ኢትዮጵያ ቡና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው ውድድሩን በሁለተኝነት በማጠናቀቅ ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ማለፉ በጣም ቢያስደስተውም እንደ ግል ደግሞ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ይዞት በቀረበው አቋሙ ግን ራሱን እንዳላገኘው የተከላካይ ስፍራው ተጨዋች ወንድሜነህ ደረጄ ተናግሯል፤ ከዚህ ተጨዋች ጋር ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ቆይታን አድርጓል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በቤትኪንጉ ሊጉን ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል፤ ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕም አልፏል፤ ስላሳለፋችሁት የውድድር ዘመን ምን ትላለህ?
ወንድሜነህ፡- በጣም ጥሩ የሆነ የውድድር ሲዝንን ነው ያሳለፍነው፤ በእዚህ ጊዜ ውስጥም ክለባችን አዝናኝ የሆነ እግር ኳስን ከመጫወቱም ባሻገር ሊጉን ሁለተኛ ሆኖም አጠናቅቆበታል፤ ይህ ውጤት ደግሞ ክለቡን ከ9 ዓመት በኋላም ወደ ኢንተርናሽናል ውድድርም መልሶታልና ያ ሊሆን መቻሉ አስደስቶናል፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛ ደረጃ አያንሰውም?
ወንድሜነህ፡- እንደ ክለቡ ትልቅነትማ ውጤቱ ያንሰዋል፤ ምክንያቱም ቡና ሁሌም ቢሆን ለሻምፒዮናነት የሚጫወት ቡድን ነውና ያም ሆኖ ግን በአሁን ሰዓት ላይ ቡድናችን በአዲሱ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የሀላፊነት ዘመን መመራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አዲስ አይነት አጨዋወትን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኝበት ሁኔታዎች ላይ ስላለና እነዛ ጥቃቅንና ለወደፊቱ እየታረሙ የሚመጡ ክፍተቶቻችን ደግሞ በመጀመሪያው የሻምፒዮናነት ረድፍ ላይ እንዳንቀመጥ አድርገውናልና ከዛ ስህተቶቻችን ልንማር ተዘጋጅተናል፤ እንደ አጠቃላይ ግን የቡድናችንን የዘንድሮ ውጤት ስንመለከተው የአዲሱን አጨዋወት ትገበራ ላይ ከመሆናችን አኳያ ያመጣነው ውጤት ጥሩ የሚባል ነው፤ ክለቡም እኛ ባልጠበቅነው ሁኔታም ነው ሁለተኛ በመውጣታችን ተደስቶም ሽልማትን ሊያበረክትልን የቻለውና በእዚህ አጋጣሚ ታላቅ ምስጋናን ለክለቡ ለማቅረብ እፈልጋለው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን ሻምፒዮና እንዳይሆን ያደረገው ሌላ የምትጠቅሰው ነገርስ አለ?
ወንድሜነህ፡- እግር ኳሱን በሜዳ ላይ ጥሩ አድርገን ብንጫወትም ለሻምፒዮናነት ከመጫወታችን አንፃር ነጥብ መጣል በሌለብን ጨዋታዎች ላይ ነጥቦችን ስንጥል ቆይተናል፤ ይሄ ደግሞ ከፊታችን ያለውን ፋሲል ከነማን በውጤት እንዲርቀን መንገዱን ከፍተንለታልና እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችና በኳሱ ውስጥም ሊያጋጥሚ በሚችሉም ክፍተቶቻችንም ነው ሻምፒዮና ሳንሆን የቀረነው፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ቡና የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎህ ውስጥ አልፎ አልፎ ስህተቶችን ትሰራ ነበር፤ በዛ ስህተት ውስጥም ቡድኑ ላይ ጎል የተቆጠረበት አጋጣሚም አለና ከዛ መነሻነት የጥፋተኝነት ስሜት አይሰማህም?
ወንድሜነህ፡- እንደ ኢትዮጵያ ቡና ተጨዋችነቴ ዘንድሮ በነበረን የሊጉ ተሳትፎ ስህተትን አልሰራውም አልልም፤ ቡና ሲሳሳት ደግሞ እንደ ቡድን ጭምር እንጂ እንደ ግል ብቻም አይደለም፤ ስህተት አይደለንም እኛ በዓለም ላይ ያሉ ታላላቅ ተጨዋቾችም የሚፈፅሙት ተግባር ነው፤ በኢትዮጵያ ቡና አዲሱ አጨዋወት ውስጥም ስህተቶች በደንብ አሉ፤ በተለይ ደግሞ እነዛ ስህተቶች ኳስ ተመስርቶ በሚመጣበት የግብ ጠባቂና የመከላከል ክፍል ላይ ጎል ስለሚቆጠርብህ በደንብ ጎልተው ይታያሉና ከዛ መነሻነት ነው ብዙ ነገሮች እኛ ተከላካዮች ላይ የሚያነጣጥሩትና አሰልጣኛችን ካሳዬ አራጌ ከሚነግረን ነገር በመነሳት ነው በእዛ አጨዋወት ውስጥ በመቀጠል ስህተቶችን እየቀነስኩ በመሄድ መጓዝን የምፈልገው፡፡ በቡና ቆይታዬ ዘንድሮ ስህተቶችን እንደፈፅምኩ ባልክድም የጥፋተኝነት ስሜቱ ግን አሁንም አይሰማኝም፤ ምክንያቱም በቡና አጨዋወት ውስጥ ኳስ ተመስርቶ የሚመጣው ከኋላ ነው፤ በዛም አካባቢ ነው ስህተት የሚፈጠረው፤ ስለዚህም አሰልጣኙ ሁሉም ቦታ ላይ ስህተት እንዳለ የነገረን ቢሆንም ያን ስህተት እየቀነስን በመምጣት መጫወት ከቻልን ምርጡንና ውጤታማውን ቡድን ማግኘት እንደምንችልም ልናውቅ ችለናል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በቤትኪንግ ተሳትፎው ሁለተኛ መውጣቱን ተከትሎ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ላይ ይሳተፋል፤ ይሄን ውድድርም በእዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ያደርጋል፤ ስለሚኖራችሁ ተሳትፎና ስለምታስመዘግቡት ውጤት ምን ትላለህ?
ወንድሜነህ፡- አሁን እንግዲህ በእረፍት ላይ ነን የምንገኘው፤ የዓመቱ መጨረሻ ላይ ላለብን የእዚሁ የኢንተርናሽናል ውድድር ተሳትፎም ከወዲሁ ቡድኑን ሊጠቅሙ የሚችሉ ውል የሚጨርሱ ተጨዋቾችንና ከሌሎችም ክለቦች እኛን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ልጆችንም በአሰልጣኞቻችን ጥቆማና በክለባችን አጋዥነትም በማምጣት የውድድሩን ተሳትፎ ልናደርግ ነው የሚገባንና በቅርቡ ዝግጅትን በመጀመር እዛ ላይ ነው ትኩረት ልናደርግ የሚገባን፤ ቡና በዚሁ የውድድር ተሳትፎውም ሲሳተፍ ለተካፍሎ ብቻ አይደለም ወደ ውድድሩ የሚገባው፤ የያዘውን ከኳስ ጋር የተያያዘ አጨዋወቱን በአፍሪካና በተቀረው ዓለም ላይ ማስመልከት ይፈልጋል፤ ከዛ ውጪም የከዚህ በፊት ሪከርዱንም በማሻሻል እስከ ሩብ ፍፃሜና ከዛም በበለጠ ደረጃም ላይ መገኘትንም ይፈልጋልና ይሄ ትልቅ ውድድር ለአብዛኛዎቻችን ተጨዋቾችም አዲስ ነውና ራሳችንን በምርጥ ብቃት ላይ ልናስገኘውም ይገባናል፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ ቤትኪንጉን በሻምፒዮናነት አጠናቀቀ፤ የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስርም በኮከብ ተጨዋችነትና ግብ አግቢነትም ዘንድሮ ክብሩን ተጎናፀፈ፤ በዚህ ዙሪያ ምን አልክ?
ወንድሜነህ፡- ለሁለቱም ይህ ዓመት ልዩ ነበር፤ ለፋሲል ከነማ በነጥብ ለአቡበከር ደግሞ በጎል ከተከታዮቻቸው በጣም ርቀው ሊጉን የጨረሱበትና ከዛም ውጪ ደግሞ አሁንም ፋሲል ከነማ ሻምፒዮና የሆነው አንድ ጨዋታን ብቻ በእኛ ክለብ ተሸንፎና በታሪክ አራት ጨዋታም ሲቀር ባለድል የሆነበት እንደዚሁም አቡበከርም በውድድር ዓመቱ ላይ አራት ጊዜ ሀትሪክ ከመስራት ባሻገር የኢትዮጵያን የግብ ሪከርድም የሰበረበት ዓመት ስለሆነ ክብሩ ለሁለቱም ይገባቸዋል፤ በዚሁ አጋጣሚም ለሁለቱም እንኳን ደስ ያላችሁ ልላቸውም እፈልጋለው፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮ የቡድንህ ተሳትፎ ምን ነገርን ተማርክ?
ወንድሜነህ፡- ብዙ ነገሮችን ተምሬያለው፤ ዘንድሮ ራሴን በምፈልገው አቋምና ብቃት ላይ አላገኘሁትም፤ ለመጪው ዘመንም ራሴን በዚህ ደረጃ ላይ ማግኘትም አልፈልግም፤ ለደጋፊዎቻችንና ለአድናቂዎቼ ጭምርም ነው በዚህ አቋሜ ላይ ዳግም መገኘትን የማልፈልገውና ከወዲሁ ራሴን በስነ-ልቦናም ሆነ እረፍት በማድረግም ዝግጅትን ማድረግ እጀምራለውና የመጪው ዓመት ላይ በምርጥ ብቃቴ ላይ ሆኜ እንደምቀርብ እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ?
ወንድሜነህ፡- ቤትኪንግ ውድድሩ ዘንድሮ በዲ.ኤስ.ቲቪ መተላለፉ ለሁሉም ተጨዋቾች መልካም አጋጣሚ ነው፤ ይሄን ውድድርም ቡና በመጪው ዘመን ላይ ስህተቱን ቀንሶ እንዲያነሳም ከጓደኞቼ ጋር የተቻለኝን ሁሉ ጥረት አደርጋለው፤ ይህን ካልኩ ሌላ ለማለት የምፈልገው ነገር ቢኖር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተሳትፎዬ ላይ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በያዘው ቡድን ውስጥ አባል ሆኜ መጨረሻ በኮትዲቯሩ ጨዋታ ላይ ብቻ ሳልገኝ በመቅረት እኔን ጨምሮ ሌሎችም በዚህ ደረጃ ላይ ያሉ ተጨዋቾች የሽልማት ገንዘቡ ይቅርና ለሀገር ላበረከትነው አስተዋፅኦ የምስጋና ሰርተፊኬት እንኳን ሳይሰጠን በመቅረቱ ለፌዴሬሽኑ ቅሬታ አለኝና እንዲህ ያሉ ነገሮች ሊስተካከሉ የሚገባቸው ነው፡፡