ወልቂጤ ከተማ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የጅማሬ ጨዋታዎች ነጥብ ሊጥል ቢችልም ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ደግሞ ግጥሚያዎቹን በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉ የደረጃ ለውጥና መሻሻልን እንዲያሳይ አድርጎታል፤ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ከሊጉ ላለመውረድ የተጫወተው ይኸው ክለብ ዘንድሮስ ሊጉን በምን ውጤት ያጠናቅቃል? የእስካሁን ጉዞውስ ምን ይመስላል? የክለቡ ተጨዋቾች ሰሞኑን ልምምድ በማቆማቸውና በሌሎች ጥያቄዎች ዙሪያ የቡድኑን የአጥቂ ስፍራ ተጨዋችና ካፒቴን የሆነውን ጌታነህ ከበደን የሊግ ስፖርቱ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አናግሮት ተጨዋቹ ምላሹን ሰጥቶታል፤ ቃለ-ምልልሱም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ወልቂጤ ከተማን ከሌሎች ቡድኖች የተለየ ምርጫው አድርጎ ስለተቀላቀለበት መንገድ
“ወደ ወልቂጤ ከተማ ያመራሁት ይህ ቡድን ሌሎች ካቀረቡልኝ ጥቅም አንፃር የተሻለ የሚባለውንና እኔም የጠየቅኳቸውን ሁሉንም ነገሮች ሊያሟሉልኝ ስለቻሉ ነው፤ የእግር ኳስ ተጨዋች ስትሆን ሁሌም የተሻለ ነገርን ትፈልጋለህ፤ እኔም በዛ ደረጃ መጠቀሙን ስለፈለግኩ ቡድኑን ተቀላቅያለው”፡፡
ስለ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎ አጀማመራቸው
“የአምስቱን ሳምንታት የሊግ ጨዋታ ጅማሬያችንን እንደተመለከትኩት መጀመሪያ ላይ በቂ ዝግጅትንና የአቋም መለኪያ ጨዋታን ካለማድረጋችን አኳያ በውጤት ማምጣቱ ላይ ተቸግረን ነበር፤ አሁን ላይ ግን ጠንካራ ግጥሚያዎችንም በስኬት እየተወጣን በመምጣት ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ጥሩ መሻሻሎችና ለውጦች ይታዩብናል”፡፡
ስለ ጠንካራና ክፍተት ጎናቸው
“የእኛ ጠንካራ ጎን ጎል ካስቆጠርን በኋላ ስንከላከል በጣም ጥሩ መሆናችን ነን፤ ጥሩ ግብ ጠባቂም አለን፤ ታዳጊ ተጨዋቾቹም ከነባሮቹ ጋር ያላቸው ጥምረትም መሻሻሎች እየታዩበት ስለሆነ ይሄን ነው በቀዳሚነት የምጠቅሰው፤ ወደ ክፍተት ጎናችን ሳመራ ደግሞ ተጨዋቾቻችን አምና ላለመውረድ ከተጫወቱበት ስሜት ገና አልወጡም፤ እንዲህ ያሉ ችግሮች ቡድንን የሚጎዱ ናቸውና ይህን በፍጥነት ልንቀርፈው ይገባናል”፡፡
የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ቡድንበርካታ ተጨዋቾች ከፊርማ ክፍያ ጋር በተያያዘ ልምምድን ስለማቆማቸውና ይሄ ሁኔታም በክለቡ ውስጥ ስለሚፈጥረው ተፅህኖና ችግር
“ወልቂጤ ከተማ ተከታታይ ድሎችን እየተጎናፀፈ በመጣበትና በከፍተኛ ሞራል ላይም በሚገኝበት የአሁን ሰዓት ላይ ነባር ለሚባሉት ተጨዋቾቹ ዓምና ቃል የገባላቸውን የፊርማ ክፍያ ጋር በተያያዘ ገንዘባቸውን ሊከፍላቸው ባለመቻሉ ምክንያት ልምምድን ያቆሙበት ሁኔታ በጥሩ ሞራል ላይና የአሸናፊነት መንፈስ ላይ የሚገኘውን ቡድናችንን ክፉኛ የሚጎዳው ነው፤ አንተ እንደሰማከውም የእውነት ነው ተጨዋቾቹ ከእዚህ ክፍያ አለመከፈል ጋር ተያይዞ ልምምድን አቁመዋል፤ አሁን እየሰራን ያለነው ለቡድኑ አዲስ የፈረምነው ተጨዋቾችና ከወጣት ቡድኑ ያደጉት ጥቂት ልጆች ናቸው፤ ሌሎች አንድአንድ ልምምድን እየሰሩ ያሉ ልጆችም አሉ፤ ብዙዎቹ ግን እኛን ሊጠቅሙ የሚችሉ ነባር ተጨዋቾቻችን የአሁን ሰዓት ላይ ከእኛ ጋር የሚገኙ ባለመሆኑና ባለፈው ድሬዳዋ ከተማንም ባሸነፍንበት ጨዋታ ላይ በአሰልጣኙና በአንድ አንድ አመራሮች ልመናም የተጫወቱ በመሆኑም የክለቡ ቀጣይ ውጤት ማምጣት ላይ አደጋ የተደቀነም ይመስለኛልና ለእዚህ ጉዳይ ከወዲሁ ክለቡ ሊያስብበት ይገባል”፡፡
ከፊርማ ክፍያው አለመሰጠት ጋር በተያያዘ እንደ ቡድኑ ካፒቴንነትህ ከተጨዋቾቹ ጋር የተነጋገርክበት ሁኔታ አለ..?
“አዎን፤ ይህን ቡድን የተቀላቀልኩት ዘንድሮ ነው፤ ተጨዋቾቹ ስላልተከፈላቸው የአምና ክፍያም ለእኔ ነግረውኛል፤ ባለፈው ድል ባደረግንበት ጨዋታ ላይም ግጥሚያውን ላለማድረግ ወስነውም ነበር፤ አንተ ቡድኑ ውስጥ ስላለክና በአሰልጣኙ ጭምር ስለተለመንም ነው እሺ ብለን ልንጫወት የቻልነውም ብለውኛልና እንዲህ ያሉ ችግሮችን ከአምና አንስቶ ተሸክመው እየተጫወቱ መሆናቸውንም ሊነግሩኝ ችለዋል፤ ከእዚህ በመነሳት እንደ አንድ አዲስ የቡድኑ ተጨዋች እኔ ማለት የምፈልገው ክለባችን ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታ መልስ ሁለት ጨዋታዎችን ልክ እንደ ወላይታ ድቻ በድል የተወጣ በመሆኑና አሸናፊ ክለብንም ማበረታታት የግድ ስለሆነ ይህ ሞራላችን ሳይወርድና መፍትሄም በመፈለግ ለተጨዋቾቹ ክፍያቸው ቢፈፀምላቸው ጥሩ ነው፤ ከክፍያ ጋር በተያያዘ አምና አዳማ ከተማን አይተነዋል፤ክፍያ ባለክፈሉ በአቋም ደረጃ ደካማ ነበር፤ ዘንድሮ ደግሞ ተጠናክሮና ተሻሽሎ መጥቷል፤ ለተጨዋቾቹ ከመክፈል ጀምሮም ቡድኑን ይበልጥ የሚያጠናክሩለትን ተጨዋቾችም እስከማምጣት ደርሷል፤ ሲዳማ ቡናን አይተካል፤ ክፍያን እየፈፀመ ነው፤ ሀዲያ አሁንም ባለመክፈሉ ውጤቱን እየተመለከትን ነው፤ ዓምና ከሊጉ ላለመውረድ ለፕሌይ ኦፍ የተጫወተውና አስቀድሞ ክፍያን ካለመክፈል ጋር በተያያዘ ለከፍተኛ ወጪ ተዳርጎ የነበረው ጅማ አባጅፋር እንኳን አሁን ላይ በውድድሩ ጅማሬ ውጤት እምቢ አለው እንጂ ለተጨዋቾቹ አስፈላጊውን ክፍያ እየፈፀመ ይገኛልና የእኛም ክለብ ከኋላቸው ስራቸውን እንደዚሁም ደግሞ ቤተሰቦቻቸውን ለሚመሩት ተጨዋቾች ክፍያውን ቢፈፅምላቸው ጥሩ ነው፤ ያ የማይሆን ከሆነ እኛወደ አሸናፊነቱ ብንመጣም የተጨዋቾቻችን ከፊርማ ክፍያ ጋር የተያያዘ ልምምድ ማቆማቸው ቀጣይ ውጤታችን ላይ ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሮብኛል”፡፡
ከአርባ ምንጭ ከተማ ጋር በምታደርጉት የዛሬው ጨዋታ ምን ውጤትን ትጠብቃለህ..?
“ለእዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት በጣም ነው የሚከብደኝ፤ ምክንያቱም የቡድናችን ሁኔታ አሁን ላይ አያስተማምንም፤ ይኸውም አብዛኛዎቹ የእዚህ ቡድን ተጨዋቾች ክፍያቸው ካልተፈፀመላቸው በስተቀር በዚህ ግጥሚያ ላይ እንደማይኖሩ ስለተናገሩም ነው”፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታችሁ በጣም ያስቆጨህ ግጥሚያ የቱ ነው
“ከባህርዳር ከተማና ከአዳማ ከተማ ጋር ያደረግነው፤ ሁለቱንም ጊዜ ቀድመን አግብተንና መርተን ነበር አቻ የተለያየነው፤ የሐዋሳ ዩንቨርስቲ ሜዳ ለጨዋታ ምቹ አይደለም፤ አንድ ሁለት እንኳን አትቀባበልበትም፤ የሜዳው ጥሩ አለመሆን ጭምር ውጤቱን አስከብረን እንዳንወጣ ስላደረገን ያ ጨዋታ የሚያስቆጨን ነው”፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮ ተሳትፎ ላይ በፋሲል ከነማ ላይ የፍፁም ቅጣት ምት ስለሳተበት አጋጣሚና ተቆጭቶ እንደሆነ
“ይህ በእግር ኳሱ ዓለም የሚያጋጥም ነው፤ የብሔራዊ ቡድን ተጨዋች ሆኜም ከዚህ ቀደም በትልቅ ጨዋታ ላይ ስቻለውና ብዙም አልተቆጨሁም፤ ከቁጭት ይልቅ ወደ ራሴ በመመለስ ሌላ ግብ ስለማስቆጠር ነው የማስበው”፡፡
ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ማን እንደሚያነሳ
“አሁን ላይ ይሄ ቡድን ዋንጫ ያነሳል፤ ይሄ ቡድን ደግሞ ከሊጉ ይወርዳል የምትልበት ጊዜ ላይ አይደለም ያለነው፤ ሊጉ ገና ጅማሬ ላይ ነው፤ በደረጃው ሰንጠረዥ እታች የነበረ አንድ ቡድን ሁለት ጨዋታዎችን በተከታታይ ሲያሸንፍ ወደ ላይ የሚመጣበት ነገር አለ፤ የእኛን ቡድንም የእዚህ አይነት ውጤት አጋጥሞታል፤ ከጨዋታው ሜዳ ጋር በተያያዘም ይሄ ቡድን ያሸንፋል ብለህ ለመናገርም አስቸጋሪ የሆነ ሁኔታን እየተመለከትንም ነው የሚገኘውና አሸናፊውን ቡድን ማወቅ ከባድ ነው የሚሆነው”፡፡
ስለ ሐዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም
“ስለ ሜዳው ብዙ ተብሏል፤ ለጨዋታ ፈፅሞ አመቺ አይደለም፤ በጥሩ ሁኔታ መቀባበልም ይናፍቅሃል፤ በዛ ላይም ተጫውተህ ከወጣክ በኋላም እግርህን ትታመማለህ፤ ሐዋሳ ይህን ውድድር እያዘጋጀችና በኢንቬስትመንቱ ደረጃም በተለይ ከሆቴል አንፃር በብዙ ነገሮች እየተጠቀመች ሜዳውን ለማስተካከል ጥረት አለመደረጉ በጣም ነው የሚገርመው፤ ስለዚህም ጥሩ ጨዋታን እንድንመለከት የሊግ ካምፓኒውን ጨምሮ መስተዳደሩና ሆቴሎቹ ጭምር ተጠቃሚ ከመሆናቸው አኳያ ለሜዳው መፍትሄ ቢፈልጉለት መልካም ነው ብዬ አስባለው”፡፡
ወልቂጤ ከተማ አዲሱ ቡድንህ ከመሆኑ አኳያ ዘንድሮ ምን ግልጋሎትን ልትሰጠው አስበሃል
“ያው አጥቂ እንደ መሆኔ ከእኔ ጎል ይጠበቃል፤ ጎል ማስቆጠርም ጀምሬያለው፤ ከእዚህ በኋላ በሚኖረኝ የጨዋታ ጉዞዬ ደግሞ ሌሎች ተጨማሪ ግቦችንም በማስቆጠር ክለቤን በተሻለ ቦታ ላይ ማስቀመጥ እፈልጋለው”፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ጎልቶ የተመለከትከው ተጨዋች ካለ
“በየቱ ሜዳ ላይ ነው ተጨዋቹ ጎልቶ የሚወጣው፤ አንድ ሁለት እኮ አትቀባበልበትም፤ ስለዚህም እስካሁን አላየሁም”፡፡
ስለ ወልቂጤ ከተማ ደጋፊዎች
“ክለቡን የሚወዱ ጥሩ ደጋፊዎች ናቸው ያሉን፤ ከሲዳማ ቡና በመቀጠል፤ እንደዚሁም ደግሞ እንደ ወላይታ ድቻና አርባምንጭ ደጋፊዎችም ያህል በመሆኑ እያበረታቱን ይገኛል፤ ያም ሆኖ ግን አሁን ላይ ክለባችን ጥሩ ውጤትን እያስመዘገበ ባለበት ሰዓት ላይ ክለቡ ውስጥ ስለተፈጠረው ችግር ደጋፊው የሚያውቀው ነገር ስለሌለ ወደ ክለቡ ቀርበው በሰከነ አህምሮ በመነጋገር በቀጣይነት ለምናስመዘግበው ውጤት ያለብን ችግር እንዲፈታ ቢያደርጉ መልካም ነው”፡፡
በካሜሮን አስተናጋጅነት ስለሚካሄደው የብሔራዊ ቡድናችን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ
“ይህ ውድድር ከአንድ ወራት በኋላ የሚካሄድ ነው፤ በማጣሪያ ጨዋታዎቻችን ላይ የነበረንን አቅም እናውቀዋለን፤ ለአፍሪካ ዋንጫ ካለፍን በኋላም በዓለም ዋንጫው የማጣሪያ ግጥሚያዎቻችን ላይም በአፍሪካ አህጉር ጠንካራ ከሚባሉት ቡድኖች ጋር በመጫወት በምን ደረጃ ላይ እንደምንገኝና ይባስ ብሎም እነሱን ፈትነንም በመጫወት ጥሩ ቡድን እንዳለን ያስመለከትንበት ሁኔታ ስላለ የአፍሪካ ዋንጫውም ላይ ጠንካራ ቡድንን ይዘን እንቀርባለን የሚል ሙሉ እምነት አለኝ፤ ዋልያዎቹን በተመለከተ ከእዚህ ቀደም ለቡድኑ ስንጠራ በኮቪድ የተነሳና ኮማንድ ፖስትም ስለነበር ከየቤት ነበር የተጠራነው፤ ያኔ የቡድናችን ተጨዋቾች ላይ የሰውነት መጨመርም ይታይ ነበር፤ በዛ ሁኔታ ነው ውድድርን ጀምረን ጥሩ ቡድንን የሰራነው፤ አሁን ላይ ደግሞ ለአፍሪካ ዋንጫ የሚመጥነውን ቡድን አሰልጣኙ ከውድድር ላይ የሚመርጥም ስለሆነ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተጨዋቾች ስብስብ የተሻለ የሚባለውን ይመርጣል ብዬም ስለማስብ በዋናው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎአችን ከተደለደልንበት አዘጋጇ ሀገር ካሜሮን፣ ቡርኪናፋሶና፣ ኬፕቨርዲ ምድብ ጥሩ ውጤትን በማስመዝገብና ወደ ተከታዩም ዙር በማለፍ የከዚህ ቀደም የውጤት ታሪካችንን ለመቀየር ከፍተኛ ጥረትን እናደርጋለን”፡፡