Google search engine

“ከኢትዮጵያ ቡና ባለን ጨዋታ ውጤቱ ከ90 ደቂቃ በኋላ የሚወሰን ቢሆንም ወደ ኮንፌዴሬሽን ካፑ ለማለፍ ከፍተኛ ጥረትን እናደርጋለን”“ለሀድያ ሆሳዕና ትንሽ ነገር ሰርቼ ብዙ ተወርቶልኛል”ዳዋ ሆቴሳ /ሀድያ ሆሳዕና/

 

ሀድያ ሆሳዕና በዘንድሮው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን ተሳትፎው ለተጨዋቾቹ ደመወዝ ካለመክፈል ጋር ተያይዞ ብዙ ችግሮችን ቢያሳልፍም፤ ብዙ ነገሮች ቢነሱበትም ሻምፒዮናውን ክለብ ፋሲል ከነማንና ቡናን  በመከተል በ3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ እያስደነቀው ይገኛል፤ ሀድያ ሆሳዕና በኢትዮጵያ ቡና በሁለት ነጥቦች በመበለጥ በሶስተኛ ደረጃ ላይ በሚገኝበት የአሁን ሰዓት ላይም ነገ ከቡና ጋር እንደዚሁም በቀጣይነት ከጅማ አባጅፋር ጋር ያለው ጨዋታ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ሊያሸጋግረውና እነዚህ ጨዋታዎችም ቡድኑን ወደ ኮንፌዴሬሽን ካፕ እንዲያልፍ ፍንጭ የሚሰጡም ስለሆኑ በቡድኑ ተጨዋቾች ዘንድ የግጥሚያው ወሳኝነት በጉጉት እየተጠበቀም ይገኛል፡፡

የሀድያ ሆሳዕናውን የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች ዳዋ ሆቴሳን የሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ በቡድኑ እና በራሱ ዙሪያ ላቀረበለት ጥያቄዎችም ተጨዋቹ ምላሹን ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፡፡

ሊግ፡- ሀድያ ሆሳዕና ዘንድሮ ሊጉን እስከመምራት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር፤ በኋላ ላይ ሊያፈገፍግ ችሎ አሁን ላይ ለኮንፌዴሬሽን ካፑ ለማለፍ እየተጫወተ ይገኛል፤ በቡድናችሁ አቋም ዙሪያ የምትለው ነገር ካለ?

ታፈሰ፡- የውድድር ዘመኑ ሲጀመር ልክ ነህ ቤትኪንጉን እየመራን ነበር፤ በተለይ አዲስ አበባ ላይ በነበረን ቆይታም በጥሩ ብቃት ላይ እንገኝም ነበር፤ ፋሲል ከነማ አስቀድሞ ዋንጫውን አነሳ እንጂ እኛ በዛ በነበረን አቋም ብንቀጥል ኖሮ ከስር ከስር እንከተለው ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘና ሌሎች ጥቃቅን ችግሮቻችን ውጤትን ሊያሳጣን ስለቻለ አሁን ላይ ለኮንፌዴሬሽኑ ካፕ ለማለፍ ለሚደረገው ፉክክር ብቻ ግጥሚያችንን እየተጠባበቅን ነው የምንገኘው፤ በተለይ ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ያልተከፈላቸው ተጨዋቾች አሉ፤ ሁሉም የራሱ ቤተሰብም አለው፤ ኳስ ጨዋታ ደግሞ አህምሮም ነውና ያ ክፍተት ተደፍኖ ቢሆን ኖሮ ቡድናችን ከዚህ በላይም ይጓዝም ነበር፡፡

ሊግ፡- ከኢትዮጵያ ቡና የሚኖራችሁ የነገው ጨዋታ ወደ ኮንፌዴሬሽን ካፑ ለማለፍ ፍንጭን የሚሰጣችሁ ነው፤ በጨዋታው ዙሪያ ምን ትላለህ?

ታፈሰ፡- ለእዚህ ጨዋታ እኛ እንደ ሌላው ጊዜ ሁሉ ነው ጥሩ ዝግጅትን እያደረግን የምንገኘው፤ የውድድሩ ሁለተኛ ሆነን ሊጉን እንድናጠናቅቅም ይህ ግጥሚያ ወሳኝ ስለሆነም ከፍተኛ ትኩረትም ሰጥተነዋል፤ በሁለታችን መካከልም ጥሩ ፉክክር ይደረጋል ብዬም ስላሰብኩ የጨዋታው መዳረሻ ሰዓት እያጓጓኝም ይገኛል፡፡

ሊግ፡- የእሁዱ ጨዋታ አሸናፊ ሀድያ ሆሳዕና ወይንስ ኢትዮጵያ ቡና?

ዳዋ፡- ይሄ ውጤት ከ90 ደቂቃ በኋላ ይወሰናል፤ በጨዋታው ጥሩ የሚሆነው ቡድንም ያሸንፋል፡፡

ሊግ፡- የሀድያ ሆሳዕና በርካታ ተጨዋቾች ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ራሳቸውን ከውድድሩ አግልለዋል፤ ክለቡም ቀጥቷቸዋል፤ አንተ ግን ለቡድኑ እየተጫወትክ ነው፤ ደመወዝ ተከፍሎ ነው የምትጫወተው?

ዳዋ፡- አዎን፤ ለቡድኑ ለምሰጠው ግልጋሎት ባለኝ ስምምነት ደመወዝ  ተከፍሎኝ ነው ስራዬን እየሰራው የምገኘው፡፡

ሊግ፡- በቤትኪንጉ ሀድያን ዘንድሮ እንዴት አገኘኸው?

ዳዋ፡- የውድድር ዓመቱ ጅማሬ ላይ አዲስ አበባ እያለን ጥሩ ነበርን፤ ወደ ጅማ ከተጓዝን በኋላ ግን ውጤት ተበላሸብን፤ አሁን ላይ ደግሞ መልሶ በፊት ወደነበረን አቋም በመመለስ ላይ ስለሆንን ምንም እንኳን የሻምፒዮናውን ዋንጫ ፋሲል ከነማ ሊያነሳብን ቢችልም ወደ ኮንፌዴሬሽን ካፑ ሊያሳልፈን የሚያስችለው ሁለተኛ ሆነን የምናጠናቅቅበት ዕድሉ አለንና ለእነዛ ጨዋታዎቻችን እየተዘጋጀን ነው የምንገኘው፡፡

ሊግ፡- በርካታ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾቻችሁ ራሳቸውን ከቡድኑ ባገለሉበት ሁኔታ ላይ ነው አሁን ብዙ ወጣት ተጨዋቾችን ጨምራችሁ  እየተጫወታችሁ የሚገኘው፤ በተጨዋቾቹ ብቃት ላይ ምን ልዩነትን አየህ?

ዳዋ፡- የልምድ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በችሎታቸው ላይ ልዩነትን አላየሁባቸውም፤ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾቻችን  ግን ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ራሳቸውን ከቡድኑ አገለሉ እንጂ አሁን ላይ እነሱ ቢኖሩልን ኖሮ የበለጠ ጥሩ ይሆንልን ነበር፤ ምክንያቱም በዚህ ሰዓት እኛ ጥቂት የምንባል ሲኒየር ተጨዋቾች በየቦታው የብዙ ወጣት ተጨዋቾችን ቦታ እየሸፈንን እየተጫወትን በመሆኑም ነው፤ አንድ ሰው የብዙ ሰው ቦታን እየሸፈነም ነው የሚጫወተው፤ በዛ ላይ ልጆቹ ወጣት ስለሆኑም በብዙ ነገር እየረዳናቸውና እያደፋፈርናቸውም ነው የምንጫወተውና ወደፊት ልምዱን ሲያገኙ ምርጥ ተጨዋች እንደሚሆኑ እምነቴ ነው፡፡

ሊግ፡- በዘንድሮ የውድድር ዘመን በጥሩ ብቃቴ ላይ ነው የምገኘው ትላለህ?

ዳዋ፡- በአብዛኛው አዎን፤ የቡድኑ አቋም በወረደ ጊዜ ደግሞ እኔም አንድ ላይ የወረድኩበት ሁኔታም አለ፤ ምክንያቱም ቡድንህ ላይ አንድ ነገር ተፈጥሮ ውጤትን ስታጣ አንተም ጥሩ የማትሆንበት ሁኔታም አለና ዘንድሮ እኔን ያም አጋጥሞኛል፡፡

ሊግ፡- ሀድያ ሆሳዕና አሁን በ3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፤ ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎቹን ካሸነፈ ደግሞ ሊጉን በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሆኖ ሊያጠናቅቅ ይችላልና፤ በዚህ ዙሪያ የምትለው ነገር ካለ?

ዳዋ፡- ለሀድያ ሆሳዕና ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ቡድኑ ብዙ ችግሮችን እያስተናገደ ባለበት ሰዓት ላይ እነዚህ ውጤቶች በተለይም ደግሞ ሁለተኛ ሆነን የምናጠናቅቅበት ሁኔታ ከተፈጠረ ለቡድናችን ትልቅ ስኬት ነው፤ የሁለተኝነት ውጤት ደግሞ ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን የሚያሳትፍ በመሆኑም በእነ እገሌ ጊዜ ነው ይህ ውጤት የተገኘውም ተብሎ ስለሚወራልህም ይህ ውጤት ካልተሳካ ደግሞ በደረጃው ፉክክር የሚያስገባንን ሶስተኛ ደረጃን ይዘን ካጠናቀቅንም ለእኛ ምርጥ የሚባል ውጤት ነው፡፡

ሊግ፡- ፋሲል ከነማ ቤትኪንጉን አሸንፏል፤ ድሉን አስመልክተህ ምን ትላለህ?

ዳዋ፡- ሁሉንም አሳምነው ነው ባለድል የሆኑት፤ ከጅማሬው አንስቶ ጥሩ ስለነበሩ የሻምፒዮናነቱ ውጤት ይገባቸዋል፤ በዚህ አጋጣሚም እንኳን ደስ አላችሁ ልላቸውም እወዳለው፡፡

ሊግ፡- አቡበከር ናስርም በ27 ግብ በጌታነህ ከበደ ተይዞ የነበረውን ሪከርድ ሰብሯል፤ በእሱ ዙሪያስ ምን አልክ?

ዳዋ፡- ስለ አቡበከር ብዙ ተብሏል፤ በጣም ጎበዝ አጥቂ ነው፤ ወደፊት ገና ከዚህ በላይም መጓዝ ይችላልና እሱንም በጌታነህ ከበደ ተይዞ የነበረውን የግብ ሪከርድ ከአራት ዓመት በኋላ ስለሰበረው እንኳን ደስ ያለህ ልለው እወዳለው፡፡

ሊግ፡- በመጨረሻ…?

ዳዋ፡- የሀድያ ሆሳዕና ደጋፊዎች ቡድኑ ውስጥ ባለኝ ቆይታ ለእኔ የሚሰጡኝ አድናቆትና ፍቅር ላቅ ያለና የተለየ ነው፤ ለእዚህ ምስጋናዬን አቀርባለው፤ ስለእነሱ ይሄን ካልኩ እኔ ትንሽ ነገርን ሰርቼ ነውና ብዙ እያወሩልኝ ያሉትና ጥሩ ነገርን ባደርግላቸው ብዬም እየተመኘው ነው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P