ሊግ፡- ሀድያ ሆሳህናን በሁለተኛው ዙር ተቀላቅለህ ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲገባ ካስቻሉት ተጨዋቾች መካከል አንዱ ሆነሃል፤ የድል ስሜቱ በአንተ ዘንድ ምን ይመስላል?
ሱራፌል፡- በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በመጫወት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሳልፍ የአሁኑ የመጀመሪያዬ ጊዜ ነው፤ ከሀድያ ሆሳህናም ጋር ይህንን እልሜን ሳሳካ በእኔ ውስጥ የተፈጠረብኝ የደስታ ስሜት የማላውቀው እና በጣም ለየት ያለም ስለሆነ አሁንም ድረስ ጥሩ የሆነ ስሜት እየተሰማኝ ነው የሚገኘው፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ከፍተኛው ሊግ ላይ ስትወዳደሩ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማለፍ የቻላችሁበት ዋንኛው ጥንካሬያችሁ ምን ነበር?
ሱራፌል፡- የሀድያ ሆሳህና እግር ኳስ ክለብን ከአዳማ ከተማ በመምጣት የተቀላቀልኩት ከሁለተኛው ዙር አንስቶ በመሆኑ ለእኔ ከዛ ጊዜ ጀምሮ ያለውን ብናገር ደስ ይለኛል፡፡ የሀድያ ሆሳህናን ክለብ ካወቅኩበት ጊዜ አንስቶ የነበረው ጥንካሬ የቡድኑ አጠቃላይ ተጨዋቾች ማለትም ቤስቱ፣ ቤንቹ እና ከ16 ውጪ ያሉት ተጨዋቾች እርስ በርስ ያላቸው ግንኙነት ጥሩ ነበር፤ ከአሰልጣኝ ግርማ ብዙዎቻችን እንደምንጠራውም ከመንቾ ጋር ጥሩ ቀረቤታ አላቸውና እንዲህ ያለ ነገርን በሌላ ቡድን ውስጥ አይቼ አላውቅም፤ ከዛ ውጪ በእንቅስቃሴ ደረጃ የቡድኑ ተጨዋቾች ያላቸው ተነሳሽነት ጥሩ ነው፤ ቡድኑ በማጥቃት ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴንም ነው የሚከተለው፤ በመከላከሉም ላይ ጥሩ ነውና ካለው የቡድን መንፈስ አኳያ ነው የፕሪምየር ሊጉን ልንቀላቀል የቻልነው፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የውድድር ተሳትፎአችሁ ላይ ክፍተቶቻችሁስ ምን ነበሩ?
ሱራፌል፡- እኔ ቡድኑን የተቀላቀልኩት የግማሽ አመት ላይ በመሆኑ ክፍተትን ብዙም አልተመለከትኩም፡፡ ያም ሆኖ ግን ቡድኑ ውስጥ ያሉት ተጨዋቾች ለእኔ እንደነገሩኝ ቡድኑ ጋር ምንም አይነት ችግርም ሆነ የጎደለ ነገር እንዳልነበረ ነው፤ የውድድር አመቱ ሲጀመር ሀድያ ሆሳህናን ወደ ፕሪምየር ሊግ ማስገባት ታስቦ ስለነበር በዛ ላይ ጥንቃቄ የተሞላበት አሰራር እንደነበር ነው የነገሩኝ፤ የክለቡ አመራሮች ጥሩ ስለሆኑም ለክለቡ የተጠየቀውን ነገር ሁሉ ያሟሉ ነበርና በዚህ በኩል ምንም አይነት ችግርም ሆነ ክፍተቶች ቡድኑ ውስጥ አልነበሩም፡፡
ሊግ፡- በከፍተኛ ሊጉ የሀድያ ሆሳህናን ደጋፊዎች በምን መልኩ ነው የተመለከትካቸው፤ ለእናንተስ ውጤታማነት የነበራቸው ሚናስ የቱን ያህል ነበር?
ሱራፌል፡- የሀድያ ሀሳዕና ደጋፊዎች የሚገርሙ ናቸው፤ በየጨዋታው የሚሰጡን ድጋፍ ለእኛ ትልቅ የሞራል ስንቅም ሆኖልናል፤ በተለይ ደግሞ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ባለፍንበት ጨዋታ ወደሜዳ የመጣው እና የተመለሰው ደጋፊያችን ያለፈውን አይነት ሀገራችን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ስታልፍ የነበረው የብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ቀን አይነት ደጋፊን የተመለከትንበት እና ጨዋታውንም ዛፍ ላይ ጭምር በመንጠልጠልም የተመለከቱ፤ ሲመለከቱም ከዛፍ ላይም የወደቁ እና የተጎዱ ደጋፊዎችንም መኖራቸውን የሰማንበትም ሁኔታ አለና እንዲህ ያለ ደጋፊ ባለቤት መሆናችን ይገርማል ያስደንቃልም፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ተቀላቅላችኋል፤ ድሉ ይገባችኋል?
ሱራፌል፡- አዎን፤ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማለፋችን በትክክል ይገባናል፤ ከሶስቱ ምድብ የእኛን ስትመለከት ሁለት ጨዋታ እየቀረንና ተከታዮቻችንን በሰፊ ነጥብ በልጠን ነው ሊጉን የተቀላቀልነው፡፡
ሊግ፡- በሀድያ ሆሳህና ክለብ ውስጥ የነበረህ ቆይታህና ወቅታዊ አቋምህ ምን ይመስላል?
ሱራፌል፡- ሀድያ ሀሳዕናን ከተቀለቀልኩበት የሁለተኛው ዙር የውድድር ጊዜ አንስቶ እስካሁን በቡድኑ ውስጥ ያለኝ ቆይታም ሆነ ወቅታዊ አቋሜ ጥሩ የሚባል ነው፡፡ ከሚዛን ጋር ከነበረን ጨዋታ በስተቀር በሁሉም ላይ የመጫወት እና ክለቡንም የመጥቀም ብቃቴን አሳይቻለውና በዚህ ውስጥ ማለፌ በጣም ነው ያስደሰተኝ፡፡
ሊግ፡- የሀድያ ሀሳዕናው አሰልጣኝ ብዙ ባይነገርለትም በሚሰራው ጥሩ ስራ ብዙዎች ያደንቁታል አንተስ እሱን እንዴት ነው የምትገልፀው?
ሱራፌል፡- አሰልጣኝ ግርማ /መንቾ/ ጥሩ የሙያው ባለቤትና በአሰለጣጠን ብቃቱም የሚገርም አይነት አሰልጣኝ ነው፤ ከተጨዋቾች ጋር ያለው መቀራረብ እና በጋራም የመስራት ችሎታው ቡድኑን ለታላቅ ስኬት እንዲበቃ አድርጎታል፤ በእዚህ አጋጣሚ እኔን የሁለተኛው ዙር ላይ ወደ ቡድኑ አምጥቶኝ በማጫወት ለክለቡ ስኬታማነት ከጓደኞቼ ጋር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረክት ስላደረገኝ በዚህ አጋጣሚ ላመሰግነው እወዳለሁ፡፡
ሊግ፡- የከፍተኛው ሊግ ተሳትፎአችሁ ላይ ለእናንተ በጣም ጠንካራ የነበራችሁ ቡድን ማን ነበር..?
ሱራፌል፡- በሁለተኛው ዙር ላይ ነው በተለይ ይሄ የሆነው፤ አርባምንጭ ከተማ እና ነቀምት ከተማ በጣም አስቸግረውን ነበር፡፡
ሊግ፡- ሀድያ ሀሳህና የገባኸው አዳማ ከተማን በመልቀቅ ነበር፤ ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ?
ሱራፌል፡- የአዳማ ከተማን ለቅቄ ወደ ሀድያ ሆሳዕና የተሸጋገርኩት ቀደም ሲል ጉዳት ላይ የነበርኩ ቢሆንም በኋላ ላይ ተሽሎኝ እያለ ከህክምና ጋር በተያያዘ እና ከአሰልጣኙም ጋር በመለሰፍ እና ባለመሰለፍ ዙሪያ የመጫወት እድልን ካለማግኘት ጋር ነው፡፡
በኋላ ላይ ግን የሀድያ ሆሳህና እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ ግርማ /መንቾ/ ለአዳማ ከመፈረሜ በፊትና መድኖችም ይፈልጉኝ በነበረበት ሰዓት እሱ አስቀድሞ ይፈልገኝ ስለነበር የሁለተኛው ዙር ላይ ቡድኑን እንድቀላቀል ሊያደርገኝ ችሏል፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…..
ሱራፌል፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ገና ወጣት ተጨዋች ከመሆኔ አንፃር የራሴን ችሎታ ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሳደግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስን እፈልጋለሁ፤ ለዚህ ደግሞ ከቡድን ልምምድ በተጨማሪ የራሴን የግል ዝግጅትንም መስራት አስፈላጊ ነውና ለዚያ ራሴን እያዘጋጀሁትም ነው የምገኘው፤ በተረፈ በእግር ኳስ የእስካሁን የህይወት ቆይታዬ አሁን ለደረስኩበት ደረጃ በቅድሚያ ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ ከዚያ ውጭ ከዚህ በፊት ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች፣ ቤተሰቦቼን፣ ለሀድያ ሆሳህናው አሰልጣኝ ግርማ፣ ለቡድኑ አመራሮች፣ ለተጨዋቾቻችን እና ለደጋፊዎቻችንን ምስጋናን አቀርባለሁ፡፡