ባለፉት ተከታታይ ዓመታቶች በሜዳ ላይ ምርጥ የኮስ ብቃቱን ሊያሳየን ችሏል፤ በብዙዎቹ የእግር ኳስ አፍቃሪዎችም ከፍተኛ አድናቆትን ሊያተርፍም ችሏል፤ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለክለቡ ወልቂጤ ከተማ በመጫወት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያሳየ የሚገኘውና ቡድኑንም በጥሩ ሁኔታ እየጠቀመ ያለው አብዱልከሪም ወርቁ ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር ስለ ቡድናቸው ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ፣ በካሜሩን በሚገኘው የዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ ባለመካተቱ፣ ስለ ብሄራዊ በቡድናችን ሊያስመዘግቡት ስለሚችሉት ውጤትና ከራሱ አቋም ጋር በተያያዘ ቃለ-ምልልስን አድርገንለት ተጨዋቹ የሚከተለውን ምላሽ ሊሰጠን ችሏል፤ ምልልሳችንም እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ሊግ፦ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ከተቋረጠ በኋላ የእረፍት ጊዜህን እቤትህ በመቀመጥ እያሳለፍክ ነው?
አብዱልከሪም፦ ወይ መቀመጥ፤ መቀመጥ ምን ያደርጋል፡፡ ይሄ ውድድር እኮ ገና አላለቀም ብዙ ግጥሚያዎችም ይቀሩታል፡፡ ከተቀመጥክማ በሰውነት ላይ የመጨመር ነገሮች ስለሚኖሩ እኔ በትንሹም ቢሆን የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በመስራት ላይ ነው የምገኘው፡፡
ሊግ፦ በዘጠኝ ሳምንቱ የሊጉ ጉዞ ከመሪው ፋሲል ከነማ በ3 ነጥብ በማነስ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ችላችዋል፤ ያስመዘገባችሁት ውጤት ምርጥ ነው ማለት ይቻላል?
አብዱልከሪም፦ አዎን፤ የእኛ ቡድን የሚቀረው ነገር ቢኖርም በውጤት ደረጃ ያስመዘገብነውን ውጤት ስንመለከት ግን ውጤታችን ጥሩ ነው፤ በቀጣይ እየተሻሻልን ስንመጣ ደግሞ ከእዚህ የሚሻል ስኬት የምናስመዘግብ ይመስለኛል፡፡
ሊግ፦ ወልቂጤ ከተማን እንደ ወቅታዊ አቋሙ ስትመለከተው በአንተ አንደበት እንዴት ነው የሚገለፀው?
አብዱልከሪም፦ ብዙ ጊዜ ወጥ የሆነ አቋም የለንም፤ ከዛም ውጪ የራሳችን የምንለውም የምንጫወትበትን መንገድ ገና አልያዝንምና እዛ ላይ በትኩረት መስራት አለብን፡፡
ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮ ተሳትፎአችሁ ቡድናችሁ ምን ውጤትን ሊያስመዘግብ ይችላል?
አብዱልከሪም፦ አብዛኛው የስፖርት ቤተሰብ ዓምና ከሊጉ ላለመውረድ ስንጫወት ከነበረበት ሁኔታ በመነሳት አሁን ላይ ያስመዘገብነውን ውጤት ላይጠብቅ ቢችልም እኛ ግን በስኬት ጉዞው ላይ በጥሩ መልኩ እየተራመድን በመሆኑ ዘንድሮ ባለን ስብስብ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ውጤት የምናስመዘግብ ይሆናል፡፡
ሊግ፦ ወልቂጤ ከተማ ምርጥ የተጨዋቾች ስብስብ ነው ያለው?
አብዱልከሪም፦ አዎን፤ በጣም ምርጥ ስብስብ ነው ያለን፤ ስብስቡም ከፍተኛ ውጤት ማምጣት የሚችል ነው፡፡
ሊግ፦ ባላችሁ የተጨዋቾች ስብስብ ብቻ ውጤቱን የምታመጡ ይመስልሃል?
አብዱልከሪም፦ ስብስብ ብቻማ ውጤት አያመጣም፤ ወጥ የሆነ አቋም መያዝና የራሳችን የምንለው አጨዋወትም ሊኖረን ይገባል፡፡
ሊግ፦ ይሄን በቀጣይ ዙር ጨዋታዎች ላይ ከቡድናችሁ እንጠብቅ?
አብዱልከሪም፦ በትክክል፤ ምክንያቱም ያለህን ክፍተት ካወቅህ በእዛ ላይ ጠንክረህ ስራህን ትሰራለህ፤ ያኔም የሚታረሙ ነገሮች ስለሚኖሩ የምትፈልገውን ውጤት ታመጣለህ፡፡
ሊግ፦ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዘንድሮ በምን መልኩ አገኘኸው?
አብዱልከሪም፦ የእዚህ ዓመት የውድድር ፉክክርን በክለቦች መካከል ብዙም ልዩነትን ያላየሁበት ነው፤ በተለይ የሐዋሳ ዩንቨርስቲ የመጫወቻ ሜዳው ለምታደርገው እንቅስቃሴ አለመመቸት መቻሉ ሁሉንም ክለቦች እኩል አድርጓቸዋልና ይሄንን ነው ላስተውል የቻልኩት፡፡
ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ አስፈሪ ቡድን የለም እያልክ ነው?
አብዱልከሪም፦ በእስካሁኑ የውድድር ጉዞ አፌን ሞልቼ መናገር እችላለው አዎን አስፈሪ ቡድንን አልተመለከትኩም፤ ሜዳው ሁሉንም ክለብ አስፈሪ ሳይሆን እኩል አድርጎታል፡፡
ሊግ፦ የመጫወቻ ሜዳው ሲቀየርና አሪፍ ሲሆንስ የትኛው ቡድን አስፈሪ ይሆናል?
አብዱልከሪም፦ ከእዚህ ቀደምም ተናግሬያለው፤ አሁንም ልድገመው ጨዋታዎቹ በተመቻቹ ሜዳዎች ላይ ከተከናወኑ ፋሲል ከነማ የያዘው ስኳድ ምርጥ ስለሆነ አስፈሪ የሚሆነው ቡድን እሱ ነው፤ በተለይም ደግሞ የእዚህ ቡድን ተጨዋቾች የአብሮነት ቆይታም ስላላቸው ያ ሁኔታም አስፈሪነታቸውን ይበልጥ የሚጨምርላቸውም ይመስለኛል፡፡
ሊግ፦ በወልቂጤ ከተማ ክለብ ውስጥ ምርጥ ብቃትህን ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ብታሳይም ወደ አፍሪካ ዋንጫ ባመራው የዋልያዎቹ የተጨዋቾች ስብስብ ውስጥ ግን ለመካተት አልቻልክም፤ ባለመመረጥህ ተቆጭተሃል?
አብዱልከሪም፦ አዎን፤ ማንኛውም እግር ኳስ ተጨዋች ለብሔራዊ ቡድን ተመርጦ መጫወትና እንደ አፍሪካ ዋንጫ ባሉ ትላልቅ የውድድር መድረኮች ላይም ተገኝቶ የሀገሩን ባንዲራ በመወከል መሳተፍ መቻል የሚሰጥህ እርካታ አለና ሳትኖር ስትቀር ሰው ነህና የሚሰማህ የቁጭት ስሜት አለ፡፡ ያም ቢሆን ግን ያን የቁጭት ስሜት ወደ ጎን አድርጌ በቀጣይ ለሚኖረው የብሄራዊ ቡድን ለመመረጥ ጠንክሬ ነው የምሰራው፡፡
ሊግ፦ በካሜሩን አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ዋልያዎቹን በምን መልኩ እንጠብቃቸው?
አብዱልከሪም፦ የእኛን የውድድር ተሳትፎ በካሜሩን የምጠብቀው በኳሱ እንቅስቃሴ ብዙዎቹን በሚስብ መልኩ የምንቀርብበትና በውጤት ደረጃም የቶርናመንቱ ክስተት በሚባል ደረጃ ጥሩ ነገርን ያሳዩናል ብዬ ነው ከወዲሁ የምገምተው፡፡
ሊግ፦ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ከስምንት ዓመት በፊት ደቡብ አፍሪካ አስተናግዳው ወደነበረው ውድድር ማለፍ ችለን ነበር አሁን ደግሞ ወደ ካሜሩን ልናልፍ ችለናል፤ ማለፊያ የሆኑትን ጨዋታዎች የት ሆነህ ነበር የተከታተልካቸው? ስናልፍስ የነበረህ ስሜት ምን ይመስላል?
አብዱልከሪም፦ ለአፍሪካ ዋንጫው ከ31 ዓመታት በኋላ ስናልፍ ከሱዳን ጋር የነበረንን እና ያሸነፍንበትን ጨዋታ የተመለከትኩት በወቅቱ ልጅ ስለነበርኩ በብሄራዊ ቲያትር አካባቢ በተሰቀለ ስክሪን ላይ ነበር፤ ያኔ ጨዋታውን በስክሪን ላይ ሳይም አንድ ቀን የእዚሁ ቡድን አባል እሆናለው እያልኩ በማሰብና ያሸነፈችው ደግሞ ሀገርም ስለሆነች ሁሉም ሰው ነው ተደስቶ የጨፈረው፤ የእኔም ደስታ ልዩ ነበር፡፡ አሁን ወደ ካሜሩን ያለፈውን ቡድን ጨዋታ የተመለከትኩት ደግሞ በድሬዳዋ ከተማ ላይ ሆኜ ነበር፡፡ ይህን ጨዋታ እኛ በኮትዲቭዋር ብንሸነፍበትም ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ የኒጀርንና የማዳጋስካርን ውጤት መጠበቅ ስለነበረብንም በአጠቃላይ የምድቡ ውጤት እኛ ተሽለን ስለተገኘን ኮትዲቯርን በመከተል ልናልፍ ችለናልና በእዚሁም በጣም ነው ደስተኛ የሆንኩት፡፡
ሊግ፦ ዋልያዎቹን በእግር ኳስ ደረጃቸው ከፍ ካሉት ሀገራት ጋር ስታነፃፅራቸው እንዴት ነው የምትገልፃቸው ?
አብዱልከሪም፦ አሁን አሁን እንደበፊቱ ብዙ ልዩነት የለንም፤ ይህን በሜዳ ላይም ልናስመለክት ችለናል፡፡ ከእዚህ በኋላም በእነሱ ደረጃ ላይ ለመቀመጥና በተሻለ ደረጃ ላይም ለመገኘት ደግሞ ካሉብን ችግሮች መካከል በስነ-ልቦናው ብቁ መሆን መቻልና ጠንክሮ የመስራት ችግርም አለብንና እዛ ላይ ትኩረት ልናደርግና በደንብ አድርገንም ልንሰራበት ይገባል፡፡
ሊግ፦ በእግር ኳስ ተጨዋችነትህ የት ድረስ መጓዝ ነው እልምህ?
አብዱልከሪም፦ በእግር ኳሱ ሁሌም ራሴን የማስበው በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ከሀገር ወጥቶ ስለመጫወትና ለብሄራዊ ቡድንም በመመረጥ ስኬታማ ግልጋሎትን ስለመስጠት ነው፤ ይሄንም
ራዕዬን አሳካለው፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ አሁን በደረስክበት ደረጃ በርታና ጠንክር በማለት ዕለት ከዕለት ምክራዊ አስተዋፅኦን የሚያደርግልህ አካላቶች አሉ?
አብዱልከሪም፡- ይህን በማድረግ በኩል እስካሁን ከቤተሰቦቼ ውጪ ብዙም አልገጠመኝም፤ በእግር ኳስ ተጨዋችነቴ በአብዛኛው እዚህ ደረጃ ላይ የደረስኩት በራሴ ከፍተኛ ጥረት ነውና ይህን ነው ለማለት የምፈልገው፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ህይወትህ ደስተኛ ነህ?
አብዱልከሪም፡- በጣም፤ ግን ብዙ የሚቀሩኝ ነገሮች አሉ፡፡
ሊግ፡- ወልቂጤ ከተማን አጠር ባለ መልኩ ስትገልፀው?
አብዱልከሪም፡- ይሄ ቡድን ለእኔ የኳስ ህይወት ትልቁን አስተዋፅኦ ያደረገልኝና አንድ እርምጃም ወደፊት እንድጓዝ ያደረገኝ ነው፤ ክለቡን እንደ ቤቴ ስለምቆጥረውም የቡድኑን አመራሮችና ደጋፊዎቻችንን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡
ሊግ፡- በወልቂጤ ከተማ ክለብ ውስጥ በጣም አዝናኙና ቀልደኛው ተጨዋች ማን ነው?
አብዱልከሪም፡- አልዓዛር ዘውዴ እሱ ካለ ጨዋታ አለ፡፡
ሊግ፡- አኩራፊውና ዝምተኛው ተጨዋችስ?
አብዱልከሪም፡- አኩራፊው አህመድ ሲሆን ዝምተኛው ደግሞ እኔው ነኝ፡፡
ሊግ፡- በወልቂጤ ከተማ ካምፕ ውስጥ የቡድን አጋር ጓደኛህ ማን ነው?
አብዱልከሪም፡- የእኔ የቅርብና የካምፕ ጓደኛዬ ረመዳን ናስር ነው፤ ከእሱ ጋር ከኳሱ ውጪም አብረን ነው ጊዜያችንን የምናሳልፈው፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ……?
አብዱልከሪም፡- የብሔራዊ ቡድናችን በካሜሮን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ የተሻለ የሚባል ነገርን ያሳያሉ ብዬ የምጠብቅ ሲሆን መልካም የሚባል ውጤትን እንዲያመጡም እመኛለሁ፡፡