Google search engine

“ከእኔ የተሻሉ አጥቂዎች ስላሉ ለዋልያዎቹ ባለመመረጤ አይከፋኝም” ይገዙ ቦጋለ /ሲዳማ ቡና/

 

ይገዙ ቦጋለ /ሲዳማ ቡና/

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ 5 ግቦችን በማስቆጠር ከቅ/ጊዮርጊሱ ኢስማሄል ኦሮ አጎሮ ጋር በጋራ  የኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ይገኛል፤ ለክለቡ ሲዳማ ቡና ባለፉት ተከታታይ ዓመታትም ግቦችን በማስቆጠር በአጥቂ ስፍራው ላይ ተስፋ ሰጪ ችሎታ እንዳለውም በማስመስከር ላይ ይገኛል፤ ይህ ተጨዋች ይገዙ ቦጋለ ሲባል የሊግ ስፖርት ጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ አነጋግሮት ምላሹን እንደሚከተለው ሰጥቶታል፡፡

ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ 5 ግቦችን በማስቆጠር የኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ይገኛል፤ ለብሔራዊ ቡድን ግን አልተመረጥክም፤ መመረጥና ወደ ካሜሮንም መሄድ ነበረብኝ ብለህ ታስባለህ?

ይገዙ፡- በፍፁም፤ ምክንያቱም ለዋልያዎቹ የተመረጡት አጥቂዎች ከእኔ በልምድም ሆነ በችሎታቸው የተሻሉ ተጨዋቾች እንደሆኑ ስለማውቅ ነው፤ ስለዚህም ለዋልያዎቹ ባለመመረጤና ወደ ካሜሮን ባለመሄዴ ቅር አልተሰኘውምም አልተከፋውምም፡፡

ሊግ፡- ወደፊት ለሚመረጠው የብሔራዊ ቡድንስ የቡድኑ አባል የምትሆን ይመስልሃል?

ይገዙ፡- በእርግጠኝነት አዎ ነው የምልህ፤ አሁን ላይ በእግር ኳሱ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን በማሳየት ላይ ነው ያለሁት፤ ብዙ ልምዶችን በመቅሰምም ላይ ነው የምገኘው፤ ይሄ በመሆኑም በቀጣይነት ብዙ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች ስላሉ ከፈጣሪ እርዳታ ጋር የቡድኑ ተጨዋች እንደምሆን አምናለውኝ፡፡

ሊግ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ተቋርጣል፤ የእረፍት ጊዜህን በምን መልኩ እያሳለፍክ ነው?

ይገዙ፡- የእግር ኳስ ተጨዋች ስትሆን ሁሌም ቢሆን የእረፍቱን ወቅት ካለፉት የውድድር ተሳትፎክ ምን ደካማ ጎን ነበረኝ፤ ምንስ ጠንካራ ጎን አለኝ ብለህ ራስህን በመፈተሽ ለቀጣይ ጨዋታዎች መዘጋጀት ስላለብህ እኔም የአሁን ሰዓት ላይ ቀለል ያሉ የአካል ብቃት ማጠናከሪያ ልምምዶችን በመስራት ራሴን በብቁ ሁኔታ እያዘጋጀሁት ነው፡፡

ሊግ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሲቋረጥ ወላይታ ድቻን በመርታት ነበር ወደ እረፍቱ ያመራችሁት፤ ያ ውጤት ለእናንተ የሚገባችሁ ነበር?

ይገዙ፡- አዎን፤ ውጤት እንደሚገባንም ሁሉም ጨዋታውን ስለተመለከተም ከእኔ ይልቅ መናገር ይችላል፤ በእዛን ዕለት ጨዋታ የእኛ ቡድን አሸናፊ የሆነው ከእነሱ በተሻለ መልኩም ጥሩ ስለተንቀሳቀሰ ነው፡፡

ሊግ፡- ወላይታ ድቻን በምን መልኩ አገኛችሁት?

ይገዙ፡- ወላይታ ድቻ ጠንካራ ቡድን እንደሆነ ብናውቅም ከእኛ ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ ግን የእኛ ጥሩነት ጎልቶ በመታየቱ እነሱን ከእንቅስቃሴ ውጪ ሊያደርጋቸው ችሏል፡፡

ሊግ፡- በወላይታ ድቻ ላይ የድል ግብን ማስቆጠር ችለህ ነበር?

ይገዙ፡- አዎን፤ ቡድናችን ከእዛ ግጥሚያ ሶስት ነጥብን አጥብቆ ይፈልግ ነበርና በጨዋታው ግብ ሳስቆጥር በጣም ነበር የተደሰትኩት፡፡

ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ያስመዘገባችሁትን ውጤት በምን መልኩ ትገልፀዋለህ?

ይገዙ፡- የእግር ኳስ ጨዋታ ላይ አንድ አንዴ የውጤት ማጣት የሚያጋጥም ቢሆንም የእዚህ ዓመት የውድድር ተሳትፎአችን ላይ ግን እኛ እያስመዘገብን የሚገኘው ውጤት የሚገባን አይደለም፤  ውጤቱ ጨርሶም እኛን አይመጥነንም፡፡

ሊግ፡- ቤትኪንጉ ከእረፍት ሲመለስ ስኬታማ ትሆናላችሁ?

ይገዙ፡- ለእዛማ አትጠራጠር፤ አሁን ወደ አሸናፊነት መንፈሱ መጥተናል፤ ተነሳሽነታችንም ጨምሯል፤ ስለዚህም ሊጉ ዳግም ሲጀመር ሲዳማ ቡና በአሸናፊነቱ በመቀጠል ወደ ውጤታማነቱ ያመራል፡፡

ሊግ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሲጀመር ምን ውጤትን ማምጣት ነበር ያሰባችሁት፤ አሁንስ…?

ይገዙ፡- ሊጉ ሲጀመርም ሆነ አሁን እኛ ልናመጣ የምናስበው ውጤት ከ1-3 ባለው ደረጃ ላይ ሆነን ማጠናቀቅ ነው፤ በእርግጥ የሊጉ ጅማሬ ላይ ክለባችን ፈፅሞ ያልጠበቀውን ጥሩ ያልሆነ ውጤት አስመዝግቧል፤ አሁን ደግሞ ወደ አሸናፊነቱ ስለተመለሰና በክለቦች መካከልም ያለው የነጥብ ልዩነትም ብዙም ያልተራራቀ ስለሆነም ጊዜው አልረፈደብንምና እስከ መጨረሻው ቀን ጨዋታ ድረስ ያቀድነውን ውጤት እናስመዘግባለን፡፡

ሊግ፡- ሲዳማ ቡናን በሚጠብቀው መልኩ ውጤት እንዳያመጣ አድርጎታል የምትለው ነገር ምንድን ነው?

ይገዙ፡- የውድድሩ ተሳትፎአችን ላይ እኛን ጎድቶናል ብዬ የማስበው የልምምድ ሜዳ ላይ ያለንን ጥሩነት በዋናው ግጥሚያ ላይ ልንተገብረው ያለመቻላችን ነው፤ ከዛም በተጨማሪ በሶስት ግጥሚያዎች ላይ ቀድመን ጎሎችን እያስቆጠርን በማይሆኑ ጥቃቅን ስህተቶች ጎሎችን በማስተናገድ ነጥብ የጣልንባቸው አጋጣሚዎች ስላሉና የአሸናፊነት ስነ-ልቦናው ላይም ድክመት ስለነበረብን እነዚህ ነገሮች ሊጎዱን ችለዋል፡፡

ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ 5 ግቦችን አስቆጥረህ ኮከብ ግብ አግቢነቱን ከቅ/ጊዮርጊሱ ኢስማሄል አጎሮ ጋር እየመራ ይገኛል፤ ይሄ ግብ አግቢነትህ ይቀጥላል?

ይገዙ፡- አዎን፤ በቀጣይ ግጥሚያዎችም ተከታታይ ግቦችን ስለማስቆጠርና ቡድኔንም ውጤታማ ስለማድረግ ነው እያሰብኩኝ ያለሁት፡፡

ሊግ፡- ዋልያዎቹ ለአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ወደ ካሜሮን አምርተዋል፤ ምነው የእዚህ ቡድን አባል በሆንኩ ብለህ አልተመኘህም?

ይገዙ፡- እንዴት አልመኝም፤ አይደለም እኔ ማንኛውም ተጨዋች ነው የሀገሩን ባንዲራ ወክሎ መጫወትን የሚፈልገው፤ ይሄ ደግሞ ጊዜውን ጠብቆ ስለሚመጣ ወደፊት የማሳከው ነው የሚሆነው፡፡

ሊግ፡- በመጨረሻ…?

ይገዙ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በካሜሮኑ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎው ጥሩ ውጤት እንደሚያመጣ ቡድኑ ካለው የአብሮነት ቆይታና በስኳዱም ከያዘው የተጨዋቾች ስብስብ አኳያ የተረዳሁት ነገር አለ፤ የእነሱ ወደስፍራው መጓዝም እዚህ ላለነው ተጨዋቾችም ከፍተኛ መነቃቃትና ተነሳሽነትን ስለሚጨምርልንም ጥሩ ውጤት እንዲገጥማቸውም ምኞቴ ነው፤ ከዛ ውጪም ሌላ ማለት የምፈልገው ነገር በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ቡድናችን ጥሩ አሰልጣኝና ተጨዋቾች ስላሉት ቀጣዮቹ የሊጉ ጨዋታዎች ሲጀመሩ የቡድናችንን ደጋፊዎች በውጤት እንደምናስደስታቸውም ነው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P