Google search engine

“ወደ አሸናፊነቱ ለመምጣት የምናገኛቸውን የግብ ዕድሎች መጠቀም ይኖርብናል” “ሽሬ ላይ ጎል ሳስቆጥር ኳሷን ማሊያዬ ስር ከትቼ ደስታዬን የገለፅኩት ታላቅ እህቴ በመውለዷ ነው” ምንተስኖት አዳነ /ቅ/ጊዮርጊስ/

ሊግ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የሊጉ
መሪ ሐዋሳ ከነማ ተጠባቂ ጨዋታ ነገ
እሁድ ይደረጋል፤ ስለ ዝግጅታችሁ እና ስለ
ጨዋታው የምትለን ነገር ካለ?
ምንተስኖት፡- የሐዋሳ ከነማን
የምንፋለምበት የ4ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታ
እነሱ በመሪነት ደረጃ ላይ ከመገኘታቸው አንፃር
ጨዋታው ጥሩ ፉክክር የሚደረግበት ነው፤
ለነገው ጨዋታም ቡድናችን ጥሩ ዝግጅቱን
አድርጓል፤ ይህንን ጨዋታም በሜዳችንና
በደጋፊዎቻችን ፊት የምናከናውነው ነው፤ ያ
ስለሆነም ነገ በሚኖረን ግጥሚያ ለጨዋታው
የምንቀርበው ያለፉት ጨዋታዎቻችንን
ክፍተቶች በመሸፈንና ከሜዳችን ውጪም
ባደረግነው ያለፈው ሳምንት ጨዋታ ላይ
ሽንፈትን ተጎናፅፈን የመጣንበት ስለነበር
ያን ውጤት ለማካካስ ስንል በጨዋታው ላይ
ጠንክረን በመቅረብ ግጥሚያውን በአሸናፊነት
ለማጠናቀቅ በሙሉ ዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡
ሊግ፡- ሐዋሳ ከነማ የነገው ተጋጣሚያችሁ
ከመሆኑ አንፃር ስለ ወቅታዊ አቋሙ ምን
የምትሉት ነገር አለ?
ምንተስኖት፡- ሐዋሳ ከነማ የሊጉን
ውድድር እየመራ ከመሆኑ አኳያ በአሁን
ሰአት በጥሩ ሞራል ላይ ነው የሚገኘው፤
ወጣቶችን ጨምሮም ጥሩ የተጨዋቾች
ስብስብም አለውና የነገው የሁለታችን ጨዋታ
ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፤ ያም ሆኖ
ግን ሁለታችን በሚኖረን የነገው ጨዋታ አሸ
ናፊነቱ በእኛ ቡድን የበላይነት ይጠናቀቃል፡፡
ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስ የሊጉ ጅማሬ
ጨዋታዎች ላይ ሁለት ሽንፈትን
አስተናግዷል፤ እንደ ቡድኑ ተጨዋችነትህ
ያገኛችሁት ውጤት ምን አይነት ስሜት ነው
የፈጠረብህ?
ምንተስኖት፡- የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ
ውስጥ እስካለህ ድረስ ክለባችንን ብዙ ጊዜ
የውጤት ማጣት አያጋጥመውም፤ ከቀድሞ
ጊዜ ጀምሮም ተደጋጋሚ ሽንፈት ቡድናችንን
ብዙ ጊዜም አያጋጥመውምና የሊጉ የጅማሬ
ጨዋታዎቻችን ላይ ሁለት ሽንፈትን
ስናስተናግድ እንደ ቡድኑ ተጨዋችነቴ በጣም
ነው የተከፋሁት፤ ደጋፊዎቻችንም ናቸው
ያሳዘኑኝ፤ ያም ሆኖ ግን የሊጉ ውድድር ገና
መጀመሩ ስለሆነ ያለፉትን ጨዋታዎቻችንን
ሽንፈቶች ወደኋላ ረስተናቸው እና
ክፍተቶቻችንንም አርመን በመምጣት
ወደለመድነውና ወደምንታወቅበት የአሸናፊነት
መንፈሳችን በፍጥነት እንመለሳለን፡፡
ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስ የተሸነፈባቸው
ጨዋታዎች በሜዳው ላይ ከባህር ዳር ከነማ
ጋር ያደረገውን እና ከሜዳው ውጪ ደግሞ
ሐዋሳ ላይ ከሲዳማ ቡና ጋር የነበረውን ነው፤
ስለሁለቱ ጨዋታዎች ሽንፈት ምን ልትለን
ትችላለህ?
ምንተስኖት፡- ቅ/ጊዮርጊስ በባህር ዳር
ከነማም በሲዳማ ቡናም ሲሸነፍ ሜዳ
ላይ በነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴም ሆነ
በተደጋጋሚ የግብ እድሎችን በመፍጠሩ
በኩል እኛ የተሻልን ነበርን፤ አጨዋወታችን
ለክፋት የሚሰጥም አልነበረም፡፡ ያም ሆኖ ግን
በግጥሚያዎቹ ላይ ውጤትን የሚቀይርልንን
ነገር ልናደርግ አለመቻላችን ይኸውም
እድሎችን እያገኘን ጎሎችን አለማስቆጠራችን
ብቻ ሊጎዳን ችሏል፡፡
ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስ ስሁል ሽሬ እንደስላሴን
በሰፊ ግብ ባሸነፈበት ጨዋታ ከድሉ ግቦች
ውስጥ አንዷን አንተ አስቆጥረሃል፤ የተከላካይ
ስፍራ ተጨዋች ሆነህም ለክለቡ ግብ
ማስቆጠሩን ቀጥለህበታልና በእዚህ ዙሪያ ምን
ትላለህ? ያን እለት ግቧን ካስቆጠርክ በኋላም
በደስታ የማሪያምን ምስል ከቁምጣህ ስር
አውጥተህና የያዝከውን ኳስም ባደረግከው
ማልያ ውስጥ ከተህ ሆድህ ላይ አሳይተህ
ነበርና ይሄን ያደረግክበት የተለየ ምክንያት
ነበር?
ምንተስኖት፡- የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ
ውስጥ የመሰለፍ እድሉን አግኝቼ መጫወት
ከጀመርኩባቸው ጊዜያቶች አንስቶ በትኛውም
ቦታ ላይ ማለትም በአማካይ ስፍራውም ሆነ
በተከላካይ ቦታው ስጫወት ተደጋጋሚ ግቦችን
አስቆጥሬያለሁ፤ በተለይ በተከላካይ ስፍራው
በርካታ ግቦችንም አስቆጥሬያለሁ፡፡ የእኔን ግብ
የማስቆጠር ብቃት አንዳንዶች ምንአልባት
ከእድለኝነት ጋር አያይዝው ሊናገሩ ይችሉ
ይሆናል እንጂ እኔ የማስቆጥራቸውን ግቦች
ግን እንደ እድል መቼም አላስባቸውም፤
ምክንያቱም አንድ ተጨዋች በመጀመሪያ
የጎል ማስቆጠር ኳሊቲ ሊኖረው ይገባዋልና፤
ለእኔ ግብ ማስቆጠር የጠቀመኝና የረዳኝ
የራሴ የሆነ ነገር አለኝ ያንን ነው መናገር
የምፈልገው፡፡ ለምሳሌ ብዙ ጊዜ ተከላካዮች
ጎልን የሚያስቆጥሩት ወይንም ደግሞ ግብ
ሊያስቆጥሩ የሚችሉበትን እድል ሊፈጥሩ
የሚችሉት የኮርና /የማህዘን/ ምትን
ተጠቅመው ነው ያኔም እኔ ኮርና ልሻማ
ስሄድ የሚኖረኝ እይታ መጀመሪያ ክሮሶቹን
የሚያሻማውን የቡድናችንን ተጨዋች
ኳሊቲ በደንብ እመለከታለሁ፤ ምን አይነት
ክሮስም ነው የሚያሻማውም ብዮ በአትኩሮት
እከታተለዋለው፤ ክሮሱ ሲደረግም ራሴን
ነፃ አድርጌ እንዴት መቆም እንዳለብኝም
ካካበትኩት ልምድ በመነሳትም ነው ጎሎችን
የማስቆጥረው እንጂ የጎል ማግባት ብቃቴ
ከሌላ ምንም ነገርና ከእድለኝነት ጋር
የሚያያዝም አይደለም፡፡
የስሁል ሽሬ ክለብን በሰፊ ግብ በረታንበት
ጨዋታም እኔ ጎሉን ካስቆጠርኩ በኋላ
የማሪያምን ምስል በመያዝ እና የያዝኩት
ኳስንም ሆዴ ላይ ባለው ማልያ ውስጥ ከትቼ
ደስታዬን ልገልፅ የቻልኩት የእኔ ትልቅ እህቴ
የሆነችው ምህረት ልጅ ወልዳና እኛ ቤት
ውስጥም ስለነበረች በአጋጣሚ የጨዋታው
ቀን ላይ ከቤት ስወጣ ዛሬ ጎል ታገባለህ፤
ቀኑም 23 ነው፤ የማልያ ቁጥርክም 23 ነው
ብላኝና በ23ኛው ቀን ላይ ደግሞ ከእዚህ
በፊትም ጎሎች ያገባሁበት ሁኔታ ስለነበር እሷ
ለእኔ ጥሩ ነገር ተመኝታልኝ ስለነበር ነው
ጎሉን ካስቆጠርኩ በኋላ የጎሉን ማስታወሻነት
ለእኔ የእግር ኳስ ህይወት ከማንም በላይ
ብዙ ነገርን ላደረገችልኝ ታላቅ እህቴ
ምስጋናዬን ለመግለፅ ስል ነው ምልክቱን ወደ
ደጋፊዎቻችን ሄጄ ያሳየሁት፡፡
ሊግ፡- ለእግር ኳስ ህይወቴ የዛሬ እዚህ
ደረጃ ላይ መድረስ ከላይ እንደገለፅከው የእህቴ
ምህረት አስተዋፅኦ ከማንም በላይ ነው
ብለሃልና፤ ስለእሷ የምትለን ነገር ካለ?
ምንተስኖት፡- የእውነት ነው ያን እለት
ጎል ካስቆጠርኩ በኋላ የእሷን መውለድ አስቤ
ደስታዬን በእዚያ መልኩ ልግለፅ እንጂ ታላቅ
እህቴ ለእኔ የኳስ ህይወት ያደረገችልኝ ነገር
ተነግሮ የማያልቅ ነው፤ ከአጠገቤ ታላቅ እህቴ
ባትኖር ኖሮ ዛሬ ላይ ኳስ ተጨዋች እሆናለው
ብዬም አላስብም ነበር፡፡ ልጅ እያለው ቤተሰቦቼ
ኳስ እንድጫወት አይፈልጉም ነበር፤ እኔም
ኳስ ተጨዋች የመሆን ፍላጎቱ አልነበረኝም፤
ሆኖም ግን በጊዜው በሰፈር ደረጃ ስጫወት
ጥሩ መንቀሳቀስ ስችል ነው እህቴ የታክሲ
ብር እየሰጠችኝ ጭምር በርታህና አይዞህም
እያለችኝ ልደግፈኝ ስለቻለች ነው ለኳስ
ተጨዋችነቱ ያበቃችኝና ያ ውለታዋም ነው
ጎሉን ካስቆጠርኩ በኋላ እሷን እንዳስብ
ያደረገኝና በእዚሁ አጋጣሚ ለታላቅ እህቴ
ከፍ ያለ ምስጋናዬን በፈጣሪ ስም ይድረሳት
እላለሁ፡፡
ሊግ፡- የቅ/ጊዮርጊስ ክለብን በሊጉ
ውድድር ዘንድሮ እንዴት እንጠብቀው….
የቡድናችሁ ክፍተት ጎኑስ ምኑ ላይ ነው?
ምንተስኖት፡- ቅ/ጊዮርጊስ ሊጉ ላይ
ባደረጋቸው በተለይ ደግሞ ሽንፈትን
ባስተናገደባቸው ጨዋታዎች እንደ ክፍተት
የተመለከትኩት ነገር ቢኖር ጎል የማስቆጠር
ችግራችንን ነው፤ ከባህር ዳር ከነማ ጋር በነበረን
ጨዋታ ብዙ የጎል እድሎችን የፈጠርነው እኛ
ሆነን ግብ ማስቆጠር አልቻልንም፡፡ ከሲዳማ
ቡና ጋር በነበረን ጨዋታም እነሱ በ35ኛው
ደቂቃ ላይ ጎል ያስቆጠሩብን እንጂ ያን ግብ
ከማስቆጠራቸው በፊት በውኑ እኛ ሁለትና
ሶስት ኳሶችን አግኝተን ስተናልና ያ ጎድቶናል፤
በሊጉ ውድድር ብዙ ጊዜ ከሜዳህ ውጪ
ስትጫወት አንድ ግብ አስቀድመህ በማስቆጠር
እድሉን መጠቀም ካልቻልክ ሁኔታዎች ሁሉ
ለአንተ ከባድ ይሆናሉና እኛንም የጎዳን
ግብ አለማስቆጠራችን ነው፤ ቅ/ጊዮርጊስ
ከዚህ ቀደም ሻምፒዮን ሊሆን ከቻለባቸው
ምክንያቶች መካከል ከሜዳው ውጪ ሲጫወት
የመጫወቻ ሜዳዎቹ ለእንቅስቃሴ አስቸጋሪ
ስለሆኑ አንድ ግብን ቀድሞ ያስቆጥርና ያንን
አስጠብቆ የመውጣት ብቃት ነበረውና ያ ነው
ሲጠቅመው የነበረው፤ የአሁን ቡድናችን
ላይ ደግሞ በየጨዋታዎቹ ውጤታማ
ለመሆን የአጨራረስ ችግራችንን ማስተካከል
ይኖርብናልና እዛ ላይ ጠንክረን እየሰራን ነው፡፡
ከዛ ውጪም አሁን ላይ በጉዳት ላይ የነበሩት
ስመጥር አጥቂዎቻችንም በመልካም ጤንነት
ላይም ስለሚገኙ ቀድሞ ወደነበርንበት
ብቃታችን እንመለሳለን፤ ብዙ ጎሎችንም
በአጭር ጊዜ ውስጥ በተጋጣሚዎቻችን ላይ
እናስቆጥራለን፤ የሊጉን ዋንጫ በማንሳትም
ዘንድሮ ባለድል እንሆናለን፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…
ምንተስኖት፡- የቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊዎች
በሜዳችንም ሆነ ከሜዳችንም ውጪ ሁሌ
ስንጫወት ከእኛ ጎን ሆነው በሚያምረው
ዜማቸው የሚያበረታቱን ናቸው፤ ዘንድሮ
እንኳን ለመጀመሪያ ጊዜ ወጥተን ከሲዳማ
ቡና ጋር ባደረግነው የሊጉ ጨዋታ
የሰጡንን ጥሩ ድባብ ያለው ድጋፍ በሚገባ
ተመልክተናልና በሊጉ ጀማሬ እነርሱን
ሙሉ ለሙሉ ባናስደስትም ከዚህ በኋላ
በሚኖሩን ጨዋታዎቻችን ጥሩ በመጫወትና
በውጤትም በማንበሽበሽ ደስተኛ እንዲሆኑም
ነው የምናደርጋቸውና ይህን ጠብቁ ነው
የምለው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: