Google search engine

“ወደ አሸናፊነት መመለሳችን ቢያስደስተንም የአምናው ቡድን መፍረሱ ግን ጎድቶናል” አስራት ቶንጆ /ኢት.ቡና/

“ወደ አሸናፊነት መመለሳችን ቢያስደስተንም የአምናው ቡድን መፍረሱ ግን ጎድቶናል”

አስራት ቶንጆ /ኢት.ቡና

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/

ኢትዮጵያ ቡናን በጥሩ ብቃታቸው ከሚያገለግሉ ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነው አስራት ቶንጆ ቡድናቸው   ደደቢትን ባስተናገደበት የተስተካካይ ጨዋታው ንታምቢ ክሪዚስቶን፣ አቡበከር ናስር እና አህመድ ረሺድ /ሺሪላ/ ባስቆጠሯቸው ሶስት ግቦች ማሸነፍ መቻላቸውና ወደ አሸናፊነት መንፈስ ስሜቱም መምጣታቸው ሊያስደስታቸው ቢችልም ያለፈው ዓመት ቡድን መፍረስ መቻሉ ዘንድሮ የሚጠብቁትን ስኬታማ ውጤት እንዳያመጡ እንዳደረጋቸው አስተያየቱን ሰጥቷል፤ የኢትዮጵያ ቡናው አስራት ቶንጆ ከጅማ ከተማ ክለብ ወደ ቡና በመምጣት አዲሱን ክለቡን ከተቀላቀለ በኋላ አበረታች እንቅስቃሴን ያሳይ የነበረ ተጨዋች ሲሆን አሁን ላይም ከጉዳቱ ከተመለሰ በኋላ ክለቡን ዳግም በስኬታማ ብቃቱ ለመጥቀም መዘጋጀቱንም ይናገራል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናውን አስራት ቶንጆ እኛም ለክለቡ ግልጋሎቱን እየሰጠ ባለበት የአሁን ሰዓት ስለ ኳስ  ሕይወቱ እና በቡና ክለብ ቆይታው ዙሪያ እንዲሁም ተያያዥ የሆነ ጥያቄን አጠር ባለ መልኩ አቅርበንለት ምላሽን ሰጥቷል፡፡  

ሊግ፡- በቅድሚያ ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ ቃለ-ምልልስን ለመስጠት ፍቃደኛ ስለሆንክ ከልብ እናመሰግናለን?

አስራት፡- እኔም እናንተን የጋዜጣችሁ እንግዳ አድርጋችሁኝ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናችኋለው፡፡

ሊግ፡- የእግር ኳስ ጨዋታ ጅማሬህ ምን ይመስላል?

አስራት፡- የእግር ኳስን መጫወት የጀመርኩት  ወደ ሰበታ መስመር በሚወስደው እና ከካራ ቆሬ ወረድ ብሎ በሚገኘው የወለቴ አካባቢ ነው፤ እዛም ነው ከልጅነት ዕድሜዬ አንስቶ በጣም የምወደውን እና የማፈቅረውን የእግር ኳስ በመጫወት የጀመርኩት፡፡

ሊግ፡-  የእግር ኳስን የተጫወትክበት የመጀመሪያ ክለብህ ማን ነው?

አስራት፡- በክለብ ደረጃ የእግር ኳስን ለመጀመሪያ ጊዜ ገብቼ የተጫወትኩበት ቡድን  የሰበታ ከተማ ተስፋ ነው፤ ለቡድኑ የተመረጥኩትም 2006 ላይ ተካሂዶ ከነበረው የመላው ኢትዮጵያ ውድድር ላይ ነው፤ ከዚሁ ቡድን ቆይታዬ በኋላም ለሰበታ ከተማ እና ለጅማ ከተማ ክለቦች በመጫወት  የኳስ ተጨዋችነት ህይወት ውስጥ ዘልቄ ለመግባት ችያለው፡፡

ሊግ፡-  የልጅነት ዕድሜህ ላይ ኳስን ስትጫወት የቤተሰቦችህ አመለካከት የቱን ያህል ነበር? ሞዴልህ ተጨዋችስ ማን ነበር?

አስራት፡-  ቤተሰቦቼ በልጅነት ዕድሜዬ ላይ በኳስ መጫወቴ ላይ የነበራቸው አመለካከት ምንም እንኳን በኑሮ ደረጃ ከደካማ ቤተሰብ የተገኘው ቢሆንም ጥሩ ነበር፤ ኳስን እንዳልጫወት አይከለክሉኝም ነበር፤ እንደውም የኳስ መጫወት ፍላጎቴን ለሟሟላት ደፋ ቀና ይሉም ነበር፤ በዚህ ረገድ በተለይ እናቴ ትልቁን ድርሻ ትወስዳለች እና የእሷ እኔን በአቅሟ መንከባከቧ ለዛሬ የእዚህ ደረጃ ላይ መድረሴ ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክታለችና በእዚሁ አጋጣሚ በጣሙን ላመሰግናት እወዳለው፡፡

የእግር ኳስን ልጅ ሆኜ ስጫወት ሞዴል የሆኑኝ የሀገር ውስጥ ተጨዋቾች ብዙ ባይኖሩም ከውጪ ግን የባርሴሎናዎቹ ዣቪ  እና ኢንዬስታ ለእኔ ምርጦቹ ተጨዋቾች ነበሩና እነሱን ነው ተምሳሌቴ ያደረግኳቸው፡፡

ሊግ፡- በቤተሰባችሁ የእግር ኳስን የምትጫወተው አንተ ብቻ ነህ?  ስንት ወንድምና እህትስ አለህ?

አስራት፡- የእግር ኳስን የምጫወተው እኔ ብቻ ነኝ፤ 5 እህቶች እና 3 ወንድሞችም ነው ያሉኝ፡፡

ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡናን  በምን መልኩ ተቀላቀልክ? ወደ ቡድኑ ስትገባስ የተሰማህ ስሜት ምን ይመስላል?

አስራት፡- ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀልኩት የ2009 ዓ/ም የውድድር ዘመን ላይ ለክለቤ ጅማ ከተማ ስጫወት ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት በተደረገው ውድድር ላይ ባሳየሁት ጥሩ ብቃት በክለቡ ልፈለግ በመቻሌ ነው፤ ወደ ቡናም ሳመራ ቡድኑ ትልቅ እና በበርካታ ደጋፊዎች የሚወደድም ስለነበር በመግባቴ በጣም ነው የተደሰትኩት፡፡

ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ ከገባህ በኋላ የነበረክን ቆይታ እንዴት ነው የምትገልፀው? ለቡድኑስ ምርጡን ብቃቴን አውጥቼ ተጫውቻለው ብለህ ታስባለህ?

አስራት፡- በኢትዮጵያ ቡና ያለኝ  የተጨዋችነት ቆይታ ገና የአጭር ጊዜያትን ያስቆጠረ ቢሆንም በክለቡ ደስተኛ ነኝ፤ በቡና ቆይታዬም ለክለቡ የአቅሜን ያህልም ግልጋሎት እያበረከትኩኝ እገኛለው፤ አሁን ባለኝ ብቃት ግን ለቡድኑ ምርጡንና እምቁን ችሎታዬን ሙሉ ለሙሉ አውጥቼ ተጫውቻለው ብዬ ስለማላስብ በቀጣዩ ጊዜ ከእኔ የሚፈለገውን ሁሉ ለማድረግ ጥረትን አደርጋለው፡፡

ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ስትጫወት ጠንከር ያለ ጉዳትን አስተናግደህ ነበር፤ ጉዳቱ ሲደርስብህ ምን ተሰማህ?

አስራት፡- በጊዜው በጣም ነበር ያዘንኩት፤  ቡናን  በችሎታዬ ጠቅሜው ውጤታማ ለማድረግ በማስብበት ሰዓት  የደረሰብኝ ከፍተኛ ጉዳትም ስለነበር ተቆጭቼም ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ፈጣሪን ይመስገነውና  አሁን ላይ ወደ መልካም ጤንነቴ ስለተመለስኩ እና ቡናንም ለመጥቀም ስለተዘጋጀው ደስ ብሎኛል፡፡

ሊግ፡- በኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ ስትጫወት በድፍረት ኳስን ወደ ተቃራኒ ቡድን ድሪብል እያደረግክ የምትገባበት አጨዋወት በብዙዎች ዘንድ ይደነቅልካል፤ ይህን አጨዋወት ከምን ተነስተህ አመጣህ?  

አስራት፡- ይሄ በስራ የተገኘ አይደለም፤ አጨዋወቱን ፈጣሪ የሰጠኝ ስጦታ ነው፤ በተፈጥሮ አዳብሬው የመጣሁት ስለሆነም ወደፊት ደግሞ ከዚህ በላይም ብቃቴን አውጥቼ እንደምጫወት እርግጠኛ ነኝ፡፡

ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎአችሁ ደደቢትን በተስተካካይ ጨዋታ ማሸነፍ ችላችኋል፤ የዘንድሮ ውጤታችሁ  ግን አሁን ላይ እንደታሰበው በውጤታማነት የታጀበ አይደለም?

አስራት፡- አዎን፤ ልክ ነው፤ ቡና ደደቢትንም ሆነ ባለፈው ጨዋታ ደግሞ ወልዋሎ አዲግራትን ማሸነፍ ይቻል እንጂ በአሁን ሰዓት ላይ የሚገኝበት ሁኔታ እና ያለበት ደረጃ ቡድኑ በሚጠብቀው መልኩ አይደለም፤ ቡና በሊጉ ጅማሬው ጥሩ ሄዶ ነው አሁን ላይ ውጤትን ያጣው ይሄ የውጤት ማጣትም ሁላችንንም አስቆጭቶናል፤ ይሄ ስለሆነም አሁን ወደ አሸናፊነት መንፈሱ የተመለስንበትን አጋጣሚዎች እስከመጨረሻው ጨዋታዎቻችን ድረስ በማስቀጠል ውድድሩን በጥሩ ውጤት ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረትን እናደርጋለን፡፡

ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን በውጤት ማጣቱ ላይ ያጋጠመው ዋንኛው  ችግሩ  ምንድን ነው?

አስራት፡- በመጀመሪያ ደረጃ ዘንድሮ ቡናን ውጤት አሳጥቶታል ብዬ የማስበው የዓምናው ቡድን በመበተኑ ነው፤ የዓምናው ቡድን ባይበተን እና ቢቆይ ኖሮ አሁን ላይ እያጣን ለነበረው ውጤት የሚጠቅመን ነገር ይኖር ነበር፤ የዚህ ዓመት ላይ ሌላው የጎዳን የተጨዋቾች ጉዳት እና የቡድናችን ተጨዋቾችም በወጣቶች ከመገንባቱ አኳያ የልምድ ማነስም ስላለባቸው ይሄ የጎዳን ሆኗል፡፡

ሊግ፡- የፋሲል ከነማ ጋር ሰኞ ትጫወታላችሁ፤ ምን ውጤትን ታስመዘግባላችሁ?

አስራት፡- ኢትዮጵያ ቡና አሁን ወደ አሸናፊነቱ ተመልሷል፤ ወደ አሸናፊነቱ የተመለሰውም  የልምምድ ሰዓት ላይ ሁላችንም ባለፉት የክለቦቻችን ግጥሚያዎች ላይ ባሉብን ክፍተቶች ላይ በደንብ ተነጋግረንበት ስለሰራን እና የሊጉንም ውድድር በጥሩ ውጤት ለማጠናቀቅም ስለምንፈልግ ከፋሲል ከነማ ጋር የምናደርገውን የሰኞም ጨዋታ ሆነ ሌሎቹን ቀሪ ግጥሚያዎቹን ለማሸነፍ በሚገባ ተዘጋጅተናል፡፡

ሊግ፡- በመጨረሻ….

አስራት፡- የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች የሚሰጡን ድጋፍ ሁሌም ድንቅ ነው፤ እነሱን በቃላት መግለፅም ከባድ ነው፤ በዚህ ሊመሰገኑ ይገባል፤ ከዛ ውጪ ማለት የምፈልገው በኳሱ አሁን ለደረስኩበት ደረጃ የረዱኝን ቤተሰቦቼን ከሰፈር አንስቶ ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞቼን እንደዚሁም ደግሞ የሰበታ ከነማ ክለብን እና ኢትዮጵያ ቡናን ማመስገን እፈልጋለው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P