 13ኛ ምንም አይነት ትርጉም ስለሌለው ከላይ ባስቀመጥናቸው እቅዶቻችን ነው በመንቀሳቀስ ላይ የምንገኘው፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሲዳማ ቡና ያለው ጥንካሬና ድክመቱ ምን ይመስላል? ምን ማሻሻልስ ይፈልጋል?
ሙሉዓለም፡- ቡድናችን በዋናነት ያለው ጥንካሬው ሲከላከል ነው፤ በማጥቃቱ ላይ ደግሞ የቡድናችን ወጣቱ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች ይገዙ ቦጋለም በተቻለው አቅም ሁሉ ጎል እያስቆጠረና የግብ እድሎችንም እየፈጠረ ስለሆነ ያን በቡድናችን ላይ ተመልከተናል፤ በክፍተት በኩል የማነሳው ደግሞ በመሀል ክፍሉ ላይ ቡድናችን ከኳስ ጋር የሚያደርገው እንቅስቃሴ ጥሩ ሆኖ ሳለ ያለ ኳስ በምናደርገው እንቅስቃሴ ላይ የስፍራው አንድ አንድ ተጨዋቾች በኳሱ ጥሩ ሆነው ሳለ ፊዚካሊ አነስ ስለሚሉ ያለ ኳስ የምናደርገው አጨዋወት ላይ ልናስተካክላቸው የሚገቡን ነገሮች አሉ፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ካደረጋችሁት ግጥሚያ የቱ አስቆጨህ?
ሙሉዓለም፡- በጣም ያስቆጨኝ ጨዋታ ከሰበታ ከተማ ጋር ያደረግነውና አቻ የተለያየንበትን ነው፤ እነሱን እየመራናቸው ነበር በትንሽ ስህተት ጎል ያስቆጠሩብን ያ ጨዋታ የሚረሳኝ አይደለም፡፡
ሊግ፡- በጣም ያስደሰተህ ጨዋታስ?
ሙሉዓለም፡- ከሁሉም በተሻለ ያስደሰተኝ ጨዋታ በሐዋሳ ከተማ ላይ በነበረን የውድድር ቆይታችን ወላይታ ድቻን ያሸነፍንበትን ነው፤ ይህ ግጥሚያም ከነበረን አነስተኛ ነጥብ አኳያም ለእኛ ጫና ውስጥ ሆነን ያደረግነውና በደጋፊዎቻችን ፊትም የተጫወትነው ነበር፤ የሐዋሳ ቆይታችንም የመጨረሻው ጨዋታችንም ነበር፤ ይህን ጨዋታ ካሸነፍን ደረጃችንን ወደ ላይ ከፍ የምናደርግበት ከተሸነፍን ደግሞ ወደ ኋላ የምንቀርበት ስለሆነ ጠንክረን ገብተን ተጫውተን አሸነፍን፤ ይህም ጨዋታ ዛሬ ላይ በስነ-ልቦናው በኩል ጠንካራ እንድንሆንና በስኬታማነት እንድንጓዝም የጥርጊያውን በርም የከፈተልን ጨዋታ ስለሆነ በአስደሳችነቱ ወደር የማላገኝለት ግጥሚያ ነው፡፡
ሊግ፡- በዘንድሮ የውድድር ዘመን መጀመሪያ ላይ ለክለብህ በቋሚ ተሰላፊነት እየተጫወትክ አልነበርክም፤ በኋላ ላይ ደግሞ በተደጋጋሚ ጨዋታዎች ላይ ስትሰለፍ አየንህ፤ በእዚህ ዙሪያ የምትለን ነገር ካለ…?
ሙሉዓለም፡- እውነት ነው፤ የሊጉ ውድድር ሲጀመር ለቡድኔ እየተሰለፍኩ አልነበረም፤ ይሄ ሊሆን የቻለውም ለረጅም ጊዜ በእረፍት ላይ ስለነበርኩና የክብደትም /የሰውነት/ መጨመር ችግርም ስላጋጠመኝ በምፈልገው የማች ፊትነስ አቋሜ ላይ ልገኝ ስላልቻልኩና ወደምፈልገው አቋሜም በፍጥነት ለመመለስም ጊዜ ስለወሰደብኝ ነው፤ ሌላው ደግሞ በእኔ ቦታ ላይ ይሰለፍ የነበረውም ወጣቱ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ብርሃኑ አሻሞም በችሎታው ጥሩ አቅም ያለው ተጨዋች ስለነበርና ቡድናችንንም እስከተጎዳበት ጊዜ ድረስ በስኬታማነትም ያገለግል ስለነበርም ከእኔ የማች ፊትነስ ችግር ጋር ተዳምሮ ሳልጫወት ቀርቼ ነበር፤ ወደ በኋላ ላይ ግን የማች ፊትነስ ችግሬን ለማስተካከል ጠንክሬ ስለሰራውና ብርሃኑም ሲጎዳ እኔ ተክቼው በመግባት ጥሩ ስለተጫወትኩ ለቡድኔ በቋሚ ተሰላፊነት እየተጫወትኩ እገኛለው፡፡
ሊግ፡- በሲዳማ ቡና ባለህ የአሁን ቆይታ በችሎታህ ላይ ለውጦችን እየተመለከትክ ነው?
ሙሉዓለም፡- አዎን፤ ለእዛ ደግሞ የቡድኑ ኳስን መስርቶ መጫወቱ ጠቅሞኛል፤ ከእዛ ውጪ ደግሞ የመሀል ክፍሉም ጥሩ መሆን መቻሉም ለአጨዋወትህ የተለዩ አማራጮችንም ስለሚፈጥርልህና በቡድኑ ውስጥም ለክለቡ በሚስማማ መልኩ ኳሱን በምትፈልገው ሁኔታ እንድትጫወትም ነፃነቱም ስላለህ በእዛ መልኩ እየተጫወትኩ አበረታች እንቅስቃሴን በማሳየት ላይ ነው የምገኘው፡፡
ሊግ፡- በዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ ለእናንተ ቡድን የትኛው ፈታኝ ይሆንባችኋል?
ሙሉዓለም፡- የሊጉን ውድድር መገመት አስቸጋሪ ስለሆነ ማን ፈታኙ ክለብ እንደሚሆን አይታወቅም፤ ምክንያቱም በቅርብ የተከናወኑትን ጨዋታዎች ስንመለከት እንኳን አዲስ አበባ ከተማ ሰበታ ከተማን በጣም ሰፊ በሆነ ውጤት ያሸንፋል ብሎ የገመተ ማንም የለም ነበር፤ ከዛ ውጪም ቅ/ጊዮርጊስን አርባምንጭ ከተማዎች ነጥብ ያስጥሉታል ተብሎም አልታሰበም ነበርና በውድድሩ ቀላል የምትለው ቡድን አንድ አንዴ ከባድ ስለሚሆንብህ እና ውጤትም እየተመዘገበ ያለው በዕለቱ በምታደርጋቸው ጨዋታዎች እንደ አለህ ዕለታዊ ብቃትም እየተወሰነ በመሆኑ ለሁሉም ክለቦች እኩል የሆነ ግምትን ከመስጠት ውጪ ይሄ ቡድን ፈታኝ ይሆንብናል ብለን እያሰብን አይደለም፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎ ከእናንተም ሆነ ከተቃራኒ ቡድን ተጨዋቾች ውስጥ የትኛው ተጨዋች ጎልቶ ወጥቶብሃል?
ሙሉዓለም፡- ከተቃራኒ ቡድን ተጨዋቾች ውስጥ በዛ መልኩ ጎልቶ የወጣብኝ ተጨዋች ማንም የለም፤ ከእኛ ቡድን ከሆነ ግን የአጥቂው ስፍራ ተጨዋቻችን ይገዙ ቦጋለ ለቡድናችን ውጤት ማማር የራሱን አስተዋፅኦ ከማበርከት ውጪ ስምንት ግቦችንም በማስቆጠር በኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክር ውስጥ ቀዳሚ ከሚባሉት ተጨዋቾች መካከል አንዱ ስለሆነ እሱን ነው በጥሩ ተጨዋችነቱ ጎልቶ ወጥቷል ብዬ የማስበው፡፡
ሊግ፡- ቤትኪንጉን እንደ አጠቃላይ በምን ሁኔታ ተመለከትከው?
ሙሉዓለም፡- ውድድሩ ምንም እንኳን ገና ቢሆንም ጥሩ ጥሩ ነገሮችን እየተመለከትንበት ነው፤ በውጤት የተነሳ ሁሉም ቡድን ከእዚህ ሊግ ላለመውጣት ታትሮ እየሰራም ነው፤ ከስር ያሉ ቡድኖች የላይኛዎቹን ነጥብ በማስጣልም እየፈተኑና በክለቦች መካከልም ተመጣጣኝና የተቀራረበ አቋምም እየታየ በመሆኑ ለውድድሩም ድምቀት እየሆነ ነው፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የቱ ቡድን ሻል ያለ አቋሙን እያሳየ ይገኛል?
ሙሉዓለም፡- ቅ/ጊዮርጊስ በውጤት ደረጃም ሊጉን እየመራ ስለሆነ ካሉት ቡድኖች ጥሩ በመሆኑ የተሻለ ነገርን እያሳየ ይገኛል፤ ሌላው የምጠቅሰው ክለብ ሐዋሳ ከተማን ነው፤ ይሄ በወጣቶች የተገነባው ቡድንም እንቅስቃሴው ተስፋ ሰጪም ነው፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ባሳለፍከው ህይወት ደስተኛ ነህ?
ሙሉዓለም፡- በጣም፤ ምክንያቱም ኳስ ጨዋታ ለእኔ የደስታዬ ምንጭ እና ስራዬም ስለሆነ ነው፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ መችስ ተከፍተህ ታውቃለህ?
ሙሉዓለም፡- ቅ/ጊዮርጊስ እያለው ነዋ! ወደዚህ ቡድን ሳመራ ከክለቡ ትልቅነት አንፃር የዋንጫ እልሜን አሳካለው ብዬ ነበር፤ ግን አልሆነም፤ በያኔ በነበሩኝ ቆይታዎቼም ዋንጫውን ከቡድኑ ጋር ስላላነሳው ልከፋና ላዝን እንደዚሁም ደግሞ ልንገበገብም ቻልኩ፡፡
ሊግ፡- በአርባምንጭ ከተማ ውስጥ የሚጫወት እንዳልካቸው መስፍን የሚባል ታናሽ ወንድም አለህ፤ በተቃራኒነት አብረኸው ልትጫወትም ችለሃል፤ በዛ ምን ተሰማህ? ስለ እሱ ወቅታዊ የእግር ኳስ አቋምስ ምን ትላለህ?
ሙሉዓለም፡- እንዳልካቸው ለፕሪምየር ሊጉ አዲስ የሆነና ገናም ታዳጊ የሆነ ልጅ ነው፤ ስለ እሱ ማለት የምፈልገውም በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያው ዓመት ተሳትፎው ላይ አበረታች የሚባል እንቅስቃሴን በማሳየቱ ተስፋ ሰጪ ችሎታ እንዳለው እያስመሰከረ ነውና በዛ ጥሩ አቋሙም ደስ ብሎኛል፤ እኔ እሱ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርስ በምክርም ሆነ በሌሎች ነገሮች እያገዝኩትም ነው፤ እሱን እስካሁን ስመለከተውም ከእኔ በተሻለ ትልቅ ደረጃ ላይ ይደርሳልም ብዬ አስባለውና ያን እልሙን እንዲያሳካም እመኝለታለው፤ በተረፈ ሌላ ማለት የምፈልገው ነገር ቢኖር ደግሞ ከእሱ ጋር እኔ የሲዳማ ቡና እሱ ደግሞ የአርባምንጭ ከተማ ተጨዋች ሆኖ በተቃራኒነት የተጫወትንበትንም አጋጣሚ አግኝቻለውና በዛም መደሰቴን ለመናገር እፈልጋለው፡፡
ሊግ፡- ወደማጠቃለያ እንሂድ አንድ ነገርን ተንፍስ እስኪ….?
ሙሉዓለም፡- ክለባችን ሲዳማ ቡና በውድድር ዘመኑ ያስቀመጠው የራሱ ግብ አለው፤ ያን እልማችንን ለማሳካት ከቡድን አጋር ጓደኞቼ ጋር ጠንክረን ሰርተን ወደፊት እንጓዛለን፤ ለእዚህ ስኬት ማማርም ከእዚህ ቀደም ውጤት ባጣንበት ሰዓት ከእኛ ጋር ተጋጭተውና በኋላም ላይ ጥፋታቸውን በማመን ፌዴሬሽኑንና የሊግ ካምፓኒውን ይቅርታ የጠየቁ ምርጥ ደጋፊዎች ስላሉን እነሱ ከጎናችን ሆነው እንዲደግፉንና እኛም በአፀፋው በውጤት ልናስደስታቸው መዘጋጀታችንን ለመናገር እወዳለው፤ ከዛ ውጪ በፈጣሪ እርዳታም ጥሩ ውጤት እንዲገጥመንም እመኛለው፡፡