ጅማ አባጅፋር /ኢትዮጵያ/ vs ቴሌኮም /ጅቡቲ/
የጨዋታ ቀን፡- ማክሰኞ ህዳር 25/2011
የጨዋታ ሰዓት፡- 10፡00
የጅማ አባጅፋር እግር ኳስ ክለብ ባለፈው ሳምንት ወደ ጅቡቲ በመጓዝ ቴሌኮምን 3ለ1 በሆነ ውጤት ያሸነፈ ሲሆን
የድል ግቦቹንም ሁለቱን//////// አንዷን ደግሞ አስቻለው ግርማ አስቆጥሯል፤ የሁለቱ ቡድኖች የመልስ ጨዋታም
ማክሰኞ ይከናወናል፤ የአጠቃላይ ጨዋታው አሸናፊ ቡድንም በቀጣዩ ግጥሚያ የግብፁን አልአህሊ ክለብ ይፋለማል፡፡
የጅማ አባጅፋር ክለብ ከቴሌኮም ጋር ስላደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ እና የመልሱን ፍልሚያ አስመልክቶ እንደዚሁም
ሌሎችን ጥያቄዎችን ከቡድኑ ተጨዋቾች መካከል አንዱ ለሆነው ተከላካዩ አወት ገ/ሚካኤል አቅርበንለት ምላሹን
እንደሚከተለው ሰጥቶናል፤ ተከታተሉት፡፡
ሊግ፡- በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ቶታል ካፕ የመጀመሪያው ዙር የማጣሪያ ጨዋታ የጅቡቲውን ቴሌኮም 3ለ1
አሸንፋችኋል፤ ግጥሚያው ምን መልክ ነበረው? በማሸነፋችሁስ ምን ተሰማህ?
አወት፡- የጅቡቲው ቴሌኮም እና የእኛው ክለብ ጅማ አባጅፋር ማክሰኞ ዕለት ያደረጉት ጨዋታ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት
ነው፤ ግጥሚያው በከፍተኛ ሙቀት እና እግርህን በሚያቃጥልም የጅቡቲው ሜዳ ላይ ያከናወነው ነው፤ ሙቀቱ በተለይ
ለእኛ ቡድን ከሜዳችን ውጪ ሄደን እንደመጫወታችን በጣም አስቸጋሪ ሆኖብንም ነበር፤ ያም ሆኖ ግን በጨዋታው
እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ ታግለን በመጫወት በመጀመሪያዎቹ ሰባት ደቂቃዎች ባገባናቸው ሁለት ግቦችና በኋላም
ላይ አንድ ባስቆጠርነው ተጨማሪ ግብ ግጥሚያውን ልናሸንፍ ክለባችን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎ ባደረገበት
የኢንተርናሽናል ውድድሩ ይህንን ጨዋታ በድል በመወጣቱ በጣም እንድደሰትም አድርጎኛል፡፡
ሊግ፡- የጅቡቲው ቴልኮምን ስትፋለሙ አቋማቸውን በምን መልኩ አየከው..? ከሁለታችሁስ በእንቅስቃሴ ማን
የተሻለ ነበር?
አወት፡- ጅማ አባጅፋርና ቴሌኮም ያደረጉት ጨዋታ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት እና ምንም እንኳን ግጥሚያው በእኛ
አሸናፊነት የተጠናቀቀ ቢሆንም ተጋጣሚያችን ቀላል ግምት የሚሰጣቸው አልነበሩም፤ ቴሌኮሞች የመጀመሪያዎቹ
20 ደቂቃዎች ውስጥ እና ጨዋታው ሊጠናቀቅም ሲቃረብ አስቀድመን ግቦችን አስቆጥረንባቸው ስለነበር እነሱም ጎል
ለማግባት ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግና ፈጣን በሆኑት ተጨዋቾቻቸው አማካኝነትም በመጠቀም አስቸግረውን ነበር
ያም ሆኖ ግን በአጠቃላይ የጨዋታው እንቅስቃሴ ያን ዕለት እኛ የተሻልን ስለነበርን ጨዋታውን ልናሸንፍ ችለናል፡፡
የጅቡቲውን ቴሌኮም አቋም በሜዳ ላይ እንደተመለከትናቸው ከጨዋታው በፊት ደካማ ናቸው ብለን ልናስብ ብንችልም
እንደዚያ ግን አልነበሩም ከጠበቅናቸው በላይ ሆኖ ነው ያገኘናቸውና ለመልሱም ጨዋታ ተጠንቅቀን እንድንጫወት ነው
ከፍልሚያው መረዳት የቻልነው፡፡
ሊግ፡- የጅማ አባጅፋርን እና የቴሌኮምን የመልስ ጨዋታ እንዴት እንጠብቀው?
አወት፡- የጅቡቲው ቴሌኮም እና ጅማ አባጅፋር ማክሰኞ ዕለት የሚያደርጉት የመልስ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር የሚደረግበት
ነው፤ የመጀመሪያው ጨዋታ ምንም እንኳን በእኛ ክለብ 3ለ1 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ቢሆንም ግጥሚያው ገና
አላለቀም፤ ለእዛም ሲባል ቡድናችን ለጨዋታው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶት የመልሱን ጨዋታም ለማሸነፍና ወደ ቀጣዩ
ዙር ለማልፍም ዝግጁ ሆኗል፤ አሁን ላይ ካለን ጥሩ ብቃት ስንነሳም እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው የግብፁን ጠንካራ ክለብ
አልአህሊን በቀጣይ የማጣሪያ ጨዋታ ላይ የምንፋለመው እኛ ጅማ አባጅፋሮች ነን፡፡
ሊግ፡- ከጅማ አባጅፋርና ከቴሌኮም የአጠቃላይ ውጤት አሸናፊው የግብፅን አልአህሊ ይፋለማል፤ ኃላፊው እናንተ
ከሆናችሁ ስለ ሁለተኛው ዙር የማጣሪያ ጨዋታ ከወዲሁ ምን አስባችኋል? ምንስ ውጤት የምታመጡ ይመስልሃል…
አወት፡- የግብፁ እና የአፍሪካው ጠንካራ ቡድን አልአህሊ የቀጣይ ዙር ተጋጣሚያችን እንደሆነ ብናውቅም የአሁን ሰዓት
ላይ ከዚያ ጨዋታ በፊት እኛ የቅድሚያ ትኩረትን የሰጠነው ለማክሰኞው የመልስ ጨዋታ ነው፤ ያንን ድል ካደረግን
በኋላ ስለ አልአህሊው ጨዋታ እናስባለን፤ ከእነሱ ጋር ስለሚኖረን ጨዋታም አልአህሊ በጣም ጠንካራና የአፍሪካም
ትልቁ ክለብ ነው፤ ለዋንጫ ሲጫወት የተመለከትንበት አጋጣሚው ስላለ ከእነዚያ ግጥሚያዎች በመነሳትና ባለንም
ጥሩ የተጨዋቾች ስብስብ በመጠቀም ጨዋታውን ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ አድርገን አሸንፈን ለመውጣት ከፍተኛ
ጥረትን እናደርጋለን፡፡
ሊግ፡- በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የሁለተኛው ዙር ቀጣይ ጨዋታችሁን ከአልአህሊ ስታደርጉ የመጀመሪያ ጨዋታችሁ
ከሜዳችሁ ውጪ የሚከናወን ነው፤ ምን አይነት እንቅስቃሴን ትከተላላችሁ
አወት፡- የግብፁ አልአህሊ ጋር በሚኖረን የሜዳችን ውጪ ጨዋታ ክለቡ ጠንካራና አጥቅቶም የሚጫወት ክለብ ስለሆነ
በእነሱ ሜዳ ላይ የምናደርገው ጨዋታ ያለምንም ፍራቻ ኳስን ይዘንና ጥንቃቄ የተሞላበትን እንቅስቃሴ የምናደርግበት
እንጂ የመከላከልን አጨዋወት ፈፅሞ የምንምርጥበት አይደለምና ለውጤታማነት ሊረዳን የሚችል ጥሩ ጨዋታን
እንደምናሳይበት ነው የማምነው፡፡
ሊግ፡- በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ አጠቃላይ ተሳትፎአችሁ ላይ ምን ውጤትን የምታስመዘግቡ ይመስልሃል?
አወት፡- የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የዘንድሮው የውድድር ዘመን ተሳትፎአችን ምንም እንኳን የመጀመሪያችን ቢሆንም
ውድድሩ ውስጥ እስከገባን ድረስ በዚህ ተሳትፎአችን ልናመጣ ያሰብነው ውጤት ጥሩ የሚባል እና በአገራችንም ከዚህ
ቀደም ከተመዘገቡት ሁሉ የተሻለ የሚባለውን አመርቂ ውጤት ለማምጣት ነው፤ ስለሆነም የውድድሩ ጅማሬ ላይ
የምናገኛቸውን ቡድኖች ሁሉ አሁን ከፊታችን በቀጣዩ ዙር የሚገጥመንን አልአህሊን ጭምር አክብረነው ለማሸነፍ እና
አዲስ ሪከርድም ለማስመዝገብም ጭምር ነው የምንጫወተው፤ በእንዲህ ያለ ጠንካራ የውድድር ተሳትፎም ወላይታ
ድቻ አምና ዛማሌክን በማሸነፍም ከውድድሩ እንዲወጣ ያደረገበት ክስተትም አለና እኛም ያንን ለመድገምና
እልማችንንም ሩቅ ለማድረግም ዝግጁ ነን፡፡
ሊግ፡- እንደ ተጨዋችነትህ አዲሱ ክለብህን ጅማ አባጅፋር የቱን ያህል ትጠቀመዋለህ? የእስካሁኑ ቆይታክስ ምን
ይመስላል?
አወት፡- የጅማ አባጅፋር ክለብ ቆይታዬ ምንም እንኳን ገና አጭር ቢሆንም የቡድኑ አጨዋወት ኳስ በመያዝ ላይ
ያተኮረ እና እኔም የምመርጠው እንቅስቃሴ ስለሆነ ቡድኑ እስካሁን በጣም ተመችቶኛል፤ መልካም ጊዜንም በማሳለፍ
ላይ እገኛለሁ፤ በሚኖረኝ ቀጣይ ቆይታም ክለቡን በደንብ አድርጌ ከመጥቀም ባሻገር ስኬታማ ጊዜያቶችንም ለማሳለፍ
ዝግጁ ነኝ፡፡
ሊግ፡- ጅማ አባጅፋር በሊጉ የውድድር ተሳትፎው በእዚህ አመት ምን ውጤት የሚያመጣ ይመስልሃል?
አወት፡- ጅማ አባጅፋር የሊጉን ዋንጫ አምና ያነሳ እና በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግም ደረጃ የሚወዳደር ክለብ ስለሆነ
አሁንም በውጤት ደረጃ ሊጉ ላይ የሚያሳካው በድል ጎዳና ወደፊት የሚያራምደውን እንጂ ወደኋላ የሚልበትን አይደለም፤
ስለዚህም የሊጉን ዋንጫ ዳግም ለማንሳት ነው ውድድሩን የጀመርነው፡፡
ሊግ፡- ከጅማ አባጅፋር ጋር በክለብ ደረጃ ያደረግከው የኢንተርናሽናል ግጥሚያ ለአንተ የመጀመሪያክ ነው፤ ምን ስሜትን
ፈጠረብህ?
አወት፡- ከፍተኛ ደስታ ነዋ! በኤሌክትሪክ ክለብ ታሪክ ውስጥ ኳስን ስጫወት በእንዲህ ያሉ የኢንተርናሽናል
ግጥሚያዎች ላይ ተሳትፌ ስለማላውቅ ሁሌም ይከፋኝ ነበር፤ አሁን ላይ ግን ይህንን በኢንተርናሽናል ጨዋታ የመሳተፍ
እድልን ከአዲሱ ክለቤ ጋር ሳገኝ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ በተለይ በጨዋታው ሀገርህን፣ ህዝብክንና ባንዲራህን ወክለህ
የምትጫወትበት ስለሆነም ያለው የደስታ ስሜት ከማሸነፋችን ጋር ተዳምሮ እጥፍ ድርብ ነው ሊሆንልኝ የቻለው፡፡
ሊግ፡- ጅማ አባጅፋርን እስካሁን እንደተመለከትከው ያለው ጥንካሬ እና ድክመቱ ምኑ ጋር ነው?
አወት፡- የጅማ አባጅፋር ጠንካራው ጎን ኳስን ተቆጣጥረው በሚጫወቱ ተጨዋቾች መገንባቱና ከማንም የተሻለም
ከፍተኛ የሊጉ ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾች አሰባስቦ የያዘና የአሸናፊነትን መንፈስ የተላበሰ ቡድን መሆኑ ጥንካሬው
ነው፤ ቡድኑ ላይ እንደ ክፍተት የምንመለከተው እና ልናሻሽለው የምንፈልገው ነገር ደግሞ ከጌም በመራቃችን የተነሳ
የፊትነስ ችግር ይታይብን ነበርና ያ በቀጣይ ጊዜ የሚስተካከል ነው የሚሆነው፡፡
Like this:
Like Loading...
Related