test
Google search engine

“ከአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ጋር አይግባቡም ተብሎ ሲነገር የነበረው ወሬ አሉባልታ ነው”ሽመክትጉግሳ /ፋሲል ከነማ/


“ከአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ጋር አይግባቡም ተብሎ ሲነገር የነበረው ወሬ አሉባልታ ነው”


“የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ከፍ አድርገን የምናነሳበት ትክክለኛው ጊዜ ዘንድሮ ነው”ሽመክትጉግሳ /ፋሲል ከነማ/

በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለፋሲል ከነማ የውጤት ማማር ትልቁን አስተዋጽኦ እያደረጉ ከሚገኙት ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ሽመክት ጉግሳ በእስከዛሬው የፕሪምየር ሊግ የተጨዋችነት ተሳትፎው ለአንድም ጊዜ ከተጫወተባቸው ክለቦች ጋር አለማንሳቱ የቁጭት ስሜት እንደፈጠረበት እና ይህ አጋጣሚም በዘንድሮ የውድድር ዘመን ዳግም እንደማይከሰት ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል።


ፋሲል ከነማ በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ የአዲስ አበባ እና የጅማ ከተማ የውድድር ተሳትፎው ባጠራቀመው የድምር ውጤት ሊጉን በ25 ነጥብ እየመራ ሲሆን ተከታዩን ኢትዮጵያ ቡናና ሌሎቹን ክለቦችም በ5 ነጥብ እና ከዛ በበለጠ ውጤትም ርቋቸው ይገኛል።
የፋሲል ከነማ ተጨዋቹ ሽመክት ጉግሳ ይህን ተንተርሶም ቡድናቸው ከነገ ጀምሮ በሚያደርገው የባህር ዳር ከተማ ላይ ቀጣይ ተሳትፎውም የባህርዳር ስታድየም ለጨዋታ በጣም ምቹ ከመሆኑ ጋር አያይዞ የአሸናፊነታቸውን ስኬታማነት እንደሚያስቀጥሉት እና ከተከታዮቻቸው ጋርም ያላቸውን የነጥብ ልዩነትን በማስራቅ የእዚህ ዓመትን የሊግ ዋንጫ አጠቃላይ ውድድሩ ሊጠናቀቅ ጥቂት ጨዋታዎች ሲቀሩ ብቻ አስቀድሞ ለማንሳት እንደተዘጋጁም ሊግ ስፖርት ላቀረበችለት ሌላኛው ጥያቄ ምላሹን አክሎ ሰጥቷል።
ከፋሲል ከነማው የኮሪደር ስፍራ ተጨዋች ሽመክት ጉግሳ ጋር ሊግ ስፖርት በአጠቃላይ ያደረገችው ቆይታም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፤ ተከታተሉት።


የፋሲል ከነማ የአዲስ አበባ እና የጅማ ከተማ ተሳትፎው


“የቤት ኪንግ የሊግ ውድድሩን በአዲስ አበባ ስታድየም ላይ ስንጀምር ቅ/ጊዮርጊስን እናሸንፍ እንጂ ከቡድኑ ተጨዋቾች ውስጥ አንድአንዶቻችን ከብሄራዊ ቡድን ጋር ስለነበርንና ልምምዳችንንም ካሉት እና ወደ ቡድናችንም ከመጡት አዳዲስ ተጨዋቾች ጋር በሚገባ የሰራን ባለመሆኑ ተግባብቶ በመጫወቱ ዙሪያ ክፍተቶች ይታዩብን ነበር። በኋላ ላይ ግን ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ስናመራ ቡድናችን እየተስተካከለ በመምጣቱ ራሳችንን በሚገባ እንድንመለከት አድርጎን ወደ ጅማ ለሌሎች ጨዋታዎች እንድንጓዝ አስችሎናል።
ጅማ ላይ በነበረን ቆይታ ደግሞ ክለባችን በጣም ጥሩ ነበር። ሁሉንም ጨዋታ በማሸነፍ እና አንድ ጎልም ሳይቆጠርበትም ነው ውድድሩን ያጠናቀቀው። ይህ ውጤት ሊመጣ እንደሚችልም ካለን ጥሩ ስነልቦና አንፃርም አስቀድመን ገምተን ነበር። እንደ ቡድን ተከላክለንና አጥቅተን ስለተጫወትንም ነው አሸናፊ የሆነውና በቆይታችን ጥሩ እና ምርጥ የሚባል ጊዜን ነው ልናሳልፍ የቻልነው”።


በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአቸው የሚያስቆጫቸው ጨዋታ


“ከኢትዮጵያ ቡናና ከባህርዳር ከተማ ጋር ያደረግናቸው ጨዋታዎች ናቸው የእነሱ አንድ እና ሁለት ተጨዋቾች በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቶባቸው እያለ እኛ በመዘናጋታችን እነዛን እድል ሳንጠቀም በመቅረት ተሸንፈንና አቻ ወጥተን ነጥብ በመጣል ውድድሩን ልናጠናቅቅ የቻልነው። ያ የውጤት ማጣት የቀን ጉዳይ ሆኖ ሊያጋጥመን ቢችልም ከእነዛ ጨዋታ ግን ለሁሉም ቡድኖች እኩል ትኩረት መስጠት እንዳለብንና ሌሎችም ብዙ የተማርናቸው ነገሮች ስለነበሩ ያ ለቀጣዮቹ ውጤት ላመጣንባቸው ፍልሚያዎች ሊረዱን ችለዋል”።


ፋሲል ከነማ ዘንድሮ ይለያል….. ወይንስ?


“ይለያል እንጂ! ቡድናችን በአሁን ሰዓት ሊጉን ከመምራት ውጪ በጥሩ አቋሙም ላይ የሚገኝ ስለሆነ ደስ የሚል እና ጥሩ ጊዜን ነው እያሳለፍን የሚገኘው ይሄን ውጤታማነታችንን እንደምናስቀጥለውም ያለፉት የጅማ ከተማ የውድድር ቆይታችን ማሳያም ነው የሚሆነው”።
በቤት ኪንግ የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአችሁ ዘንድሮ ተቃውሞን ያስተናገዳችሁበት ወቅትም ነበር
“በአንድ ሁለት ጥሩ ባልነበርንበት እና ነጥብንም በጣልንበት ጨዋታ ላይ በቡድናችን ዙሪያ ዝም ብሎ የሚወራብን ነገር ነበር። ያ የሚወራብንን ነገርም እኛ ተጨዋቾች ከምን ተነስተው ሊባሉ እንደቻሉ የምናውቀው ስለነበር ተቋውሞው እኛን ሊያጠነክረን ችሏል። በኳስ አልፎ አልፎ ጥሩ አለመሆን ሊያጋጥምህ ይችላል። ቅዋሜው ግን ለቡድኑ ታስቦ ከሆነ ጥሩ ነው። በዛ ደረጃ ውጤትን ከመፈለግ እና ቡድኑን ከመውደድ አንፃር የሚቃወሙ እንዳሉም እናውቃለን። እነሱ ከጎናችን ያሉ ናቸው። አንድአንዶቹ ግን እንደዛ አይደሉምና ልክ ቡድናችን ላይ እነዛ ተቃውሞች ሲጀመሩ እኛ ተጨዋቾች ከአሰልጣኛችን ጋር እና እርስበርስም በቡድኑ ዙሪያ በመነጋገራችን እንደዚሁም ደግሞ በቀጣይነት በምናደርጋቸው ጨዋታዎች ላይም በፍፁም ቸልተኛ መሆን እንደሌለብን በማወቃችንም አሁን ላይ ውጤታማነታችንን ተከትሎ ቡድናችን ላይ የነበሩት ተቋውሞዎች ሊቆሙ ችለዋል”።


ፋሲል ከነማ እና ሌሎች ቡድኖችን ዘንድሮ ምን ይለያቸዋል?


“በእስካሁኑ የውድድር ቆይታችን የእኛን ቡድን ከሌሎች አንፃር እንደተመለከትኩት የሚለየው ነገር ቢኖር በጋራ እንደ ቡድን ኳስን አጥቅቶ በመጫወት ጎሎችን እንደሚያስቆጥረው ሁሉ በብዛት ጎልን የማያስተናግድ መሆኑ ነው። በተለይ ጅማ ላይ ባደረጋቸው ጨዋታዎች አንድም ግብን ባለማስተናገድ ብቸኛው ቡድንም ነበርና ይሄ ለየት እንዲል ያደርገዋል”።

የፋሲል ከነማ ተጨዋቾች ከአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ጋር ባለመግባባት ልዩነት ነበራቸው ስለመባሉ


“ይሄን አሉባልታ የሆነ ወሬ እኛ አስቀድሞ ጭምር በፍፁም ያልተቀበልነው ነው። አንድአንዴ ውጤት ስታጣ እንዲህ ያሉ ወሬዎች ሊኖሩ ሊያጋጥሙህና ሊበዙ ይችላሉ። የቡድናችን ተጨዋቾችን ግን ለእነዛ ለሚወሩት ነገሮች ጆሮ ዳባ ልበስ በሚል ትኩረት ስላልሰጠነው የሚወሩት ወሬዎችን ልናጠፋቸው ችለናል። ከአሰልጣኝ ስዩም ጋርም በፊትም ሆነ አሁን ተግባብተንና በሚሰጠን ስልጠናም ተመችቶን ነው ልምምዳችንንም እየሰራን የምንገኘው። ከዛ ውጪ እሱን የምናከብረው አሰልጣኝም ነው”።


ፋሲል ከነማ ዘንድሮ ውጤትን ቢያጣ ማን ተጠያቂ እንደሚሆን


“ያ አያጋጥመንም እንጂ ምንአልባት ቢፈጠር ለውጤት መታጣቱ ተጠያቂነቱን እኛ ወደ አንድ አካል ላይ ብቻ ወስደን የምናነጣጥር አይደለንም። ሁሉም ማለትም አሰልጣኙ ብቻ ሳይሆን ተጨዋቹ ጭምርም ነው የየራሱ ድርሻ ያለውና በጋራ ነው ልንጠየቅ የሚገባን”።


ፋሲል ከነማ ዘንድሮ ውጤትን ቢያጣ ማን ተጠያቂ እንደሚሆን


“ያ አያጋጥመንም እንጂ ምንአልባት ቢፈጠር ለውጤት መታጣቱ ተጠያቂነቱን እኛ ወደ አንድ አካል ላይ ብቻ ወስደን የምናነጣጥር አይደለንም። ሁሉም ማለትም አሰልጣኙ ብቻ ሳይሆን ተጨዋቹ ጭምርም ነው የየራሱ ድርሻ ያለውና በጋራ ነው ልንጠየቅ የሚገባን”።


የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማን ከፍ አድርጎ ያነሳዋል?


“እኛ ነን ሃ! ዋንጫውን ከፍ አድርገን የምናነሳበት ትክክለኛው ሰዓት ዘንድሮም ነው። ይህን ያልኩትም ያለ ምክንያት አይደለም። ባለፉት 5 ጨዋታዎቻችን ሁሉንም ግጥሚያዎች ከማሸነፋችን አንፃር እና ባህርዳር ላይም በምናደርገው ጨዋታ የመጫወቻ ሜዳው ለእንቅስቃሴያችን ስለሚያመች ለዛ ነው አሁን የያዝነውን ነጥብ ከፍ አድርገን በመጓዝ በእርግጠኝነት ሻምፒዮና እንሆናለን የምለው”።


ለፋሲል ከነማ በቀጣይነት ምን አይነት ግልጋሎትን እንደሚሰጥ


“በሊጉ ተሳትፎው ብዙ ጥንካሬ ላለው ፋሲል ከነማ በቀጣይ ጊዜ የውድድር ቆይታችን ውጤታማ እንዲሆን በሜዳ ላይ እኔ ላበረክትለት የምፈልገው ጥቅምና ግልጋሎት ከዚህ ቀደም ከነበረው ከፍ ያለ ነው። በተለይ ደግሞ በእዚህ ዓመት ላይ ይህን ዋንጫ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜም ማግኘትን አጥብቄ ስለምፈልግም ምርጥ ብቃቴን ማሳየቴም አይቀርም”።


የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ እስከዛሬ አለማንሳቱ


“የደደቢት ቆይታዬ ላይ እና በአሁኑ ቡድኔ ፋሲል ከነማ ቡድን ውስጥ ይህን ስኬት ለመጎናፀፍ ከጫፍ ደርሼ ነበር። ያም ሆኖ ግን ዕድለኛ ካለመሆንና በዛ ላይ ደግሞ በውጫዊ ችግሮች ምክንያት እኛ ዋንጫውን እንዳናነሳ በመፈለጉና በኮቪድ ወረርሽኝም ሊጉን እየመራን በነበርንበት ሰዓት ሊጉ ስለተቋረጠ የሻምፒዮናነቱን ዋንጫ እንዳናገኝ አድርጎናልና ያ መሆኑ የሚያስቆጨኝ ነው”።


ከእነሱ ቤተሰብ ውስጥ እግር ኳስን ስለሚጫወቱት ሁለቱ ወንድሞቹ አንተነህ ጉግሳ እና ቸርነት ጉግሳ


“ለወላይታ ዲቻ እየተጫወቱ ስላሉት ስለ እነዚህ ሁለቱ ወንድሞቼ ሁሌም ሳወራ ቃላቶች ናቸው የሚያንሱኝ። ጥሩ ወንድሞችም ስላሉኝ እድለኛም ነኝ። ከዛ ውጪ እነሱ ከጥሩ ተጨዋችነታቸው ባሻገር በጣም ጨዋዎችና ለቤተሰባቸውም የሚያስቡ ጭምር ናቸው። በሜዳ ላይ ያላቸው ኳሊቲም ይገርማል። ቸርነትን በተመለከተ በጣም ጎበዝ ተጨዋች ነው። ብዙ ነገርን ማድረግ ይችላል። አንተነህም በመከላከሉ ላይ ኳስን ቀለል አድርጎ እየተጫወተ ብቃቱን እያሳየም ይገኛል እና ለእነዚህ ወንድሞቼ እኔ ኳስና ማልያ ከመስጠት እና ከመምከር ባሻገር ሌላ በተለይም ደግሞ ወደ ተለያዩ ክለቦች ውስጥ ገብተው እንዲጫወቱ ያደረግኩላቸው ምንም ነገር ስለሌለ፤ በራሳቸው ጥረትም እዚህ የደረሱም በመሆኑ እና እኔም የምፈልገው በዛ መልኩም እንዲመጡም ስለነበር ይሄ መሆኑ ደስተኛ እንድሆን አድርጎኛል። ምክንያቱም በሰው ክለብ ስትገባ መውደቅ ያጋጥማል። በእንትና በኩል መጣህም ይባላል እና እነሱ በራሳቸው ጥረት ክለብ ስለገቡ እና ለጥሩ ደረጃ ላይ ስለደረሱ እንደዚሁም ደግሞ በተቃራኒነትም አብሬያቸው ስለተጫወትኩኝ በጣም ነው ልደሰትባቸው የቻልኩት”።


በቤተሰባቸው አካባቢ ሶስቱም ወንድማማቾች የእግር ኳስን መጫወት ሲጀምሩ ስለነበረው ፍላጎት


“በእኛ ቤተሰብ ውስጥ ለወላጅ አባቴና እናቴ የመጀመሪያው ልጅ እኔ ስለነበርኩ በፊት ትምህርትን እንድማር ከመፈለግ አኳያ በተወሰነ መልኩ ተፅህኖ የነበረው እኔ ላይ ነበር። ያ ግን ወዲያው ሊቆም በቅቷል። በኋላ ላይ ሁለቱ ወንድሞቼ ወደ ኳሱ ሲመጡ ግን የእኔን ፍላጎት ተከትለው ስለነበር ምንም አይነት ተፅህኖ አልነበረባቸውም። እንደውም በመበረታታትም ነው ያደጉት”።


ፋሲል ከነማ አሁን ከያዘው አቋም ሊያሻሽል የሚገባው


“የተወሰኑ ልናሻሽላቸው እና ልናስተካክላቸው የሚገቡን ነገሮች አሉን። እነዛን ክፍተቶቻችንን እና ድክመቶቻችንን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማረም እርግጠኛ ነኝ ዘንድሮ ለቡድናችን የተሻለ ነገር እንሰራለን”።


በዲ.ኤስ.ቲቪ የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድራችን ስለ መተላለፉ


“ጨዋታዎቹ መተላለፋቸው ለእኛ ሀገር መልካም ዜና ነው እየሆነ ያለው። አሁን ስለእኛ ኳስ በደንብ መወራት ጀምሯል። ሰውም የትኛው ተጨዋች ጥሩ ብቃት እንዳለው እና እንደሌለው ማወቅንም ጀምሯል። ስለ ክለቦቻችን ይዘትም በሁሉም ዘንድ እየታወቀም ይገኛል። ከዛ ውጪ ደግሞ የጨዋታው መተላለፍ ጥቅሙ ወደፊት ወደ ኳሱ ለሚመጡት የታዳጊ ወጣት ተጨዋቾች እና ለሀገራችንም የኳስ እድገት ጭምር ስለሆነ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ወደ ኳሱ የሚልኩበት ሁኔታም ይፈጠራል። ሌላው ጥቅም ደግሞ ያለ ችሎታ ከዚህ በኋላ በጓደኝነትና በመግባባት ብቻ ሁሉም ስለሚተዋወቅ ክለብ መግባትም እየቀረ ይመጣልና ጥቅሙ ብዙ ነው”።
በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለአንተ ምርጡ ተጨዋች
“ስም መጥራትን ስላልፈለግኩኝና ማበላለጥ እንዳይሆንብኝ እንጂ ብዙ ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾችን ተመልክቻለሁ። አንዳንዶቹ ወጣት ተጨዋቾች ናቸው ከዚህ የበለጠ ገነው መውጣት ይችላሉ”።


ስለ ቡድናቸው ተጨዋች ሱራፌል ዳኛቸው ወቅታዊ አቋም


“ሱሬ ጥሩና ጎበዝ ተጨዋች እንደሆነ ማንም ያውቀዋል። ቡድናችንን በብዙ ነገርም ያግዘዋል። በእሱ ሜዳ ውስጥ መኖርም ሁልጊዜ ደስተኛ እንድሆንም ያደርገኛል። ይሄ ሆኖ ሳለ ግን አንድአንዴ በሜዳ ውስጥ በሚያጋጥም አይነት የአቋም መዋዥቅ ጥሩ ላትሆን ስትችል ስለ አንተ ብዙ ሊባልም ይችላልና እሱንም በኳሱ ሊከሰት የሚችል ችግር አጋጥሞታል። በጅማ በተካሄደው ጨዋታ ላይ ደግሞ እሱ ገኖ የወጣበት ግጥሚያም ስላለ የተሻለውን ብቃቱን ወደማምጣትም ተቃርቧልና በሱራፌል ላይ የሚወራው ወሬ ብዙ ባይጋነን ደስ ነው የሚለኝ”።


በመጨረሻ……


“በኳስ ተጨዋችነቴ ከጎኔ ሆናችሁ የምትደግፉኝን ቤተሰቦቼን፣ የቡድኔን ደጋፊዎች እና አሰልጣኛችንን ማመስገን እፈልጋለሁ። ይህን ካልኩ አይቀር ለደጋፊዎቻችንም እንደ ቀድሞው ሁሉ አሁንም ከቡድኑ ጎን የምትቆሙበት ትክክለኛው ወቅት ላይም ስላለን ድጋፋችሁና ብርታታችሁ አይለየን። ስጋትም አይግባችሁ ዋንጫውንም እናመጣላችኋለን”።

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

P