በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ለተቀላቀለው ሀዲያ ሆሳዕና በአማካይ ስፍራ የሚጫወተው ሱራፌል ጌታቸው ስለ ክለቡ፣ ስላሰለፈው የኳስ ህይወትና ሌሎችን ጥያቄዎች ጠይቀነው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፡፡
ሊግ፡- የፕሪ-ሲዝን ዝግጅታችሁን ረቡዕ ዕለት ጀምራችኋል፤ እንዴት አገኘኸው?
ሱራፌል፡- የሀድያ ሆሳዕና የፕሪ ሲዝን ዝግጅት በክለቡ የቀሩ 9 ያህል ነባር ተጨዋቾችን በመያዝ እና ለቡድኑ የፈረሙ አዳዲስ ተጨዋቾችን በማካተት በጥሩ መልኩ የጀመረ ሲሆን በተከታታይ ቀናት ደግሞ ሌሎች ፊርማቸውን የሚያኖሩ ልጆችን በመጨመር የልምምዱን ሂደት በተጠናከረ መልኩ ይሰራል፡፡
ሊግ፡- ሀድያ ሆሳዕና ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲገባ በሱራፌል ውስጥ ምን አይነት የደስታ ስሜት ነው የተፈጠረው?
ሱራፌል፡- ሆ! ሀድያ ሆሳዕና ባሳለፍነው ዓመት ባካሄደው የከፍተኛው ሊግ ውድድር የምድቡ አሸናፊ በመሆን የፕሪምየር ሊጉን ሲቀላቀል በእኔ ውስጥ የተፈጠረው የደስታ ስሜት ከምነግርህ በላይ በጣም ከፍ ያለና ልዩ የሆነም ነበር፤ ቡድኑን የግማሽ አመት ላይ የተቀላቀልኩና በእነዚያ ጊዜያቶችም ውስጥ ለቡድኑ ጥሩ ጥቅምና ግልጋሎትንየሰጠሁበት አጋጣሚም ስለነበር እንዲህ ያለ የደስታ ስሜትም ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡
ሊግ፡- ሀድያ ሆሳዕናንከአዳማ ከተማ ክለብ በመምጣት ነው የተቀላቀልቀው፤ ወደ ቡድኑ ስትመጣ ምን አይነት አቀባበል ነበር የተደረገልህ? ከክለቡ ቆይታህ በኋላስ በግልጋሎትህ ምን አይነት ምላሽን አገኘህ?
ሱራፌል፡- አዳማ ከተማን በመለያየት ወደ ሀድያ ሆሳዕና ስመጣ የተደረገልኝ አቀባበል በጣም ጥሩና አጥብቄም የወደድኩት ነው፤ በተለይ ደግሞ አሰልጣኙ ግርማ /መንቾ/ የእኔን የሜዳ ላይ ብቃት በደንብ አድርጎ ያውቅና በእኔም ላይ ጥሩ እምነት ያለው ባለሙያ በመሆኑ በክለቡ ቆይታዬ ነገሮችን ሁሉ ሊያቀልልኝም ችሏል፡፡
የሀድያ ሆሳዕናን ክለብ ከተቀላቀልኩበት ያለፈው ሲዝን ግማሽ አመት ጀምሮም በቡድኑ የነበረኝ ተቀባይነትም ከፍተኛ ነበር፤ በጊዜው በእያንዳንዱ ጨዋታዎች ላይ ስኬታማና ውጤታማ ብቃቴን ሳሳይ ነበር፤ ይሄ ደግሞ በቡድናችን አሰልጣኝም ሆነ በክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ እምነት እንዲጣልብኝ ያደረገ በመሆኑ በከፍተኛው ሊግ ዓምና ያሳለፍኩት የውድድር ዘመን ለዘንድሮው የፕሪምየር ሊግ ውድድር ለእኔ ከፍተኛ ብርታትና ጥሩ ስሜትን የሚሰጠኝ ይሆናልና በእዚህ መልኩ ኳሱን ተጫውቼ ማለፌ በጣሙን አስደስቶኛል፡፡
ሊግ፡- ሀድያ ሆሳዕና ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ምርጡና ጥሩ ቡድን ነበር? ወይንስ በተቃራኒው?
ሱራፌል፡- ጥሩ ቡድን ነበርን እንጂ! ለእዛም ምክንያቶችን ማስቀመጥ ይቻላል፤ የኢትዮጵያ ከፍተኛው ሊግ ላይ አምና ቡድናችን ራሱን በወጣት ተጨዋቾች ነበር የገነባው፤ በእዛ መልኩም ተጫውቶ በሜዳ ላይ ጥሩ መንቀሳቀሱና ወደ ፕሪምየር ሊጉም ከምድቡ በቀዳሚነት ማለፍ መቻሉ ምርጥ ቡድንነቱን አሳይቷልና ይሄን ነው ለማለት የምፈልገው፡፡
ሊግ፡- ሀድያ ሆሳህና ዘንድሮስ….?
ሱራፌል፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት በአሁን ሰዓት ክለባችን ጥሩ ችሎታና ክለቡንም ሊጠቀሙ የሚችሉ ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾች እያስፈረመ ይገኛል፤ ይሄን አሳካን ማለት በክለቡ ውስጥ ያለነው ነባርና ቡድኑን በሚገባም የምንጠቅመው ልጆች አለንና የዘንድሮው የውድድር ዘመን ላይ የሚኖረን ቡድን ለእኔ ጥሩ የሚሆን ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- አንድአንዶች የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ዘንድሮ ከመቀላቀላችሁ አኳያ ልትቸገሩ እንደምትችሉ ግምትን እየሰጡ ይገኛል?
ሱራፌል፡- ልምምዳችንን ጠንክረን ከሰራን እና ዓመቱን ሙሉ ከለፋን ለምን እንቸገራለን፤ ደግሞም እኛ የመጣነው ከፍተኛ ፉክክርና እልህ አስጨራሽ ግጥሚያ ከሚደረግበት የከፍተኛው ሊግና ተፈትነንም የመጣን ስለሆነ ከዛ ባሻገር ደግሞ አሁን ላይ ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾችንም በስኳዳችን የያዝን በመሆኑ በሊጉ ጥሩ ውጤት እንደምናመጣ አልጠራጠርም፡፡
ሊግ፡- በሙገር ሲሚንቶ የተጨዋችነት ቆይታህ ምርጥ እና ጥሩ ጊዜን ለማሳለፍ ችለሃል፤ ስለዚያ ቡድን ትውስታ ዛሬ ላይ ሆነህ ምን የምትለው ነገር ይኖርሃል?
ሱራፌል፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግየተጨዋችነት ቆይታው ላይ በሙገር ሲሚንቶ ቡድን ውስጥ ተጫውቶ ያሳለፈ ማንኛውም ተጨዋች በክለቡ በነበረበት ጊዜ የራሱ የሆነ ትውስታ አለው፤ እኔም በእግር ኳስ ተጨዋችነቴ ከነገሌ ቦረና መጥቼ በነበርኩበት ጊዜ ያሳለፍኳቸውን ጊዜያቶች መቼም ቢሆን አልረሳቸውምና ለሙገር የተለየ ቦታ ነው ያለኝ፤ ከዛ ውጪም ሙገርን ተጫውቼና ጥሩ ጊዜም ያሳለፍኩበት ቡድን ስለሆነም ክለቡን በቀላል ቃላቶችም ብቻ የምገልፀው አይደለም፤ ሙገር እናት የሆነ ቡድን ነው፤ የሙገርን ጥሩነት የምታውቀውም ክለቡን ለቅቀህ ስትወጣ ነውና ያ ስኬታማ የተጨዋችነት ጊዜን ያሳለፍኩበት የቀድሞው ቡድኔ ሲፈርስ በጣም ነው ያዝንኩትና ይሄ ቡድን ተመልሶ ተቋቁሞ ባየው ምኞቴና ደስታዬም ነው፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጨዋችነት ቆይታህ ለአንተ አስደሳች እና አስከፊ የሚባሉት ጊዜያቶችህ የትኞቹ ናቸው?
ሱራፌል፡- በተጨዋችነት ዘመኔ አስደሳች የምለው ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ /ድሬ/ ይሰለጥን ለነበረው የኢትዮጵያ ታዳጊ ብሄራዊ ቡድን ስመረጥና ከቱኒዚያ አቻችንም ጋር ባደረግነው ጨዋታ ጥሩ ለመንቀሳቀስ የቻልኩበትን አጋጣሚ ነው፤ በአስከፊነቱ የምጠቅሰው ደግሞ ለአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር እግር ኳስ ቡድን ለመጫወት ፊርማዬን ካኖርኩ በኋላ ለክለቡ በበርካታ ጨዋታዎች ላይ ለመሰለፍና ቡድኑንም ለማገልገል ስንቅን ሰንቄ ያጋጠመኝ የእግር ጉዳት የህልሜን እንዳላሳካ ስላደረገኝና የክለቡም አመራሮች ከእኔ ጎን መቆም ሲገባቸው ለአንድም ጊዜ ዞር ብሎ ካለማየትና ለእኔም ምንም አይነት ጥቅምን ሳያደርጉልኝ ከክለቡ ለመቀነስ የሄዱበት መንገድ ጥሩ ስራን እንዳልሰሩ አመላክቶኛልና ያ በጊዜው በጣም ያሳዘነኝ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን እኔ መብቴን ለማስከበር የሄድኩበት መንገድ በድል አድራጊነት ለማጠናቀቅ የቻልኩበት ጊዜ ነበርና ያ አልፎ አሁን ላይ በሀድያ ሆሳዕና ክለብ ውስጥ ጥሩ ቆይታን እያሳለፍኩ ነውና የምገኘው በእዚህ ሁኔታ ላይ መገኘቴ በጣሙን አስደስቶኛል፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ?
ሱራፌል፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ አሁን ላይ እየተጓዘ ያለበት መንገድ ለማናችንም በጎና ጥሩ ጎን የለውም፤ ያ ስለሆነም የዘንድሮ ውድድራችንን ራሳችንን ከፖለቲካና ከዘር ነፃ በማድረግ ኳስና ኳስን ብቻ መሰረት አድርገን ብንጫወት መልካም ይመስለኛል፤ ኳስ ጨዋታ ሁሉንም ነገር የሚያስታርቅ ስፖርትም ነውና ሊጋችንን በሰላማዊ ውድድር እንድንመራው ምኞቴ ነው፡፡ ከዛ በተረፈ የእግር ኳስን ተጫውቼ ባሳለፍኩባቸው የእስካሁኑ አመታቶች ላይ እዚህ ደረጃ ላይ እንድደርስ ያደረጉኝን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ የመጀመሪያው ፈጣሪዬ ነው፤ ከዛ ቤተሰቦቼ፣ በመቀጠል በሙገር ያሰለጠኑኙን ግርማ ሀ/ዮሃንስ እና ጨፍቅ ካሳን እንደዚሁም ደግሞ ከልጅነቴ ጀምሮ ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች አመሰግናለሁ፡፡