በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/
ጊዜው በ1990ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታቶች አካባቢ ነው። ያኔ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በስሩ ከሚያካሂዳቸው ውድድሮች አንዱ በሆነው የአንደኛ ዲቪዝዮን ውድድር ላይ ተጨዋቹ ለአብነት እና ለዩኒቲ ኮሌጅ እግር ኳስ ቡድኖች ለመጫወት ችሏል። ለአብነት ቡድን ከ1980ዎቹ የመጨረሻ ዓመታቶች ጀምሮ በተጫወተባቸው የአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥም ከ60 በላይ ግቦችንም ሊያስቆጥር ችሏል። ፈጣን ጉልበተኛ እና የተቃራኒ ቡድን ተከላካዮችም በቀላሉ ገርስሶ በማለፍም ግቦችን የሚያስቆጥርም ነበር። በተለይ ደግሞ ከአሸናፊ ገላን አቡ ጋር የነበራቸው ጥምረትም ምርጥ የሚባልም ነበር። በእዛን ጊዜ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታውም ይሄ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች የውድድር ዘመኑ ኮከብ ግብ አግቢ ተብሎ 500 ብር ሲሸለም በጊዜው ትልቅ የሚባለውን ይህን የብር ሽልማት ለራሱ ኪስ አላዋለሁም። በቀጥታ የተሸለመውን ብር ወደ ማዘጋጃ ቤት ይዞ በማምራት ለተቸገሩ ወገኖቼ ይሰጥልኝ በማለት የበጎ አድራጎት እርዳታን አድርጓል።
ደስታዓለም ምንአልባትም እኔ እስከማውቀው ድረስ በእግር ኳስ ተጨዋቾች ታሪክ የተሸለመውን ገንዘብ ያውም በእዛን ወቅት ለተቸገሩ ወገኖቼ ይሰጥልኝ ብሎ ስጦታ መስጠቱ የመጀመሪያውም ተጨዋች የሚያደርገው ይመስለኛልና በአስገራሚነቱ ይጠቀሳል። በጣሙን ሊመሰገንም ይገባል።
አሁን ደግሞ ወደ ተጨዋቹ ታሪክ እናመራ ደስታለም ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ አብነት አካባቢ ነው የአሁኑ ኪሎው እና ቁመቱ ባይታወቅም ያኔ ግን ኪሎው 65 ቁመቱ ደግሞ 1ሜትር ከ68 ነበር።
የእግር ኳስን በክለብ ደረጃ መጫወት የጀመረው በመድን የታዳጊ ቡድን ውስጥ ነው፤ በመቀጠል ደግሞ ለሜታ አቦ ቢራ ለአብነት እና ለዩኒቲ ኮሌጅ ቡድኖች ለመጫወት ችሏል።
ደስታዓለም ስለ ቀድሞ የእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኑ ያኔ አንድ አንድ ነገር ብሏልና ለቅምሻ ይሄን ብለናችኋል።
በመድን ታዳጊ ቡድን ውስጥ ስለነበረው ቆይታ
“ለመድን ታዳጊዎች ስጫወት ጥሩ ችሎታው እና ቆይታው ነበረኝ፤ ባለኝ የኳስ ብቃትም ለወጣት ቡድኑ እንድጫወት አድጌ በራሴም ላይ ከፍተኛ ለውጦችን አይቻለው። ያም ሆኖ ግን በወቅቱ ብሩህ እና ጥሩ ተስፋን በእግር ኳስ ጉዞዬ ላይ ለመመልከት ብችልም ከቡድኑ ሳልስማማ ቀረውና ለአራት ወራት ያህል ወደ ተጫወትኩበት የሜታ አቦ ቢራ ቡድን አመራሁኝ”።
ከመድን ሳይስማማ ቀርቶ ክለቡን ስለለቀቀበት ሁኔታ
“ከመድን ወጣት ቡድን ሳልስማማ ቀርቼ ቡድኑን ልለቅ የቻልኩት ከልምምድ መልስ እኔና አሁን በስዊዘርላንድ ሀገር የሚገኘው ቴዎድሮስ አለማየሁ በስታድየም ዶልፊን አካባቢ ስለታየን ብቻ ልጠጡ ነው በሚል እና እኔንም አሰልጣኙ እንደገፋፊም ስለቆጠረኝ /ነፍሱን ፈጣሪ ይማረው አሰልጣኙ አሁን ላይ ህይወቱ አልፏል/ በእዚሁ መንገድ ነው ከአሰልጣኙ ጋር መስማማት ሳልችል ቀርቼ የወጣሁት”።
የእግር ኳስ ጫማውን ሰቅሎ ወደ ግል ስራው ስላመራበት መንገድ
“ከመድን ወጣት ቡድን ሳልስማማ ቀርቼ እና ወደ ሜታ አቦ ቢራም ክለብ በማምራት ለአራት ወራት ያህል ከተጫወትኩ በኋላ ቡድኑ ሲፈርስ ኳስ መጫወቱን አቁሜ ወደ ግል ስራ ያመራሁት የእግር ኳስ ጨዋታ የሚያዋጣ መስሎ ስላልታየኝ እና በአጠቃላይ የእኛ ሀገር ተጨዋቾቻችንም ላይ የኑሮ ለውጥን ላይባቸው ስላልቻልኩ እኔም አባቴን ስራ እየሰራው ማገዝ አለብኝ በሚል ምክንያት በስራ ተወጥሬ ስለነበርኩኝ ነው”።
ለአብነት እና ለዩኒቲ ኮሌጅ ዳግም ወደ እግር ኳሱ ተመልሶ ስለመጫወቱ እና ስለነበረው ቆይታ
“ወደ እግር ኳሱ ዳግም ተመልሼ በሰፈሬ ደረጃ ተቋቁሞ ለነበረው የአብነት እና በኋላም ለዩኒቲ ኮሌጅ ለመጫወት የቻልኩት የግል ስራዬን በማይነካ እና በማይሻማ መልኩ ለስሜት ነበር። ሁለቱም ክለቦች ጋር ጥሩ ቆይታ ነበረኝ፤ ምርጥም ቡድን ነበረን። በእዛን ወቅት የኮከብ ግብ አግቢም ተብዬ የተሸለምኩበትም ጊዜ ስለነበር ያን ወቅት መቼም ቢሆን አልረሳውም”።
ወደ ትላልቅ ክለቦች ገብቶ ለመጫወት አለመሞከሩ
“በግል ስራ ነበር የምተዳደረው። ስለዚህም ወላጅ አባቴን እየሰራው ማገዝ አለብኝ ብዬ ስላሰብኩና ኳሱም አዋጭ መስሎ ስላልታየኝ ሌሎች ጋር ሄጄ ለመጫወት ሙከራን አላደረግኩም”።
የእግር ኳስን ከቤተሰቡ ውስጥ የሚጫወተው እሱ ብቻ እንደሆነ
“በጊዜው ኳስ ተጨዋቹ እኔ ብቻ አልነበርኩም። ታናሼ አፈወርቅም ለኪቤአድ ቢ ቡድን ይጫወት ነበር። በኋላ ላይ እሱም በስራ ምክንያት ኳሱን አቁሟል”
የሚያደንቀው ተጨዋች
“ማራዶናን፤ እሱን የሚደርስበት ማንም የለም”።
ማግባት የሚያስደስተው የግብ አይነት
“ተከላካይ እና በረኛን አልፎ ማስቆጠር”
የሚጠላው እና የሚወደው
“ወረኛ ሰውን ስጠላ ሀቀኛ እና ግልፅ ሰው ይመቸኛል”።
በመጨረሻ…
“የሀገራችን እግር ኳስ ትልቅ ደረጃ ላይ የሚደርሰው ሁሉም የታዳጊ ወጣቶች ላይ ተረባርቦ የሚሰራ ከሆነ ነው”።
ደስታዓለም ከተንበረከኩት ከግራ ወደቀኝ 6ኛው ነው።