Google search engine

“ወደ ዋንጫው ፉክክር ስለመግባት እያለምን ነው” ፍሬዘር ካሳ /ሀዲያ ሆሳዕና/

 

ሀዲያ ሆሳዕና ኢትዮጵያ ቡናን ድል ባደረገበት ጨዋታ የተከላካይ ስፍራው ተጨዋች ፍሬዘር ካሳ የአሸናፊነቷን ግብ አስቆጥሯል፤ ቡድኑ ያገኘው ውጤትም የደረጃ መሻሻሎችን አስገኝቶለት ከነበረበት ስፍራ ወደ 3ኛ እንዲያመራም አድርጎታል፡፡

ሀዲያ ሆሳዕና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ ውድድር ጅማሬው የአማረለት ባይሆንም አሁን አሁን ላይ ግን ተከታታይ ድሎችን ሊያስመዘግብ መቻሉ ወደ ዋንጫው ፉክክር ውስጥ ስለመግባት እንዲያልምም እንዳደረገው ፍሬዘር ካሳ ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል፡፡

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎአቸው እና ከራሱ ወቅታዊ አቋም  ጋር በተያያዘ ከፍሬዘር ካሳ ጋር ያደረግነው አጠር ያለ ቆይታም የሚከተለውን ይመስላል፡፡

በተከታታይ ጨዋታዎች ድል ስለማስመዝገባቸው

“የሊግ ውድድሩ ሲጀመር የእኛ ቡድን ከተጨዋቾች ክፍያ ጋር በተያያዘ ውጤታችን ጥሩ አልነበረም፤ ያ መሆን መቻሉ ደግሞ እኛን በጣም ያስቆጨን ነበር፤ አሁን ላይ ግን ያሉብን ችግሮች እየተስተካከሉ ሊመጡ ስለቻሉ፤ በቀጣይነትም ችግሮቹ ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀረፉ ተነግሮን ልምምዳችንን በጥንካሬ ስለሰራንና  የአሰልጣኛችንንም ታክቲክ በሚገባ ለመተግበር ስለቻልን ወደ ውጤታማነቱ ልንመጣ ችለናል፤ እያስመዘገብነው ያለው ተከታታዩ ድልም እኛን ስላስደሰተን ከወዲሁ ወደ ዋንጫው ፉክክር ውስጥ ስለመግባትም እንድናልምም አድርጎናል”፡፡

በዘጠነኛ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን ድል ስላደረጉበት ጨዋታ

“የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ትልቅ ቡድን ከሆነው ኢትዮጵያ ቡና ጋር ያደረግነው ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር የተደረገበት ቢሆንም እነሱ ካላቸው ልምድና ለዋንጫውም ፉክክር ከመጫወታቸው አኳያ ለግጥሚያው የሰጠነው ግምት ከፍ ያለ ስለነበር ነው ጨዋታውን በአሸናፊነት ልንወጣ የቻልነው፤ ያገኘነው የድል ውጤትም የሚገባን ነው”፡፡

በኢትዮጵያ ቡና ላይ የድል ግብ ስለማስቆጠሩ

“ግቧን ሳገባ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ምክንያቱም ያስቆጠርኩበት ቡድን የሀገሪቱ ትልቅና ለእኛ ደግሞ ከእንደዚህ አይነት ጠንካራ እና ለዋንጫ ከሚፎካከሩ ቡድኖች ጋር የምታገኘው ውጤት በጣም አስፈለጊያችንም ስለሆነ ነው”፡፡

ስለ ቡድናቸው ጠንካራና ደካማ ጎን

“በእግር ኳስ ደካማ ጎን ሁሌም ይኖራል፤ አሁን አሁን ላይ ግን ይሄ ችግር እኛ ጋር ብዙ አለ ማለት አልችልም፤ የእኛ ጥንካሬያችን ደግሞ እንደ ግል ሳይሆን እንደ ቡድን በህብረት ሆነን መጫወት መቻላችን ነው፤ ይህንን አካሄድ ወደፊትም እናስቀጥለዋለን”፡፡

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአቸው ሊያመጡት ስላሰቡት ውጤት

“የእኛ የቅድሚያ እልም የውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን መቻል ነው፤ ከዛ ደግሞ ግጥሚያዎቻችችን እያሸነፍን ስንመጣና የቡድናችንም የአጨዋወት ቅርፅ ሲስተካከል ወደ ዋንጫው ፉክክር ስለመግባት እናልማለን”፡፡

የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ስለማንሳትስ አታልሙም

“ይሄን የምታልመው በቀጣዮቹም ጨዋታዎች ላይ እያንዳንዱን ግጥሚያዎች እያሸነፍክ በምትጓዝበት ጊዜ ነው፤ ያኔማ መች ማለምህ ይቀራል፤ አሁን ላይ ግን ሊጉ በርካታ ጨዋታዎች የሚቀሩት ስለሆነም እርግጠኛ ሆነህ ይህን ዋንጫ አነሳለው አትልም”፡፡

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ስላስደሰተውና ስላስቆጨው ጨዋታ

“ለእኔ በጣም ያስደሰተኝ ግጥሚያ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ በድሬዳዋ ከተማ እና በኢትዮጵያ ቡና ላይ የተቀዳጀነውን ድል ነው፤ በተለይ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በነበረን ጨዋታ ሁለት ጊዜ በመመራት ከኋላ አንሰራርተን በመምጣት ያሸነፍንበት ስለነበር ውጤቱ ለእኛ ይበልጥ ጣፋጭ ነበር”፡፡

ቤትኪንጉ ተቋርጦ ወደ ውድድሩ ሲመለስ በምን መልኩ ሊቀርቡ እንደሚችሉ

“በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ምክንያት ሊጉ ተቋርጦ ሲመለስ እኛ የሚኖረን አቋም ከአሁን በተሻለ በጣም ጥሩ ሊሆን እንደሚችል አምናለው፤ አሁን የጥቂት ቀናት እረፍት ተሰጥቶናል፤ ስንመለስ ያሉብን የተወሰኑ ክፍተት ችግሮቻችን ላይ እንሰራለን፤ ጠንካራ ነገራችንንም እናስቀጥላለን”፡፡

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ከአምናው ስታነፃፅረው

“የዘንድሮ ውድድር እንደ አምናው አንድ ወይንም ደግሞ ሁለት ክለቦች ብቻ የዋንጫውን እጀታ ለመጨበጥ ፉክክር የሚያደርጉበት አይደለም፤ በሊጉ አዲስ ነገር እየታየ ነው፤ ካለው ጥሩ ፉክክር አኳያም ሊጉን ማን እንደሚያሸንፍ የምታውቅበትም አይደለምና ይሄን ልዩነት ልመለከት ችያለው”፡፡

ፈታኝ ቡድን ማን እንደሚሆንባቸው

“አሁን ላይ ትልቅና ትንሽ የሆነን የሊግ ቡድን ገና ስላላየን እንደዚሁም ደግሞ በእያንዳንዱ ግጥሚያም ላይ ይሄ ቡድን ያሸንፋል ብለህ እርግጠኛ የምትሆንበት ነገር ስለሌለ የዘንድሮ የውድድር ተሳትፎአችን ላይ ይሄ ቡድን ነው እኛን ይፈትነናል ብሎ መናገር አይቻልም”፡፡

ስለ ወቅታዊ አቋሙ

“ሀዲያን በተቀላቀልኩበት የዘንድሮው የውድድር ጉዞዬ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ከፍተኛ መሻሻሎችን እያሳየው እገኛለው፤ ቡድኔንም በመከላከሉ ላይ እየጠቀምኩት እገኛለው፤ ከእዛ ውጪም ከመከለከሉ ባሻገር የቅጣት ምቶችና የማዕዘን ምቶች በሚገኙበት ሰዓት ላይም በግምባር መግጨቱ ላይ ጥሩ  የሆነ ብቃትም ስላለኝ እነዛን ለመጠቀም እሞክራለው፤ ይሄን መሻሻሌንም በቀጣይ ጨዋታዎች ላይም ማስቀጠልና በኳሱም ትልቅ ደረጃ ላይም መድረስን እፈልጋለው”፡፡

በመጨረሻ..

“የሀዲያ ሆሳዕና ክለብ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ ሁላችንም የቡድኑ ተጨዋቾች በአሁን ሰዓት በቁርጠኝነት አቋም ላይ እንገኛለን፤ አሁን ላይ በጣም እየተሻሻልን መጥተናል፤ ጥሩ ተጨዋቾችና አሰልጣን አለን፤ እርስበርስም በደንብ እየተግባባን ይገኛልና ዘንድሮ ደጋፊዎቻችንን በውጤት እንደምናስደስታቸው እርግጠኛ ነኝ፤ በተረፈ በእያንዳንዱ ጨዋታዎቻችን ወቅት ውጤት ሲኖረንም ሳይኖረንም ከሆሳዕና ድረስ በመምጣትና ከእኛ ጎንም በመሆን የሚደግፉን ደጋፊዎች አሉና ለእነሱ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለው”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P