Google search engine

ወደ ውጪ ካላመራሁ በስተቀር ከቅ/ጊዮርጊስ የሚለየኝ የለም” አስቻለው ታመነ (ቅዱስ ጊዮርጊስን)


የቅዱስ ጊዮርጊሱ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች አስቻለው ታመነ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ይናገራል
ሊግ፡- በቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ ባሳለፍከው የተጨዋችነት ቆይታህ በጣም ደስተኛ ነህ?
አስቻለው፡- አዎን፤ እንዴትስ ነው ደስተኛ የማልሆነው፤ ይሄ ክለብ እኮ ለእኔ ብዙ ነገሮችን አድርጎልኛል፤ ከዛ ውጪም ለእዚህ ታላቅ ክለብ ለመጫወት መቻሌም የተለያዩ የውጤታማነት ክብሮችን እንድጎናፀፍ አድርጎኝም ጥሩ ስምና ዝናን ሊያስገኝልኝም ችሏልና ምርጥ ጊዜያቶችን ነው ከቡድኑ ጋር እያሳለፍኩ ያለሁት፡፡
ሊግ፡- በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታህ ምርጥ ስኬቶቼ እና ተደስቼባቸዋለው የምትላቸው የጨዋታ ጊዜያቶችስ የትኞቹ ናቸው?
አስቻለው፡- ለእኔ እንደ ቡድንም እንደ ግልም ምርጦቹ ጊዜያቶቼ በ2008 እና በ2009 ዓ/ም ላይ ያሳለፍኳቸው የስኬታማነት ወቅቶች ናቸው፤ እነዛም ክለቡን ገና የተቀላቀልኩባቸው ሁለት ዓመታቶች ስለነበሩ የሊጉን ዋንጫ ለተከታታይ ጊዜ ላገኝባቸው ችያለው፤ ከዛም ባሻገር የሀገሪቱን የኮከብ ተጨዋችነት ክብርንም ከቡድኑ ጋር ልጎናፀፍም ችያለው፤ የተለያዩ ሌሎች ዋንጫዎችንም አግኝቻለው፤ ሌላው ደግሞ በአፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ የውድድር ተሳትፎአችንም ላይ ቡድናችንን 16 ውስጥ እንዲገባ ካደረጉት ታሪካዊ ተጨዋቾች መካከልም አንዱ ልሆን በቅቻለውና በዛ ደረጃ ማለፌ በጣም ያስደስተኛል፡፡
ሊግ፡- ለቅ/ጊዮርጊስ ስትጫወት የተቆጨሁበት ጊዜስ ብለህ የምታስበው?
አስቻለው፡- በእግር ኳስ ቁጭትማ መች ይጠፋል ብለህ ነው፤ ያም በመሆኑም በክለቡ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ በጣም የተቆጨሁበት ጊዜ አሁንም በአፍሪካ ክለቦች የቻምፒዮንስ ሊግ የውድድር ተሳትፎአችን ላይ ወደ ስምንት ውስጥ የምንገባበትን እድል አግኝተን በሜዳችን ከደቡብ አፍሪካው ሰንዳውንስ ክለብ ጋር ስንጫወት በሜዳችን ላይ ነጥብ በመጣላችን እልማችንን ሳናሳካ የቀረንበትን ጊዜ ነው፤ ከዛ ውጪ ሌላው ቁጭቴ ደግሞ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2010 የውድድር ተሳትፎአችን ላይ ዋንጫውን የማንሳት እድሉ ኖሮን በግፍ ያን ድል እንዳናገኝ የተደረገበት ወቅት ነበርና ሁለቱን ፈፅሞ አልረሳቸውም፡፡
ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ በግፍ አጥቷል ብለሃል፤ በዛ ምክንያት ብቻ ነው ያጣችሁት?
አስቻለው፡- እንደዛ ብቻ ብዬ አልናገርም፤ የራሳችንም ድክመት ነበረብን፤ በተለይ ደግሞ መሀል ላይ የጣልናቸው ነጥቦች በጣም ጎድተውናል፤ ያኔ በአንድአንድ ጨዋታዎች ላይ ድክመት ቢኖርብንም ነጥቦችን ብንጥልም ወደ መጨረሻዎቹ ጨዋታዎች አካባቢ ደግሞ የሊጉን ዋንጫ የማንሳት እድሉ ኖሮን ሳለ ከጅማ አባጅፋር ጋር ጅማ ላይ ባደረግነው ጨዋታ ግን የግጥሚያው መደበኛ ሰዓት ተጠናቆ 5 ተጨማሪ ደቂቃ ብቻ መጫወት ሲገባን 13 ደቂቃ እንድንጫወት ስለተደረግንና በእኛም ቡድን ላይ ተጨዋቻችን የሆነው ምንተስኖት አዳነ የእነሱን አጥቂ ኦኪኪ አፉላቢን በክልላችን ውስጥ ምንም ሳይነካው የፍፁም ቅጣት ምት እንዲሰጥብን በመደረጉ በዛ ምክንያት ጨዋታውን በአቻ ውጤት ለማጠናቀቅ ችለናልና ያ ግጥሚያ የሊጉን ዋንጫ እንድናጣ ትልቁ ምክንያት ሊሆነን ችሏል፡፡
ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስ ለሁለት ዓመታት ከዋንጫ ራቀ፤ ይሄ በክለቡ ብዙም ያልተለመደ ነው፤ ዘንድሮ ደግሞ በኮቪድ 19 የሊጉ ውድድር በመሰረዙ ለማንም ቡድን ዋንጫ ባይሰጥም ከዋንጫ ጋር የተራራቀበትን ዓመት ግን ወደ ሶስት አድርሶታል፤ ይህን ስታይ ክለቡ በፍጥነት ወደለመደው ድል ይመለሳል?
አስቻለው፡- ምንም ጥያቄ የለውም፤ ክለቡን ያለ ዋንጫ ማየት ያማል፤ ምክንያቱም ቅ/ጊዮርጊስ ትልቅ ቡድን ነው፤ ብዙ ዝነኛ ተጨዋቾችም ተጫውተው ያሳለፉበት ነው፤ ከዛ ውጪም ብዙ የሌላ ክለብ ተጨዋቾችም የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ፍለጋ እና በቡድኑም ስምና ዝናን ለማግኘትም ሊጫወቱበት የሚመርጡት ቀዳሚው ክለብ ስለሆነ እና ሁሌም ደግሞ ዋንጫን ለማንሳት ብቻ ወደ ውድድርም የሚገባም ክለብ ስለሆነና ዋንጫንም ለበርካታ ጊዜያቶችም ያገኘ ስለሆነ የአዲሱ የውድድር ዘመን ፈጣሪ ብሎ ከተጀመረ ያን ድል ለማሳካት ወደ ኋላ የምንልበት ምንም ነገር የለም፤ ደግሞም ባለ ድል እንሆናለን፡፡
ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስን አዲስ ግደይ ከሲዳማ ቡና ከነዓን ማርክነህ ደግሞ ከአዳማ ከተማ በመምጣት ክለቡን ተቀላቅለዋል፤ የእነዚህ ተጨዋቾች ወደ ቡድኑ መምጣት ለክለቡ ጥንካሬን ይጨምርለታል?
አስቻለው፡- አዎን፤ ለዛ በጣም እርግጠኛም ነኝ፤ የእነሱን መምጣት ለመስማት በመቻላችንም ለእኛ መልካም የሆነም ዜና ነው፤ ምክንያቱም ሁለቱ ተጨዋቾች በየሚጫወቱበት ቦታ ላይ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ናቸው፤ ያንንም ጥሩ ችሎታቸውንም በተደጋጋሚ ጊዜ አሳይተዋል፤ ያ ስለሆነም ባለን ሀይል ላይ እነሱ ሲጨመሩበት የክለቡን ጥንካሬ የበለጠ ያሳድገዋል፤ አንድ ደረጃ ወደ ላይ ከፍ እንድንልም ያደርገናል፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታህ በሁሉም ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፍክ ተጨዋች ሆነሃል፤ ይሄን መስማት መቻል ለአንተ ምን የተለየ ነገርን ፈጥሮልሃል? ምን ነገርንስ አስገኝቶልሃል?
አስቻለው፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ለክለቤም ሆነ ለሀገሬ ብሔራዊ ቡድን ስጫወት ሜዳ ላይ በማሳያቸው መልካም የሚባሉ እንቅስቃሴዎች በጥሩ እይታ ታይቼ እና በችሎታዬም ታምኖብኝ በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን ለማግኘት መቻል ለእኔ የፈጠረልኝ ነገር ቢኖር ከፍተኛ ደስታ ነው፤ እነዛን ጥሩ ችሎታዬንም ለማሳየት የቻልኩት ሁሌም ጠንክሬ ልምምዶቼን ስለምሰራ፤ ከዛ በተጨማሪም አቅሜንና ጉልበቴን ሳልሰሰት ስለምጫወት እንደዚሁም ደግሞ የምጫወትበት ክለብ ውጤታማ ሆነም አልሆነም እንደ ግል አልሸነፍ ባይ ተጨዋች ሆኜ የሚጠበቅብኝን ነገር ሰርቼ ከሜዳ ስለምወጣ እና በዛ ደረጃ ላይም ለማለፍ በመቻሌ ዛሬ ላይ የጥሩ ተጨዋችነትን ስም ሊያስገኝልኝ ችሏል፤ ብዙዎቹ ያን ተመልክተውም ነው ያደነቁኝ፤ ስለዚህም በእዚህ አጋጣሚ እነዚህ አካላቶችን ለእኔ ክብር ሰጥተው ምስክርነታቸውን ስለሰጡኝ በጣም አመሰግናቸዋለውኝ፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወይንም ደግሞ በሀገር ውስጥ ተጨዋችነት ብቻ የአንተን የኳስ ህይወት ተገድቦ መቅረቱን ብዙዎቹ በቁጭት መልክ ሲያነሱት ይስተዋላሉ፤ በዚህ ዙሪያ ምን የምትለው ነገር አለ?
አስቻለው፡- ያን የሚሉት ሰዎች ትክክል ናቸው፤ ምክንያቱም የእግር ኳስን ስትጫወት ከነበርክበት ሁኔታ አንድ ደረጃ ወደ ላይ ከፍ ማለት ይጠበቅብሃልና፤ በእግር ኳሱ አሁን ላይ እኔ የምጫወትበት ክለብ በሀገሪቱ ትልቅ ስም ያለውና ገናና የሆነ ቡድን ነው፤ በእዚህ ክለብ ውስጥም ጥሩ የሚባሉ የውድድር ጊዜያቶችንም አሳልፌያለው፤ ክለቤንም ጠቅሜያለው፤ ቀጥሎ ደግሞ የራሴን አቅምና ችሎታ ለመፈተሽ ወደ ውጪ ሀገር በመውጣትም በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃ ለመጫወት እነዛን ሙከራ አድርጌም ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ከጥቅም ጋር በተያያዘ ለመስማማት ስላልቻልኩ ወጥቼ ሳልጫወት ቀርቻለውና ለእኔ ጥሩ ነገርን ከመመኘት አኳያ ነው ብዙዎች ወደ ውጪ ሀገር ወጥተህ መጫወት አለብህ የሚሉኝ፡፡
ሊግ፡- በፕሮፌሽናልነት አሁንም ወደ ውጪ ሀገር ወጥተህ ለመጫወት እንቅስቃሴ ላይ መሆንህን ሰማን? የእውነት ነው?
አስቻለው፡- አዎን፤ ኮቪድ 19 ከገባ በኋላ ወደ ውጪ ሀገር ወጥቼ ለመጫወት የምችልባቸውን ክለቦች አግኝቻለው፤ ከአንድ አንድ ክለቦች ጋርም የተነጋገርኩበት አጋጣሚዎች አለ፤ ያም ሆኖ ግን በአሁን ሰዓት ላይ በክለቤ የአንድ ዓመት ቀሪ ውል ስላለብኝ እና የክለቡም ንብረት ስለሆንኩኝ እስካሁን ድረስም የተፈጠሩ ምንም ነገሮችም ስለሌሉ ምላሽን ለፈለጉኝ ክለቦች ልሰጣቸው አልቻልኩም፤ ስለዚህም በቀጣዩ ወቅቶች ክለቤ ከፈቀደልኝ ያገኘሁት እድል ጥሩ ስለሆነና የቡድኔን ስምም የማስጠራበት ስለሆነም ከእነሱ ጋር ተነጋግሬም ከውሳኔ ላይ የምደርስ ነው የሚሆነው፤ በዚህ ደግሞ የክለቤ አመራሮች የእኔን እድገት በጣም የሚፈልጉ እንጂ ወደ ኋላ እንድቀር የሚፈልጉ ስላልሆኑ በጣም ይረዱኛል፤ ይደግፉኛልም ብዬ ነው ተስፋን የማደርገው፤ ስለዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስን ለቅቄ ወደ ውጪ ሀገር ወጥቼ መጫወት የምችለው ከክለቤ ፈቃድን ብቻ ሳገኝ ነው፤ ወደ ውጪ ሀገር ካላመራው ግን ቅዱስ ጊዮርጊስን መቼም ቢሆን መልቀቅ አልፈልግም፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዝግ ስታድየም ሊደረግ ከውሳኔ ላይ ተደርሷል፤ ያን ስትሰማ ምን አልክ?
አስቻለው፡- ያለ ደጋፊ ኳስን መጫወት መቻል በጣም ከባድ ነገር ነው፤ ሁሉም ነገርም ያስጠላሃል፤ ይሄን ከዚህ በፊት ከሐዋሳ ከተማ ጋር ስንጫወት ልንመለከተው ችለናልና ያለው ድባብ ደስ የማይል ነው፤ በርካታ ደጋፊዎች ላላቸው ክለቦችም በዛ ደረጃ መጫወት ብዙ ነገሮችንም ስለሚያሳጣቸው ለእነሱም ነገሮች ከባድ ነው የሚሆንባቸው፤ እንደዛም ሆኖ ግን አሁን ላይ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዓለምን ያማከለ ስለሆነና የእኛም በዝግ ስታድየም መጫወት በጥናት ተሰርቶ የቀረበ በመሆኑ ከጊዜው አንፃር መቀበሉን የግድ ነው የሚለን፡፡
ሊግ፡- የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ያለ ተመልካች በዝግ ስታድየም ሲካሄዱ ቆይተው የፍፃሜ ተፋላሚዎቹ ክለቦች ታውቀዋል፤ እነዛን ግጥሚያዎች ቁጭ ብለህ ስትከታተል ምን አይነት ስሜት በውስጥ ተፈጠረህ?
አስቻለው፡- የእነሱን ግጥሚያዎች ካለው አስከፊ ጊዜ አኳያ በቤት ውስጥ ቁጭ ብለን ለመከታተል መቻላችን ለእኛ እግር ኳስን ለምንወድ አካላቶች ከፍተኛ መፅናኛ እየሆነን ነው ያለው፤ የእኛም ቢኖርና እነሱ በሚጫወቱበት ሁኔታም ብንጫወትም ብለህ ትመኛለህና በዛ ጊዜያችንን እያሳለፍን ነው የሚገኘው፡፡
ሊግ፡- የቻምፒዮንስ ሊግ ውድድሮቹን እንዴት ተመለከትካቸው፤ ከባየር ሙኒክ እና ከፓሪስ ሴይንት ጀርሜንስ ማን በነገው ውድድር ላይ አሸንፎ ሻምፒዮና ይሆናል?
አስቻለው፡- ጨዋታዎቹን እንደተከታተልኩት ከዚህ በፊት ለዋንጫ የምትገምታቸውና አያል የሆኑ ተጠባቂ ቡድኖች ከውድድሩ ውጪ የሆኑበትን ሁኔታ ተመልክተናል፤ በርካታ ግቦችንም ልንመለከት ችለናል፤ ያልተጠበቁ ጥሩ ቡድኖችን ለማየትም ችለናል፤ በነገው ምሽት ጨዋታ ደግሞ የእዚህ ውድድር አሸናፊ ባየር ሙኒክ ይሆናል፡፡
ሊግ፡- የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን /ካፍ/ በኮቪድ 19 ሰርዞት የነበረውን የአህጉሪቱን የማጣሪያ ጨዋታዎች በጥቅምት ወር ወደ ውድድር እንዲመለስ ከውሳኔ ላይ ደርሷል፤ ለተወዳዳሪ ክለቦችም ይህን አሳውቋል፤ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደዚህ የውድድር ተሳትፎ በምን መልኩ ለመምጣት ይችላል?
አስቻለው፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኮቪድ ወደ አገራችን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የሀገሪቱ የሊግ ውድድሮች በመቋረጣቸው ተበትኖ ያለ ነው፤ የዋልያዎቹ የተጨዋቾች ስብስብም ይህን ተከትሎ ከእንቅስቃሴ ከራቁም ሰነባብተዋል፤ ከዛ ውጪም ቡድኑ ከአሰልጣኙ ጋር በመለያየቱም አሰልጣኝ አልባ ሆኗል፤ ስለዚህም የእዚህ ቡድን ሁሉም ተጨዋቾች ከእንቅስቃሴ ከመራቃችን በአቋማችን ላይ የሚፈጠርብን ችግር ስለሚኖርና ከሪትም ስለምንወጣ አሁን ላይ የእኛን ከምድባችን ተወዳዳሪ ሀገራት አኳያ ወደ ውድድር ልንመለስ መሆናችንን ሳስብ ነገሮችን በጣም ነው ከባድ የሚያደርግብን፤ ምክንያቱም የእኛ ምድብ ተወዳዳሪ ሀገራት አብዛኛዎቹ ተጨዋቾቻቸው ፕሮፌሽናሎች ናቸው፤ በውድድር ላይም ቆይተዋል፤ ስለዚህም የእኛ ቡድን ብቻ ከእንቅስቃሴ ስለራቀ እና አሰልጣኝም ስለሌለው፤ ወደ ውድድር ስንመለስም የሚኖረን የዝግጅት ጊዜም አጭር ስለሆነ ያለንበት ሁኔታ ለእኛ በብዙ ነገሮች አስቸጋሪም ነው የሚሆንብን፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዚህ ደረጃ ላይ ከመገኘቱ በፊት ምን ማድረግ ነበረበት ብለህ ታስባለህ?
አስቻለው፡- አሁን ላይ እንዲህ መሆን አለበት ብለን ለመናገር ከባድ ነው፤ ጊዜውም የረፈደ ነው፤ አሰልጣኝ የመቅጠር እና ያለመቅጠር እንደዚሁም ደግሞ የማሰናበት እና ያለማሰናበት ውሳኔዎች የእነሱ እስከሆነ ድረስ አስቀድመው ነበር ሁሉንም ነገር ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ስራቸውን መስራት የነበረባቸው፤ የብሔራዊ ቡድናችን አሰልጣኝ አብርሃም በነበረበት ሰዓት ለእኛ ተጨዋቾች መፅሀፍቶችን የምናነብበት ነገር ተፈጥሮ ነበር፤ በቪዲዮ ኮንፈርንስም አፕሊኬሽን ተጭኖልን በምን መልኩ መለማመድ እንደሚኖርብን ስራ ተጅምሮም ነበር፤ በኋላ ግን ከአሰልጣኙ አለመኖር ጋር ተያይዞ ብዙ ነገር ሊቀርብን ችሏልና ከዚህ በኋላ እነሱ አሰልጣኝን ቀጥረው ተዘጋጁ በሚሉን ሰዓት ለውድድሩ ለመዘጋጀት ውሳኔያቸውን እየተበቅን ነው የሚገኘው፡፡
ሊግ፡- እንደ አንድ እግር ኳስ ተጨዋች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዚህ ደረጃ ላይ በተለይ ደግሞ አሰልጣኝ ሳይኖረው መገኘቱን ስታይ ምን አይነት ስሜት ነው በውስጥህ የተሰማህ ?
አስቻለው፡- የእኔ ብቻ ሳይሆን የብዙ ተጨዋቾችም ሀሳብ ነው፤ መጀመሪያ በአሰልጣኙ መሰናበት እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የራሱ የሆነ ምክንያት ቢኖረውም ስለ ስምምነታቸው እኛ ብዙ ባናውቅም የእሱ መነሳት ግን ደስተኛ አላደረገንም፤ እሱ አሁን ላይ ኖሮ ቢሆን ኖሮም ብለን እያሰብን ነው፤ ምክንያቱም አሰልጣኙ ኖሮ ቢሆን አሁን ላይ የአንድ ወር ክፍተት ብቻ ስለሚኖርና ያም ደግሞ ምንም ማለት ስላልሆነም ፌዴሬሽንም ደግሞ ትልቅ ተቋምም ስለሆነ አሰልጣኙ ቢኖር ኖሮ ለእኛ ከመላመዳችን አኳያ እና ቡድኑን በጥሩ መልኩ እየገነባው ከመሆኑ አኳያም ጥሩ ነገር ነበር የሚሆነው፡፡
ሊግ፡- ለመጪው የውድድር ዘመን ራስህን አሁን ላይ በምን መልኩ እየዘጋጀከው ነው የምትገኘው?
አስቻለው፡- ኮቪድ 19 ምንም እንኳን አስቸጋሪ ወረርሽን ቢሆንም ወደ እኛ ዲላ ከተማ ላይ አስቀድሞ ያልገባ ስለነበር ለአዲሱ የውድድር ዘመን እንዲረዳኝ እንደ ግልም እንደ ጋራም በመሆን አስፈቅደን በሳምንት አራት ቀን ልምምዴን ከጓደኞቼ ጋር በመሆን በጥሩ መልኩ እየሰራው ነበር፤ አሁን ላይ ግን ይሄ ወረርሽን የእኛንም ከተማ ማጥቃት በመጀመሩ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረግኩ በቤት ውስጥ ልምምዴን እየሰራው ነው፤ ለመጪው የውድድር ዘመንም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በምርጥ ብቃቴ ላይ እንደምቀርብም እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
አስቻለው፡- በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጉዳይ አንድ ተጨማሪ ነገርን ለማለት እፈልጋለው፤ የእግር ኳስ ፌዴሬሽናችን ለውድድር የምንመለስበት ወቅት አጭር ከመሆኑ አንፃርና የብዙ ተጨዋቾችም ከውድድር ከመራቃቸው አኳያ ኪሎ የመጨመር ነገር ስለሚኖር እንደዚሁም ደግሞ የወዳጅነት ጨዋታዎችንም ከማግኘት አኳያም ቶሎ አሰልጣኝን ሾመው ወደ ስራ በፍጥነት ልንገባ የምንችልበት ሁኔታ ቢፈጠርልን ለእኛ መልካም ነው፤ ከዛ ባሻገር ደግሞ በኳሱ አሁን ላይ ለደረስኩበት ደረጃ ከእኔ ጎን ለሆኑት ሁሉ በተለይ ደግሞ ለገብረ ክርስቶስ ቢራራ ለአሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌ እና ለጌታነህ ከበደ ምስጋና አለኝ፤ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች እና አመራሮችም ከምስጋና ባሻገር ልዩ ፍቅርና አክብሮትም እንዳለኝ በእዚህ አጋጣሚ ለመናገር እፈልጋለው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P