በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮ የክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት በኢትዮጵያ ቡና በጥብቅ ቢፈለግም የተጨዋቹ የመጨረሻ ማረፊያ ግን ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን ተከትሎ ባህርዳር ከተማ ሆኗል፤ የእግር ኳስን ለአዳማ ከተማ ለአራት ዓመታት እንደዚሁም ለሰበታ ከተማ ለአንድ ዓመት በመሀል ሜዳው ላይ በመጫወት ጥሩ ብቃቱን በሜዳ ላይ እያሳየ የሚገኘው ፉአድ ፈረጃ በሰበታ ከተማ ውስጥ የነበረውን የውል ጊዜ ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ባህርዳር ከተማ ስላደረገው ዝውውር እንደዚሁም ደግሞ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ስለነበረው የቡድናቸውና የራሱ ቆይታን በማካተት የሊግ ስፖርት ጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ የተለያዩ ጥያቄዎችን ለተጨዋቹ አቅርቦለት የሚከተሉትን ምላሽ ሰጥቶታል፤ መልካም ንባብ፡፡
ሊግ፡- የሰበታ ከተማ የውል ጊዜህን እንዳጠናቀቅ በመጨረሻም ወደ ባህርዳር ከተማ አመራህ?
ፉአድ፡- እውነት ነው፤ ለሰበታ ከተማ ለመጫወት ተስማምቼ የነበረው ለአንድ ዓመት ለሚደርስ የውል ጊዜ ነበር፤ ከክለቡም ጋር የኮንትራት ጊዜዬን እንዳጠናቀቅኩኝ በርካታ ክለቦች እኔን የቡድናቸው ተጨዋች ለማድረግ ይፈልጉ ነበር፤ ከእነዛም መካከል ኢትዮጵያ ቡና አንዱ ነበርና በተደጋጋሚ ጊዜ እኔን ለመውሰድ ጊዜ ፈጅተው ከእነሱ ጋር ልንነጋገርም ችለናል፤ በዝውውር መስኮቱ ልንስማማ ከጫፍ ብንደርስም በስተመጨረሻ ግን ባህርዳር ከተማዎች ለእኔ የተሻለ የሚባል ክፍያን ሊያቀርቡልኝ ስለቻሉ የመጨረሻ ምርጫዬ እነሱ ጋር ሊሆን ችሏል፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ቆይታህ በሰበታ ከተማ ያሳለፍከው የውድድር ጊዜ ምርጥ የሚባል ነበር?
ፉአድ፡- አዎን፤ ቆይታዬ ሁለት አይነት መልክ ያለው ቢሆንም በአብዛኛው ግን ጥሩ የሚባል ነው፤ የመጀመሪያው ከውድድሩ ጅማሬ አንስቶ በብዙ ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ስንቀሳቀስ ነበር፤ ለክለቤም በሚቻለኝ አቅም ስኬታማ ግልጋሎትንም ሰጥቻለው፤ በመሀል ላይ ግን የዓላ ፈቃድ ሆኖ የደረሰብኝ ጉዳት በምፈልገውና ባሰብኩት መልኩ ብዙ ርቀት እንዳልጓዝ ቢያደርገኝም እንደ አጠቃላይ ሲታይ የወደድኩት ቆይታ ነበረኝ፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎህ በብዙዎች እይታ ውስጥ ገብተህ ነበር፤ ይህን ታውቃለህ?
ፉአድ፡- አዎን፤ ለእዚህ ልበቃ የቻልኩበት ዋናው ምክንያትም የውድድሩ ፎርማት ከዚህ ቀደም ከነበረው አይነት አዲስ በመሆኑና ጨዋታዎቹም በዲ.ኤስ.ቲቪ የቀጥታ ስርጭትን ያገኙ በመሆናቸው ነው ኳሱ ራስህን ለማሳየት ጥሩ አጋጣሚን ስለፈጠረልኝ በዛ ነው በሜዳ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየቴን ተከትሎ በኳሱ ተመልካች እይታ ውስጥ ልገባ የቻልኩት፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሰበታ ከተማ ያስመዘገበውን ውጤት በምን መልኩ ነው የምትገልፀው?
ፉአድ፡- በውድድር ዘመኑ ቡድናችን አዲስ አጨዋወትን ከመከተሉና በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥም ሆኖ ለመግባባት እኛ ተጨዋቾች ላይ የተወሰነ ጊዜን ከመውሰዱ አንፃር ያስመዘገብነውን የአምስተኛ ደረጃን እንደ ውጤት ሳየው በጣም ትልቅና ከጠበቅነው በላይም ነው፡፡
ሊግ፡- በአዳማ ከተማ ነው የኳስ ህይወትህ የተጀመረው፤ ያ ቆይታህ እንዴት ይገለፃል?
ፉአድ፡- በጣም ምርጥ ቆይታህ ነው የነበረኝ፤ በኳስ ህይወቴ ደስተኛ እንድሆንም ያደረገኝ ከዛን ጊዜ አንስቶ የመጣሁበት የእስካሁን መንገድም ነው፤ አዳማ ለእኔ የእግር ኳስ ህይወት እዚህ ደረጃ ላይ መገኘት ትልቁን አስተዋፅኦ ያደረገልኝና የምወደው ክለቤ ነው፤ ከታዳጊ ቡድኑ አንስቶም ነው እስከዋናው ቡድን ደረጃም የተጫወትኩት፤ ከዛ ባሻገርም የዚሁ ቡድን ተጨዋች ሆኜ ሀገርን በሚወክል ደረጃም የተመረጥኩባቸው አጋጣሚዎች ስላሉም እነዚህ የማይረሱኝ ናቸው፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ የተቆጨህበት አጋጣሚ አለ?
ፉአድ፡- በፍፁም፤ እንዲህ ያሉ ነገሮች አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት አሁን የመጣህበት መንገድ ፈጥኗል? ወይንስ ዘግይቷል?
ፉአድ፡- ፈጥኗልም፤ አልፈጠነምም ማለት ይቻላል፤ ከወጣትነት እድሜዬ አንፃር በአጭር የውድድር ዓመታቶች እስከ ብሔራዊ ቡድን ደረጃ ልመረጥና በተስፋ ቡድን ደረጃም ሀገሬን ወክዬ ለመጫወት በመቻሌ ይሄ እድገቴን ያፋጠነው ይመስለኛል፤ በሌላ በኩል ሳየው ደግሞ የአዳማ ከተማ ወጣት ቡድን ተጨዋች በነበርኩበት ሰዓት ወደ ዋናው ቡድን ማደጉ ላይ ጫና ስለነበረብኝ እንደ ሌሎቹ አብሬያቸው እንደተጫወትኳቸው ተጨዋቾች ቶሎ በማደግ አሁን ካለሁበት ስፍራ ከፍ ባለ ደረጃ ላይም መገኘትን እችልም ነበርና ሁለቱንም በዚህ መልኩ ነው የምገልፃቸው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን መጫወትን በጀመርክባቸው ጊዜያቶች በቤተሰብ ዘንድ ተፅህኖ ነበረብህ?
ፉአድ፡- በአባቴ በኩል ኳስ እንድጫወት ፈቃደኝነት ነበር፤ እሱ እንደውም የአዳማ ከተማን ጨዋታዎች ሜዳ እየወሰደ ያሳየኝና በአንድ አንድ ነገሮች ይረዳኝም ነበር፤ በወላጅ እናቴ በኩል ደግሞ ነገሮች ሁሉ ዝግ ነበሩ፤ እሷ በፍፁም ኳስን እንድጫወት አትፈልግም፤ በትምህርቴ ላይ ብቻ እንዳተኩር በመፈለግም ነው ጫና ታደርግብኝም የነበረችው፤ ይባስ ብላም እግር ኳስ በሚገኝበት ስፍራም ላይ እንዳልደርስም ለአክስቴ በአደራ መልኩ ሰጥታኝ እዛ እንድኖርም ያደረገችበት አጋጣሚም ነበር፤ ያም ሆኖ ግን በኋላ ላይ የእኔ የኳስ ፍቅር ከፍተኛ መሆኑን ስታውቅና ነገሮችንም ወደመረዳቱ ስትመጣ በእኔ የኳስ ፍቅር ተሸንፋና ተቆጭታም ኳሱን እንድጫወት ፈቀደችልኝና ከዛም በኋላ ነው ሁለቱም ወላጆቼ እኔን እየረዱኝ በመምጣታቸው በኳሱ ለዛሬው ደረጃ ልበቃ የቻልኩት፡፡
ሊግ፡- ከእናንተ ቤተሰብ ውስጥ ሌላ እግር ኳስ ተጨዋች አለ?
ፉአድ፡- አዎን፤ አራት ወንድሞችና ሁለት እህቶች ቢኖሩኝም ከእነዛ ውስጥ አንዱ ወንድሜ ነው በዚህ ሰዓት ከእኔ ውጪ እግር ኳስን በፕሮጀክት ደረጃ እየተጫወተ የሚገኘው፤ ይህ ወንድሜ ገና የ15 ዓመት ልጅ ሲሆን የአዳማ ከተማ ታዳጊ ቡድንን ይቀላቀላል ተብሎ እየተጠበቀም ነው፤ እስማሄል ፈረጃ ይባላል፤ የዚህን ታዳጊ ተጨዋች ችሎታ በተመለከተም ብዙዎች ከወዲሁ ከአንተ በላይም ነው ይሉኛልና በርታ ነው የምለው፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት የአንተ ራዕይና ግብህ የት ድረስ ነው?
ፉአድ፡- የትኛውንም ተጨዋች በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ብትጠይቀው መጀመሪያ ለብሔራዊ ቡድን ስለመመረጥና ስለመጫወት ይነግርሃል፤ እኔም ይህንን እድል ለማግኘት ተቃርቤም ተሳክቶልኛልና የመጀመሪያው ራዕዬ ይሄ ነው፤ ምክንያቱም በአዳማ ከተማ ክለብ በነበርኩበት ሰዓት መጀመሪያ ለኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን የመመረጥ እድሉን በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ስር አግኝቼ ጨዋታው ቢቀርም ለአዳማ ከተማ ወደ ዋናው ቡድን ባደግኩኝ በሁለት ዓመት ውስጥ ሌሎች ውድድሮች ነበሩና በድጋሚ ለእዚሁ ቡድን ተመርጬ ከጅብቲ ጋር የነበረንን ጨዋታ በፓስፖርት ችግር ምክንያት ባልጫወትም ከሩዋንዳ ጋር የነበረንን ግጥሚያ ተቀይሬ በመግባትና ከኡጋንዳ ጋርም የነበረንን የአቋም መለኪያ ጨዋታም ተቀይሬ በመግባት የተጫወትኩባቸው አጋጣሚዎች አሉና እነዚህ ሁኔታዎች የማይረሱኝ ናቸው፤ ከዛ ሌላም ወደ አፍሪካ ዋንጫው ባለፈው ቡድን ውስጥም ነገሮች በፈለግኳቸው መንገዶች ባይሄዱልኝም ከማዳጋስካርና ከኮትዲቯር ጋር በነበረን ጨዋታ ላይ የቡድኑ አባል ነበርኩና በዛ ውስጥ በማለፌ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ የእግር ኳስ ተጨዋች ስትሆን ከሀገር በዘለለም ግብህ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃ እስከመጫወትም ሊሆን ይገባልና ቀጣዩ እቅዴም በድጋሚ የዋልያዎቹን ስብስብ ከመቀላቀል ባሻገር ወደ ውጪ ሀገር ሄዶ መጫወትም ነውና ከዓላህ እርዳታ ጋር ያን ለማሳካት ጥረትን አደርጋለው፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኑ ተምሳሌት /ሞዴሉ/ ስለሆኑት ተጨዋቾች?
ፉአድ፡- በዚህ ረገድ የምጠቅሳቸው ተጨዋቾች ሶስት ናቸው፤ አዲስ ህንፃ አዳማ ከተማ በነበረበት ሰዓት በኳሱ ላይ ለውጥ እንዳመጣ ለእኔ ብዙ ነገሮችን ያደርግልኝ ነበር፤ ከእሱ ሌላ ደግሞ የሰበታ ከተማ ክለብን ዘንድሮ ስቀላቀል ከመስዑድ መሐመድና ከዳዊት እስጢፋኖስ ጋር በመጫወቴ በጣም ደስ ያለኝ ከመሆኑ ባሻገር ሁለቱ ተጨዋቾች በኳሱ ጥሩ አቅም እንዳለኝ እየነገሩኝ ሲመክሩኝም ነበርና ለሁለቱ ያለኝ አድናቆት ከፍተኛ ነው፤ እነዚህ ሁለት ተጨዋቾች ለእኔ ትምህርት ቤቶቼም ናቸውና የማይረሳ ጊዜንም ነው ያሳለፍነው፡፡
ሊግ፡- ጥያቄዎቼን ጨረስኩ በምን እናጠቃል?
ፉአድ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት እስካሁን ለመጣሁበት መንገድ ከፈጠረኝ ዓላ በመቀጠል ቤተሰቦቼ እንደዚሁም ደግሞ በአዳማ ከተማ እያለው ያለኝን ጥሩ አቅም ተመልክቶ ወደ ዋናው ቡድን እንዳድግ ያደረገኝን አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ ከእሱ ውጪም ረዳቱን አስቻለው ሀ/ሚካሄልንና በታዳጊ እድሜዬ ያሰለጠነኝን ዳዊት ታደለን፤ በመጨረሻም ለብሔራዊ ቡድን ከዚህ ቀደም አቅሜን አይቶ የመረጠኝን ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱንና በእኔ ስር ያለፉትን ባለሙያተኞችና ጓደኞቼን ከልብ ለማመስገን እፈልጋለው፡፡