Google search engine

“ወደ ቅ/ጊዮርጊስ የማመራ ይመስለኛል” ታፈሰ ሰለሞን

በ መሸሻ ወልዴ

የሐዋሳ ከነማ ቡድን ውስጥ ባለፉት
ዓመታቶች ጥሩ የውድድር ጊዜን
አሳልፏል፤ ከዛ በፊት በነበረው የኒያላና
የኤሌክትሪክ ቡድን ቆይታውም እንደ ሐዋሳ
ከነማ ሁሉ አስገራሚ የኳስ ብቃቱን
በማሳየት በስፖርት አፍቃሪው ከፍተኛ
አድናቆትን ሊያገኝም ችሏል፤ ይሄ ተጨዋች
ታፈሰ ሰለሞን ሲሆን አሁን ላይ ከክለቡ
ሐዋሳ ከነማ ጋር ያለውን የውል ጊዜ
በማጠናቀቅ በርካታ ክለቦች የእሱ ፈላጊ
ሆነዋል፤ ታፈሰ ሰለሞን ከክለብ ባሻገር
ለብሔራዊ ቡድንም ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን
የአሁኑ ቡድን ተጨዋችም ነው፤ የብሔራዊ
ቡድን የከዚህ ቀደም ቆይታው ግን ብዙም
የተረጋጋ ካለመሆኑ አንፃር አንዴ ይጠራና
ሲመለስም የታየ ነው፤ ለእዚህ ተጨዋች
ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ የተለያዩ
ጥያቄዎች አንስቶለት የሰጠው ምላሽ
የሚከተለውን ይመስላል፡፡


ሊግ፡- የእረፍት ጊዜህን በምን መልኩ
ነው የምታሳልፈው?
ታፈሰ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
ውድድርከተጠናቀቀ በኋላ አብዛኛውን
የእረፍት ጊዜዬን የማሳልፈው ከጓደኞቼ
ጋር በመጠራራት የፉትሳል ጨዋታዎችን
በማድረግ ሲሆን ከዛ ውጪም ያለውን ቀሪ
ጊዜ ደግሞ ወደ ሲኒማ ቤቶች በማምራት
የአማርኛ ፊልሞችን ነው የምከታተለው፡፡
ሊግ፡- በክረምቱ ወራት ራስህን ዘና
ለማድረግስ ከአዲስ አበባ ውጪ በመውጣት
ወደ ክልሎችስ ትሄዳለህ?
ታፈሰ፡- አልፎ አልፎ አዎን፤ በተደጋጋሚ
የሄድኩትም ወደአዳማና ወደ ባህር ዳር
ከተሞችም ነው፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ
በተጨዋችነት በማሳለፍህ ደስተኛ ነህ?
ታፈሰ፡- በጣም እንጂ፤ የእግር ኳስ
ጨዋታ የሚወደድ ስፖርት ነው፤ ከዛ
ተነስቼም ነው አብዛኛውን የተጨዋችነት
ጊዜዬን ደስተኛ ሆኜ እያሳለፍኩ ያለሁትና
ወደፊትም ከዚህበበለጠ ነው በተጨዋችነቴ
የምደሰተው፡፡
ሊግ፡- ግን እኮ ደስተኛ ያልሆንክበት ጊዜ
ነበር?
ታፈሰ፡- አዎን፤ ያን አልክድም፡፡ የኒያላ
ክለብ ከፕሪምየር ሊጉ የወረደ ጊዜ በጣም ነው
ቅር ያለኝ፤ በጣምም ነው የከፋኝ፤ በጊዜው
የክለቡ ተጨዋች በነበርኩበት ሰዓት የሐዋሳ
ከተማ ቡድንን 4ለ0 እየመራን ሳለ በዕለቱ
በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ጨዋታው
ተቋረጠ፤ በነጋታውም ግጥሚያው እንደአዲስ
በድጋሚ ሲደረግ ጊዜ እነሱ 3ለ1 አሸነፉንና
ይሄ ጨዋታችን ከሊጉ ለመውረዳችን አንዱ
ምክንያት ነበርና ይሄንን ሀዘኔን መቼም
ቢሆን የምረሳው አይደለም፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህን
ዛሬ ላይ ወደ ኋላ ቆም ብለህ ስትመለከተው
በፈለግኩት ስፍራና ደረጃ ላይ ተገኝቻለሁ
ትላለህ?
ታፈሰ፡- በፍፁም አልልም፤ በኳስ
ተጨዋችነት ህይወቴ ደስተኛ ብሆንም
የፈለግኩበት ስፍራ ላይ ግን ገና አልደረስኩም፤
ብዙ ሰዎች እንደውም አንተ ወደውጪ ሀገር
ወጥተህ መጫወት ትችላለህ ስለሚሉኝም
ወደፊት ይህንንእልሜን ለማሳካት ከፍተኛ
ጥረትን አደርጋለሁኝ፡፡
ሊግ፡- ወደ ውጪ ሀገር በመውጣት
በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ለመጫወት
ያደረግከው ጥረት አናሳ ነው ልበል?
ታፈሰ፡- አዎን፤ በተጨዋችነት ዘመኔ
ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው ወደ ሱዳን በመጓዝ
ይህንን የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ሙከራን
ያደረግኩት፤ በኋላ ላይ ግን ጥረቴ ብዙም
ሊሳካ ስላልቻለ ሁሉን ነገር ወዲያው ልተወው
ችያለሁ፡፡
ሊግ፡- ሌሎች ሙከራዎችን ለምን
አላደረግክም?
ታፈሰ፡- እኛ ሀገር በዚህ በኩል
ሙከራ ማድረግ ብዙም ስላልተለመደ
ነው፤ ከዛ ውጪም በዋናነት ይሄንን እድል
የምታገኝበትን መንገድ የሚያመቻቹልህ ብዙ
ኤጀንቶች ስለሌሉንም እኔም ከሱዳን ሙከራው
በኋላ ያደረግኩት ጥረት የለም፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብዙኋን ኳስ
ተጨዋቾችን ማን በኳስ ችሎታው
ያስደስታችኃል፤ ከማን ጋርስ መጫወት
ብትችሉ የመጀመሪያ ምርጫችሁ ይሆናል
ብለን ስንጠይቃቸው በዋናነት የአንተን
ስም ያስቀድማሉ፤ የእዚህ ጥያቄ መልሱ
በተቃራኒነት ለአንተስ ቢቀርብ የትኛው
ተጨዋች ነውየመጀመሪያ ምርጫህ
የሚሆነው?
ታፈሰ፡- በዋናነት የማስቀድመው
አስቻለው ታመነን ነው፤ እሱ ሲጫወት
በጣም ደስ ይላል፤ እልኸኛ ነው፤ ሜዳ ከገባ
ቀልድ አያውቅም፤ ሁሌም በጥንቃቄ ነው
ኳስን ታጋይ ሆኖ ጭምር የሚጫወተው፤
አስቻለውን አንድ ለአንድ አግኝተህ ማለፍ
በጣም ከባድ ነው፤ ለእኔም አስቸጋሪ የሆነብኝ
ተጨዋች እሱ ነውና ከእሱ ጋር መጫወት
በጣም ነው ደስ የሚለው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ችሎታቸውን አሁንም
ድረስ ተመልክተህ በጣም ያደነቅካቸው የባህር
ማዶ ተጨዋቾችስ እነማን ናቸው?
ታፈሰ፡- እነሱ ሊዮኔል ሜሲና ኔይማር
ናቸው፤ የሁለቱ ችሎታ ይገርማል፤ ቀልብንም
ይስባልና ሁሌም ነው የማደንቃቸው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን እየተጫወትክ
ባለህበት የአሁን ሰአት እነማን የቅርብ
ጓደኞችህ ናቸው?
ታፈሰ፡- የእኔ የቅርብ ጓደኞች አስጨናቂ
ሉቃስ፣ አስቻለው ታመነ እና ጋዲሳ መብራቴ
ሲሆኑ፤ እነዚህም ተጨዋቾች ሁለቱ በክለብ
ደረጃ አብሬያቸው የተጫወትኳቸው እና
ከአስቻለው ታመነ ጋር ደግሞ በብሄራዊ ቡድን
ደረጃ አብረን የተጫወትን እና ጥሩም ጓደኛዬ
ስለሆነ በአጠቃላይ የሶስቱንም ተጨዋቾች
ስም ነው ሁሌም የምጠራው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ
ሻምፒዮና ውድድር አንድ ቀሪ ግጥሚያውን
ሳይካሂድ በመቐለ 70 እንደርታ አሸናፊነት
ፍፃሜውን አግኝቷል፤ እንደተጨዋችነትህ
ስለአጠቃላይ ውድድሩ ምን ትላለህ?
ታፈሰ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የእዚህ
ዓመት የሻምፒዮና ውድድርን በተመለከተ
የፍፃሜው ግጥሚያ እስኪደረግ ድረስ
ሶስት ክለቦች ዋንጫውን ለማንሳት አንገት
ለአንገት የተያያዙበት ሁኔታ ከመፈጠሩ
ውጭ የሊጉ ግጥሚያዎችም ሊጠናቀቁ
በተቃረበበት ሰዓት ወደታችኛው ሊግም
ላለመውረድ ወሳኝ የሚባሉ ጨዋታዎች
የተደረጉበት መሆኑ በጥሩ እና በአጓጊ መልኩ
ብገልፀውም የውድድር ዓመቱ ግን በአብዛኛው
የተጠናቀቀው ብዙ የጎላስህተቶችን ይህም
ማለት የእግር ኳሱ ከፖለቲካ፣ ከዘርና ከጎሳ
ጋር ተገናኝቶ በርካታ የአዕምሮም ሆነ የአካል
ጉዳቶችን በማስተናገድ የተጠናቀቀ መሆኑ
የሊጉውድድሩ ለእኔ ብዙም አልተመቸኝም፤
ያ ስለሆነም ለወደፊቱ የኳስ እድገታችን እና
ለውጣችን የምናስብ ከሆነ ከወዲሁ ለዚሁ
ጉዳይ እልባት ልናስገኝለት ነው የሚገባን፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከስፖርታዊ
ጨዋነት ጋር በተያያዘ ምን ቢያደረግ ለውጥን
ማምጣት ይችላል?
ታፈሰ፡- ለእዚህ ጉዳይ በቅድሚያ
መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን
ተወዳዳሪ ክለቦች፣ የእግር ኳስ ተጨዋቾች፣
አሰልጣኞች፣ ዳኞች፣ የክለብ አመራሮች፣
የደጋፊ ማህበራት አመራሮች፣ እንደዚሁም
ደግሞ ለኢትዮጵያ ኳስ የሚያስቡ ከየስፍራው
የሚመረጡ የስፖርት አፍቃሪዎችን በሊጉ
ችግሮች ላይ በማወያየት ሁሉም እግር
ኳስና እግር ኳስን ብቻ የሚያንፀባርቁ ገንቢ
የሆኑ አስተያየቶችን በማቅረብ ስራ ቢሰራ
አገራችን የተሻለ ነገርን ማግኘት የምትችል
ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን
ለካሜሩን የቻን አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከጅቡቲ
ብሄራዊ ቡድን ጋር ተጫውቶ 4ለ3 አሸንፏል፤
ይሄ የድል ውጤትም የአገራችንን እግር ኳስ
ወደየት እያመራው ነው በሚልኳሱ በጣም
የወደቀ ያህል አስቆጥሮባችሁ በብዙዎች ዘንድ
ተቀባይነትን ሳያስገኝላችሁ ቀርቷል፤በዚህ
ዙሪያየምትለው ነገር አለ?
ታፈሰ፡- አዎን፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ
ቡድን ተጨዋች ሆኜ የጅቡቲን ብሄራዊ ቡድን
በቻን የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያ
ላይ ከአንዴም አልፌ ለ3 ጊዜያት የገጠምኩ
ቢሆንም አሁን ላይ የብሄራዊ ቡድናችን
ያሸነፈበት የድል ውጤት የእውነትም ልክ
ነው፤ የወረደም ነው፤ ያም ቢሆን ግን የእኛ
ዋናው ዓላማው ጅበቲን አሸንፈን ወደቀጣዩ
የማጣሪያ ጨዋታ ለማለፍና በኋላም ላይ
በካሜሮን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የቻን
የአፍሪካ ዋንጫ መብቃትም ስለሆነ ከጅቡቲ
ጋር ባደረግነው ጨዋታ ላይ ስላገኘነው የድል
ውጤት ሰው ብዙ ነገርን ሊያወራ ቢችልም
እኛ በእዚህ ዙሪያ ግጥሚያውን በማሸነፍ ወደ
ተከታዩ ዙር ስላለፍን ብዙ የምንጨነቅበት
ነገር አይኖርም፤ ቡድናችን ከጅቡቲ ጋር
ባደረገው ጨዋታ ከግጥሚያው የሚፈልገውን
የአሸናፊነት ውጤት ማግኘት ችሏልና አሁን
ላይ እያሰብን የምንገኘው ደግሞ ስለቀጣዩ
የሩዋንዳው ጨዋታ ብቻ ነው፡፡
ሊግ፡- የጅቡቲ ብሄራዊ ቡድንን በጠባብ
ውጤት እንዴት ግን 4ለ3 ብቻ አሸነፋችሁ?
ታፈሰ፡- የመጀመሪያው ምክንያትበአሁን
ሰዓት በኳሳቸው ላይ ተሻሽለውና ተለውጠው
መምጣታቸው ነው በጠባብ ውጤት
እንድናሸንፋቸው ያደረገን፤ ጅቡቲዎችን ከእኛ
ጋር ባደረጉት ጨዋታ ከጠበቅኳቸው በላይ
ሆነው ነው ያገኘኋቸው፤ ኳስን በከፍተኛ
ፍላጎትና እልህም ነው የሚጫወቱት፤
ለጨዋታው በአዕምሮህ በኩል በጥሩ ሁኔታም
ነው ተዘጋጅተው የመጡት፤ ከዚህ ቀደም
3 እና 4 ጎል እያስቆጠርን የምናሸንፋቸው
ቢሆንም በአሁኑ ጨዋታ ብዙ አይከብዱንም
በሚል ይሄን ውጤት ለመድገም ብንፈልግም
ከፍተኛ ትኩረትስላልሰጠናቸው፤ የድሬዳዋ
ከተማም ስቴድየም ኳስን ይዞ ለመጫወት
አስቸጋሪ ስለሆነብንም ነው ተጋጣሚያችንን
በሰፊ ግብ እንዳናሸንፍ ያደረገን፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የጅቡቲ
አቻውን በጠባብ ውጤት ማሸነፉን ተከትሎ
ለመጣው አጥጋቢ ያልሆነ ውጤት ችግሩ
ያለው እናንተ ተጨዋቾች ጋር ነው ወይንስ
አሰልጣኙ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ
ጋር?
ታፈሰ፡- የጅቡቲ አቻችንን ተፋልመን
በጠባብ ውጤት ላሸነፍንበት ጨዋታ
የአሰልጣኝ ችግር ነበረብን ብዬ አላስብም፤
ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ቡድናችን
ኳስን መሰረት አድርጎ እንዲጫወት ይፈልግ
ነበር፤ የእሱ ታክቲክ ይህ የነበረ ቢሆንም
የድሬዳዋ ሜዳ ኳስን ለማንሸራሸር ብዙም ምቹ
አልነበረምና ያን በአግባቡ ሳናሳካው ቀረን፤
ጎል የገባብንም ሜዳው እኛ ለምንፈልገው
እንቅስቃሴ አመቺም ስላልነበረ ነው፤ ከእዚያ
ውጪም የዘንድሮ ፕሪምየር ሊግ በተደጋጋሚ
ጊዜ በፖለቲካ እና በዘር ችግርም ምክንያት
ይበጠበጥ እና ይቆም ስለነበር ተጨዋቾቹም
ውድድሩ ሳይቀጥል ሲቀር በቂ የሆነ
ልምምድን የማንሰራበት ጊዜም ስላጋጠመን
በአካል ብቃቱ /ፊትነስ/ በኩልም ብዙ ነገር
የከበደንም ሁኔታ ስለነበር ከአሰልጣኙ ይልቅ
እነዚህ ነገሮች ናቸው እኛንም ያስቸግሩንና
በቀጣይ ጊዜ ጨዋታዎቻችን ይህንን
ችግሮቻችንን እያስተካካልን ከወዲሁ ከፍተኛ
ዝግጅትን እናደርጋለን፡፡
ሊግ፡- የሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን የቻን
አፍሪካ ዋንጫው ቀጣይ ተጋጣሚያችን ነው፤
ስለግጥሚያው ምን ትላለህ?
ታፈሰ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን
በቻን አፍሪካ ዋንጫ ላይ እያደረገ ያለው
የማጣሪያ ጨዋታ ዋናው ግቡ በካሜሩን
አስተናጋጅነት ለሚካሄደውውድድር ለማለፍ
ነው፤ የመጀመሪያ የማጣሪያ ግጥሚያውንም
በማሸነፍ ግብን ማሳካት ጀምሯል፤ አሁን
ደግሞ ከሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን ጋር በሚኖረው
ጨዋታ የአሁኑ የብሄራዊ ቡድን ስብስብ ጥሩ
ፍቅር እና አንድነት ስላለው ከዛ ውጪ ደግሞ
የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ኢንስትራትክተር
አብርሃም መብራቱም በግብፅ አስተናጋጅነት
የተካሄደውንየአፍሪካ ዋንጫን ውድድር
መነሻ በማድረግ እና እነ ማዳጋስካርን
የመሳሰሉ አገራትም ብዙ ሳይጠበቁ ጥሩ
ውጤት ለማምጣታቸው በዋናነት የረዳቸው
በጋራ ያላቸው አንድነትና ፍቅር መሆኑንም
ስለገለፀልንከሩዋንዳ ጋር በሚኖረን ጨዋታ
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
ከሐዋሳ ከተማ ጋር ያለህ የውል ጊዜ
ተጠናቋል፤ ቀጣይ ማረፊያ የት ይሆን?
እንደተለመደው እዛው ትቀጥላለህ? ወይንስ
ወደ አዲስ ቡድን ታመራለህ?
ታፈሰ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ከመከፈቱ
በፊትም ሆነ አሁን ላይ ከሐዋሳ ከተማ ጋር
ያለኝን የውል ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ
በርካታ ክለቦች እና የበፊት ቡድኔም ሐዋሳም
እኔን ለመውሰድ እና ለማስቀጠል ጥረቶችን
እያደረጉ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ግን
እኔ ለማንም ቡድን ፊርማዬን አላኖርኩም፤
ያም ሆኖ ግን የእኔ ቀጣዩ ቡድኔ የሚሆነው
የአዲስ አበባ ክለብ ነው፡፡
ሊግ፡- አዲስ አበባን ካነሳህ በዚህ ደረጃ
ስምህ በተለይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ጋር
በስፋት እየተያያዘ ይገኛል?
ታፈሰ፡- አሁን ላይ በዝውውሩ መስኮቱ
እኔን የሚፈልጉኝ ቡድኖች ብዙ ቢሆኑም
እስካሁን ግን ፊርማዬን ለማንም ክለብ ገና
አላኖርኩም፤ ያም ሆኖ ግን ወደ ቅ/ጊዮርጊስ
የማመራ ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን
የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታውን
ለማድረግ ከኮትዲቩዋር፣ ማዳጋስካርና
ኒጀር ጋር ተደልድሏል፤ ይሄን እንዴት
ትመለከተዋለህ…?
ታፈሰ፡- በአፍሪካ ዋንጫው ላይ
የተመደብንበት ምድብ ከባድ ነው፤ በግብፅ
አስተናጋጅነት የተካሄደውን ውድድር
እንደተመለከትነው የእኛ ምድብ ላይ
አሁን ላይ የተደለደለችው ኮትዲቭዋር
እንደቀድሞው ሁሉ ጠንካራነቷን
አሳይታለች፤ ሌላዋ የምድባችን ተወዳዳሪን
ማዳጋስካርንም ተመልክተን ነበርና
ከዚያ በመነሳት የማጣሪያ ውድድራችንን
የምናደርገው ከወዲሁ በጥሩ መልኩ
ተዘጋጅተንና ወደ አፍሪካ ዋንጫውም
ለማለፍ ስለሆነ ዝግጅታችንን ጠንክረን
እንሰራለን፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን
ከዚህ ክረምት አንስቶ እስከ መጪዎቹ
ጊዜዎች ድረስ በርካታ የአለም ዋንጫ
የቻን የአፍሪካ ዋንጫና የአፍሪካ ዋንጫ
ማጣሪያ ጨዋታዎች ስላሉት ይሄ ቡድናችን
አሁን የፈጠረውን አንድነት ይዞ ወደ ሜዳ
ስለሚገባና ስለሚጓዝ በውድድሩ ውጤታማ
ይሆናል ብዬ ነው የማሳበው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ
ተጨዋችነትህ ላይ ምን ናፍቆሃል?
ታፈሰ፡- የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ
ከተጫወትኩባቸው ክለቦች ጋር ለአንድም
ጊዜ ስላላነሳው ይሄን ዋንጫ ማግኘት
ናፍቆኛል፤ በቅርብ ጊዜያት የማገኘው
ይመስለኛል፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P