Google search engine

“ወላይታ ድቻ በኳሱ ከፍተኛ እውቅናን ያስገኘልኝ ብቻ ሳይሆን ምርጥ ጊዜንም ያሳለፍኩበት ቡድን ነው” ባዬ ገዛኸኝ /ወላይታ ድቻ/


ለወላይታ ድቻ ዳግም ለመጫወት ውሉን ያራዘመው ባዬ ገዛኸኝ በቀጣዩ የውድድር ዘመን ላይም ለቡድኑ ከእሱ የሚጠበቀውን ጥሩ ግልጋሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን ይናገራል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሶስት ለሚደርሱ ክለቦች የተጫወተው ባዬ ከሊግ ስፖርት ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሾቹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷልረሰ ለተለያዩ
ሊግ፡- ወላይታ ድቻ፣ መከላከያ እና ሲዳማ ቡና በፕሪምየር ሊጉ ደረጃ የተጫወትክባቸው ክለቦች ናቸው፤ ምርጡ ጊዜ የት እያለህ ያሳለፍከው ነው?
ባዬ፡- ወላይታ ድቻ ነዋ! በእዚህ ቡድን ውስጥ የነበረኝ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ከሌሎቹ በጣም ይለያል፤ ወላይታን ለሁለት ጊዜያት ያህል ነው ተቀላቅዬው ለመጫወት የቻልኩት፤ የመጀመሪያው ከወራቤ ከተማ በመጣሁበት ሰዓት እና ሌላው ደግሞ ለሲዳማ ቡና ከተጫወትኩ በኋላ ዳግመኛ ክለቡን ተቀላቅዬ የተጫወትኩበት ነው፤ በሁለቱም ወቅት ጥሩ ጊዜን አሳልፌያለው፤ ለክለቡ ባበረከትኩት መልካም የሚባል የጨዋታ እንቅስቃሴዬም በደጋፊዎቹ ዘንድ እስከመወደድ ደረጃም ደርሻለሁና በእዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
ሊግ፡- ወላይታ ድቻን ከዓመታት ቆይታ በኋላ በድጋሚ እንድትቀላቀል ያደረገህ ዋንኛው ምክንያት ምን ነበር?
ባዬ፡- ወላይታ ድቻን ለቅቄ ወደ መከላከያ ከዛም በመቀጠል ወደ ሲዳማ ቡና ካመራሁ በኋላ የቀድሞ ቡድኔን ዳግም እንድቀላቀል ያደረገኝ ወላይታ ድቻ ከሲዳማ ቡና ባደረጉት ጨዋታ ላይ የሲዳማ ቡና ተጨዋች ሆኜ ጥሩ ለመንቀሳቀስ ስለቻልኩ በደጋፊዎቹ ዘንድ ባዬ ወደ ቡድኑ ይመለስ የሚል ተቋውሞን በማሰማታቸውና እንድመለስም በመደረጉ ነው፤ ወላይታን በአሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃ የኃላፊነት ዘመን ግን ዳግም ስቀላቀል በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች አካባቢ እነዛ ይመለስ ያሉት ደጋፊዎችም ሆኑ ሌሎች ደጋፊዎች ከእኔ የሚጠብቁትን ነገር በሜዳ ላይ ስላላዩ መልሰው ተቃውሞን አቀረቡብኝ፤ በሌሎች በርካታ ጨዋታዎች ደግሞ መልሶ ጥሩ ለመንቀሳቀስ ስችል ከጎኔ መሆናቸውን አረጋገጡ፤ በተለይ ደግሞ የእዚህ ዓመት የክለቡ ቆይታዬ ላይ በኮቪድ 19 የሊጉ ውድድር እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ 9 የሚደርሱ ግቦችንም ያስቆጠርኩበት አጋጣሚም ስለነበር በእዛ እነሱ በእኔ ደስተኛ ናቸው፡፡
ሊግ፡- በወላይታ ድቻ የነበረህን ውል ብታጠናቅቅም መልሰህ ለማራዘም ችለሃል፤ ከእዚህ ውሳኔ ላይ የደረስክበት ምክንያትስ ምን ነበር?
ባዬ፡- በደጋፊዎቹ መወደዴ እና ጥሩም ጊዜንም ከክለቡ ጋር ማሳለፌ ነዋ!፤ ከዛ ውጪም ይሄ ቡድን ለእኔ የኳስ ተጨዋችነት ዘመን እውቅናም የመጀመሪያውን የጥርጊያ መንገድ ስላመቻቸልኝ እና ከክለቡም የምፈልገውን ነገር ለማግኘት ስለቻልኩ ውሌን አራዝሜ ልቆይ ችያለሁ፡፡


ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በመጪው ዓመት ሲጀመር ወላይታ ድቻ ከአንተ ምርጥ ግልጋሎትን ማግኘት ይችላል?
ባዬ፡- አዎን፤ በእዚህ በጣም እርግጠኛ ነኝ፤ ምክንያቱም የእዚህ ዓመት የውድድሩ ተሳትፎዬ ላይ ለክለቤ 9 ጎሎችን ላስቆጥርለት ስለቻልኩ እና አሁን ደግሞ የመጪው ዓመት ቡድናችን ስብስብ /ስኳዱም/ እየተጠናከረ በመሆኑ ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ለክለቤ ካለፈው ዓመት በተሻለ መልኩ ጥሩ ነገር እንደምሰራ አምናለሁኝ፡፡
ሊግ፡- ወላይታ ድቻን ለየት ያደርገዋል የምትለው ነገር አለ?
ባዬ፡- አዎን፤ ቡድናችን በታዳጊ እና በወጣት ተጨዋቾች ላይ ያለው እምነት እንደዚሁም ደግሞ ጥሩ የሆነው ደጋፊው ለየት እንዲል ያደርገዋል፤ በተለይ ደጋፊው ከእዚህ ቀደም ተጫውቼ ካለፍኩበት ክለብ ደጋፊዎች አንፃርም ሆኖ ከሌሎች አንድአንድ ክለብ ደጋፊዎች አኳያ ስመለከታቸው ለየት የሚሉበት ነገር አለ፤ ይህም ጥሩ በሆንበትም ሆነ ባልሆንበት ሰዓት ላይ እንኳን ከጎናችን በመሆን ጭምር የሚያበረታቱን ናቸውና በእዚህ አጋጣሚ እነሱን እንደምወዳቸውና እንደማከብራቸውም መናገርን እፈልጋለሁ፤ ይህ እንዳለን ካወቅን ደግሞ ይህን ቡድን የሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ አድርገንና ለዋንጫም የሚጫወት ቡድንንም ገንብተን ህዝቡ የሚደሰትበትን ነገር መስራት የግድ ነው የሚለን፡፡
ሊግ፡- በመከላከያ ክለብ ውስጥ የነበረህ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታህ በምትፈልገው መልኩ የሄደልህ ነው?
ባዬ፡- በፍፁም፤ የትም ልጫወት እንደ ወላይታ ድቻ የሆነልኝ ክለብ ማንም የለም፤ ወደ መከላከያ ስገባ አሰልጣኙ ገ/መድህን ሀይሌ ነበር፤ በመጀመሪያው ዓመት ላይ ወደ ቡድኑ ሳመራ ተጠባባቂ ተጨዋች ነበርኩ፤ ተቀይሬም ነበር የምገባው፤ ወደ መጨረሻዎቹ ግጥሚያዎች ላይ ደግሞ ጥሩ ስሆን ተሰልፌ መጫወት ጀመርኩኝ፤ ያም ሆኖ ግን በቀጣዩ ዓመት ላይ የደረሰብኝ ጉዳት ከሜዳ ሊያርቀኝ ስለቻለ ይሄ ነው በምፈልገው መልኩ መከላከያ ክለብ ውስጥ እንዳልጫወት ያደረገኝ፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ዘመንህ ደስተኛ ነህ?
ባዬ፡- ፈጣሪ ይመስገን፤ አዎን ደስተኛ ነኝ፤ እግር ኳሱም ብዙ ነገሮችንም አስገኝቶልኛልና፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ዘመንህ የሚከፋህ ወቅትስ?
ባዬ፡- የሚከፋኝ ከሰዎች ጋር ቶሎ የመቀራረብ ችግር አለብኝ፤ በተለይ ደግሞ የእግር ኳስ ተጨዋች ብዙ ጓደኛ ስለሌለኝ እና ከእነሱም ጋር አብሬም ስለማልውልና ስለማልጨዋወት ከዛም በተጨማሪ ከአጠገቤም የቡድናችን ተጨዋቾች ሳይኖሩ ሳይ እነዚ ነገሮች ይከፉኛል፡፡
ሊግ፡- ኮቪድ 19 ከገባበት ወቅት አንስቶ እያደረግክ ያለው ጥንቃቄ ምንድን ነው የሚመስለው? ጊዜውን የትስ እያሳለፍክ ነው?
ባዬ፡- ለዓለም እና ለአገራችን ከፍተኛ ስጋት የሆነው ኮቪድ ወደ እኛ ሀገር ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ጊዜዬን እያሳለፍኩ ያለሁት መጀመሪያ ላይ በወላይታ ነበር፤ እዛም ረጅሙን ወቅት አሳለፍኩ፤ ቀጥዬ ደግሞ ወንድሜ በሐዋሳ ከተማ ላይ ይገኝ ስለነበር እዛ ሄጄ በማሳለፍ በቢዝነሱም የስፖርት እንቅስቃሴዎችንም በማድረግ ለ3 ወራት ያህል ቆይታዬን አደረግኩኝ፤ በከተማው ላይ የተለያዩ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን በምንሰራበት እና እዛም ከሚገኙ ሌሎች ተጨዋቾችም ጋር እንደ ፉትሳል አይነት ጨዋታን ከተጫወትንና ከወረርሽኙም ጋር በተያያዘ መጫወቱን በፖሊስ ከተከለከልን በኋላ ደግሞ ጊዜዬን የማሳልፈው በግል የሚሰሩ ልምምዶችን በቤት ውስጥ በመስራት እና አንድአንዴም ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ሻይ ቡና በማለት ነው፡፡ ለኮቪድ እያደረግኩ ስላለው ጥንቃቄ ደግሞ መናገር የምፈልገው ይሄ ወረርሽኝ በጣም ከባድ ሆኗል፤ ያን ስላወቅኩም ራሴንም ቤተሰቦቼንም ከበሽታው በመጠበቅ ላይ እገኛለው፡፡
ሊግ፡- አሁን ላይ ወደ ቢዝነሱ /ንግዱ/ ዓለም ላይ ጠልቀህ ገብተሃል ማለት ይቻላል?
ባዬ፡- ወደዛ መንደርደሩን ጀምሬያለሁ፤ የእግር ኳስ ተጨዋች ስትሆን ደግሞ ኳስን የምትጫወትበት እድሜ ብዙ ስላልሆነና በጉዳትም ልታቆም ስለምትችል ወደ ቢዝነሱ መግባት የግድ ስለሆነም ነው እኔም የእግር ኳስ ተጨዋች ባልሆኑ ጓደኞቼ አማካኝነት ስለንግድ እንቅስቃሴ ጠቃሚነት ነግረውኝ ዘልቄ ልገባ የቻልኩበት እና ይሄን ስራዬን ከኳሱ ጎን ለጎን ወደፊትም አጠናክሬ እቀጥልበታለው፡፡
ሊግ፡- ባዬ ወደ ትዳር ዓለሙ መች ያመራል?
ባዬ፡- አሁን ኮቪድ 19 ስለሆነ አልተሳካም፤ በባህር ማዶ የምትኖር ጓደኛ አለችኝ፤ የመጪው ዓመት ክረምት ላይ ጋብቻዬን እፈፅማለው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ተጨዋች ሆንክ እንጂ ባትሆን ኖሮ ነጋዴ ነበር የምትሆነው?
ባዬ፡- አይደለም፤ ነጋዴ መሆንን ያለምኩት በቅርብ ጊዜ ነው፤ እኔ ልሆን የምችለው በጋራዥ ውስጥ በሙያው እሰራ ስለነበር ሜካኒክ ነበር የምሆነው፡፡
ሊግ፡- ለሲዳማ ቡና ስለሚጫወተው ወንድምህ እናውራ ስለ እሱ አንድ ነገር በል እስኪ? በተለይ እንዳለው ጥሩ አቅም እና ችሎታ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ተገኝቷል ማለት ትችላለህ?
ባዬ፡- በፍፁም፤ የእኔ ወንድም ሀብታሙ ገዛኸኝ ምንም እንኳን በጠንካራው ክለብ ሲዳማ ቡና ውስጥ ይጫወት እንጂ ካለው እምቅ ችሎታና አቅም አንፃር በሀገሪቱ እግር ኳስ ላይ ስሙ ጎልቶ እየታየ አይደለም፤ ችሎታው በሰዎችም ተሸፍኗል፤ ይሄ ተጨዋች በቡድኑ ቆይታው ላይ አሁን ክለቡን ለለቀቀው አዲስ ግደይ በርካታ የግብ ኳሶችንም በማስቆጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦም ያበረከተ ተጨዋች ነው፤ ከእዚህ በመነሳት በጣም ስለምወደው ወንድሜ ማለት የምፈልገው ነገር ቢኖር የእሱ ስም በጣም እንዳይገን ያደረገው በእዚህ ቡድን ውስጥ ብቻ ቆይታን ማድረጉ ስለሚመስለኝ በቀጣይነት ወደሌሎች ትላልቅ ወደሚባሉ ቡድኖችም በማምራት ራሱን ቢያይ ለውጦችን የሚመለከት ይመስለኛልና ይሄን ነው ልል የምፈልገው፤ ከዛ ውጪ ስለ ሀብታሙ መናገር የምፈልገው እሱ በባህሪው ዝምተኛ እና ሼመኛ የሆነ ልጅ ነው፤ ከሰው ጋር ቶሎ አይግባባም፤ በእዚህ በኩልም ከእኔ ጋር ይመሳሰላልና በእዚህ ደረጃ ላይ የሚገለፅ ተጨዋች ነው፤ ይህን ካልኩ በኳሱ ሀብታሙ ትልቅ ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ሙሉ እምነት ነው ያለኝ፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
ባዬ፡- የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ የተሰማኝ የደስታ መጠን በጣም ከፍ ያለ ነው፤ ይህ ለእኛ ሀብታችን ብሎም ደግሞ ባህላችን እንደዚሁም ደግሞ ግብፅም አለአግባብ ሙሌቱ አይሞላም ባላ እየተከራከረችን ላለችሁ የግድቡ ሁኔታ እኛ ኢትዮጵያኖች እያደረግን ያለነው በጎ ተግባር ይበል የሚያሰኝ ነውና ይሄን የሀገር ጉዳይ ለሆነ ነገር የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን ልንቀጥልበት ይገባል፤ እኔም በበኩሌ ለህዳሴ ግድቡ 8100 ኤ ብዬ ድጋፌን እያደረግኩኝ ይገኛል፡፡ ከዛ ውጪ ኮቪድ ምንም የማያውቁ ህፃናቶችን ጭምር ሲይዝ የተመለከትኩበት ሁኔታም አለና ያን ማየት ያማል ስለዚህም አስፈላገውን ጥንቃቄ እኛ አዋቂዎች እያደረግን ራሳችንንም ቤተሰቦቻችንንም ከወረርሽኙ ልንጠብቅ ይገባል፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P