Google search engine

ወድቆ የተነሳው ባንዲራ


ሚያዝያ 27 በሀገራችን ኢትዮጵያ ልዩ ክብር የሚሰጠው፣ ጀግና አርበኛ እናት አባቶቻችን የሚታሰቡበት ቀን ነው፤ ከ1928 – 1933 ዓ.ም ፋሽስት ጣሊያን በሀገራችን በነበረባቸው አመታት አርበኞች በዱር በገደሉ ለእናት ሀገራቸው ሲታገሉ ፣ በከተማ ትግሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከነበራቸው ዋነኛና ቀዳሚው ግን አርበኛው ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ መሆኑን ታሪክ ይመሰክራል፡፡
ከፋሽስት መግባት ወራትን ቀደም ብሎ የተመሰረተው የአራዳው ጊዮርጊስ እግርኳስ ቡድን በ1928 ወርሀ ታህሳስ ተመስርቶ የመጀመሪያውን ግጥሚያ ከአራራት አርመን ክለብ ጋር ካደረገ በኋላ ሁለተኛውን ጨዋ ከኦሎምፒያኮስ ጋር ለማድረግ በሚሰናዳበት ወቅት ጣሊያን በሚያዝያ ወር ሀገራችንን ወረረ፤ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ ሁለት አመታት በኋላም በ1930 ዓ.ም የሐበሻ ክለቦች የሚሳተፉበት የእግርኳስ ውድድር እንዲካሔድ ተወሰነ፤ሆኖም ቅዱስ ጊዮርጊስ በስሙ እንዲመዘገብ ጥያቄ ቢያቀርብም ለምዝገባ ፈቃድ ባለማግኘቱ ከኮሚዩኒቲ ቡድኖች ጋር በመሆን ውድድር ለማዘጋጀት የማስተባበሩን ሀላፊነት ተወጣ፤ በዚህም ውስጥ ጊዮርጊስን ጨምረው የአርመንና ግሪክ ኮሚኒቲ ቡድኖች ተመዘገቡ፤ የመጀመሪው ጨዋታ አራራት ከኦሎምፒያኮስ ፣ የህንድ ኮሚኒቲ ደግሞ ከጊዮርጊስ ተደለደሉ፤ አራራት ኦሎምፒያኮስን 1ለ0 አሸነፈ፤ የጊዮርጊስን የህንድ ኮሚኒቲ ቡድኖች ገና ረፍት ሳይወጡ በከባድ ዝናብ ምክኒያት ተቋርጦ ድጋሚ ጨዋታ በማግስቱ ለማድረግ ቀጠሮ ቢያዝም በጃንሜዳ የጠበቃቸው ግን የጣሊያን ፖሊስ ነበር፤ ከአንድ ቀን በፊት የተጫወቱት የአርመንና ግሪክ ቡድኖች አስተባባሪዎች እስርቤት መግባታቸውን አወቁ፤ የዚህ ውድድር መዘዝ ከዚህም በላይ ነበር ጥቁርና ነጮች አብረው እንዳይጫወቱ ህግ ለመውጣቱም ምክኒያት ሆነ፤
የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስም የጣሊያንን ፈተና ተቋቁሞ እስከ 1933 ዓ.ም በመስዋእትነት ዘለቀ፡፡
ሚያዚያ 26/1933 ዓም ለቅዱስ ጊዮርጊስ እና ለአገራችን ኢትዮጵያ ታሪካዊ ቀን ነው። ታሪካዊነቱ ግን ከዋዜማው ይጀምራል፤ ሚያዝያ 25 ቀን 1933 ዓ.ም የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች ለመጨረሻ ጊዜ የተዘጋጀውን መዝሙር ጀምበር ማዘቅዘቅ ስትጀምር በድጋሚ ዘመሩት፡፡ ሌሎች ቀስቃሽ ሀገራዊ ዝማሬዎችም ተዘጋጁ፤ ወጣቶቹ በጠዋት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ለመገናኘት ተቀጣጠሩ፡፡ በድብቅ በልዩ ቦታ ተሸሽጐ የነበረው ሶስቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ማሊያዎች በቡድኑ ተጨዋቾች ፊት ለእይታ ቀረቡ፡፡ ማሊያዎቹን ሲያዩ አንዳንዶቹ አለቀሱ፡፡ ያለቀሱት ማሊያው ወቅቱን ስላስታወሳቸው ነው፡፡ ማሊያው ሙሉ ነጭ ሆኖ ሆዱ ላይ ዙሪያው አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ያለበት ነው፡፡ ይሄ ማሊያ የተሰራው ጣሊያን ከመግባቱ በፊት ነው፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ ባንዲራ ያለበትን ቀለም ጣሊያን ስላልተመቸው ከተጫዋቾቹ ላይ እያባረረ ቀማቸው፡፡ ከጣሊያን እጅ ያመለጡት ማሊያዎች እነሆ ዛሬ ወደ አደባባይ መጡ፡፡
በማግስቱ ሚያዚያ 26 ቀን 1933 ዓ.ም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ተቀጣጠሩ፡፡ ወጣቶች ጣሊያን ሉቶሪዮ ውቤ ሰፈር አራዳ ብሎ የሰየማቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ተጫዋቾች ናቸው፡፡ የተቀጣጠሩት ሁለት ቦታ ባንዲራ ለመትከል ነው፡፡ ከሶስት ዓመት ጀምሮ ጣሊያን በሚያወዳድራቸው ጊዜ ከጨዋታው በፊት ባንዲራ አውጥተው ሙሶሎኒን የሚያወድስ መዝሙር እንዲዘምሩ ከጨዋታው በኋላ የጣልያንን ባንዲራ አውርደውና ስመው (የስኳድራ ሹሙ ነው የሚስመው) በክብር እንዲያስቀምጡ ይገደዳሉ፡፡
አንድ ጊዜ ዶቶር ካሩዝ ያደረገው አይረሳቸውም፡፡ አንድ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ደጋፊ በለበሰው ጋቢ ውስጥ የኢትዮጵያ ባንዲራ ይዞ ነበር፡፡ ይህ ወጣት ጥቅምት 19 ቀን 1932 በግራዚያኒ ከተገደሉት ሰዎች አንዱ ነው፡፡ የተገደለው ለአርበኞች መረጃ ያቀብላል መሳሪያ ደብቋል በሚል ነው፡፡ የተያዘው ኳስ ሜዳ ነው ሲፈተሽ የኢትዮጵያ ባንዲራ በጋቢው ስር ይዞ ነበር፡፡ ባንዲራውን ከጋቢው ውስጥ ካወጡት በኋላ ከውድድሩ በፊት እንደተለመደው በኳስ ሜዳው ግራና ቀኝ ሜዳው ጋር ባሉት ቦታዎች ተጋጣሚ ቡድኖች ከጣሊያን ባንዲራ ይሰቅላሉ፡፡ ዋናው ባንዲራ የክብር እንግዶች ከሚቀመጡበት ጀርባ በትልቁ የብረት ዘንግ ላይ ይሰቀላል፡፡ የዚያን ቀን ባንዲራውን ዕጣ የወጣለት ቡድን አምበል ሲሰቅል ዶቶር ካሩዝ ባንዲራ ከሚሰቅለው ተጨዋች አጠገብ ቆሞ ያሰቅል ነበር ፡፡ ካሩዝ የቆመው መሬት ላይ በተነጠፈ የኢትዮጵያ ባንዲራ (ከሰውየው የወሰደው ባንድራ) ላይ ነበር፡፡ ድርጊቱ ሁሉንም ተጨዋቾች ያናደደ ነበር፡፡
ይህ ከሆነ ከጥቂት አመት በኋላ ጣሊያን ሲወጣ ሚያዝያ 26 የተሰባሰቡት ወጣቶች የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዘው ከተቀጣጠሩበት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ቁልቁል ወደ ለገሀር ተመሙ፡፡ ተጨዋቾቹ ሰሞኑን ያሰሩት ባንዲራን በእንጨት ላይ ይዘው እየዘመሩ ሲሄዱ በብዙ ታዳጊ ወጣቶች ታጅቦ ነበር፡፡ ጣሊያን ከወጣ በኋላ እንዲህ እየተዘመረ በብዙ ወጣቶች ታጅቦ ሲሄድ የመጀመሪያው ነበር፡፡ እንዲህ አይነት ነገር ከታየ በጣም ረጅም ጊዜ ነው፡፡
ወጣቶቹ እነዚያ እየዘመሩ ሲያልፉ ከየቤቱ እናቶች በእልልታ አባቶች «አይዟችሁ» እያሉ በማበረታታት ሸኝተዋቸዋል፡፡ እነዚህ የቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣቶች የሚሄዱት አሁን ሴንጅ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ወደሚባለው ስፍራ ነው፡፡ እነሱን ያዩ አንዳንዶቹ በእልህና በቁጭት የጣሊያንን ባንዲራ እስከ ማቃጠል ደረሱ፡፡ የቡድኑ መስራች አቶ አየለ አትናሽ ነገሩን እንዲህ ያስታውሳሉ፡፡
‹‹…ሁሉም ሰው ብዙ ነገር አስታወሰ፡፡ በተለይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ተጫዋቾች ላይ ብዙ ግፍ ተሰርቷል፡፡ ጓደኛዬ ጆርጅ ወህኒ ቤት ታስሯል፡፡ ሌሎች ተጫዋቾቻችን ታስረዋል፤ ተገድለዋል፡፡ እነዚያን ነገሮች ባንዲራ ልንሰቅል ስንሔድ እያስታወስናቸው ነው።» ይላሉ፡፡
በወቅቱ ተጨዋቾቹ መድፈኛ ሜዳ በደረሱ ሰዓት በሩ ላይ አንዱን ባንዲራ ሰቀሉ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ተጨዋቾቹ የሚሰቅሉበት ቦታ ሌላውን አደረጉ፡፡ ከእዚህ በኋላ መሳለሚያ ሔዱ፡፡ እዚያ ለጥቁሮቹ የተዘጋጀ ሜዳ ላይ ገቡ፡፡ የጊዮርጊስ ተጨዋቾች ባንዲራውን ይዘው እዚህ ሲደርሱ በበርካታ ወጣቶች ታጅበው ነው፡፡ ጣሊያኖች እዚህ ሜዳ ላይ የጣሊያንን ባንዲራ የሚሰቅሉት ስመው ዘምረው ነበር፡፡ አሁን ግን እንደዚህ ሆነ፡፡ ያኔ ዶቶር ካሩዝ ያደረገውን አስታውሱ፡፡ የኢትዮጵያ ባንዲራን መሬት ላይ አንጥፎ ላዩ ላይ ቆሞ ረግጦ የጣሊያን ባንዲራ እንዲውለበለብ ያደረገው ነበረ ፡፡ አሁን ደግሞ ተራው የሌላ ነው፡፡
የጣሊያን ባንዲራ ሲሰቀልበት የነበረው ቦታ ከእንግዶች መቀመጫ ጀርባ ባለው የብረት ዘንግ ላይ ሲሰቀል አካባቢው በጩኸት ተደበላለቀ፡፡ ሁካታና ፉጨት ነበር፡፡ባንዲራውን የሚያወጣው አየለ ነው፡፡ ቀስ ብሎ ነው የሚሰቅለው፡፡ ባንዲራዋ ወደ ላይ ስትወጣ የተሰበሰቡት ወጣቶች ፉጨትና ጩኸት ሊያቋርጥ አልቻለም፡፡ አጠገቡ የነበሩት እነዶጮና ተስፋዬ መሬት ላይ የዘረጉት የጣሊያን ባንዲራ ላይ በእግራቸው እያሹ ከጭቃው ጋር እየለወሱት ነበር፡፡ ይሄ ሲሆን ዶቶር ካሩዝን አስታወሱት፡፡ ብዙዎቹን የጊዮርጊስ ተጨዋቾች ጣሊያኖች በባንዲራው ሲቀልዱ አንድ ቀን ይሄ ይለወጣል ሲሉ ነበር፡፡
ሚያዝያ 26 እዚያው ሜዳ ላይ መሬት የነበረው ባንዲራ ላይ ወጥቶ ሲውለበለብ ላይ የነበረው ባንዲራ መሬት ላይ ተገኘ፡፡ የብዙ ወጣቶች ወሬ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአርበኞቹ የሰጠው ድጋፍ ለኢትዮጵያ አንድነት ያበረከተውን ሚና እያሞገሱ ከዚህ በኋላ ከክለቡ ጐን ለመቆም ቃል የገቡበት ጊዜ ነበር፡፡ ይሄ የሆነው ሚያዝያ 26 ቀን ነው፡፡ በነጋታው ሚያዝያ 27 ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ የኢትዮጵያን ባንዲራ በመላው ሐገሪቱ በክብር እንዲውለበለብ አደረጉ፡፡ ይሄ ቀን የተመረጠው ጣሊያን አዲስ አበባ ገብቶ ባንዲራውን ያውለበለበው በዚሁ ቀን በመሆኑ ነው፡፡
ከዚህም ጊዜ በኋላ የመጀመሪው ኢትዮጵያዊ የእግርኳስ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚገጥሙትን ፈተናዎች እያለፈ መኖሩን ታሪክ ይነግረናል፡፡
( ከቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የተገኘ)

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P