Google search engine

“ከአፍሪካ ዋንጫው በጊዜ ብንወጣም በኳሱ ከሌሎች ሀገራት ርቀት አለን ብዬ አላስብም” ሳምሶን ጥላሁን /ሀድያ ሆሳዕና/

“እያንሰራራ ያለውን ቡድናችንን ለዋንጫው ፉክክር ጠብቁት”
“ከአፍሪካ ዋንጫው በጊዜ ብንወጣም በኳሱ ከሌሎች ሀገራት ርቀት አለን ብዬ አላስብም”
ሳምሶን ጥላሁን /ሀድያ ሆሳዕና/
በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ሀድያ ሆሳዕናን በመሀል ሜዳው ላይ በማገልገል ጥሩ ጥቅምን እየሰጠ የሚገኘው ሳምሶን ጥላሁን በክለባቸው የሐዋሳ ከተማ የዘጠኝ ሳምንታት የውድድር ተሳትፎአቸው ዙሪያና ስለ ዋልያዎቹ የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ቆይታ እንደዚሁም ደግሞ በቀጣይነት ስለሚኖረው የቤትኪንጉ ፕሪምየር ሊግ ፉክክር ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ከሆነው ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር ቆይታን አድርጎ ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶታል፤ ተከታተሉት፡፡
ሊግ፡- በቅድሚያ ከጥምቀት በዓል እንነሳ፤ በዓሉ እንዴት አለፈ?
ሳምሶን፡- የጥምቀት በዓልን ያሳለፍነው በልምምድ ነው፤ ልምምዳችንን ከሰራን በኋላም በድምቀት ልናሳልፈው ችለናል፡፡
ሊግ፡- የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ ጅማሬያችሁ መልካም የሚባል አልነበረም፤ በሂደት ደግሞ መሻሻሎችን አሳይታችኋል?
ሳምሶን፡- የእውነት ነው፤ ውድድሩን ስንጀምር ከአንድ አንድ እኛን ባጋጠመን የፋይናንስ ችግር ቡድናችንን ውጤት አሳጥቶት ነበር፤ ቀስ በቀስ ግን ችግሮቻችን እየተቀረፉ በመምጣታቸው ወደ ውጤታማነት ልንመጣ ችለናል፤ አሁን ያለንበት ሁኔታም ጥሩ የሚባል ነው፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘጠኝ ሳምንታት ጉዞአችሁ የነበራችሁ ጠንካራና ደካማ ጎን ምንድን ነበር?
ሳምሶን፡- ሀድያ ሆሳዕና በእዚህ ዓመት እያደረገ ባለው የውድድሩ ተሳትፎ የተወሰኑ ግጥሚያዎችን ተሸንፎ ቢሆንም ከግብ አጨራረስ ችግሩ በስተቀር በእንቅስቃሴ ደረጃ ደካማ የሚባል አቋም አልነበረውም፤ ከእዛ ይልቅ እንደሁም ብዙ ጠንካራ ጎን ያለው ቡድን ነው ያለን፡፡
ሊግ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ እስኪቋረጥ ድረስ በነበሩት ያለፉት ዘጠኝ ሳምንታት ጨዋታዎቻችሁ በጣም ያስቆጨህ ጨዋታ የትኛው ነበር?
ሳምሶን፡- ብዙዎቹ ውጤት ያጣንባቸው ግጥሚያዎች እኛን ያስቆጩን ቢሆንም በዋናነት ግን ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር አድርገን የነበረው ሁላችንንም ያስቆጨን ነው፤ ሌላው የተቆጨንበት ደግሞ ከባህርዳር ከተማ ጋር ያደረግነውም ነበር፡፡
ሊግ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ቀጥሎ በድሬዳዋ ከተማ ላይ ይካሄዳል፤ ለእዛ ውድድር ራሳችሁን በምን መልኩ እያዘጋጃችሁ ነው?
ሳምሶን፡- የድሬዳዋ ከተማ ለምታስተናግደው ለእዚህ ውድድር በቀን ሁለት ጊዜ ነው በመለማመድ ላይ የምንገኘው፤ በሐዋሳ ቆይታችን የቡድናችን ጠንካራና ደካማ ጎን በደንብ ስላወቅነው ከእዛ በመነሳት ነው በክፍተቶቻችን ዙሪያ ሰርተን በመምጣት ካለፈው በተሻለ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ጥረት የምናደርገው፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮና መሆን፣ የደረጃ ፉክክር ውስጥ መግባት፣ መሀል ሰፋሪ ላይ ሆኖ መጨረስና ከሊጉ ላለመውረድ መጫወት የቡድኖች እቅድ እንደሆነ ይታወቃል፤ እናንተ ከየትኛው ውስጥ ነው የምትመደቡት?
ሳምሶን፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎአችን ጅማሬያችን የአማረ የሚባል ባይሆንም አሁን አሁን ላይ ግን እየተሻሻልን የመጣንበት ሁኔታ ታይቷል፤ ከእዛም በመነሳት በዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎአችን ልናስመዘገብ ያሳብነው ውጤት ከሊጉ መሪ ቡድኖች ጋር ብዙም ያልራቀ የነጥብ ልዩነት ስላለን በቡድኑ ታሪክ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ የሚባል ውጤትን ማስመዝገብ ነው፡፡
ሊግ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን እንደ አጠቃላይ እንዴት ተመለከትከው?
ሳምሶን፡- ከአምናው አኳያ ያን ያህል አስደሳች አልነበረም፤ የሜዳው ለጨዋታው ምቹ አለመሆንና አየሩም ከበድ ይል ስለነበር ቡድኖች ጥሩ ነገርን እንዳያሳዩ ተፅህኖ አድርጎባቸዋል፡፡
ሊግ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን የትኛው ቡድን ሊያነሳ ይችላል?
ሳምሶን፡- በእዚህ ሰዓት እና አሁን ላይማ ውድድሩ ገና በርካታ ግጥሚያዎች የሚቀሩት ከመሆኑ አኳያና ቡድኖችም ደግሞ ወጥ የሆነ አቋምን እያሳዩ ስላልሆኑ ዋንጫውን የሚያነሳውን ቡድን ማወቅ በጣም ከባድ እና አዳጋች ነው፡፡
ሊግ፡- የእዚህ ዓመት ወቅታዊ አቋምህን እንዴት ተመለከትከው?
ሳምሶን፡- በአዲስ ቡድን ውስጥ ብገኝም ያንን ያህል መጥፎ ጊዜን በክለቡ ውስጥ አላሳለፍኩም፤ ጥሩ ቆይታ ነበረኝ፤ ከእዚህ በኋላም ደግሞ ለክለቤ ከእኔ የሚጠበቀውን ጥሩ ነገርን አደርጋለው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን /ዋልያዎቹ/ በካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎን አድርጎ በአንድ ነጥብ ወደ ሀገሩ ተመልሷል፤ ስለ ቡድኑ ምን ማለት ይቻላል?
ሳምሶን፡- በአፍሪካ ዋንጫው ተሳትፎአችን ከሌላው ጊዜ ግጥሚያዎቻችን የተሻለ ነገርን አይቻለው፤ በተለይም ደግሞ በለመድነው አጨዋወትና በሰለጠንበት መንገድ ለውድድሩ መቅረባችንን ሳየው እንደ ጥሩ ጎኑ ነው የወሰድኩት፡፡
ሊግ፡- በውድድሩ ጉዞአችን እንደ ጥሩ ያልሆነ ጎን የወሰድከው ነገርስ ምንድን ነበር?
ሳምሶን፡- ጥሩ ለመጫወት ብንሞክርም የአቅም፤ የፊትነስ ችግሮች ነበሩብን፡፡ እነዚህን ለቀጣይ ልናስተካክል ይገባናል፤ ይሄ ከተስተካከለም የአፍሪካ ጠንካራ ቡድን የማንሆንበት ምክንያት ምንም የለም፡፡
ሊግ፡- በካሜሮን አፍሪካ ዋንጫው ለአንተ ምርጡ ቡድን ማን ነው?
ሳምሶን፡- በእስካሁኑ ጨዋታዎች ናይጄሪያ ነች ለእኔ ምርጧ፤ ቡድናቸውን በአብዛኛው ያዋቀሩት በወጣት ተጨዋቾች ነው፤ ረጋ ብለው ጥሩ ኳስን ይጫወታሉ፤ ታክቲካል ዲስፕሊን ናቸው፤ በፊትነሱ ረገድም ጥሩ ስለሆኑ እነሱን አድንቄያቸዋለው፡፡
ሊግ፡- በአፍሪካ ዋንጫው ለዋልያዎቹ መጫወት አያጓጓህም?
ሳምሶን፡- ያጓጓል እንጂ ይሄ ጉጉት ደግሞ የእኔ ብቻ ሳይሆን የሌሎችም ተጨዋቾች ነው፤ ሁሌም በውድድሩ ላይ ተሳታፊ ብሆን በጣም ነው ደስ የሚለኝ፤ ዘንድሮም መጫወትን እፈልግ ነበር፤ በአሰልጣኝ ምርጫ አልተካተትኩም፤ ከዚህ በኋላ በሚኖረው ቡድን ውስጥ ግን ተካትቼ ለመጫወት ከፍተኛ ጥረትን አደርጋለው፡፡
ሊግ፡- በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ የዋልያዎቹ የተጨዋቾች ስብስብ ውስጥ የትኛው ተጨዋች ለአንተ ምርጡ ነበር?
ሳምሶን፡- እንደ ግል በዋናነት አማኑኤል ዩሃንስ ጥሩ ነገርን አሳይቶናል፤ ይህ ተጨዋች በብዙዎች ዘንድም ከፍተኛ አድናቆትን ሊያተርፍም ችሏል፤ ከእሱ ሌላ ደግሞ ግብ ጠባቂያችን ተክለማሪያም ሻንቆም ላይ ጥሩ ነገር ታይቷል፤ ከእሱ ውጩ አስቻለው ታመነም ጥሩ መጫወት ችሏል፡፡
ሊግ፡- በአፍሪካ ዋንጫው ተሳትፎአችን ዋልያዎቹን ከሌሎች ሀገራት አኳያ እንዴት ተመለከትካቸው?
ሳምሶን፡- የእኛን ቡድን ስመለከት በእግር ኳሱ ከእነሱ ጋር ሰፊ ርቀት አለን ብዬ ፈፅሞ አላስብም፤ የእኛ ችግር ጥሩ መጫወት እንጀምርና ከአቅም ማነስ በእዛው ቴምቦ ያለመቀጠል ችግር ነው፤ ከዛ ውጪም የአየር ላይ ኳስ ችግርም አለብን፤ እነዚህን ክፍተቶች ደግሞ በጠንካራ ስራም መቅረፍ ይቻላልና እዛ ላይ በደንብ ብናተኩር ለወደፊቱ ለምንገነባው ብሔራዊ ቡድናችን መልካም ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- ስለ አሰልጣኛችሁ ሙሉጌታ ምህረት ምን የምትለው ነገር አለ?
ሳምሶን፡- እሱን በሚመለከት ብዙ ሰው ያውቀዋል፤ ወደ ስልጠናው ዓለም የገባውና ስራውን የጀመረውም በቅርብ ነው፤ ለተጨዋቾች በሚሰጠው ነፃነት ይወደዳል፤ የሚያሰራው ልምምድም ጥሩ ነው፤ ሁላችንም የምናከብረው አሰልጣኝም ነው፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…..?
ሳምሶን፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ ተሳትፎአችን የእኛ ቡድን በእንቅስቃሴም ሆነ በውጤት ደረጃ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ለውጦችን እያስመለከተን የመጣበት ሁኔታ ስላለ ይሄን ጉዞአችንን አሁንም በድሬዳዋ ከተማ ላይ በሚኖረን ቆይታ የምናስቀጥለው ይሆናል፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: