በመሸሻ_ወልዴ /G.BOYS/
ለመቀለ 70 እንደርታ በመጫወት ጥሩ ብቃቱን በሜዳ ላይ አሳይቷል። ከእዛም በፊት በጅማ አባቡናም በነበረው ቆይታው ተመሳሳይ ብቃቱን አሳይቶ ከሁለቱም ክለቦች ጋር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ አንስቷል። ይህ ተጨዋች አሚን ነስሩ ሲሆን አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ ሲፈልግ ተከላካይ አሊያም ደግሞ የመሀል ተጨዋችም እያደረገው ሲጠቀምበትም ታይቷል።
የሁለገብ አይነት ጥሩ ችሎታ ያለውን አሚን ነስሩን በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ አናግረነዋል። ምላሹንም በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል።
ሊግ:- እንኳን ለ1441ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል ከእነ ቤተሰቦችህ በሰላም አደረሰህ?
አሚን:- በጣም አመሰግናለሁ።
ሊግ:- የኢድ አልፈጥር ፆምን እንዴት ነበር ያሳለፍከው?
አሚን:- ፆሙ ጥሩ ነበር። በፀሎት እና በዱሀም ነው ያሳለፍኩት።
ሊግ:- በዓሉን አስመልክቶ የምታስተላልፈው መልዕክት ካለ?
አሚን:- ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በዓሉ የፍቅር የሰላም የመተሳሰብ እንዲሆን እየተመኘው ለአጠቃላይ ኢትዮጵያንም ይህን ክፉ ጊዜ አሳልፈን የምንገናኝበት ወቅት እንዲሆንልንም ምኞቴ ነው።
ሊግ:- ኮቪድ 19 አስጊና በጣም አስፈሪ ሆኗል። ጊዜህን የት እያሳለፍክ ነው?
አሚን:- ለኢትዮጵያ ቡና የማደግ ዕድሉን ካገኘው ወንድሜ ፉሀድ ጋር የተለያዩ የአካል ብቃት ልምምዶችን በመስራት ነው የማሳልፈው። ከእዛ ውጪ ያለውን ጊዜ ደግሞ እቤት ውስጥ በመቀመጥ ነው።
ሊግ:- በቤት ውስጥ ስትውል ምን ምን ነገሮችን ታደርጋለህ?
አሚን:- በዋናናት ኮቪድ 19 በጣም ስጋት እየሆነ በመምጣቱ ፀሎት እና ዱሀ ነው የማደርገው። ሌላውን ጊዜ ደግሞ የእግር ኳስና ሌሎችን ፊልሞች በማየት አሳልፋለው።
ሊግ:- ኮቪድ 19 በኮልፌ አካባቢ…..? እና ሰፈራችሁን ስትገልፀው?
አሚን:- ኮልፌ ምርጥ እና አስማት የሆነ ሰፈር ነው። እስካሁንም ኮሮና ያለ አይመስልም። ያም ሆኖ ግን የምናደርገው ጥንቃቄም ዕለት ከዕለትም ሊሆን ይገባል።
ሊግ:- የዘንድሮውን የፆም ወቅት የእግር ኳስ ውድድሩ ተቋርጦ ነው ያሳለፍከው። ከበፊት አንፃር ክብደት እና ቅለቱን ስትመለከተው?
አሚን:- በመጀመሪያ ደረጃ ፆም ለማንኛውም ሰው ብርታት ነው የሚሆነው። አይደለም ኳሱ ተቋርጦ ስንፆም በፊት እንኳን ከባድ ልምምድ በምንሰራ ሰዓትም አይከብደንም ነበር።
ሊግ:- በኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ስለሚገኘው ኳስ ተጨዋች ወንድምህ ማለት የምትፈልገው?
አሚን:- ፉዐድ ጥሩ አቅም ያለው ተጨዋች መሆኑን አምናለው። ያም ሆኖ ግን የሚያስበው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ በምንም ነገር ሳይዘናጋ ብዙ መልፋት ይኖርበታል። ከዛ ውጪም በኳስ ጨዋታ ውስጥ ብዙ ነገር አለ አንዳንዶቹ እንደውም ተስፋ የሚያስቆርጡም ናቸው። ስለዚህም እነዚህን ጭምር ከወዲሁ አውቆ እና ትዕግስትም አድርጎ ስራው ላይ ብቻ አተኩሮ ሊሰራ ይገባል።
ሊግ:- በኢትዮጵያ ቡና የዋናው ቡድን ውስጥ ተካተህ ስላለመጫወትህ ምን ትላለህ?
አሚን:- ለኢትዮጵያ ቡና በጊዜው አድጌ ብጫወት በጣም ነበር ደስ የሚለኝ። መጫወትም እፈልግ ነበር። ያ ግን አልሆነም። ባለመጫወቴም የደረሰብኝ ችግርም ሆነ ያጋጠመኝ ነገር ብዙም የለም። እንደውም ወደ ሌሎች ቡድኖች በማምራቴና ለዋንጫ የሚጫወት ቡድን ውስጥ በመግባቴ በሊጉ ዋንጫ የማግኘት እልሞቼን ላሳካ ችያለው።
ሊግ:- የሊጉን ዋንጫ ለሁለት ጊዜያት ያህል አንስተሃል። ሶስተኛውን እየናፈቅክ ነው?
አሚን:- አዎን። ዘንድሮ በኮቪድ 19 ውድድሩ ተቋረጠ እንጂ ያንን ዋንጫ ለሶስተኛ ጊዜ ስለማንሳት እያሰብኩ ነበር። ፈጣሪ ግን አላለውም።
ሊግ:- በእዚህ የወጣትነት ዕድሜህ እነዚህን ዋንጫዎች በማንሳትህ እድለኛ ነህ ማለት ይቻላል?
አሚን:- አዎን። ምክንያቱም ይህንን ዋንጫ ብዙ ስምና ዝና ያላቸውም ተጨዋቾች ያላገኙ አሉና ስለዚህ ኳስ አንዳንዴ እድለኝነትንም ይጠይቃል። ከዛ ውጪ እንዲህ ያሉ ክብሮችን ለማግኘትም ጠንክሮ መስራት እና ለዋንጫ በሚጫወት ቡድን ውስጥም ልትኖር ያስፈልጋልና እኔ በእዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው እየተጓዝኩ ያለሁት።
ሊግ:- እነዚህን ዋንጫዎች ከተጫወትክባቸው ክለቦች ጋር በማንሳትህ በትውልድ ሰፈርህ አካባቢ የተለየ ነገር ተፈጥሯል?
አሚን:- አዎን። ኮልፌ በእግር ኳሱ ብዙ ተጨዋቾችን ያወጣ ሰፈር ነው። ከእነዛም መካከል የቅርብ ዓመታቱን እንኳን ብንጠቅስ እንደ እነ ሳሙሄል ደግፌ /ሚሪንዳ/ አይነት ተጨዋቾችም የሚጠቀሱ ናቸው። ሌሎችም አሉ። አሁን ላይ ደግሞ እኔ ከእዚሁ ሰፈር ወጥቼ እነዚህን ዋንጫዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ለማግኘት መቻሌ እና የአካባቢውንም ስም በማስጠራቴ በጓደኞቼም ሆነ በሰፈሩ ነዋሪ ዘንድ ከፍተኛ ደስታን ፈጥሯል። እኔንም አስደስቶኛል። እነዚህ ሰዎች ደግሞ ከመደሰት አልፈውም ወደፊት ጥሩ ደረጃ እንድደርስም እየመከሩኝ ነውና ላመሰግናቸው እወዳለሁ።
ሊግ:- በኮቪድ 19 የሊግ ውድድራችን በመሰረዙ ዙሪያ ምን ትላለል?
አሚን:- የውድድሩ መሰረዝ ልክ እና ተገቢም ነው። አይደለም በእኛ ሀገር ላይ በባህር ማዶም ተቋርጧል። እግር ኳስን የምትጫወተው ጤና ሲኖር ነው። ለዛም ነው የሊጉ ውድድር የተሰረዘው።
ሊግ:- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ የአንተ ምርጡ ጨዋታህ?
አሚን:- ጅማ እያለው በአዲስ አበባ ስታድየም ከደደቢት ጋር ያደረግነው እና እነሱን ያሸነፍንበት ጨዋታ ምርጥ ነበር።
ሊግ:- በየቦታው የየትኞቹ ተጨዋቾች አድናቂ ነህ?
አሚን:- በግብ ጠባቂነት በጅማ አብሮኝ የነበረው ዳንሄል አጄ በተከላካይነት የቅዱስ ጊዮርጊሱ አስቻለው ታመነ በአማካይ ስፍራ የእኛው ሚካኤል /ጣሊያን/ በአጥቂው ስፍራ ላይ ደግሞ ሌላውን የቡድናችንን ተጨዋች ኤማኑኤልን ነው የማደንቀው።
ሊግ:- ከአጠገብህ ጋር ሆኖ ሲጫወት ምርጥ ጥምረትህ ከማን ጋር ስትጫወት ነው?
አሚን:- በጅማ ከይሁን እንዳሻው ጋር የነበረን ጥምረት በጣም የማይረሳኝ ነው። ይሁን ጥሩ ችሎታ ያለውና ምቾትም የሚሰጥህ ነው።
ሊግ:- ከባህር ማዶ ተጨዋቾች በቀዳሚነት የምታደንቀው ተጨዋች?
አሚን:- ፖል ስኮልስ እሱ ለየት ያለ ተጨዋች ነው።
ሊግ:- በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ በጣም ያዝናና የነበረ ተጨዋች?
አሚን:- ዋናው ቢኒያም ታዬ /ግስላ/ ነው። ከእሱ ጋር ሀድያ ሆሳህና በነበርንበት ሰዓት ሁሌም እንድስቅ እና እንድደሰትም ያደረሰገኝ ነበር። ሌላው አዝናኙ ተጨዋች ደግሞ በጅማ አብሮኝ የነበረው ግብ ጠባቂው ዳዊት አሰፋ /እምሻው/ ነው። ሁለቱሞ ተጨዋቾች ቀልድና ጨዋታ ይችላሉ።
ሊግ:- ኮቪድ 19ን ታሳቢ በማድረግ በበጎ አድራጎት ስራ ላይ ተሳትፈሃል?
አሚን:- አዎን። እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በሁሉም ሰፈር የተቋቋመ የበጎ አድራጎት ኮሚቴ ስላለ እኔም በሰፈሬ ኮልፌ አካባቢ በእነሱ አማካኝነት የሚጠበቅብኝን የማህበራዊ እርዳታን ለማድረግ ችያለው።
ሊግ:- በአሁን ሰዓት በጣም የናፈቀህ ነገር?
አሚን:- ወደ ኳስ እና ስራችን በፍጥነት መመለስ። ያም ነው የናፈቀኝ።
ሊግ:- መቀለ 70 እንደርታ ወርሃዊ ደመወዛችሁን እየከፈላችሁ ይገኛል። በእዚህ ዙሪያ ምን የምትለው ነገር አለ?
አሚን:- ቡድናችን በእዚህ እንኳን አይታመም። በእዚህን ወቅት ደመወዝ የማይከፍሉ ቡድኖች ቢኖሩም የእኛ ክለብ ግን ሳያቋርጥ እየከፈለን ነው። በእዚህም ሁኔታ ለቡድናችን ከፍተኛ ምስጋና ላቀርብለት እፈልጋለሁ።
ሊግ:- በመጨረሻ…..?
አሚን:- ለኮቪድ 19 አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ እና ከተቻለም ከቤት ባለመውጣት ራሳችንን ቤተሰባችን እና ማህበረሰቡን እንጠብቅ።
https://t.me/Leaguesport