Google search engine

“ወደ ኢትዮጵያ ቡና መጥቶ መጫወት የማይፈልግ ተጨዋች ማንም የለም” ፈቱዲን ጀማል /ኢትዮጵያ ቡና/

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/

ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት ፊርማውን ያኖረው ፈቱዲን ጀማል በዘንድሮ የውድድር ዘመን የአዲሱ ክለቡ ቆይታ የተሳካ የኳስ ጊዜን እንደሚያሳልፍ ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
ከሐዋሳ ከተማ 180 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ክብረ መንግስት ከተማ ውስጥ የተወለደው ይኸው ተጨዋች ወደ ቡና ለመጫወት በመምጣቱም ደስተኛ መሆኑን ይናገራል፤ ከዚህ ተጨዋች ጋር በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ቆይታ አድርገን ምላሹን ሰጥቶናል፤ እንደሚከተለውም ይቀርባል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን በዝውውር መስኮቱ ተቀላቅለሃል፤ የፕሪ-ሲዝን ልምምድህንም እየሰራህ ይገኛል፤ ያለው ስሜት ምን ይመስላል?
ፈቱዲን፡- ወደ ኢትዮጵያ ቡና መጥቶ መጫወት የማይፈልግ ተጨዋች ማንም የለም፤ ስለዚህም ክለቡ እኔን ለቡድኑ አጨዋወት ትሆናለህ፤ ትመጥናለህም ብሎ ጥሪ ሲያደርግልኝ ዓይኔን ሳላሽ ነበር ቡድኑን የተቀላቀልኩት፤ በእዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ኢትዮጵያ ቡና ለመምጣቴም የተለያዩ ምክንያቶች አሉኝ፤ የመጀመሪያው ቡድኑ የሀገሪቱ ትልቅ ክለብ ስለሆነና በበርካታዎችም ዘንድ የሚደገፍ ስለሆነ ሌላው ከዚህ ቡድን ጋር ዋንጫ ማግኘት ስለምፈልግ ቀጥሎ ደግሞ የእኔ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በአብዛኛው ማለት ይቻላል ኳስ ይዤ የምጫወት ተጨዋች ስለሆንኩ ቡድኑ ከሚከተለው አጨዋወትም ሆነ አዲሱ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ቡና ውስጥ ለሚያራምደው የአጨዋወት ፍልስፍና ትሆናለህ የሚልም የአድናቆት ንግግሮች ከቅርብም ሆነ ብዙም ከማያውቁኝ ሰዎችም ይደርሱኝ ስለነበር ክለቡን ምርጫዬ አድርጌዋለሁ፤ የፕሪ ሲዝን ልምምዴንም አሁን ላይ በጥሩ መልኩም እየሰራው ነው የምገኘው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡና የፕሪ- ሲዝን ልምምድ ምን ይመስላል?
ፈቱዲን፡- ኢትዮጵያ ቡና በአዲሱ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በመመራት በቀን ሁለት ጊዜ እየሰራ የሚገኘው ልምምድ በጣም ጥሩ እና ደስ ብሎክም የምትሰራው ነው፤ የልምምድ አሰጣጡም ከኳስ ጋር የተያያዘና ከዚህ በፊትም ከሰራዋቸው ልምምዶች ሁሉ በጣምም የሚለይ ነው፤ እንዲህ ያለ ልምምድንም ሰርቼ አላውቅም፡፡
ሊግ፡- ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በውድድር ዓመቱ ጥሩ ጊዜን የምታሳልፍ ይመስልሃል?
ፈቱዲን፡- አዎን፤ ምክንያቱም ቡድኑ ሊከተል ያሰበውን የጨዋታ እንቅስቃሴ ወደማወቁ እየመጣሁ ስለሆነና ከዚህ በኋላ የሚኖሩትንም ልምምዶች ጠንቅቄ ለማወቅ ራሴን በሚገባ ስለማዘጋጀው፤ በእዚህ ላይ ደግሞ ወደ ቡና የመጣሁበትም አንዱ ምክንያት ከዚህ ታላቅ ክለብ ጋር ድልን መቀዳጀትም ስለምፈልግ ጥሩ ጊዜን የማሳልፍ ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን እየተላመድክ ነው?
ፈቱዲን፡- በሚገባ፤ ምክንያቱም ሊጉ ላይ ከዚህ ቀደም ተቃራኒ ሆነን ስንጫወት የማውቃቸው ተጨዋቾች አሉና ያም በመሆኑ ብዙም እየተቸገርኩ አይደለሁም፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ቡና የውድድር ዓመት ቆይታችሁ ምን ውጤትን ለማምጣት ዕቅድን ይዛችኋል?
ፈቱዲን፡- የኢትዮጵያ ቡና የእዚህ ዓመት ዕቅዱ የክለቡ የተጨዋቾች ስብስብ በአብዛኛው በአዲስ መልክ ስለተዋቀረና አዲስም የጨዋታ ፍልስፍናን ሊከተል ስለተዘጋጀ መጀመሪያ የሚጫወተው ጥሩ ተፎካካሪ ለመሆን ነው፤ በእዚህ ውስጥ ሆነንም እስከመጨረሻው ጨዋታም ድረስ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫም ለማንሳት ከፍተኛ ትግል እናደርጋለን፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን ተቃራኒ ሆነህ ከዚህ በፊት ስትገጥም ምን አይነት ስሜት ነበረህ?
ፈቱዲን፡- ከእነሱ ጋር ሁሌም ስንጫወት በጣም ነበር ደስ የሚለኝ፤ አስበው እስኪ መጀመሪያ ልክ ወደሜዳ ስትገባ አስገራሚ ደጋፊዎች ስላላቸው ስታዲየሙን ልዩ ድባብ ነው የሚያላብሱት ከዛ ውጪም ደግሞ በኳሱ ፍሰት ላይ ያላቸው አጨዋወት ሳቢ ስለሆነ ደስተኛ ሆነህ ነው ግጥሚያውን የምታደርገውና ለእዚህም ነው ማንም ተጨዋች ወደ ቡና በመምጣት ሊጫወት የሚፈልገው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በክለብ ደረጃ ለማን ለማን ቡድኖች ተጫውተህ አሳለፍክ? በኳሱ ህይወትህስ ደስተኛ ነህ?
ፈቱዲን፡- አዎን፤ በኳስ ባሳለፍኩት የእስካሁን ህይወቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ የእግር ኳስንም የተጫወትኩባቸው ክለቦች በከፍተኛ ሊግ ደረጃ ለክብረ መንግስት ከተማ /ለአዶላ አዩ/ እና ለሀላባ ከተማ ሲሆን ከዛ ውጪ ደግሞ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ለወላይታ ድቻ እና ለሲዳማ ቡና ተጫውቻለሁ፡፡
ሊግ፡- በኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ የተከፋህበት አጋጣሚስ መች ነው?
ፈቱዲን፡- ዓምና ነዋ! ሲዳማ ቡና የሊጉን ዋንጫ ያጣው በአንድ ነጥብ ተበልጦ ነው፤ ያ ጊዜ በጣም አስከፍቶኛል፤ በተለይ ከሜዳ ውጪ ነጥብ ይዞ መውጣት አስቸጋሪና ከባድ እንደሆነ ባውቅም በሜዳችን ግን ከባህርዳር ከተማና ከጅማ አባጅፋር ጋር ያደረግናቸውን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ማጠናቀቃችን ነው የጎዳን፤ ከሁለት አንዱን ግጥሚያ ብናሸንፍ ኖሮ ድሉ የእኛ ይሆንም ነበር፡፡
ሊግ፡- ወደ እግር ኳስ ተጨዋችነቱ የመጣኸው አስበህበት ነው?
ፈቱዲን፡- አይደለም፤ ድንገት ነው ሁሉም ነገር የሆነው፤ መጀመሪያ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጨዋቾች ልጅ ሆኜ ነው ኳሱን መጫወት የጀመርኩት፤ በሰፈር ደረጃ ቀጥሎ ደግሞ በትምህርት ቤት ውድድሮች ላይ ተሳተፍኩ በእዚሁም ነው ኳሱን መጫወት ጀምሬ ለዛሬ ደረጃ የበቃሁት፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ተጨዋች ባትሆን ኖሮ በምን ሙያ ላይ እናገኝህ ነበር?
ፈቱዲን፡- በንግድ ሙያ ላይ እሰማራ ነበር፡፡
ሊግ፡- ከቤተሰባችሁ ውስጥ የእግር ኳሱን የምትጫወተው አንተ ብቻ ነህ? ስንት ወንድምና እህት አለ?
ፈቱዲን፡- አዎን፤ ኳስ ተጨዋች ብቻ ሳይሆን ብቸኛውም ስፖርተኛ ነኝ፤ አራት እህቶች ሲኖሩኝ ሁለት ወንድሞችም አሉኝ፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን መጫወት ስትጀምር ማንን አድንቀህ አደግህ? ከውጪ ክለቦችስ የማን ደጋፊ ነህ?
ፈቱዲን፡- ብዙ ተጨዋቾች የሚያደንቁትን ሳላህዲን ሰይድን ነዋ! እሱ ልዩ ተጨዋችም ነው፤ ከውጪዎቹ ደግሞ የሊዮኔል ሜሲ አድናቂ ሆኜ ነው ያደግኩት፤ ከባህር ማዶ ክለቦች የምደግፈው ቡድን ማንቸስተር ሲቲንና ባርሴሎናን ነው፤ የፔፕ ጋርዲዮላ አጨዋወት አድናቂ ስለሆንኩ ሁለቱን ቡድኖች በጣሙን ወድጄያቸዋለሁ፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን መጫወት ስትጀምር እንደ አሁኑ የመሀል ተከላካይ ሆነህ ነው?
ፈቱዲን፡- አይደለም፤ መጀመሪያ የመስመር አማካይ ተጨዋች ነበርኩ፤ በኋላ ላይ ነው በአንድ ወቅት አሁን በምጫወትበት ቦታ ላይ ተጨዋች ሲጎዳ በስፍራው ገብቼ ጥሩ ስለተጫወትኩ በዚህ ቦታ ላይ የፀናሁት፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳሱን መጫወት ስትጀምር የቤተሰብ ተፅህኖ ነበረብህ?
ፈቱዲን፡- በእናቴ ወ/ሮ አለሜ አምደግቦ በኩል አዎን ኳስ ከምጫወት ይልቅ እንድማር ነበር የምትፈልገው፤ አባቴ ጀማል ዓሊ ግን በፈለገው መልኩ ይሂድ ይል ስለነበር በዚህ ነው በኳሱ ላይ አዘንብዬ ኳስ ተጨዋች ልሆን የቻልኩት፡፡
ሊግ፡- ቤተሰቦችህን በምን መልኩ ነው የምትገልፃቸው?
ፈቱዲን፡- ምን ጥርጥር አለው፤ ሁሉ ነገሬ ናቸው፤ በጣም እወዳቸዋለሁ፤ አከብራቸዋለሁ፤ እንደዚሁም ደግሞ ላደረጉልኝ ነገር ሁሉ አመሰግናቸዋለሁ፡፡
ሊግ፡- የወደፊት ምኞትህና እልምህ ምንድን ነው?
ፈቱዲን፡- አላምዱሊላሂ፤ የእኔ ህልም በጣም ጥሩ እና በተግባርም ላይ ለማዋል ከፍተኛ ጥረትን የማደርግ ነኝ፤ ከዚህ ዓመት ጀምሮም የፕሮፌሽናል ተጨዋች የመሆን እቅዱ ስላለኝ ለዛ ወደ ውጪ ሀገር ሄጄ ከሁለት ክለቦች ጋር ሙከራን የማደርግበት ሁኔታ እኔን ሊረዱኝ በሚፈልጉ ሰዎች አማካኝነት እየተመቻቸልኝ ነው፤ ይህ እንዲሳካልኝም ፈጣሪዬን እለምነዋለሁ፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
ፈቱዲን፡- የእግር ኳስ ተጨዋችነት ህይወቴን ከስር ጀምሮ ጠንክሬ በመስራት እዚህ ደረጃ ላይ እንዳደርስ ያደረጉኝ አካላቶች ብዙ አሉ፤ በጥቂቱ ከምጠቅሳቸው ውስጥ አንተ ጥሩ ችሎታ አለህ፤ ትልቅ ደረጃ ላይም ትደርሳለህ ብሎኝ በእኔ ላይ ከፍተኛ መነሳሳትን በመፍጠር ክብረ መንግስት ውስጥ ኳስን እንድጫወት ያደረገኝ ናትናኤል ጋረደው እንደዚሁም ደግሞ ቤተሰቦቼን በተለይ ደግሞ አባቴንና በእኔ ውስጥ ያለፉትን ሁሉ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P