Google search engine

“ወደ ሐዋሳ ከተማ የተዛወርኩት ለክለቡ ጥሩ ጥቅምን ለመስጠት ነው”“እግር ኳስ ተጨዋች ባልሆን ኖሮ የጤና ባለሙያ እሆን ነበር”በቃሉ ገነነ /ሐዋሳ ከተማ/

 

በኢሊባቡር መቱ ከተማ ውስጥ ተወልዶ ያደገው በቃሉ ገነነ እግር ኳስን ከፕሮጀክት አንስቶ በተለያዩ ክለቦች ውስጥ ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን በዘንድሮው የክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ደግሞ የውል ጊዜውን በአዳማ ከተማ ክለብ ውስጥ በማጠናቀቁ የሁለት ጊዜውን የፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ክለብ ሐዋሳ ከተማን ሊቀላቀል ችሏል፡፡

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ ሻምፒዮና ውጤታማ ላልነበረው አዳማ ከተማ ተሰልፎ ተጫውቶ መልካም የሚባል እንቅስቃሴን እንደ ግል ካስመለከቱን ተጨዋቾች ውስጥ አንዱ የሆነውን ይኸውን ተጨዋች ሊግ ስፖርት ጋዜጣ በጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አማካኝነት በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ አናግራው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷታል፡፡

ሊግ፡- በአዳማ ከተማ የውል ጊዜህን አጠናቀህ ወደ ሐዋሳ ከተማ አመራህ፤ ክለቡ እንዴት የቅድሚያ ምርጫህ ሆነ?

በቃሉ፡- ወደ ሐዋሳ ከተማ ለመግባት ክለቡን የመጀመሪያ ምርጫዬ ያደረግኩት በአዳማ ከተማ አሰልጥኖኝ የነበረው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በውድድር ዓመቱ ተሳትፎዬ የነበረኝን ብቃት ያውቅ ስለነበርና እሱም ቡድኑን በኃላፊነት ከተረከበ በኋላ ለእኔ ችሎታ ጥሩ ነገር ስለነበረው ከሌሎች ቡድኖች የመጣልኝን ጥሪ ወደ ኋላ ትቼ ነው ክለቡን የተቀላቀልኩት፡፡

ሊግ፡- አዳማ ከተማ ከሊጉ ከወረደ በኋላ መልሶ እንዲቆይ የተደረገው ከትግራይ ክለቦች አለመሳተፍ ጋር በተያያዘ አንድ ውድድር ተዘጋጅቶ በዛ ተጠቃሚ በመሆኑ ነውና በዛ ዙሪያ ምን የምትለው ነገር አለ?

በቃሉ፡- እውነት ነው አዳማ ከተማ ሊጉ ላይ የቆየው የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ባመቻቸው አንድ በሊጉ መቆየትና መውረድ ውድድር ላይ ያገኘውን እድል በመጠቀም ነው፤ ይሄ ቡድን ቢወርድ በጣም ያሳዝን ነበር፤ ምክንያቱም ቡድኑን ተስፋ ያደረጉ ብዙ ታዳጊ ተጨዋቾች ነበሩና ያም ስለሆነ በውድድሩ ተሳትፎአችን ክለቡን እንዳይወርድ ስላደረግንና የታሪክ ተወቃሽም እንዳንሆን ስላደረገን በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ በሊጉ መቅረታችንን ስናውቅም በታዳጊዎቹ ላይም ተነሳሽነትን ፈጥሮላቸዋል፡፡

ሊግ፡- በአዳማ ከተማ ውልህን የምታራዝምበት እድሉ አልነበረህም?

በቃሉ፡- አዎን፤ እነሱን በተመለከተ ፊታቸውን ወደ ውጪ ስላደረጉ ለድርድር እንኳን አላቀረቡንም፤ በዛ ቅር ቢለኝም በስተመጨረሻ ግን እኔን አጥብቆ ወደፈለገኝ ክለብ ሐዋሳ ከተማ ላመራ ችያለው፡፡

ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ አሁን ወደ ሐዋሳ ከተማ ክለብ ከማምራትህ አኳያ በቡድኑ ቆይታ ምን አይነት ጊዜን ታሳልፋለህ?

በቃሉ፡- ሐዋሳ ከተማ በወጣቶች የተገነባ ቡድን ነው፤ ኳስን በጥሩ ብቃትና በከፍተኛ ፍላጎትም መጫወት በሚችሉ ተጨዋቾችም የተዋቀረ ክለብ በመሆኑ በዚህ ቡድን ቆይታዬ የሊጉ ውድድር ሲጀመር ከቡድን ስራ /አጨዋወት/ በተጨማሪ ወጣትም ተጨዋች ስለሆንኩ የግሌን ጥረትም ጨምሬበት መልካምና ጥሩ ጊዜን የማሳለፍ ነው የሚመስለኝ፡፡

ሊግ፡- በወጣቶች የተገነባ ቡድንን መቀላቀል የተለየ ስሜት አለው?

በቃሉ፡- አዎን፤ ወጣትነት በጣም ደስ ይላል፤ ወጣት ስትሆን አቅሙ ስለሚኖርህ ተጋግዘህ ትጫወታለህ፤ ከ90 ደቂቃ በላይም ሊሆን ይችላል ተሯሩጠህም ትጫወታለህ፤ና በዚህ መልኩ በወጣቶች የተገነባውን ክለብ ስለተቀላቀልኩ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡

ሊግ፡- በሐዋሳ ከተማ ቆይታህ ምን ውጤትን የምታመጡ ይመስልሃል?

በቃሉ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሐዋሳ ከተማ ተስፋ ሰጪን እንቅስቃሴ በማድረግ በወጣቶች በተገነባው ቡድኑ መልካም የሚባል ውጤትን አስመዝግቧል፤ ይሄ ቡድን እያደገ ሊሄድ እንደሚችልም ምልከታን ሰጥቷልና በአዲሱ የውድድር ዘመን ክለቡ የዓምናውን እንቅሰቃሴ አስቀጥሎና አሳድጎ በመሄድ በነባር ተጨዋቾቹና እኛ አሁን አዲስ በፈረምነው እንደዚሁም ደግሞ በአዲሱ የቡድኑ አሰልጣኝ ጥረትም ይሄ ቡድን ለፕሪምየር ሊጉ የዋንጫ ተፎካካሪነትም ይጫወታል፡፡

ሊግ፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ ለማን ለማን ቡድኖች ተጫውተህ አሳለፍክ?

በቃሉ፡- በፕሮጀክት ደረጃ ኳስን ከአዲስ አበባ 700 ኪሎ መቶ ርቀት ላይ በምትገኘው አርባምንጫ ከተማ ላይ ዕድሜያቸው ከ15 እና ከ17 ዓመት በታች በሆናቸው ቡድኖች ውስጥ ከተጫወትኩ በኋላ በክለብ ደረጃ የተጫወትኩባቸው ቡድኖች የአማራ ውሃ ስራ /አውስኮድ/፣ አዲስ አበባ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማና አዳማ ከተማ ቡድኖች ናቸው፤ ከስዑል ሽረ ጋር ደግሞ ከቡድኑ ጋር ሆኜ የፕሪ-ሲዝን ዝግጅትን አድርጌያለው፡፡

ሊግ፡- ወደ እግር ኳስ ተጨዋችነት ስትመጣ ከቤተሰብ ክልከላ? ወይንስ ፈቃድን ነው ታገኝ የነበርከው?

በቃሉ፡- እነሱ ኳስን አትጫወት ብለው አይከለክሉኝም ነበር፤ ጫናም አልነበረብኝም፤ ቅድሚያ ግን እንድማር ነበር የሚፈልጉት፡፡

ሊግ፡- እግር ኳስ ተጨዋች ባትሆን ኖሮስ?

በቃሉ፡- ምንም ችግር አልነበረውም፤ በትምህርቴ ጥሩ ነበርኩና የጤና ባለሙያ እሆን ነበር፡፡

ሊግ፡- በልጅነት ዕድሜህ የማን አድናቂ ሆነህ ነው ያደግከው፤ በቤተሰባችሁ ውስጥስ ኳስ ተጨዋቹ አንተ ብቻ ነህ? ስንት ወንድምና እህት አለ?

በቃሉ፡- አንድ ወንድምና አንድ እህት ነው ያለኝ፤ የቤቱ ብቸኛው ኳስ ተጨዋችም እኔ ነኝ፤ ልጅ ሆኜ አድንቄው ያደግኩት ተጨዋች ቢኖር ደግሞ በእኔም ቦታ ላይ የሚጫወት ነበርና አሸናፊ ግርማን ነው፡፡

ሊግ፡- ከባህርማዶ ተጨዋቾች ማንን ታደንቃለህ? የማንስ ክለብ ደጋፊ ነህ?

በቃሉ፡- የአርሰናልና የባርሴሎና ደጋፊ ስሆን የማደንቀው ተጨዋች ደግሞ ሊዮኔል ሜሲን ነው፡፡

ሊግ፡- ከዋናው ስም በተጨማሪ “ባባ” ተብለህም ስትጠራ ሰማን፤ ምን ለማለት ነው?

በቃሉ፡- “ባባ” የተባልኩበት ምክንያት በአፍሪካ ዋንጫ ወቅት የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን በሚጫወትበት ሰዓት በማሊያው ላይ የእነሱ ተጨዋች የነበረውን የባባንጊዳን ስም በልጅነት አህምሮዬ አስታውስ ስለነበር ስሙን ፅፌ ነበርና ከዛ ስም በመውሰድ ነው ስሙን ሊያወጡልኝ የቻሉት፡፡

ሊግ፡- በእግር ኳስ ባለህበት ደረጃ አሁን ላይ ራስህን የት ላይ ታስቀምጠዋለህ?

በቃሉ፡- ኸረ ገና ብዙ የሚቀረኝ ተጨዋች ነኝ፤ ግን በራሴ በጣም የምተማመን ተጨዋች ስለሆንኩ ጥሩ ደረጃ ላይ እደርሳለው፡፡

ሊግ፡- በእግር ኳሱ ቀጣይ እቅድህ ምንድን ነው?

በቃሉ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለአዲሱ ክለቤ ሐዋሳ ከተማ ጥሩና ስኬታማ ነገሮችን መስራት እፈልጋለው፤ ከዛ ውጪም ጠንክሮ መስራት ዋናው ፍላጎቴ ነውና የሀገሬን ብሔራዊ ቡድን መለያ በማጥለቅ መጫወት እፈልጋለው፡፡

ሊግ፡- በጣም የተከፋክበት ወቅት መች ነው?

በቃሉ፡- ያ ጊዜ መቼም አይረሳኝም፤ የመጀመሪያው ሴት አያቴ እኔን ያሳደጉኝ ናቸውና ምንም በማልረዳቸው ሰዓት ስላለፉ ሀዘኔ ከፍ ያለ ነው፡፡ ከዛ ውጪ ያለው ሌላ ሀዘኔ ደግሞ በ2005 ላይ ለአውስኮድ  በምጫወትበት ሰዓት ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት በተደረገው ውድድር አራት ውስጥ ለመግባት ከወላይታ ዲቻ ጋር ተጫውተን 1-0 ከመራናቸው በኋላ 2-1 ተሸንፈን የወደቅንበትን ነው፡፡

ሊግ፡- አንድ ነገርን በልና እናጠቃል?

በቃሉ፡- እሺ፤ በእግር ኳሱ አሁን የምገኝበት ደረጃ እንድደርስ በመጀመሪያ የድንግል ማሪያም ልጅንና እሷን ለማመስገን እፈልጋለው፤ ሲቀጥል ቤተሰቦቼን፤ ከዛ ደግሞ ፈጣሪ ነፍሱን ይማረው አሰልጣኝ አሰፋ ጎዳናን እንደዚሁም ደግሞ በአዳማ ከተማ ውስጥ ያሰለጠነኝንና በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ውስጥ ብዙ ነገርን ይነግረኝ የነበረውን ደጉና አሰልጣኝ ዘርሐይ ሙሉን አመሰግናለው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P