Google search engine

ከአየር ንብረት እና ድህነትም በላይ የሆነው የኢትዮጵያውያን የሩጫ ስኬት

ብሪታኒያዊው ማይክል ክራውሌይ ‹‹Condition›› በሚል ርዕስ በኢትዮጵያዊያን ሯጮች ኃይል፣ የግዜ አጠቃቀምና ስኬት ላይ ባተኮረ ጥናቱ በቅርቡ በዩንቨርስቲ ኦፍ
ኤድንብራ የዶክትሬት ድግሪውን አጠናቋል:: ጥናቱን ለመስራት እ.አ.አ. በ2015 እና 2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ፣ በቆጂ እና ጎንደር ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች
ጋር በአጠቃላይ ለአስራ አምስት ወራት የዘለቀ የአብሮነት ቆይታን አድርጓል፡፡ ከአትሌቶቹ ጋር አብሮ ከመኖርና ልምምድ ከመስራት ባለፈም ለውድድር ወደ ኢስታንቡል፣ ቻይና
እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገሮች አብሯቸው ተጉዟል:: ማይክል እራሱም ሯጭ ሲሆን በቅርቡ የተሳተፈበትን የጀርመን ፍራንክፈርት ማራቶን 2 ሰዓት ከ20 ከ53 ሰከንድ በሆነ ግዜ
ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ ጥናቱን ባደረገበት ወቅት ካያቸውና ከሰማቸው ሁነቶች እንዲሁም ከተግባራዊ ተሞክሮው አንፃር የኢትዮጵያውያን አትሌቶችን የሩጫ ስኬት መንገድ
በቀጣዩ ሀተታዊ ፅሁፉ ለመግለፅ ሞክሯል (ይህ ሀተታዊ ፅሁፍ ቀደም ብሎ በእንግሊዘኛ ዘ ጋርዲያን ድረ ገፅ ላይ የወጣ ሲሆን በፀሐፊው ጥያቄ ወደአማርኛ ተተርጉሞ
ቀርቧል)፡፡

ከአራት ሰዓታት ካልዘለለው አጭር እንቅልፍ የነቃሁት ከለሊቱ 9 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ሲል ነበር፡፡ የመሮጫ ቁምጣዬን አድርጌ ስለነበር በፍጥነት የሩጫ ካናቴራዬን ደርቤ ወደ
ውጭ ወጣሁ፡፡ ውጪው በድቅድቅ ጨለማ የተሞላ ሲሆን የአየሩ ቅዝቃዜም ትንፋሼን ወደጭጋግነት ይለውጠው ጀምሯል፡፡ በግንባታ ላይ በሚገኝ ሕንፃ ውስጥ የጥበቃ ስራ
የሚሰራውና ከሀይልዬ ጋር የሚኖረው ፋሲል ዛሬ የእረፍት ቀኑ ነው፡፡ ከቤት ውጭ በሚገኝ ቧንቧ ስር ፊቱን እየታጠበ የነበረው ፋሲል ቃሌን ጠብቄ ልምምድ አብሬያቸው
ለመስራት በዛ ውድቅት ለሊት መነሳቴ አስገርሞታል፡፡ መገረሙንም ‹‹አንተ ፈረንጅ አይደለህም፡፡ ጀግና ነህ፡፡›› በሚል የአድናቆት ቃላት ገለፀልኝ፡፡
ልምምዳችንን ለመጀመር እስከ ኮተቤ ብረታ ብረት – ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ድረስ ዝግ ባለ ፍጥነት እየሮጥን ወጣን፡፡ የአስፓልቱን ቁልቁለት በዝምታ ከወረድነው በኋላ
በሀይልዬ መሪነት የመጀመሪያውን የዳገት መውጣት ሩጫ ተያያዝነው፡፡ በአካባቢው አልፎ አልፎ የሚታየው ብቸኛው ብርሀን የሚመጣው በሱቆች ደጃፍ ላይ ከተንጠለጠሉ
አምፖሎች ነበር፡፡ በዳገት መውጣት መውረዱ ልምምድ ሰባተኛ ወይም ስምንተኛ ዙር ላይ የኮረብታው ጫፍ ላይ በፍጥነት የሚደረሰው እግርን እንጂ የኮረብታውን ጫፍ እያዩ
በመሮጥ እንዳልሆነ ተረዳሁ፡፡ ለአንድ ሰዓት ያህል ከሮጥን በኋላም ሀይልዬ ‹‹ይበቃናል›› በማለት የዕለቱን ልምምድ እንደጨረስን አሳወቀን፡፡ በሶምሶማ ሩጫ ወደቤት
እየተመለስን በነበረበት ወቅት ሀይልዬ ‹‹አሁን ከቤት ውጪ በቀዝቃዛ ውሀ ገላህን ትታጠብና ትተኛለህ፡፡ ይህም ምርጥ እንቅልፍ እንድትተኛ ያደርግሀል›› የሚል ምክርን
ለገሰኝ፡፡ መሬት ጠብ ያላለ ትክክለኛ ምክር ነበር፡፡
ከላይ የተጠቀሰው የልምምድ ፕሮግራም ከኢትዮጵያውያን የረጅም ርቀት ሯጮች ጋር የመስክ ስራ ለመስራት በአዲስ አበባ ያደረግኩት ከአስራ አምስት ወራት በላይ የዘለቀ
ቆይታዬ ጅማሬ ነበር፡፡ ፋሲል እኔ ፈረንጅ ሳልሆን ሀበሻ እንደሆንኩ ሲነግረኝ አያይዞም ወደሀገሬ ዩናይትድ ኪንግደም ስመለስ እና ውድድር ላይ ስሳተፍ ተፎካካሪዎቼን ‹‹ቻው
ፈረንጅ›› እያልኩ በቀላሉ እንደማሸንፍ ጭምር በመግለፅ ይቀልድ ነበር፡፡ ‹‹ቻው ፈረንጅ›› የምትለው አባባልም ጥሩ ልምምድ በምንሰራባቸው ግዜያት ደጋግመን
የምንጠቀምባት የተለመደች ሐረግ ሆና ቀርታለች፡፡
የኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን የሩጫ ስኬት በስፖርት ሳይንቲስቶች ሲተነተን ብዙ ግዜ ከተፈጥሯዊ ዝርያቸው እና ከሚኖሩበት የአየር ንብረት ወይም ጂኦግራፊያዊ
አቀማመጥ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይገለፃል፡፡ ከዛም ሲያልፍ የከፋ ድህነታቸው ውጤት እንደሆነ ይነገራል፡፡ በስፍራው ተገኝቼ በተደጋጋሚ የሰማኋቸው ማብራሪያዎች ያስገነዘቡኝ
እውነታ ግን በጣም ድሀ ለሆኑትም ሯጭ መሆን የማይታሰብ ነገር መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ ከሩጫ ልምምድ በኋላ በቂ እረፍት ማድረግ እንዲሁም ያፈሰሱትን ላብና
ያወጡትን ኃይል ለመተካት በቂና ተመጣጣኝ ምግብ ማግኘት ወሳኝ ነገሮች ናቸው፡፡ እናም የእለት ተዕለት ኑሮን ለማሸነፍ ሰፊ ግዜን የሚወስዱ የተለያዩ የጉልበት ስራዎችን
መስራት ግድ ለሚላቸው ሯጭ መሆን በጣም ፈታኝ ነገር ነው፡፡ ለጥቂት ዓመታት ሯጭ የመሆን ሙከራ አድርጎ የነበረው የአዲስ አበባው ፀጉር አስተካካያችን በጉዳዩ ላይ
ያለውን ሀሳብ ሲገልፅ ‹‹ኢትዮጵያውያንን ሯጭ ከመሆን የሚያግዳቸው የገንዘብ ማጣት ችግር ነው›› ካለ በኋላ ‹‹በቂ ገንዘብ ቢኖረው ሁሉም ሰው ሯጭ ይሆን ነበር››
በማለትም ያክላል፡፡ አብሬያቸው እኖርና ልምምድ አብሬያቸው እሰራ የነበሩት ሯጮች የሩጫ ስኬት ከተሰጥኦ ይልቅ በልምምድ እንደሚመጣ ያምናሉ፡፡ ማንኛውም ሰው
የሌላውን ሯጭ እግር እንዴት መከተል እንዳለበት በሂደት የሚማርበትና ተደጋጋሚ ልምምዶችን የሚያደርግበት ዕድል ከተሰጠው እንዲሁም ትክክለኛ አመለካከት ካለው
ስኬታማ መሆን ይችላል ብለውም ያስባሉ፡፡

ለሊት እየተነሱ ኮረብታማ ቦታዎች ላይ መሮጥ

ኢትዮጵያውያን ሯጮች ትክክለኛውን ከባቢ ሁኔታ እና ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኝላቸውን ኩባንያ ከግምት ውስጥ በማስገባት የልምምድ ፕሮግራም ሲያቅዱ ሰዓታትን ያጠፋሉ፡፡
የተለያዩ የልምምድ መስሪያ ቦታዎችን አመቺነት አዘውትረው ይመዝናሉ፡፡ በእንጦጦ ተራራ ላይ ያለውን የአየር ክብደት ኪሎ ሜትሮችን በቀላሉ እየቆጠሩ ከሚሮጡበት
የሰንዳፋ ሳር ሜዳ ጋር፤ የጫካውን ብርድ የባህር ጠለል ከፍታው በ800 ሜትር ዝቅ ከሚለው የአቃቂ ሙቀትም ጋር ያነፃፅራሉ፡፡ ወደልምምድ ለመሄድ በሕዝብ ማመላለሻ
አውቶብስ የሁለት ሰዓት ጉዞ ማድረግ ለእኛ ያልተለመደ አይነት ነገር አልነበረም፡፡ ወደቤት ለመመለስም የትራንስፖርት ትግሉ ሌላ አራት ሰዓት ይወስዳል፡፡ ያሉበት ከባቢ ሁኔታ
የሩጫ ሕይወታቸው ስኬት ምክንያት ሁኖም ከሆነ ምንም እንከን የሌለው ‹‹ተፈጥሯዊ›› ጠቀሜታ አልነበረም፡፡ ሯጮቹ ከአካባቢያቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት
የሚያስኬዱትም ንቃትና ፈጠራ በታከለበት መንገድ ነው፡፡
በአካባቢ ጠቃሚነት ዙሪያ የሚደረጉ አንፃራዊ ውይይቶች ለብዙ ሰዓታት ሊቀጥሉ ይችላሉ፡፡ በአንድ አጋጣሚ ቅዳሜ ዕለት በጠዋት ስነሳ እኛ ካለንበት ቤት 20 ኪሎ ሜትር
በሚርቀው ለገጣፎ አካባቢ የሚኖረው ተክለማሪያም ግቢ ውስጥ በሚገኘው ቧንቧ ውሀ ፊቱን ሲታጠብ አገኘሁት፡፡ ከለሊቱ 11፡45 ሰዓት ላይ እዛ በመገኘቱ ግርምት
በተሞላበት አስተያየት እያየሁት ‹‹እዚህ ምን ታደርጋለህ?›› ብዬ ጠየቅኩት፡፡ ‹‹የዳገት ልምምድ ለመስራት መጥቼ ነው›› የሚል ምላሽ ሰጠኝ፡፡ አክብሮት በተሞላበት
ስሜት ‹‹የጥሩነሽ ኮረብታ ነው›› በማለትም የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮና ድርብርብ የወርቅ ሜዳልያ ድሎች ባለቤቷ ጥሩነሽ ዲባባ የዳገት ልምምዶችን ለመስራት
የምትጠቀምበት ቦታ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ የልምምድ መስሪያ ቦታዎች ብዙውን ጊዜ ጠቃሚነታቸው ወይም አስፈላጊነታቸው የሚወሰነው እየተለማመዱባቸው ባሉ ወይም ከዚህ
ቀደም ይለማመዱባቸው በነበሩ ሰዎች ምክንያት ይሆናል፡፡ ለምሳሌ እንጦጦ ተራራ ከሌሊቱ 11፡30 አዘውትሮ ልምምድ እንደሚሰራበት ከተነገረኝ የሀይሌ ገብረስላሴ ስም ጋር
ይያያዛል፡፡ የአንዳንድ ቦታዎች ጠቀሜታም ካላቸው የተለየ የአየር ጥራት ጋር የሚያያዝ ይሆናል፡፡ አንድ የጫካ ልምምድ መስሪያ ቦታም ከሌሎቹ ቦታዎች የተለየ ቅዝቃዜ
ስላለውና በቅዝቃዜው ለሚታወቀው የቦስተን ማራቶን የሚዘጋጁ አትሌቶች በብዛት የዝግጅት ልምምዳቸውን ስለሚያከናውኑበት ‹‹ቦስተን›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
እኛ ብዙውን ግዜ ቀለል ያሉ ልምምዶችን የምንሰራበት በደን የተሸፈነ አካባቢም ‹‹አራት ሺ›› የሚል ስያሜ አለው፡፡ የቦታው ትክክለኛ ከፍታ ምንም እንኳን ወደ 2,500
ሜትር የሚጠጋ ቢሆንም ስያሜው የተሰጠው የቦታውን ከፍታ ይገልፃል ከሚል እሳቤ እንደሆነ ተነግሮኛል፡፡

እየተሰቃዩ መሮጥ

ሀይልዬ የዳገት መውጣት መውረዱን ልምምድ መስራት እንደሚያስፈልገው አምኖ ከሚሰራባቸው ምክንያቶች አንዱ ልምምዱ በጣም ተመችቶት የሚሰራው ሆኖ መገኘቱ
ነው፡፡ የቡድን ሰርቪስ መጠቀም ከመጀመሩ በፊት በ200 ብር ወርሀዊ ገቢ ብቻ ይኖር እንደነበር ሁልግዜም ለራሱ ሊያስታውስ ይፈልጋል፡፡ በዛን ግዜ ከተማ ውስጥ ልምምድ
ለመስራት የተሸከርካሪ እና የሰው እንቅስቃሴ በማይበዛበት ለሊት መነሳት ግድ ይለው የነበረ ሲሆን ከለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት የመነሳቱ ትዝታም ያለፈ ማንነቱን ለመቀየር ይበልጥ
እንዲሰራ የሚያነሳሳው ምክንያቱ ሆኗል፡፡ በታይፎይድ ሕመም ተይዞ እየተሰቃየ እንኳን ጫካ ሄደን የሩጫ ልምምድ እንድንሰራ የጠየቀበት ግዜም አይረሳም፡፡ ምንም እንኳን
የአየሩ የሙቀት መጠን በ20ዎቹ አጋማሽ ላይ የነበረ ቢሆንም በደንብ እንዲያልበው ሁለት የመሮጫ ቱታዎችን ደርቦ ዳገቱን በዝግታ እየተራመድን ወጣነው፡፡ ‹‹ይህ ሀሳብህ
ጥሩ መሆኑን እርግጠኛ ነህ ግን?›› ስል ጠየቅኩት ‹‹ከመተኛት ሁሌም መሮጥ ይሻላል›› በማለት መለሰልኝ፡፡ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ወይም ጋሬት ቤል ጉንፋን ቢይዛቸው
እረፍት ያደርጋሉ እንጂ ኳስ አይጫወቱም፡፡ ፈረንጅ በሙሉ መሰል ነገር ቢገጥመው እረፍት ያደርጋል ሀበሻ ግን በሕመም ውስጥ ሆኖም መስራት መቀጠሉን ይመርጣል፡፡
ሀይልዬ ደጋግሞ ሩጫውን እያቆመ ግንባሩን ይደበድባል፡፡ ግንባሩን በመያዝም የማዞር ስሜት እንደተሰማው ይገልፃል፡፡ በተደጋጋሚ ወደቤት እንድንሄድ ስጠይቀው መሮጡን
ሳያቋርጥ የሰጠኝ ምላሽ ግን ‹‹መታገልና ሕመሙን መጋፈጥ አለብኝ›› የሚል ነበር፡፡ በሕመም ተይዞና በሁለቱም አፍንጫዎች ውስጥ ነጭ ሽንኩርት አድርጎ መሮጥ
ያጠነክራል ተብሎ ቢታሰብም ከሕክምና ባለሙያዎች አመለካከት ጋር በጣም የሚቃረን ነው፡፡ ሆኖም ለመሰቃየት መፍቀድና ሩጫን ያለ ቅሬታ መቀጥል ምርጥ አቋምን
የመገንባት ሂደቱ አካል ነው፡፡
ስለ ጽኑ አትሌቶች በስፖርታዊ ሳይንስ ውስጥ ጎልቶ የሚሰማው – በቲም ስካይ የብስክሌት ተወዳዳሪዎች በኩል ሰፊ ዕውቅናን ያገኘው – ንግግር ‹አንፃራዊ ውጤታማነት›
ነው፡፡ የቡድን አባላት ከውድድር በፊት ጥሩ እንቅልፍ መተኛታቸውን ለማረጋገጥ ወደውድድር ስፍራው የራሳቸውን ፍራሽ ይዘው መሄድ ወይም አትሌቶቹ የሚመገቡትን ምግብ
የምግብ ባለሙያ ቤታቸው ድረስ ማቅረብ በማሳያ ምሳሌነት ሊጠቀሱ ከሚችሉት መካከል ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሯጮችም እረፍት ስለማድረግ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡ
ሲሆን ለእኔም በልምምድ መሀል የሚደረጉ የእርምጃ እንቅስቃሴዎችን መጠቀም እንደሌለብኝ እና ከጠዋት ልምምድ በኋላ ጥሩ እንቅልፍ መተኛት እንዳለብኝ በተደጋጋሚ
ነግረውኛል፡፡
ጓደኛዬ ፋሲል ብዙውን ጊዜ በጫካ ውስጥ ስንሮጥ ከፊት ሆኖ እየመራን የገደል ጫፍ በሚመስሉ ቦታዎች ላይ በእጆቻችን የዛፍ ስሮችን እየያዝን እንድንወርድ ወይም እጆቻችንን
እና እግሮቻችንን ደም በደም በሚያደርጉ እሾሀማ ጥሻዎች ውስጥ እንድናልፍ ያደርገን ነበር፡፡ ሆን ብሎም ጅቦች በብዛት የሚኖሩበትን ቦታ እየፈለገ ጅብ ሲያጋጥመንም እየሳቀ
ድንጋይ ያነሳ ነበር፡፡ የመንገድ ምርጫዎቹን ከሩጫ ሕይወት መከራ ጋር በማያያዝ እንዲህ በማለት ያብራራል ‹‹ይህ ውጣ ውረዶች ያሉበት ጫካ እንደሆነ ታውቃላችሁ፡፡
ሁልግዜም ምቹ የሆነ ቦታ ልታገኙ አትችሉም ሳትጠብቁት በድንገት ከኮረብታማ ቦታ ጋር ትፋጠጡ ይሆናል፡፡ ልምምድ መስራት እና ሩጫ እንደዚህ ናቸው፡፡ በሩጫ ሁሉንም
ነገር በመጀመሪያ ሙከራህ ማሳካት አትችልም፡፡ ስኬታማ ለመሆን ከመብቃት በፊትም ብዙ ውጣ ውረዶች ይኖራሉ፡፡›› ለፋሲል ሆን ብሎ እንደዚህ አይነት አስቸጋሪ ሁኔታን

መቀበል በጣም የተሻለ ነገርን ሊሰጡ ለሚችሉ ነገር ግን የመከሰት አጋጣሚያቸው አነስተኛ ለሆኑ ዕድሎች እውቅና መስጠት ማለት ሲሆን አሸናፊ ስለመሆን የሚያስብ
ሰውም የስፖርቱን ሁሉንም አይነት ባሕሪዎች መቀበል እንዳለበት ያምናል፡፡ በሌላ በኩል እኔ የማውቃቸው ሯጮች የሚያገኙትን ውጤት በፀጋ የሚቀበሉና ሂደታዊ
እድገታቸውም በእነርሱ ቁጥጥር ስር ያለው በከፊል እንደሆነ የሚያምኑ ይመስላል፡፡ እንደ ኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይነታቸውም ከላይ የተገለፁት አይነት በጎ የሆኑ
ሥቃዮች እግዚአብሔር ለእነርሱ ባለው እቅዶች ላይ የሚኖራቸው ተፅዕኖ ኢምንት እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ባገኘው ውጤት እንደሚበሳጭ እጠብቀው የነበረ አንድ የማውቀው
አትሌት ከውድድር በኋላ ስለነበረው ደካማ አቋም ስጠይቀው ብዙም የስሜት ለውጥ ሳይታይበት ‹‹የእግዚአብሔር ፈቃድ አልነበረም›› ካለ በኋላ ‹‹ውድድሩን ባሸንፍ እና
መኪና መግዛት ብችል ምናልባትም በመኪና አደጋ ሕይወቴ ሊያልፍ ይችል ይሆናል፡፡ ለእኛ ጥሩ የሚሆነውን ነገር እግዚአብሔር ያውቃል›› የሚል አስተያየትን አክሏል፡፡

‹‹ለብቻ የሚሰራ ልምምድ ለጤንነት ብቻ ነው››

ብዙ ጊዜ ከኢትዮጵያውያን ሯጮች የሰማሁት ሌላኛው ምክር አንድ ሰው ብቻውን እየተለማመደ መሻሻል እንደማይችል የሚጠቁም ነው፡፡ ‹‹ለብቻ የሚሰራ ልምምድ
ለጤንነት ብቻ ነው›› የሚል አባባል ያላቸው ሲሆን ለመሻሻል ከሌሎች መማር የግድ እንደሆነም ያምናሉ፡፡ አብዛኞቹ ሯጮች በከተማ ውስጥ የሚገኙ ክለቦችን እና
የማናጀሮች ቡድኖችን ከመቀላቀላቸው በፊት ሩጫን በገጠር የስልጠና ካምፖች ውስጥ የጀመሩ ናቸው፡፡ ሩጫን ለብቻ መሮጥም ለብቻ እንደመመገብ ማህበራዊ ተቀባይነት
የሌላው ነገር ይመስላል፡፡ ሯጮች አብዛኛውን ግዜ ልምምድ የሚሰሩት በመስመር ተሰልፈው አንዳቸው የሌኛውን እግር በመከተል ሲሆን በተመሳሳይ የእግር አጣጣል ሲሮጡ
የሚታየው እንቅስቃሴም እግራቸው በማይታይ ክር የተያያዘ የሚያስመስል ነው፡፡ የማህበራዊ አውታረመረብ ላይ የጂፒኤስ ዳታን በመጠቀም በዋናነት የቢስክሌት መንዳት እና
ሩጫን ሂደቶች የመከታተል ጠቀሜታ ያለው ስትራቫ የሚባለው ሶፍትዌር አበልፃጊዎች በእነዚህ የሯጮች ቡድን ውስጥ ብዙውን ጊዜ የጂፒኤስ ሰዓቶች በጋራ ጥቅም ላይ
እንደሚውሉና የቡድኑ አባላት እንደሚዋዋሱዋቸው ሲሰሙ መደንገጣቸው የማይቀር ነው፡፡ ምርጦቹ የሥልጠና ክፍለ ጊዜዎችም ሁሉም እኩል ኃይልን ያወጡባቸው እና
እያንዳንዱ ተሳታፊ የበኩሉን ድርሻ በአግባቡ እንደተወጣ የሚታሰብባቸው ናቸው፡፡

የኢትዮጵያውያን የሩጫ ስኬት መንገድ

ከላይ የተዘረዘሩት አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ የኢትዮጵውያን ሯጮችን ጠንካራ ስራ፣ ዕቅድ እና የፈጠራ ችሎታ በደንብ ያሳያሉ፡፡ ሯጮች ክለብን ለመቀላቀል በሙከራ ውድድር
ውስጥ ማለፍ አለባቸው፡፡ አንድ ሯጭ እንደገለፀው ለ3000 ሜትር የትራክ ላይ ሩጫ ለመመረጥ ከ80 ሰዎች ጋር መፎካከር ነበረበት፡፡ ክለቡ የመጀመሪያዎቹን ሦስቱን
እንደሚወስድና አራተኛ ሆኖ ካጠናቀቀ በሚቀጥለው ዓመት በድጋሚ ዕድሉን ለመሞከር መምጣት እንዳለበትም ተነግሮታል:: ከአካባቢው ክለብ ወደ ክልል ክለብ ለመግባት
በተደጋጋሚ በተመሳሳይ ሂደት ውስጥ ማለፍ ግድ ያለው ሲሆን ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት የበቃውም ከብዙ አመት በኋላ በክልል ሻምፒዮና ላይ በሜዳልያ ደረጃ ውስጥ ገብቶ
ለማጠናቀቅ በበቃበት ግዜ ነበር፡፡
የወቅቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ተቋማዊ አደረጃጀት ጥሩ የሚባል ነው፡፡ በዩናይትድ ኪንግደም በከፍተኛ የቡድን ተፎካካሪነት ከባቢ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ
የረጅም ርቀት ሯጮችን የሙሉ ሰዓት ስልጠና እንዲያገኙ የሚደገፉበት ሁኔታ ቢኖር ኖሮ – እኛም በረጅም ርቀት ሩጫ የምንፈራ ኃይል እንሆናለን ብዬ እጠብቃለሁ – የሀገሪቱ
አትሌቲክስ አስተዳዳሪ አካል ስኬቱ የድህነት እና የሀገሪቱ የአየር ሁኔታ ውጤት ነው ተብሎ እንዲጣጣል አይሻም፡፡ የኢትዮጵያን የሩጫ ስኬትን ከከፍታ እና ድህነት አንፃር
ለማስረዳት መሞከርም ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ሯጮች ሊቆጣጠሩት ከማይችሉት ሁኔታ ጋር ማያያዝ ነው፡፡ ይህም በጣም አግባብነት የሌለው ነው::

Written by Michael Crawley & Translated by Bizuayehu Wagaw

 

ብዙአየሁ ዋጋው በኢንተር ስፖርት ጋዜጣ ላይ ይሰራቸው ከነበሩት የአትሌቲክስ ዘገባዎች በተጨማሪ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አሳታሚነት ይወጣ በነበረው ሰላምታ መፅሔት እና
በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (IOC) የለንደን 2012 ኦሊምፒክ ሪቪው መፅሔቶች ላይ ለሕትመት የበቁ የተለያዩ የአትሌቲክስ ዘገባዎችን ያበረከተ፤ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ
ፌዴሬሽኖች ማሕበር (IAAF) ይፋዊ ድረገፅ ላይ ከኤልሻዳይ ነጋሽ ጋር ለስድስት ዓመት (ከ2003 – 2009 ዓ.ም.) በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ የአትሌቲክስ ስፖርት ክንውኖዎች
ዘገባዎችን እና የኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ግለ ታሪክ ለዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ስፖርት አፍቃሪ ማሕበረሰብ የሚያስተዋውቁ ስራዎችን የሰራ፤ በለንደን 2012 እና በሪዮ ደ ጃኔዪሮ
2016 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እንዲሁም በሞስኮ 2013፣ ቤይጂንግ 2015 እና ለንደን 2017 የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድሮች ላይ በስፍራው
በመገኘት የኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ተሳትፎ እና ውጤት ዘገባ ለኢትዮጵያውያን የስፖርቱ አፍቃሪዎች ያደረሰ፤ በ2 የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች፣ በአውሮፓ እና መካከለኛው
ምስራቅ በተካሄዱ 7 የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች እንዲሁም በአውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ በተካሄዱ ታላላቅ የማራቶን እና ግማሽ ማራቶን ውድድሮች ላይ በመታደም የኢትዮጵያውያን
አትሌቶችን ተሳትፎ እና ውጤት በቅርበት የተከታተለ በአሁኑ ሰዓትም በኢትዮ ቲዩብ ድረገፅ ላይ አልፎ አልፎ የተለያዩ የአትሌቲክስ ዘገባዎችን በማቅረብ ላይ የሚገኝ ፍሪላንስ የስፖርት ጋዜጠኛ ነው፡፡

 

ማይክል ክራውሌይ ‹‹Condition›› በሚል ርዕስ በኢትዮጵያዊያን ሯጮች ኃይል፣ የግዜ አጠቃቀምና ስኬት ላይ ባተኮረ
ጥናቱ በቅርቡ በዩንቨርስቲ ኦፍ ኤድንብራ የዶክትሬት ድግሪውን አጠናቋል:: ጥናቱን ለመስራት እ.አ.አ. በ2015 እና 2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ፣
በቆጂ እና ጎንደር ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጋር በአጠቃላይ ለአስራ አምስት ወራት የዘለቀ የአብሮነት ቆይታን አድርጓል፡፡ ከአትሌቶቹ ጋር አብሮ
ከመኖርና ልምምድ

ከመስራት ባለፈም ለውድድር ወደ ኢስታንቡል፣ ቻይና እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገሮች አብሯቸው ተጉዟል:: ማይክል እራሱም
ሯጭ ሲሆን በቅርቡ የጀርመን ፍራንክፈርት ማራቶን ተሳትፎውን 2 ሰዓት ከ20 ከ53 ሰከንድ በሆነ ግዜ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ በአሁኑ ሰዓት
ከቀለም ትምህርቱ ስራ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ ከሞዮ ስፖርት ማኔጅመንት ጋር የሚሰራ ሲሆን ለኢትዮጵያውያን ሯጮች የስፖርቱን ኢኮኖሚያዊ ጎን
ፍትሀዊ እና ይበልጥ ግልፅነት የተሞላበት እንዲሆን የሚያስችሉ መንገዶችን በመፈለግ ላይ ይገኛል::

 

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P