በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/
በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ 7 ክለቦች ግማሽ ፍፃሜውን ለመቀላቀል ዛሬና ነገ ይጫወታሉ
የ14ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬና ነገ በሚደረጉት አራት ግጥሚያዎች የሚጠናቀቁ ሲሆን በእዚሁም መሰረት ዛሬ ቅዳሜ በ8 ሰአት መከላከያ ከወልቂጤ ከተማ የሚያደርጉት እና በ10 ሰአት ደግሞ ባህር ዳር ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል፡፡
የእነዚህ ሁለት ጨዋታዎች ውጤትም ወደ ግማሽ ፍፃሜ የሚያልፉትን ሁለት ቡድኖችም ያሳውቃል፡፡ በእስካሁኑ ጨዋታ መከላከያ ብዙ ጎል አገባ በሚለው ህግ በ4 ነጥብ እና በ1 ግብ ምድቡን ሲመራ ባህር ዳር ከተማ ደግሞ በተመሳሳይ ነጥብና ጎል ተከታዩን ስፍራ ይዟል፡፡ ቅ/ጊዮርገስ በ3 ነጥብና በ1 ጎል ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ወልቂጤ ከተማ ያለምንም ነጥብ 3 የግብ እዳ ኖሮበት የመጨረሻውን ስፍራ ይዞ ወደ ግማሽ ፍፃሜው የሚያልፍበት እድሉ አክትሟል፡፡
ከሌላው ምድብ ደግሞ ሰበታ ከተማ በ4 ነጥብና በአንድ ግብ ምድቡን ሲመራ ኢትዮጵያ ቡና እና ወልዋሎ አዲግራት በተመሳሳይ ሶስት ነጥብና ያለምንም ግብ ተከታዩን ስፍራ ይዘው ይገኛሉ፤ ኤሌክትሪክም በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን ስፍራ ይዞ ይገኛል፤ በእዚሁም መሰረት ነገ በሚደረጉት የ8 ሰዓቱ የወልዋሎ አዲግራትና የሰበታ ከተማ እንደዚሁም ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናና የኤሌክትሪክ ጨዋታ ጥሩ ውጤት የሚያስመዘግበው ቡድን የግማሽ ፍፃሜውን ይቀላቀላል፡፡
የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ጨዋታዎችን አስመልክተን ከየክለቡ ተጨዋቾች ጋር ያደረግነው ቃለምልልስ በሚከተለው መልኩ ይቀርባል፡፡
ኢትዮጵያ ቡና ወልዋሎ አዲግራትን ድል ስላደረገበት ጨዋታ እና ውጤቱ ይገባው እንደሆነ
“የወልዋሎ አዲግራት ጋር የነበረን የሐሙሱ ጨዋታ ለእኛ በደጋፊዎቻችን ፊት ከመጫወታችን አኳያ እንደዚሁም ደግሞ ግጥሚያውን ለማሸነፍ ከነበረን ከፍተኛ ፍላጎት አንፃርና ወደ እነሱ ጎልም ካለፈው የመጀመሪያ ግጥሚያችን በመነሳት ወደ ተቃራኒ ቡድን የጎል ክልል የደረስንበት አጋጣሚዎች ስለነበሩ ጨዋታውን ማሸነፋችን በጣም ጥሩ ነው፤ ውጤቱም ኳስን ይዘን ከመጫወታችን አንፃር የሚገባን ሆኖም ነው ያገኘሁት”፡፡
ኢትዮጵያ ቡና ሰበታ ከተማን ከገጠመበት ጨዋታ አኳያ የወልዋሎው ግጥሚያ በእንቅስቃሴ ደረጃ ሲመዘን
“ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አሰልጣኝ እና በአዲስ አጨዋወት ሜዳ ላይ እያከናወነ ባለው የሰሞኑ የሲቲ ካፕ ጨዋታዎች በእንቅስቃሴ አንፃር ሲመዘን ከወልዋሎ ጋር ካደረግነው ጨዋታ ይልቅ ከሰበታ ከተማ ጋር ያደረግነው ጨዋታ በጥሩነቱ የሚገለፅ ነው፤ የመጀመሪያው ጨዋታችን በጣም ጥሩና ከአሁኑ የተሻለ ነው፤ የወልዋሎው ግጥሚያ የሚለየው ወደ ጎል በመድረሳችን እና ጎል በማስቆጠራችን ብቻም ነው”፡፡
የወልዋሎ አዲግራትን የጨዋታ እንቅስቃሴ በተመለከተ
“ወልዋሎዎች ከእኛ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ወደሜዳ የመጡት ኳስን ለመጫወት ሳይሆን በታይት ማርክ አጨዋወት የእኛን ተጨዋቾች ሰው በሰው አስይዞ ቡድኑ ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርግና አጨዋወቱንም ለማጥፋት ነው፤ ያም ሆኖ ግን ቡድናችን እንደ መጀመሪያው ቀን በጥሩ ሁኔታ ባይንቀሳቀስም የሁለተኛው አጋማሽ ላይ በተወሰነ መልኩ የነበረን ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት መሞከር ወደ ጎል እንድንደርስ ስላደረገን የጨዋታው አሸናፊ ሊያደርገን ችሏል”፡፡
የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ስለመሸለሙ
“የወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲን ባሸነፍንበት ጨዋታ ጥሩ በመንቀሳቀሴ የጨዋታው ኮከብ ተብዬ ስሸለም የተሰማኝ የደስታ መጠን በጣም ከፍ ያለ ነው፤ ይሄን ሽልማት ለትልቅ እና ታሪካዊ ለሆነው ቡድን ተጫውቼ ያገኘሁት እና ከዚህ ቀደም ደግሞ እንዲህ ባሉ የሲቲ ካፕ ጨዋታዎች ላይም ተሸልሜ የማላውቅ ስለሆነም ደስታዬ የተለየም እንዲሆን አድርጎታልና ይሄ ለቀጣዩ የኳስ ህይወቴም ጥሩ ደረጃ ላይ እንድደርስ ከፍተኛ መነሳሻም ይሆንልኛል”፡፡
የኢትዮጵያ ቡና አጨዋወት ተመችቶት እንደሆነና ስለ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ
“ኢትዮጵያ ቡና እየተከተለ ያለው አጨዋወት ከሌሎች ቡድኖች አንፃር ስመለከተው በጣም ለየት ያለና አህምሮህንም ተጠቅመህ የምትጫወተው ስለሆነ በጣም ተመችቶኛል፤ ያን ስልህ የሚሻሻልም ነገር እንዳለም ስለማምን ነው፤ በተለይ ደግሞ የቡድናችን ሁሉም ተጨዋቾች ተሟልተው ሲመጡ በቀጣይነት ምርጡን ቡናን የምንመለከተው ይሆናልና ያን እየጠበቅን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቡናን አዲሱ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን በሚመለከት በስራው ላይ እንደተመለከትኩት እሱ ኳስን ደስተኛ ሆነህ እንድትጫወት የሚፈልግና ኃላፊነትንም ወስዶልህ እንድትጫወት የሚያደርግ ባለሙያ በመሆኑ ለየት የሚል አሰልጣኝ ነው፤ ለእግር ኳስ ተጨዋችነትህ የወደፊት ስኬታማ ህይወት እንዲኖርህ ጥሩ ጥሩ ልምምዶችን እያሰራን ይገኛልና እሱን በሚገባ ልንረዳው እና ልናግዘውም ይገባል”፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከኢትዮ-ኤሌክትሪክ ጋር ስለሚኖራቸው የነገው ወሳኝ ጨዋታና አጠቃላይ ውድድሩን በምን ውጤት እንደሚያጠናቅቁ
“ከኤሌክትሪክ ጋር የሚኖረን የነገው ጨዋታ ለእኛም ሆነ ለእነሱ ግጥሚያውን ማሸነፍ መቻል የግማሽ ፍፃሜውን እንድንቀላቀል የሚያደርግ ስለሆነ ይህን ጨዋታ ለማሸነፍ ተዘጋጅተናል፤ ከዛ ውጪ ውድድሩንም በአሸናፊነት አጠናቀን ደጋፊዎቻችንንም ለማስደሰት ከፍተኛ ጥረትንም እናደርጋለን”፡፡
በመጨረሻ…
“የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ እየተከተለ ባለው የአዲስ የአጨዋወት ፍልስፍና ውስጥ እኛ የቡድኑ ተጨዋቾች ስራውን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረትን እያደረግን እንገኛለን፤ ቡድኑ ከያዛቸው ወጣት ተጨዋቾች አኳያም አሁን ላይ እያሳየን ያለው ጅማሬም ጥሩ ነውና በሂደት ደግሞ በአጨዋወታችን ዙሪያ የሚቀሩንን ነገሮች በሚሰጠን ስልጠና አስተካክለን በመምጣት ክለቡን በሁሉም መልኩ የተሟላ ቡድን ለማድረግ እየሰራን ነው የሚገኘው፤ ከዛ ውጪም ደጋፊዎቻችንን እና ራሴን በተመለከተም ደጋፊዎቻችን ተሸነፍንም አሸነፍንም እንደ 12ኛ ተጨዋች ሆነው በድንቅ ሁኔታ እያበረታቱን ነው የሚገኘው፤ ሁሌም ከጎናችን ናቸው፤ በእዚህ ልናመሰግናቸው ይገባል፤ እኔን በሚመለከት ደግሞ በቡና ክለብ ውስጥ አሁን ላይ እያሳየሁት ባለው እንቅስቃሴ ደስተኛ ነኝ፤ ከዚህ በኋላ ደግሞ ባለኝ ጥሩ ነገር ላይ ሰርቼ በመምጣት የክለቡ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱም ምርጥ ተጨዋች ስለመሆን አስባለሁና ለእዛ ፈጣሪዬ ዓላ ምኞቴን እንዲያሳካልኝ እለምነዋለው”፡፡