የወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲው የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች ደስታ ደሙ ክለባቸው በቀጣዩ የሊጉ ጨዋታዎች ውጤታማ ሆኖ ሊጉን ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ባለው ደረጃ ላይ እንደሚያጠናቅቁ ገልፀዋል፡፡
የወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ክለብ የሊግ ውድድሩን እያከናወነ ባለበት የአሁን ሰዓት ላይ ለቡድኑ ጥሩ
እንቅስቃሴ ከሚያደርጉት ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ደስታ ደሙ ኳስን ተወልዶ ባደገበት የወንጂ ከተማ ላይ
የጀመረ ሲሆን በቤተሰቦቹም ውስጥ ከሚገኙት አንድ ወንድሙ፣ አንድ እህቱና ከቤተሰቦቹም መካከል የመጨረሻው ልጅ እና
ብቸኛው የእግር ኳስ ተጨዋችም ነው፤ የወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲን የሊግ ተሳትፎን እና የራሱንም የኳስ ህይወት
አስመልክቶ ከደስታ ደሙ ጋር ቆይታን ያደረግን ሲሆን ተጨዋቹም ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሾቹን ሰጥቷል፡፡
የወልዋሎ አዲግራት ወቅታዊ አቋም
“ወልዋሎ አዲግራት አሁን ላይ ጥሩ ኳስን ይጫወታል፤ ተደጋጋሚ ውጤቶችንም እያስመዘገበ በመምጣት አሁን ላይ ያለበትን የደረጃ ሰንጠረዥ እያሻሻለ ይገኛል”፡፡
የወልዋሎ አዲግራት ጠንካራ እና ደካማ ጎን
”የወልዋሎ ጠንካራ ጎን ኳስን ጥሩ መጫወቱ እና በመከላከሉም ላይ አስተማማኝ ሆኖ መታየቱ ነው፤ ድክመቱና ክፍተቱ
ደግሞ ወደ ግብ ብዙ ሙከራን አናደርግም፤ የምናገኛቸውን የግብ እድሎችም ባለመጠቀም ግብም አናስቆጥርም”፡፡
የወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ ቡድን ከ1ኛው ዙር በተሻለ አሁን ላይ መሻሻልን ስለማሳየቱ
“የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከ1ኛው ዙር በተሻለ የሁለተኛው ዙር ላይ ለውጥን ለማምጣት የቻልንበት ዋናው
ምክንያት ግጥሚያዎችን የማሸነፍ ፍላጎታችና ተነሳሽነታችን በጣም መጨመሩ ነው፤ በፊት ጎል አናገባም ነበር አሁን ላይ
ግን እናገባለን”፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በምን ውጤት እንደሚያጠናቅቁ
“ወልዋሎ አዲግራት
ዩንቨርሲቲ የፕሪምየር ሊጉ ውድድር ሲጀመር እቅዱ የነበረው የሻምፒዮና ውድድሩን ከ1-5 ባለው ደረጃ ላይ ሆኖ
መጨረስ ነበር፤ የመጀመሪያ ዙር ላይ ውጤት ስናጣ ያ አይሳካ ይሆናል ብለን ብናስብም አሁን ላይ መልሶ ውጤታችን
ተስተካክሎ ስለመጣ ወደዚያ ለመምጣት ጥረትን እያደረግን ይገኛል፤ እና አሁን ላይ እስከ 6ኛ ያለውን ደረጃ ይዘን
ለመፈፀም ጥረቶችን እናደርጋለን”፡፡
የደደቢት ቡድንን ስለማሸነፍ
“ወልዋሎ አዲግራት የሜዳው ላይ ጨዋታውን ያሸነፈው በጥሩ የአሸናፊነት መንፈስ ወደሜዳ ስለገባ ነው፤ ይሄም ድል ይቀጥላል”፡፡
የእግር ኳስን ተጫውቶ ስላሳለፈባቸው ክለቦች እና ከቡድኖቹ ጋር ስለነበረው ቆይታ
“የሙገር እና የደደቢት ክለቦች የእግር ኳስንቀድሜ የተጫወቱካባቸው ቡድኖች ናቸው፤ ሙገር ከወጣት ቡድኑ አንስቶ
አድጌ የተጫወትኩበት ሲሆን በፕሪምየር ሊጉም በከፍተኛ ሊጉም ደረጃ ቡድኑን በጥሩ ሁኔታ ላገለግል ችያለው፤ ያኔ
በሜዳ ላይ ባሳየሁት ብቃትም ለወጣት ብሔራዊ ቡድን ተመርጬ ነበርና የእኔን የሜዳ ላይ ጥሩነት ይከታተል በነበረው
የደደቢቱ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ፀጋዘሃብ አስግዶም አማካኝነት ወደ ደደቢት እንድመጣ ተደርጌ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ
ጥሩና የተሳካ የውድድር ዓመታትን ላሳልፍ ችያለውና በኳስ ህይወቴ ከሁለቱም ቡድኖችም ጋር ጥሩ ጊዜ ነው
የነበረኝ”፡፡
የእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኑ አስደሳች እና አስከፊ ጊዜያት
“የእግር ኳስን ስጫወት በጣም
የተደሰትኩት ለኢትዮጵያኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን ተመርጬ ማሊ ላይ ጎል ያስቆጠርኩ ቀን ነው፤ ያዘንኩት ደግሞ በ2008
ዓ/ም ላይ የሙገር ተጨዋች በነበርኩበት ሰዓት ከመከላከያ ጋር በነበረን ጨዋታ የእኛ ቡድን ከሊጉ ላለመውረድ እና
ላለመውረድ በሚጫወትበት ሰዓት መከላከያን 1ለ0 አሸንፈን እና የሌላ ቡድን ሜዳ የኤልፓን ጨዋታ ውጤት ደግሞ
መሸነፉን እንደሰማን ከሊጉ አልወረድንም ብለን ስታድየሙን እየዞርን በደስታ ብንጨፍርም የኤልፓ ውጤት ግን ተቃራኒ
ሆኖ ስላገኘነውና የእኛም ከፕሪምየር ሊጉ መውረዳችንን ስናረጋግጥ ያዘንኩትን ሀዘን መቼም አልረሳውም፤ ያኔ በጣም
ነበር ያዘንኩት ያለቅስኩትምና ይሄ ነው አስከፊው የኳሱ ጊዜዬ”፡፡
በቤተሰቡ አካባቢ የታዳጊነት ዕድሜው ላይ የእግር ኳስን ሲጫወት ስለነበረው አመለካከት
“በቤተሰቦቼ አቅራቢያልጅ ሆኜ ጀምሮ ኳስ መጫወቴ ላይ አንድም ቀን ተፅዕኖ አድርገውብኝ አያውቁም፤ እነሱ እንደውም በጣም ነበር የሚያበራታቱኝ”፡፡
የእግር ኳስን ሲጫወት የአየር ላይ ኳስ አጠቃቀሙም ሆነ ተረጋግቶ መጫወቱ ላይ ጥሩ ስለመሆኑ
“የሙገር ክለብ ውስጥ እያለሁ ነው የቢ ቡድን አሰልጣኞቼ የነበሩት ኤልያስ ኢብራሂም እና ፋሲል ቡታ በሚሰጡኝ ጥሩ
የሆነ ስልጠና ብቃቱን የበለጠ ላሻሽል የቻልኩት፤ ያኔ የእኔ የአየር ላይ ኳስ አጠቃቀም ጥሩ ነበር በዛ ላይ
ተጨማሪ ነገርን አሰልጣኞቼ ሲሰጡኝ የበለጠም ጥሩ ሆንኩ”፡፡
በጣም የሚያደንቀው ተጨዋች
“የእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኔ ላይ በጣም የማደንቃቸው እና ለእኔም አርአያዬ የሆኑኝ ተጨዋቾች ከሀገር ውስጥ ስዩም ተስፋዬ ሲሆን ከውጪ ደግሞ ቪዲች ነው፤ ለሁለቱም ልዩ አድናቆት ነው ያከኝ”፡፡
ለኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን ሲጠራ ስለተሰማው ስሜት
“ለኢትዮጵያኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን ስጠራ የተሰማኝ የደስታ ስሜት ከፍተኛ ነበር፤ ሀገሬን ወክዬ መጫወት የሁሌም
ፍላጎቴም ነበርና ያን ማሳካትና ግብ እስለማስቆጠር ደረጃም ላይ ደርሻለው፤ ወደፊትም ለዋናው ብሔራዊ ቡድን ተመርጬ
መጫወትንም ስለምፈልግ ለእዚያ በርትቼ እሰራለው”፡፡
የእግር ኳስ ተጨዋችነት የወደፊት እልሞቹ
“ዋናው እልሜ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋች መሆንና ለሀገሬም ብሔራዊ ቡድን ተመርጬ መጫወት መቻልም ነው”፡፡
የትውልድ ስፍራውን ወንጂ ሲገልፃት
“የእኔ የትውልድ ከተማ የሆነችው ወንጂ ምርጥ ሀገር ነች፤ ከእዚህ ክልል ወጥቼ ለጥሩ ደረጃ መድረስ መቻሌም
ያስደስተኛል፡፡ ያም ሆኖ ግን የብዙ የእግር ኳስ ተጨዋቾች መገኛ የሆነችው ይህቺ ምርጥ ከተማ ዛሬ ላይ ሁኔታዎች
ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆነውባት ብዙ ተጨዋቾችን ወደ እግር ኳስ መንደሩ በስፋት እንዳይመጡባት መደረጓ እንድቆጭ
ያደርገኛል፤ ስለዚህ ክልላችን አሁንም ሰዎችን ማፍራት ትችላለች እና የሚመለከተውም አካል ትኩረት ሊያደርግባት
ይገባል”፡፡
በእግር ኳሱ አሁን ላይ ባለህ አቋም የብቃቴ ጫፍ ላይ ደርሻለሁ ትላለህ….?
“በፍፁም፤ምን ሰርቼ፤ ገና ብዙ ይቀረኛል፤የራሴን ችሎታ በማሻሻል ብዙ የምሰራቸውም ነገሮች አሉና ወደፊት አሁን ያለኝን ብቃት የበለጠ አሻሽዬ ምርጥ የሚባል ችሎታዬን በተደጋጋሚ የማሳይ ይመስለኛል”፡፡
በእግር ኳሱ የሜዳ ላይ ብቃት ማሻሻል የምትፈልገው
“የእግር ኳስ ተጨዋችነቴ ላይ ማሻሻል ከምፈልጋቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ በመከላከሉ ላይ እንቅስቃሴ ብዙ ጊዜ
በአጥቂዎች ጥፋት እየተፈጠረብኝ ዳኞች ጨዋታውን ሳያስቆሙ ሲቀር እኔም የምቆምበት እና ቡድኔንም አደጋ ውስጥ
የከተትኩበት ጊዜ አለናይሄን ችግር ማረም ይኖርብኛል፤ ጥፋት ሲሰራብኝ ዳኛ ፊሽካ እስካልነፋ ድረስ ከእንግዲህ
በፍፁም አልቆምም”፡፡
በመጨረሻ….
“የእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኔ ላይ ከታዳጊነቴ ዕድሜ አንስቶ እስካሁን
ድረስ የሀገሬን ብሔራዊ ቡድን መለያ በኦሎምፒክ ቡድኑ ደረጃ ለብሼ ኳሱን እንድጫወት እና በአበረታች ደረጃም ላይ
እንድገኝ ያደረጉኝን ሰዎች ሁሉ ማመስገን እፈልጋለው፤ በቅድሚያ ምስጋናዬን የማቀርበውም ለፈጣሪዬ ነው፤ ከዛ
ለቤተሰቦቼ እና ልጅ ሆኜ ላሰለጠኑኝ እና ላበረታቱኝ አስቻለው ተስፋዬ እና ዓለሙ ወንድወሰን፤ በመቀጠልም ሙገር
ላሰለጠኑኝ ኤልያስ፣ ፋሲል እና የዋናው ቡድን አሰልጣኝ ለነበረው ግርማ ሀብተዩሃንስና ረዳቱ ጨፍቅ ካሳ፤ አሁን ላይ
ለምገኝበት ደረጃም ጥሩ መንገዱን ለከፈተልኝ ፀጋዘሀብ አስግዶም፤ ለደደቢት የቀድሞ ተጨዋቾች እና ለአሰልጣኝ
አስራት አባተ፤ ለጌታነህ ከበደ እና የአሁን ሰዓት ላይ ወደ ወልዋሎ ገብቼ ለመጫወት እንድችል ላደረገኝ አሰልጣኝ
ፀጋዬ ኪዳነማርያም እና ለአሁኑ አሰልጣኜም ዩሃንስ ሳህሌ ምስጋናን አቀርባለው፡፡ ከዛ ውጪም ለመላው የክርስትና
እምነት ተከታዮች፤ ለቤተሰቦቼ እና ለወልዋሎ አዲግራት ክለብ ደጋፊዎች መልካም የዳግማዊ ትንሳኤ በዓል
እንዲሆንላቸውም መልዕክቴን ማስተላለፍ እፈልጋለው፡፡