ኤልያስ አህመድ /አዲስ አበባ ከተማ/
“ዋንጫው ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ያመራል፤ እኛም ከሊጉ አንወርድም”
“በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ እስካሁን ጎልቶ የወጣ ተጨዋች የለም”
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮ ሻምፒዮና አዲስ አበባ ከተማ በቀሪዎቹ ዘጠኝ ግጥሚያዎች ላይ የሚጠበቅበትን ውጤት አስመዝግቦ በሊጉ ላይ እንደሚቆይ የቡድኑ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች የሆነው ኤልያስ አህመድ ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ አስተያየቱን ሰጥቷል፤ በ22ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር 3-3 ለመለያየት የቻለው አዲስ አበባ ከተማ በሊጉ ላይ እያደረገ ስላለው የውድድር ተሳትፎ እና በሌሎች ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ኤልያስ አህመድ ከጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር ያደረገው ቆይታም የሚከተለውን ይመስላል፡፡
በቅድሚያ ኢድ ሙባረክ
“አመሰግናለው”፡፡
በዓሉ እንዴት አለፈ
“በዓሉ የተከበረው የጨዋታ ቀን ቢሆንም በጥሩ ሁኔታ ነው ያሳለፍኩት፤ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር የነበረንን ግጥሚያም ካጠናቀቅን በኋላም ወደ ቤቴ ሄጄም ነው ከቤተሰቦቼ ጋር ላሳልፍ የቻልኩት”፡፡
ፆሙን ስላሳለፈበት መንገድ
“ጾሙ ለአንድ ወር ያህል ነበር የቆየው፤ ይሄም ጾም ሊፈጥንብኝም ችሏል”፡፡
በሶስቱ ከተሞች ላይ ስለነበራቸው የውድድር ቆይታ
“በአዳማ ቆይታችን የአቻ ውጤትን ነበር ያበዛነው፤ አንድ ጨዋታም ልናሸንፍና ልንሸነፍ ችለናል፤ ሐዋሳ ላይ ደግሞ ጥሩ ነበርን፤ በድሬዳዋ ቆይታችን ደግሞ ያልተሳካ ጊዜን ነበር ለማሳለፍ የቻልነው”፡፡
በእስካሁኑ የውድድር ቆይታቸው ምርጡ ሜዳ
“ምርጡ ሜዳማ የአዳማው ነው፤ ሁሉም ተመችቶት ሊጫወትበትም ችሏል”፡፡
የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማን በሻምፒዮናነት ያጠናቅቃል
“ዋንጫውማ ያለምንም ጥርጥር ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ነው የሚያመራው”፡፡
በውድድሩ ቆይታቸው ስለነበራቸው ጠንካራ እና ደካማ ጎን
“ጠንካራው ጎናችን ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ጋር መድረሳችን ነው፤ ብዙ ጎልም አግብተናል፤ ወደ 20 የሚደርሱ ጎሎችንም አግብተናል፤ ደካማ ጎናችን ደግሞ ጎሎች ይገባብናል፤ ግብ ጋር እየደረስንም የምንስተው ኳስ አለ፤ እነዚህን ክፍተቶች ልናሻሽላቸውም ይገባል”፡፡
ለአዲስ አበባ በጣም አስቆጪ ስለነበረው ጨዋታ
“ያስቆጩን ግጥሚያዎች በጣም ብዙ ናቸው፤ በተለይም ደግሞ ከአዳማ ከተማ ጋር ስንጫወት በ97ኛው ደቂቃ ላይ የገባብንና ድሬዳዋ እያለንም ደግሞ ከወላይታ ዲቻ ጋር ስንጫወት ባለቀ ሰዓት ጎል የተቆጠረብን ሁኔታ የሚያስቆጩን ናቸው”፡፡
በባህርዳር ከተማ ላይ ስለሚኖራቸው የውድድር ቆይታ
“አሁን ላይ ቡድናችን አሁን አሪፍ እየሆነ ነው፤ በጥቃቅን ስህተቶችም ነበር ነጥብ ስንጥል የነበርነው፤ ባህርዳር ላይ ደግሞ ሜዳው ለጨዋታ ምቹ ስለሆነ ጥሩ የውድድር ቆይታ ይኖረናል ብዬም ነው የማስበው”፡፡
አዲስ አበባ ከተማ ከሊጉ ይወርዳል….ወይንስ በሊጉ ላይ ይቆያል…..
“በእዛ ቀጠና ውስጥ ያሉት አብዛኛው ቡድኖች በተቀራረበ ነጥብ ላይ ነው የሚገኙት፤ የአንድ እና የሁለት ጨዋታም የነጥብ ልዩነት ኖሯቸውም ነው ሊጉን እየተፎካከሩበት የሚገኙት፤ ስለዚህም ካሉት ዘጠኝ ግጥሚያዎች አኳያም እኛ ጥሩ ውጤትን ስለምናስመዘግብ በእርግጠኝነት በሊጉ ላይ እንቆያለን”፡፡
ስለ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የእስካሁን የውድድር ቆይታና የትኛው ቡድን ምርጡ እንደሆነ
“ሊጉ በጣም አሪፍ ነው፤ ምርጡና ጠንካራው ቡድንም እስካሁን ያልተሸነፈው ቅ/ጊዮርጊስም ነው”፡፡
ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ስለነበራቸውና ግጥሚያውን መርተውም አቻ ስለተለያዩበት ጨዋታ
“ግጥሚያውን ሶስት ጊዜ መርተን ነው አቻ የተለያየነው፤ በጣም ከባድ ጨዋታንም ነው ያደረግነው፤ ያም ሆኖ ግን በእኛ መዘናጋትና ክፍተት በመጨረሻም አቻ ልንለያይ ችለናል፤ ውጤቱም የሚያበሳጭ ሆኖብናል”፡፡
ስለተጋጣሚያቸው ሀድያ ሆሳዕና
“ሀድያ ጥሩ እና ጠንካራ ቡድን ነው፤ ኳስንም በጥሩ ሁኔታ ይጫወቱታል”፡፡
በዘንድሮ የሊጉ ውድድር በጣም ምርጡ እና ጎልቶ የወጣው ተጨዋች
“ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች አሉ፤ ያም ሆኖ ግን በጣም ጎልቶ እና ነጥሮ የወጣን ተጨዋች ግን እስካሁን አላገኘሁም”፡፡
ስለ አውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች እና የውድድሩን ዋንጫ ማን እንደሚያነሳ
“ጨዋታዎቹ በጣም ምርጥ ነበሩ፤ ሪያል ማድሪድ በእዚህ ውድድር ላይ ብቻ ሳይሆን በላሊጋውም ላይ የተሻለ ቡድን ሆኖ ቀርቦብኛልና የቻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ ጠንካራና ከባድ በሚሆነው ግጥሚያ ሊቨርፑልን በማሸነፍ የሚያነሳ ይመስለኛል”፡፡
እናጠቃል
“አዲስ አበባ ከተማ እንደ ከተማው ትልቅ የሆነ ቡድን ነው፤ ይሄን ቡድንም በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮ ውድድር በሊጉ ላይ እንዲቆይ አድርገን የመጪው ዓመት ጠንካራ የዋንጫ ተፎካካሪ እናደርገዋለን”፡፡