“ከፋሲል ከነማ ይልቅ የቅ/ጊዮርጊስ አመጣጥና አካሄድ ያስፈራኛል”
“ምርጥ ቡድን አለን፤ ከቡናም ጋር ዘንድሮ ሻምፒዮና መሆንንም እፈልጋለሁ”
ታፈሰ ሰለሞን /ኢትዮጵያ ቡና/
ኢትዮጵያ ቡናን ከሐዋሳ ከተማ ክለብ በመምጣት ባለፈው ዓመት ላይ ተቀላቅሏል፤ ወደ ቡድኑ ካመራም በኋላ ጥሩ የውድድር ጊዜያቶችን አሳልፏል፤ የኢትዮጵያ ቡናው ስኬታማ አማካይ ታፈሰ ሰለሞን በቡድኑ ቆይታ ዙሪያ ከሊግ ስፖርት ጋር ቆይታን ያደረገ ሲሆን ተጨዋቹም ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽን ሰጥቷል፤ ታፈሰ የቡድናቸውን አጨዋወት አስመልክቶ ከቀረበለት ውስጥ “የቡና አጨዋወት አሁንም እንደ ዓምናው ሁሉ በጣም የተመቸኝ እና የወደድኩት ነው፤ በእዚህ አጨዋወት እና ጉዞ ውስጥም እኔም ሆንኩ ቡድኔ ከፍተኛ ደረጃ ላይም እንደርሳለን በማለትም ሀሳቡን ለጋዜጣው ሰጥቷል፡፡
ኢትዮጵያ ቡናን በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው በአማካይ ስፍራ ላይ በመሰለፍ እና ክለቡንም በስኬት በማገልገል ጥሩ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው እና ግብም ማስቆጠርም የጀመረው ታፈሰ ሰለሞን ሊግ ስፖርት በበርካታ ጥያቄዎች ዙሪያ ትናንት ጠዋት አናግራው የሰጣት ሌላ ምላሽም የሚከተለውን ይመስላል፤ ተከታተሉት፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና አዳማ ከተማን 4-1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል፤ ድሉ የሚገባችሁ እና የጠበቃችሁት ነበር?
ታፈሰ፡- አዎን፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ቡና ሁሌም የሚጫወተው የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ነው፤ ያን ድል ለማሳካት ደግሞ እያንዳንዱን ጨዋታዎች ማሸነፍ እንዳለብን ስለምናውቅ እና እነዛም ውጤቶች ከተደመሩ በኋላም ለውጤቱ ስለሚያበቃን በዛ መልኩ በመጫወት ነው ግጥሚያዎቻችንን በስኬት እየተወጣን የሚገኘው፤ ከዛም አንፃር አዳማን የረታንበት ጨዋታ በጣም አስደስቶናል፡፡
ሊግ፡- አዳማ ከተማን ድል ያደረጋችሁበት ጨዋታ ምን መልክ ነበረው?
ታፈሰ፡- በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታው እነሱ ከመረጡት የመከላከል እና የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ አንፃር በአብዛኛው በራቸውን ዘግተው ይጫወቱ ስለነበር ለእኛ በጣም ከበድ ይል ነበር፤ ራሳችንም ነን ጎል አስቆጥረን ጨዋታውን ለማሸነፍ ከነበረን ጉጉት አኳያም ግጥሚያውን እንደምናሸንፍ እርግጠኛ ስለነበርን ግብ ለማስቆጠር እንቻኮል ስለነበር ግጥሚያውን ያከበድነው፤ ከዛም እነሱ ቀድመው ግብ አስቆጠሩብንና መሩን፤ ይህ ከሆነ በኋላ ግን በእረፍት ሰዓት ላይ አሰልጣኛችን ተረጋግተን መጫወት እንዳለብን ስለነገረንና እኛም ችግሮቻችንን ስላወቅን ይህን ግጥሚያ በሰፊ ግብ ልናሸንፍ ችለናል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና ወደ ስኬታማ ማማው እየተጓዘ ይገኛል፤ ለእዚህ ውጤት ምን አበቃው?
ታፈሰ፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአችን ቡድናችን እየተጓዘ ላለበት የስኬታማነት መንገድ እያበቃን ያለው የአሸናፊነት መንፈሳችን በጣም ከፍ ያለ መሆኑና አንድነታችንም የተለየ መሆኑ ነው፤ ከዛ ውጪም የኮቺንግ ስታፋችንና የእኛ ተጨዋቾችም ህብረት የላቀ ስለሆነም ይህ ነው ሊረዳን የቻለው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡና አጨዋወት አሁንም እንደተመቸህ ነው?
ታፈሰ፡- አዎን፤ ባለፈው ዓመት በዚህ ዙሪያ ነግሬህ ነበር፤ የቡና አጨዋወት የሚመች እና ከእኔ አጨዋወት ጋር አብሮ የሚሄድም ስለሆነ ብዬም ነው ወደ ቡድኑ የመጣሁትና የዘንድሮም የክለቡ አጨዋወት ካለፈው ዓመት በበለጠ ተስማምቶኝና ተመችቶኝም ነው እየተጫወትኩኝ ያለሁት፡፡
ሊግ፡- ለልደታው ኒያላ፣ ለኢትዮ-ኤሌክትሪክ እና ለሐዋሳ ከተማ ተጫውተህ አሳልፈሃል፤ እዛ የነበረህን የኳስ ብቃት እና አጨዋወትህን ከአሁኑ የኢትዮጵያ ቡና ቆይታህ ጋር ስታነፃፅረው በምን መልኩ አገኘኸው?
ታፈሰ፡- ወደ ኢትዮጵያ ቡና ከመጣሁ በኋላ ያለኝ ብቃትና አጨዋወት ከላይ ከተጠቀሱት ክለቦች ጋር ተመሳሳይነት የሚታይበት ቢሆንም በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ በሚመራው የሐዋሳ ከተማ ክለብ ውስጥ ግን ስጫወት የነበረኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ ደግሞ ከቡና ጋር ካለው ሳነፃፅረው የቡናው ትንሽ ለየት ቢልም በጣም ተቀራራቢነት ነበረው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡና አጨዋወትህን ከሐዋሳ ከተማ ከነበረው ምንድን ነው የሚለየው?
ታፈሰ፡- ለቡና ስትጫወት ለየት የሚለው ኳስን ከበረኛ በመጀመር ነው የምትጫወተው፤ በረኛውም ትርፍ ሰው እና አንዱ የቡድኑ ተጨዋችም እንደሆነ አድርገህ ስለምትጫወት ያለ ድካምም ነው የምትንቀሳቀሰው እና ይሄን አጨዋወት በጣም ወድጄዋለው፡፡
ሊግ፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ያስቆጨህ ጨዋታ የቱ ነው?
ታፈሰ፡- ጎሎች ይገቡብናል ብለን ባለሰብንበት መንገድ ከሐዋሳ ከተማ ጋር እና ከወላይታ ድቻ ጋር ስንጫወት እነሱ ከነበሩበት የወራጅ ቀጠና አንፃር እነዛን ጨዋታዎች እናሸንፋለን ብለን አስበን የተሸነፍንባቸው ጨዋታዎች አሁን ያለፉ ቢሆኑም እኔን ያስቆጩኛል፤ አምናም በዚህ ደረጃ ላይ ለነበሩት ቡድኖች ዝቅ ያለ ግምትን የምንሰጥበት ሁኔታም ስለነበር ነው ተመሳሳይ የውጤት ማጣትም ሊገጥመን የቻለውና ይሄን ችግራችንን ልንቀርፈው ይገባናል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ አጠቃላይ ተሳትፎው በዋናነት ማሻሻል ያለበት ነገር ምንድን ነው?
ታፈሰ፡- በርካታ ጎሎችን ብናገባም፤ ጎል ይቆጠርብናል፤ ግቦች እንዳይገቡብን ችግሮቻችንን ልናስተካክል ይገባል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና ላይ ጎሎች የሚቆጠርበት መንገድ በግብ ጠባቂው እና በተከላካይ ክፍሉ ላይ መናበብ ካለመኖሩ ጋር በተያያዘ ነው፤ በዚህ ዙሪያ ምን አልክ?
ታፈሰ፡- ይሄ ግብ የሚቆጠርብን መንገድ በራሳችን የሆነ አጨዋወት እና ስታይል ውስጥ እንደ ሌሎች ቡድኖች የግብ ክልላችንን ዘግተን ከመጫወት ይልቅ ቦታውን ከፍተንና አስፍተን በምንንቀሳቀስበት ጊዜ አሰልጣኛችን ካሳዬ አራጌ በተደጋጋሚ ጊዜም በሰጠው ቃለ-ምልልስ ኳስን መቀባበሉ ላይ አልፎ አልፎ የፐርፌክሽን ችግሮች ስላሉና ኳስ ለመቀበልም ቶሎ ዝግጁ ያለመሆንም ሁኔታ ስላለ ያ ነው ክፍተቱ ይሄም በፍጥነት የሚሻሻልም ነው፡፡
ሊግ፡- ወደ ሻምፒዮናነቱ ለምታደርጉት ጉዞ የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ አካሄድና አመጣጥ እናንተን በ5 ነጥብ ከመበልጡ አኳያ አያስፈራችሁም?
ታፈሰ፡- በፍፁም፤ ፋሲልን እንደተመለከትኩት እኛን በጭራሽ አያሰጋንም፤ ከእነሱ ይልቅ እንደውም የቅ/ጊዮርጊስ አመጣጥና አካሄድም ነው እኔን እያስፈራኝ ያለውና ልንጠነቀቃቸው ይገባል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን በመጨረሻው የውድድር ዘመን የት ላይ እናገኘዋለን?
ታፈሰ፡- አሁን መጀመሪያ ላይ እየሰራን ያለነው የጨዋታ እንቅስቃሴያችንን ሳንለቅ በምንጓዝበት እና በምንጫወትበት መንገድ መቀጠል እንዳለብን ነው፤ በዚህ በኩል ተስፋ ሰጪ ነገሮችን እያገኘን ስለሆነም የውድድር ዓመቱ ሲጠናቀቅ ቡናን በውጤት ማማው ላይ የምናገኘው ይሆናል፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ቡና ውስጥ የተሰባሰቡትን ተጨዋቾች እና አሰልጣኙን ካሳዬ አራጌን በምን መልኩ እያየኸቸው ነው?
ታፈሰ፡- የእኛ ተጨዋቾች ከአምናው አንፃር በተለየ መልኩ ነው ዘንድሮ ለውድድር የቀረቡት፤ በብዙ ነገሮችም ተሻሽለዋል፤ አዲስ የመጡት ተጨዋቾችም ጥሩ ናቸው፤ ከእነሱ እና ከቡድኑ ኮቺንግ ስታፍ ጋር በጣም በመቀራረብ ለቡድኑ ውጤታማነት ጠንካራ ስራን እየሰራን ይገኛል፡፡ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን በተመለከተ እሱ እንደ አባት ጭምር ነው፤ ባለፈው ዓመት ወደ ቡድኑ ስመጣ በስም ብቻ ነበር ስለ እሱ የማውቀው፤ በስራ ላይ ሳገኘው ግን ከሚሰጠው ጥሩ ስልጠናም ሆነ አንተን ከሚረዳበት ነገር ተነስተህ ስታየው ለእኔ አንደኛ አሰልጣኝ ነው፤ በተለይ በቡና ቆይታዬ አምናም ሆነ ዘንድሮ እየሰጠን ያለው ልምምድ ተደጋጋሚ ሳይሆን የተለያዩ አይነት ታክቲኮችን ስለሆነ ከዛ ውጪ ደግሞ ከቡና ደጋፊዎች ጋር ግጭት ውስጥ በገባሁበት ጊዜና በሌላም ከእኔ ህይወት ጋር በተያያዙ ጉዳዬች ውስጥ ከእሱ ልምድ ተነስቶ በምን መልኩ መጓዝ እንዳለብኝም በግል ጭምር እየጠራ ስለሚመክረኝም ካሳዬን በቀላል ቃላቶች የምገልፀው አሰልጣኝ አይደለም፤ በጣምም ነው የማከብረው፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ከተጨዋቾቹ ውጪ ከኮቺንግ ስታፉም ጋር በጣም ነው የምትቀራረበው፤ የምትግባባውም የሚል ነገርን ሰማው?
ታፈሰ፡- የእውነት ነው፤ ከሁሉም ጋርም ነው የምግባባው፤ በተለይ ደግሞ ከገብረ ኪዳን ነጋሽ /ጋምብሬ/ ጋር እና ከሰለሞን /በእሳቱ/ ጋር በምሆንበት ሰዓት ብዙ ነገሮችን እያነሳን እንስቃለን፤ በኳስ ስላሳለፉት ነገሮችም ያወሩኛል፤ ሁለቱ ደግሞ ሲቀላለዱ ለእኔ የተለየ የደስታ ስሜትንም ስለሚፈጥርልኝ ያ ደስተኛ እያደረገኝ ነው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ አሁን የምታሳየው ጥሩ እና አበረታች እንቅስቃሴህ ከቁጭት ተነስተህ ይመስላል?
ታፈሰ፡- ልክ ነህ፤ በኳሱ ጥሩ አቅም እያለኝ እና የተሻለም ደረጃ ላይ መድረስ እየቻልኩ በምፈልገው ቦታ ላይ አልተገኘሁምና ያ ነው የቁጭቴ ሚስጥር፤ ኢትዮጵያ ቡናን ከተቀላቀልኩበት ጊዜ ጀምሮ ግን ቡድኑ ኳስን መሰረት ባደረገ እንቅስቃሴ ውስጥ ስለሚሳተፍ ያ ለእኔ በጣሙን ተስማሚዬ ሆኖ መልካም የሆነ ጊዜን እያሰለፍኩ ነው የምገኘው፤ በቡና ቆይታዬ ከክለቡ ጋር የሊጉን ዋንጫ ማንሳት እፈልጋለው፤ ይሄ ድል ዘንድሮ ቢሆን ደግሞ የበለጠ ምርጫዬም ነው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን ከመጫወትህ ህይወት ጀርባ የባለቤትህ ሚና የቱን ያህል ነው?
ታፈሰ፡- ባለቤቴ ናርዶስ ለእኔ ሁሉ ነገሬ ናት፤ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃም እሷ ዋናው ምክንያትም ናት፤ ጨዋታዬን በዲ.ኤስ. ቲቪም ትመለከታለች፤ ተከታትላ ማረም ያለብኝንም ነገሮች ትነግረኛለች፤ በተለይ ደግሞ ጎል ማግባቱ ላይ ለምን አታገባም በሚል በስልክ የምንደዋወልበት ጊዜም በርካታ ነበርና ይኸው አሁን ጎሎችን በማስቆጠሩ ምክሯን ተግባራዊ እያደረግኩኝ ነው፤ በቀጣይነትም ሌላ ጎል እንዳስቆጥርም ያለፈው ጎል እኔን የሚያነሳሳኝ ነው፡፡
ሊግ፡- ስለ ኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር ችሎታ ብዙ እየተባለ ነው፤ አንተም ስለ እሱ እያወራህ ያለኸው ነገር አለና ያ ምንድን ነው?
ታፈሰ፡- አቡበከር ናስር በኳሱ በጣም ትልቅ አቅም ያለው ልጅ ነው፤ የሀገራችንን ኳስ ለማንቋሸሽ አይሆንብኝ እንጂ አሁንም ደግሜ መናገር እፈልጋለው አርሰናል ሄዶ መጫወት ይችላል፤ ከሊጉ አቅም በላይ የሆነ ተጨዋች ነው፤ አንድአንዴ የእሱን ችሎታና እንቅስቃሴውን ሳየው በአግራሞት ከሌላ ፕላኔት የመጣ ተጨዋች እንጂ ይሄ ሰው ነው እንዴም እላለው፤ አቡበከር በአሁን ሰዓት ምርጡን ብቃት እያሳየ ይገኛል፤ ሶስት ሀትሪክም ሰርቷል፤ በቅርቡ ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ በተደረገልን ጊዜም ለብሔራዊ ቡድናችን ተጨዋቾች ለሆኑት አስቻለው ታመነ እና ጋዲሳ መብራቴም ይሄ ልጅ ቀጣይ በምናደርገው ጨዋታ አሁንም ሀትሪክ ይሰራል ብዬ ነግሬያቸው ያንን በተግባር አሳይቷል፤ ከዚህ በኋላም ተደጋጋሚ ሀትሪኮችን ከመስራት ባሻገር በጌታነህ ከበደ የተያዘውን የ25 ግብ ሪከርድ እንደሚሰብርም የምተማመንበት ተጨዋችም ነው፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና አንድአንዴ ማቀበል የምትችለውን ኳስ ወደ ግብነት የምትሞክርበትን ሁኔታም አይተናል፤ በዚህ ዙሪያ ምን አልክ?
ታፈሰ፡- ልክ ነህ፤ እንደዛ የማደርገው ጎል ለማግባት ከነበረኝ ከፍተኛ ጉጉት እና ኳሷን እንዳገኘኋትም እርግጠኛ ጎል ትሆናለች ብዬ ስላሰብኩ እንጂ ከሌላ አይደለም፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
ታፈሰ፡- ኢትዮጵያ ቡና ትልቅ እና ከፍተኛ ሀላፊነትንም ተሸክመህ የምትጫወትበት ቡድን ነው፤ ወደዚህ ቡድን ሳመራም በህይወቴ ላይ ብዙ ለውጦችን እየተመለከትኩበት ነው፤ ክለቡን አስቀድሞም የምወደው ነው፤ ይሄ ክለብ ብዙ የሊግ ዋንጫም ያስፈልገዋል፤ የአሁኑ ቡድን ደግሞ ይሄን የማሳካት አቅሙ አለውና በዚህ ደረጃ ጠንክረን ልንሰራ ይገባል፤ እኔም ለዚህ ቡድን የግብ ኳሶችን ከማቀበል እና ጥሩ እንቅስቃሴን ከማድረግ ባሻገር ቡድኑ ብዙ እንዲጓዝም እፈልጋለውና ፈጣሪ ይርዳን፡፡