Google search engine

“ካለፉት ሁለት ዓመታት የተሻለና ጠንካራ ቡድንን ይዘን ስለቀረብን ወራጅነትን አናስብም” በረከት ሳሙኤል /ድሬዳዋ ከነማ/

በመሸሻ ወልዴ

ሊግ፡- የድሬዳዋ ከነማ ወቅታዊ አቋም
ምን ይመስላል? የሊጉን ውድድርስ በምን
ውጤት ለማጠናቀቅ እቅድን ይዛችኋል?
በረከት፡- የድሬዳዋ ከነማ ወቅታዊ
አቋም ለእኔ ጥሩ የሚባል ነው፤ ቡድናችን
በአብዛኛው በወጣት ተጨዋቾች ተገንብቶም
መልካም በሚባል ሁኔታም እየተንቀሳቀሰ
ይገኛል፤ የዘንድሮ የሊጉን ውድድር
የምናጠናቅቀውም ሊጉ ገና ጅማሬ ላይ
ቢሆንም ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ባለው
ደረጃ ውስጥ ሆነን የዓመቱን መርሀ ግብር
እንፈፅማለን፡፡
ሊግ፡- ደደቢትን በሜዳችሁና
በደጋፊዎቻችሁ ፊት አሸንፋችኋል፤
ዛሬም ወልዋሎ አዲግራትን ትፋለማላችሁ
በእነዚህ ጨዋታዎች ዙሪያ ምን ትላለህ?
በረከት፡- የደደቢት ክለብ ጋር
ያደረግነው የሊጉ ጨዋታ ለእኛ
የመጀመሪያው የሜዳችን ላይ ፍልሚያ
ሲሆን ይህን ግጥሚያም ለማሸነፍ
በመቻላችን በጣም አስደስቶናል፤ የሜዳ
ላይ ጨዋታን ማሸነፍ መቻል ለብዙ
ነገሮች ይረዳካልና በቀጣይም የሚኖሩንን
ጨዋታዎች ለማሸነፍ ዝግጁ ነን፤
ከወልዋሎ አዲግራት ጋር ዛሬ በሚኖረን
የሊጉ ሶስተኛው ጨዋታችን ደግሞ
እስከመጨረሻ ሰዓት ድረስ ተፋልመን
ለማሸነፍ አልያም ደግሞ ነጥብ ተጋርተን
ለመመለስ ዝግጁ ሆነናል፡፡
ሊግ፡- ድሬዳዋ ከነማ ባለፉት
ዓመታቶች ጠንካራ ቡድንን ይዞ ባለማቅረቡ
በወራጅ ቀጠና ውስጥ ሲጫወት ቆይቷል፤
ይሄ አቋም ዘንድሮ ይሻሻል?
በረከት፡- አዎን! እርግጠኛ ሆኜ
የምነግርህ የቡድናችን አቋም ካለፉት
ጊዜያቶች አንፃር ስትመለከተው በጣም
ጥሩ ነው፤ካለፉት ሁለት ዓመታትም
የተሻለና ጠንካራ ቡድንን ይዘን ስለቀረብን
ወራጅነትን ፈፅሞም አናስብም፤ ዘንድሮ
የተሻለ ብቃት ያለውን አዲሱን ቡድንም
ወደፊት በሚኖሩን በርካታ ጨዋታዎች
ላይም የምናስመለክታችሁም ስለሆነ በዚህ
ዓመት ከእኛ ጥሩ ነገርን ጠብቁም ነው
የምለው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
ከመጀመሩ በፊት በትግራይ ሲቲ ካፕ ላይ
ተሳትፋችኋል፤ ለዋንጫም ቀርባችሁ ነበር፤
ያንን የአቋም መለኪያ ጨዋታ እንዴት
ተመለከትከው?
በረከት፡- በመቀሌው የውድድር
ተሳትፎአችን የእኛ ቡድን ጥሩ አቋምን
በመያዝ ነበር እስከፍፃሜው ጨዋታ
ደርሶ የነበረው፤ ያም ሆኖ ግን ከመቀሌ
70 እንደርታ ጋር በነበረን የመጨረሻው
ጨዋታ የውድድሩ አዘጋጆች ዋንጫው
እዚያው እንዲቀር ፈልገው የእኛ ቡድን ላይ
የዳኝነት ተፅዕኖ እንዲፈጠርበት በማድረግ
ሻምፒዮናነቱን አሳጥተውናል፡፡
ሊግ፡- ድሬዳዋ ከነማ በፕሪ ሲዝን
ከሰራው ልምምድ አኳያ በውድድር ዓመቱ
ምን አይነት የጨዋታ እንቅስቃሴን የሚከተል
ቡድንን ነው እያስመለከተን የሚጓዘው?
በረከት፡- ድሬዳዋ ከነማ በአሰልጣኝ
ዮሃንስ ሳህሌ በመመራት ከሰራው የፕሪ
ሲዝን ዝግጅቱና ልምምዱ አንፃር የውድድር
አመቱ ላይ ሊያስመለክተን ያሰበው ቡድን
በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ ሁሉንም
ያሟላ እንቅስቃሴ የሚያደርግን ጥሩ
ቡድን ነው፤ ይህንንም በቀጣዮቹ በርካታ
ግጥሚያዎች ላይም የምናየው ነው
የሚሆነው፡፡
ሊግ፡- ድሬዳዋ ከነማን በሊጉ ውጤት
ከሚያሰጡት ነገሮች ውስጥ አንዱ የምትለው
እና ያም ሊሻሻል ይገባዋል የምትለው ነገር
ካለ?
በረከት፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
የውድድር ተሳትፎአችን ላይ ድሬዳዋን ብዙ
ጊዜ ውጤት ከሚያሳጡት ነገሮች ውስጥ
ክለቡ እንደ ቡድን የራሱ የሆኑ ድክመቶችና
ክፍተቶች ቢኖሩበትም በሜዳችን ላይ
የምናደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ አንዳንዴ
ደጋፊዎቻችን በኳስ እንቅስቃሴው ወርደን
በምንገኝበት ሰአትና በእንቅስቃሴም
በምንበልጥበት ወቅት ድጋፋቸውን ለተቃራኒ
ቡድን ስለሚሰጡ ያ እኛን ተጠቃሚ
አያደርገንም፤ ጨዋታውን ከሜዳችን ውጪ
የምናደርግ ያህል ሆኖም ይሰማናል፤
የተቃራኒው ቡድን ደግሞ ግጥሚያውን
በሜዳው ላይ እንደሚያከናውን ስለሚቆጥረው
ብዙ ቡድኖች በእዚህ ተጠቃሚ የሆኑበት ነገር
አለ፤ ለምሳሌ ከቡና ጋር ስንጫወት ቡናም
የእኛን ደጋፊዎች ድጋፍ በእኩል መልክ
የሚያገኝበት ጊዜ በተደጋጋሚ ታይቷል፤
ተጠቅሟልም፡፡ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች
እኛን ይጎዱናልና ይሄ የድጋፍ አሰጣጥ
ሁኔታ ከማንኛውም ቡድን ጋር ስንጫወት
ሊስተካከል ይገባል፤ ደጋፊዎቻችን ጥሩ
ስንሆን እንደሚያበረታቱን ሁሉ ጥሩ ሳንሆን
ስንቀርም እስከመጨረሻው ሰዓት ሊደግፉን
ይገባል፤ የደጋፊዎች ድጋፍ ጥሩ ባትሆን
እንኳን ያነቃቃልና ይሄ ሊለመድ ይገባል፡፡
ሊግ፡- ከድሬዳዋ ከነማ ጋር በእዚህ
አመት ምን አይነት የውድድር ጊዜን
የምታሳልፍ ይመስልሃል?
በረከት፡- ከድሬዳዋ ከነማ ጋር በእዚህ
አመት የሚኖረኝ የውድድር ቆይታ
ካለፉት አመታቶች በጣም የተሻለ እና
ጥሩም የሚሆንልኝ ያህል ነው እየተሰማኝ
የሚገኘው፤ በውድድር ዘመኑ ለክለቤ ውጤት
ማማር ከእኔ የሚጠበቀውን ስኬታማ
ግልጋሎትን ለመስጠት ራሴን በብቁ ሁኔታ
ያዘጋጀሁበት ሁኔታም ስላለ ይህንን ቃሌን
በተግባርም ሜዳ ላይ አሳያለሁ፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ
ኳስን ስትጫወት በጣም የተደሰትክበት እና
የተከፋህበት አጋጣሚዎች የትኞቹ ናቸው?
በረከት፡- በሊጉ የውድድር ተሳትፎዬ
በጣም የተደሰትኩበት አጋጣሚ ለድሬዳዋ
ከነማ ስጫወት ክለቡ በመውረድና
ባለመውረድ ዞን ውስጥ ሆኖ አጣብቂኝ ውስጥ
በገባበት የ2008ቱ የሊጉ ተሳትፎአችን ላይ
ከጅማ አባቡና ጋር በነበረን ጨዋታ እነሱን
አቻ መውጣት ያሳልፋቸው የነበረ ቢሆንም
በመጨረሻው ሰአት ላይ እኛ የማሸነፊያ ግብ
አስቆጥረን በሊጉ ላይ እንድንቆይ ተደርገን
ነበርና ያ ያስደሰተኝ ሆኖ አልፏል፤
የተከፋሁበት አጋጣሚ ደግሞ በችሎታው
በጣም የማደንቀውና አብሬው ልጫወትም
እመኝ የነበረው የመከላከያው አማካይ
ተክለወልድ ፍቃዱ የሞተ ጊዜ ነው፡፡
ሊግ፡- የትዳር ህይወትን መሰረትክ?
በረከት፡- ጓደኛ አለኝ፤ ትዳርን ግን ገና
አልመሰረትኩም፤ ከፍቅረኛዬም ትዕግስት
ሲሳይ ጋር ወደፊት ለመጋባት እቅድን
እየነደፍን ነው፡፡
ሊግ፡- ፍቅረኛህን እንዴት ትገልፃታለህ?
በረከት፡- በጣም ጥሩ ሰው ናት፤ ከጎኔ
ሆና እያበረታታችኝም ነው የምትገኘው፤
ለህይወቴ ስለምትሆነኝም ነው እርሷን
ልመርጣትም የቻልኩትና ፈጣሪ
መጨረሻችንን እንዲያሳምርልንም ነው
የምመኘው፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…
በረከት፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ
የተጨዋችነት ቆይታዬ ላይ ዛሬ ለምገኝበት
ስፍራ ፈጣሪዬና ቤተሰቦቼ ብዙ ነገሮችን
አድርገውልኛልና ለእነሱ ላቅ ያለ ምስጋናን
አቀርብላቸዋለሁ፤ ከእነሱ በመቀጠል ደግሞ
የሙገር ቡድን ውስጥ እኔን ያሰለጠነኝ
አሰልጣኝ ግርማ ሃ/ዮሃንስም ለችሎታዬ
መሻሻልና ለውጥን ማምጣት ከፍተኛ
አስተዋፅኦ ከማድረጉ በተጨማሪ ብዙ ነገርን
ይመክረኝም ስለነበር እሱንም ማመስገን
እፈልጋለሁ፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P