በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/
በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ 7 ክለቦች ግማሽ ፍፃሜውን ለመቀላቀል ዛሬና ነገ ይጫወታሉ
የ14ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬና ነገ በሚደረጉት አራት ግጥሚያዎች የሚጠናቀቁ ሲሆን በእዚሁም መሰረት ዛሬ ቅዳሜ በ8 ሰአት መከላከያ ከወልቂጤ ከተማ የሚያደርጉት እና በ10 ሰአት ደግሞ ባህር ዳር ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል፡፡
የእነዚህ ሁለት ጨዋታዎች ውጤትም ወደ ግማሽ ፍፃሜ የሚያልፉትን ሁለት ቡድኖችም ያሳውቃል፡፡ በእስካሁኑ ጨዋታ መከላከያ ብዙ ጎል አገባ በሚለው ህግ በ4 ነጥብ እና በ1 ግብ ምድቡን ሲመራ ባህር ዳር ከተማ ደግሞ በተመሳሳይ ነጥብና ጎል ተከታዩን ስፍራ ይዟል፡፡ ቅ/ጊዮርገስ በ3 ነጥብና በ1 ጎል ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ወልቂጤ ከተማ ያለምንም ነጥብ 3 የግብ እዳ ኖሮበት የመጨረሻውን ስፍራ ይዞ ወደ ግማሽ ፍፃሜው የሚያልፍበት እድሉ አክትሟል፡፡
ከሌላው ምድብ ደግሞ ሰበታ ከተማ በ4 ነጥብና በአንድ ግብ ምድቡን ሲመራ ኢትዮጵያ ቡና እና ወልዋሎ አዲግራት በተመሳሳይ ሶስት ነጥብና ያለምንም ግብ ተከታዩን ስፍራ ይዘው ይገኛሉ፤ ኤሌክትሪክም በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን ስፍራ ይዞ ይገኛል፤ በእዚሁም መሰረት ነገ በሚደረጉት የ8 ሰዓቱ የወልዋሎ አዲግራትና የሰበታ ከተማ እንደዚሁም ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናና የኤሌክትሪክ ጨዋታ ጥሩ ውጤት የሚያስመዘግበው ቡድን የግማሽ ፍፃሜውን ይቀላቀላል፡፡
የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ጨዋታዎችን አስመልክተን ከየክለቡ ተጨዋቾች ጋር ያደረግነው ቃለምልልስ በሚከተለው መልኩ ይቀርባል፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ጅማሬህ ምን ይመስላል?
ስንታየሁ፡- የእግር ኳስን የልጅነት ዕድሜዬ ላይ ሆኜ መጫወት የጀመርኩት በአሰልጣኝ ማሞ በመሰልጠን ተወልጄ ባደግኩበት የሽሮ ሜዳ አካባቢ ነው፤ ያኔም ወደ ኳሱ እንድሳብም የአካባቢያችን ተጨዋቾች ከነበሩት መካከል አሁን ላይ ለኢትዮጵያ ቡና የሚጫወተው አማኑኤል ዩሃንስ ለእኔ ጎረቤቴ እና ከወንድሜም በላይ የሆነ ልጅ ስለነበር እሱን መመልከቴ እና አሰልጣኜም ማሞ በሚሰጠኝ ስልጠና ነው ለተጨዋችነቴ ትልቅ መነሳሻ ሆኖኝ ወደ ኳስ ተጨዋችነቱ ልመጣ የቻልኩትና ሁለቱንም ላመሰግናቸው እፈልጋለው፡፡
ሊግ፡- ከኢትዮጵያ ቡናው አማኑኤል ዩሃንስ ጋር ብዙ ሰዎች ያመሳስሏችኋል፤ ይህን ታውቃለህ? መመሳሰሉስ በምን ይመስልሃል?
ስንታየሁ፡- አዎን፤ ከአማኑኤል ጋር የሚያመሳስሉን አጨዋወታችሁ አንድ አይነት ነው በሚል እና አልሸነፍ ባይም በመሆናችን ነው፤ ከእሱ ጋር በመመሳሰሌም በጣም ነው ደስ የሚለኝ፤ አማኑኤል ጥሩ እግር ኳስ ተጨዋች እና እኔም አድንቄው ያደግኩት ተጨዋች ነው፤ ከዛ ውጪም ኳሱን መጫወት ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶም እኔን በመመልከት ምን ማድረግ እንዳለብኝ የሚመክረኝና ብዙ ነገርም እያደረገልኝ ያለ ተጨዋች ስለሆነ እሱንም ሳላመሰግነው አላልፍም፡፡
ሊግ፡- ቤተሰቦችህ በኳስ ተጨዋችነትህ ምን አይነት አመለካከት ነው የነበራቸው?
ስንታየሁ፡- መጀመሪያ ላይ እነሱ ኳስን እንድጫወት ሳይሆን እንድማር ነበር የሚፈልጉት በኋላ ላይ ግን የእኔ የኳስ ስሜት ከፍ ያለ ስለነበር በምወደው ሙያ ቀጠልኩ፤ እነሱም ፍላጎቴን ተረድተው ሊያበረታቱኝ ቻሉና በእዚህ አጋጣሚ ቤተሰቦቼን በተለይ ደግሞ አባቴን ዋልኬ ዋጊሶንና እናቴን አበበች በታቸውን ለማመስገን እፈልጋለሁ፡፡
ሊግ፡- ከቤተሰብ ውስጥ የእግር ኳስን የምትጫወተው አንተ ብቻ ነህ? ስንት ወንድም እና እህትስ አለ?
ስንታየሁ፡- አዎን፤ ኳስ ተጨዋቹ እኔ ብቻ ነኝ፤ አራት እህት እና ሁለት ወንድሞችም አሉኝ፤ እኔም 6ኛው የቤቱ ልጅ ነኝ፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን መጫወት ስትጀምር ተምሳሌትህ ማን ነበር?
ስንታየሁ፡- ከሀገር ውስጥ መስዑድ መሐመድ ሲሆን ከውጪ ደግሞ የባርሴሎናም ደጋፊ ስለሆንኩኝ ዣቪ የእኔ ምርጫዎች እና ሞዴሌ ተጨዋቾች ናቸው፤ ሁለቱ ተጨዋቾች ልዩ ብቃት ያላቸው ስለሆኑም ነው ያደነቅኳቸው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮ-ኤሌክትሪክን ከታዳጊው ቡድን አንስቶ እስካሁን አገልግለሃል፤ ቆይታህን እንዴት ትገልፀዋለህ? ከዚህ በኋላስ ቡድኑን በምን መልኩ ልጠቅመው ዝግጁ ነህ?
ስንታየሁ፡- የኢትዮ-ኤሌክትሪክ የተጨዋችነት ቆይታዬን አሁን ላይ ስመለከተው ከታዳጊው ማለትም ከ15 ዓመት በታች አንስቶ እስከ 17 ዓመት በታች እንደዚሁም ደግሞ እስከዋናው ቡድንም ድረስ የዘለቀ ስለሆነ በእዚህ ቡድን በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ከዛ ውጪም ወደዋናው ቡድን እንዳድግ አሰልጣኝ ብርሃኑ ባዬ እንደዚሁም ደግሞ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በነበረንም ጨዋታ ለዋናው ቡድን የመጀመሪያዬን ግጥሚያ ማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስላበረከቱልኝ በዚህ ላመሰግናቸው እፈልጋለው፤ ይሄን ካልኩ ስለቀጣይ ጊዜ የቡድኑ ቆይታዬም አሁን ላይ የማስበው ኤሌክትሪክን ከሚጫወትበት ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲሸጋገርና ራሴንም ለፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ማብቃት ነው ዓላማዬና ያን ለማሳካት ጥረትን አደርጋለው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ከባህር ዳር ከተማ ጋር በነበረው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የጨዋታው ኮከብ ተብለህ ተሸልመሃል፤ ደስታው እንዴት ነበር?
ስንታየሁ፡- ኤሌክትሪክ ከባህር ዳር ጋር ባደረገው ጨዋታ የግጥሚያው ኮከብ ተጨዋች ተብዬ ስለተሸለምኩ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ይሄም በቀጣይነት ሌሎች ስኬታማ ነገሮችን እንድሰራም ያበረታታኛል፡፡
ሊግ፡- የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ያላችሁን የውድድር ተሳትፎ እንዴት አገኘኸው? ቡናንስ በምትገጥሙበት የነገው ጨዋታ ምን ውጤትን ታስመዘግባላችሁ?
ስንታየሁ፡- ኤሌክትሪክ በሲቲ ካፑ ላይ እያደረገ የሚገኘው የውድድር ተሳትፎው ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማለፍ ለሚያስችለው የዘንድሮው የከፍተኛ ሊግ ውድድሩ አቋሙን በሚገባ እየለካበት ሲሆን ከወልዋሎ ጋር ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታው ሽንፈትን ቢያስተናግድም ከግጥሚያው ተምሮበታል፤ በሁለተኛው ከባህር ዳር በነበረው ጨዋታ ጥሩ ተንቀሳቅሷል፤ አሁን ደግሞ ቡናን ነገ ሲገጥም በተሻለ መልኩ ተንቀሳቅሶ የጨዋታው አሸናፊ ለመሆን ተዘጋጅቷል፡፡