በመሸሻ ወልዴ
ለመቐለ 70 እንደርታ በተከላካይ እና በአማካይ ስፍራ ላይ የሚጫወተው አሚን ነስሩ ክለባቸው የዘንድሮውንም የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ዳግም እንደሚያነሳ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጿል፤ መቐለ 70 እንደርታ በአሁን ሰዓት በሊጉ በሶስተኝነት ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህ ውጤትና ደረጃም ቡድናቸውን እንደማያስፈራውም ተናግሯል፤ ከተጨዋቹ ጋር ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ በተለያዩ የክለባቸው ጉዳይ ጋር ተያይዞ ባደረገው ቆይታም የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፡፡
ሊግ፡- መቐለ 70 እንደርታ 5 ሐዋሳ ከተማ 1 የሚል ውጤት በእዚህ ሳምንት ተመዝግቧል፤ ጨዋታው ምን መልክ ነበረው?
አሚን፡- ሐዋሳ ከተማን በሰፊ ግብ ያሸነፍንበት የቅዳሜው ዕለት ጨዋታ ለእኛ ከሽንፈት መልስ ያደረግነውና ግዴታም ይህን ጨዋታ ረተን ወደ አሸናፊነት መንፈስ መምጣት ስለነበረብን በሁሉም መልኩ ኳስን ከእነሱ ተሽለን የተጫወትንበት ነው፤ እንደነበረን ብልጫም ግጥሚያውን ከ5 ግብ በላይ አስቆጥረን ማሸነፍ እንችልም ነበር፡፡
ሊግ፡- በፋሲል ከነማ በሜዳችሁ እና በደጋፊያችሁ ፊት ሽንፈትን ያስተናገዳችሁበት ጨዋታን በቅርቡ አድርጋችሁ ነበር፤ ያ ሽንፈት እንዴት ሊያጋጥማችሁ ቻለ?
አሚን፡- ፋሲል ከነማ እኛን ያሸነፈበት የቅርቡ ጨዋታ ውጤት ራሳችን በፈጠርነው ጥቃቅን ስህተት ተሸነፍን እንጂ ከነበረን የኳስ ቁጥጥር የበላይነት እና ጎል ሙከራ አንፃር ውጤቱ አይገባንም ነበር፤ እነሱን ግብ ጠባቂያቸው ይዟዋቸውም ወጥቷል፡፡
ሊግ፡- የፕሪምየር ሊጉ የአምናው ሻምፒዮና በአሁን ሰዓት ላይ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፤ መቼ መሪ ይሆናል?
አሚን፡- በቅርብ ነዋ! ምክንያቱም የአንደኛው ዙር ላይ ከባድ ከባድ እና ጠንካራ የሚባሉ ጨዋታዎችን ከሜዳችን ውጪ ወጥተን ስለተጫወትንና በቀጣዩ የሁለተኛው ዙር ላይ ደግሞ በሜዳችን ላይ ስለምናደርግ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ስለሚሆንልን ነው፡፡
ሊግ፡- መቐለ 70 እንደርታ ከአምናው ቡድን አንፃር ዘንድሮ ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ጠንካራ እና ክፍተት ጎኑስ?
አሚን፡- በልዩነት ደረጃ የማነሳው የያዝነው የተጨዋቾች ስብስብ ከአምናው በጣም ጥሩ እና የተሻለ መሆኑ ነው፤ ጠንካራ ጎኑም ያመዝናል፤ ክፍተት ጎኑ ደግሞ በጉዳት አንድአንድ ተጨዋቾቻችን የምናጣበት አጋጣሚ አለና የእሱ ችግር ሲቀረፍ ቡድናችን ምንንም ነገር መስራት እንደሚችል የሚያሳየን ነው፡፡
ሊግ፡- የፕሪምየር ሊጉን የሻምፒዮንነት ድል ዘንድሮ የምትደግሙት ይመስልሃል?
አሚን፡- ኢንሻ ዓላ፤ አዎን! ዋንጫውን በድጋሚ እናነሳዋለን፡፡
ሊግ፡- ለመቐለ 70 እንደርታ በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ በቋሚ ተሰላፊነት ስትጫወት አልተመለከትንህም…..?
አሚን፡- አዎን፤ ይሄ የአሰልጣኝ ስራ ነው፤ አሰልጣኙ ለሚጠቀምበት የጨዋታ ታክቲክ ሲልም ነው ሳያጫውተኝ የቀረው፤ አሁን ላይ ደግሞ በመሀል ሜዳው ላይ በስኪመር ስፍራ እያጫወተኝ ይገኛል፡፡
ሊግ፡- በመሃል ሜዳ እና በተከላካይ ስፍራ ላይ ስትጫወት ተመልክተንሃል፤ ጥሩ ለመጫወት ለአንተ የትኛው ቦታ ይሻልሃል?
አሚን፡- በጅማ አባጅፋርም ሆነ በመቐለ 70 እንደርታ ቡድን የተጨዋችነት ቆይታዬ ሁለቱም ቦታዎች ለእኔ በጥሩ መልኩ የተጫወትኩባቸው ስፍራዎች ስለሆነ አንድ ናቸው፤ አስበልጬ የምመርጠው ቦታም የለኝም፡፡
ሊግ፡- ከወቅታዊ አቋምህ እንነሳና ለመቐለ 70 እንደርታ በእዚህ ዓመት ምን ልታደርግለት ዝግጁ ነህ?
አሚን፡- ለመቐለ 70 እንደርታ ስጫወት አሁን ላይ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ጊዜም የሊጉ ጨዋታዎች ቡድኑን ወደ ውጤታማነት ማማ የሚወስደውን ጥሩ ብቃቴን አውጥቼ ለማሳየት የሚቻለኝን ሁሉ ጥረት አደርጋለው፤ እስካሁን እየሰጡት ባለው ግልጋሎቴም ደስተኛ ነን፤ ይሄ ጥሩ የሆነ ጉዞዬም ለብሄራዊ ቡድን እስከምመረጥበት ጊዜ ድረስም አብሮኝ የሚቀጥል ነው የሚሆነው፡፡
ሊግ፡- በፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎ ለመቐለ 70 እንደርታ ዋንኛ ተፎካካሪዎች እነማን ይሆናሉ?
አሚን፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማ ናቸዋ! ሌላ ማንም አይሆንም፤ ሶስታችን ብቻም ነው ለዋንጫው የምንፎካከረው፡፡ ሻምፒዮና የምንሆነው ግን እኛ ነን፡፡
ሊግ፡- በፕሪምየር ሊጉ ስትሸነፉና ስታሸንፉ ያለህ ስሜት በምን መልኩ ይገለፃል?
አሚን፡- ቡድናችን ሲሸነፍ እንደማንኛውም ስፖርተኛ በጣም ይከፋኛል፤ ያኔም ስለሽንፈቱ ምክንያት ለማወቅ ጥረትን አደርጋለው፤ ቡድናችን ሲያሸንፍ ደግሞ እደሰታለሁ፡፡
ሊግ፡- ከባህር ማዶ ክለቦች የየትኛው ቡድን ደጋፊ ነህ?
አማን፡- የማንቸስተር ዩናይትድ፡፡
ሊግ፡- ማንቸስተር ዩናይትድ ጥሩ ውጤትን እያስመዘገበ አይደለም?
አሚን፡- አዎን፤ በእግር ኳስ ጨዋታ አሰልጣኝ በተቀያየረ ቁጥር ሁሌም አዲስ ቡድንን ስለምትሰራ እንዲህ ያለ የውጤት ማጣት ያጋጥማል፤ ስለዚህ የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር መታገስ ነው፤ ማንቸስተር ደግሞ አሁን ላይ ቡድኑን በታዳጊና በወጣት ልጆች እያዋቀረ በመሆኑ ክለቡ ወደተሻለ ነገር እንደሚመጣ ተስፋ አለኝ፡፡
ሊግ፡- ሊቨርፑል የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ሊያነሳ ተቃርቧል፤ እንደማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊነትህ ምን የምትለው ነገር አለ?
አሚን፡- ሊቨርፑል 100 ፐርሠንት የሊጉ ዋንጫ ይገባዋል፤ እኔ የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ ብሆንም ሁሌም ጥሩ የተጫወተ ቡድን ዋንጫውን ያግኝ ነው የምለው፤ ስለዚህም ለእኔ ክሎፕንና ሊቨርፑሎችም በያዙት አጨዋወት ይመቹኛልና ዋንጫውን እነሱ እንዲያነሱ እፈልጋለው፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት የእስካሁን ህይወትህ በጣም ደስተኛ ነህ?
አሚን፡- አዎን፤ በጣም ምክንያቱም የእግር ኳስ ጨዋታ መዝናኛህ እና ስራህ ከመሆኑ ባሻገር የራስህንም ጤንነት የምትጠብቅበት እና የልጅነት ህልምህንም የምታሳካበት ስለሆነ እኔ ሁሌም ደስተኛ ሆኜ ነው ኳስን እየተጫወትኩ የምገኘው፡፡
ሊግ፡- የተከፋህበት ወቅትና አጋጣሚዎችስ አሉ?
አሚን፡- ይኖራል፤ ግን ብዙም አላስታውስም፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ለሁለት ጊዜያት ያህል አንሰህ ልበል?
አሚን፡- አዎን፤ ከጅማ አባጅፋርና ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ሆኜ ያለፉትን ሁለት ዓመታት እነዚህን ድሎች ተቀዳጅቻለው፤ ሶስተኛዬን ዋንጫ ደግሞ በተከታታይ ዓመታት ዘንድሮ አነሳለሁ፡፡
ሊግ፡- የእስካሁኑ የእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህን በስኬታማነት ሆነህ ስታጠናቅቅ የተለየ ስሜት ነው ያለህ?
አሚን፡- አዎን፤ በጣም! ከዚህ በላይ ሌላ ምን ደስታ አለ ብለህ ነው፡፡
ሊግ፡- ከሰዎች ባህሪያት የሚመችህ ምንድነው?
አሚን፡- ግልፅነት እና መደባበቅ የሌለበት ነገር ሁሌም ይመቸኛል፡፡
ሊግ፡- የመቐለ 70 እንደርታ ክለብ ካምፕ ውስጥ የአንተ የክፍል ጓደኛህ ማን ነው?
አሚን፡- ሄኖክ ኢሳያስ፡፡
ሊግ፡- የክለባችሁ ቀልደኛ እና አዝናኙ ተጨዋች ማን ነው?
አሚን፡- ሁሉም ማለት ይቻላል ቀልደኛ ነው፤ ከእነዛ መካከል ደግሞ እነ ሚካኤል ደስታ /ጣሊያን/፣ ሳሙኤል ሳሊሶ፣ አስናቀ ሞገስ እና ዳንኤል ደግሞ በቀልድ እና በጨዋታቸው ለየት ይላሉ፡፡
ሊግ፡- ዝምተኛው ተጨዋችስ?
አሚን፡- ሄኖክ ኢሳያስ፡፡
ሊግ፡- አንተስ እንዴት ነው የምትገልፀው?
አሚን፡- እስቃለሁ፤ እጫወታለሁ፤ እቀልዳለው፤ መዝናኛዬም ይኸው ነው፡፡
ሊግ፡- መቐለ በተለየ መልኩ የምትገለፅ ከተማ ነች?
አሚን፡- አዎን፤ አሪፍ እና ሰላም የሰፈነባት ከተማ ነች፤ ከዛ ውጪም አንድም ኮሽታ አይሠማባትም፡፡ ህዝቡም ፍቅር የሆነና እንግዳም ተቀባይ ነው፡፡
ሊግ፡- ቤተሰባችሁ ለአንተ ምን ማለት ናቸው?
አሚን፡- ቤተሰቦቼ ሁሉ ነገሬ ናቸው፤ እዚህ ደረጃ ላይ እንድደርስ ብዙ ነገርንም አድርገውልኛል፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ተጨዋች ባትሆን ኖሮስ?
አሚን፡- የጉራጌ ልጅ አይደለሁ… እንደ ቤተሰቦቼ ወደ ንግዱ ዓለም እገባና ነጋዴ እሆን ነበር፡፡
ሊግ፡- ከምግቦች በተለየ መልኩ የምትወደው?
አሚን፡- የኮልፌ ልጅ ምግብ አይመርጥም፤ ያገኘሁትን ነው የምመገበው፡፡
ሊግ፡- ኮልፌን እንዴት ነው የምትገልፃት?
አሚን፡- ሁሉም ሰው የተወለደበትንና ያደገበትን ሰፈር ይወዳል፤ እኔም ሰፈሬን እስከሚናፍቀኝ ድረስ ነው የምወደው፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ አሁን ላይ ለደረስክበት ደረጃ እነማንን ታመሰግናለህ?
አሚን፡- እነ አሰልጣኝ ገብረ መድህን ኃይሌን፣ ጳውሎስ ጌታቸውን /ማንጎ/ በያን ሁሴንና ሙሉጌታ በዳዳ ቹቻን እንደዚሁም ደግሞ ቤተሰቦቼንና ወንድሞቼን ማመስገን እፈልጋለው፡፡
ሊግ፡- ስለ እግር ኳስ ተጨዋቹ ወንድምህስ ምን ትላለህ?
አሚን፡- የአሁን ሰዓት ላይ ገና ታዳጊ ተጨዋች በመሆኑ በትልቅ ደረጃ ላይ ደርሶ ባይጫወትም ወደፊት ዕድሉን ሲያገኝ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ የሚችል ነው፡፡
ሊግ፡- የፕሪምየር ሊጉን ውድድር ከስፖርታዊ ጨዋነት አኳያ እንዴት አገኘኸው?
አሚን፡- በየውድድሩ ሜዳ በዚህ ረገድ ጥሩ ነገርን እየተመለከትን ስለሆነ ሁልጊዜም እንደዘንድሮ ቢሆን በጣም ጥሩ ነው፡፡
ሊግ፡- ለመቐለ 70 እንደርታ መሪው ተጨዋች ማን ነው? ስትገናኙስ ምንን ነገር ይነግሩአችዋል?
አሚን፡- ሚካኤል ደስታ /ጣሊያን/ ስዩም ተስፋዬ እና አንተነህ ገብረክርስቶስ ለእኛ ረጅም ጊዜ ከመጫወታቸው አኳያ እና ካላቸው ልምድ አንፃር ጥሩ መሪዎቻችን ናቸው፤ ሜዳ ስንገባም እንዴት መጫወት እንዳለብን ስንሳሳት እንዴት መረጋጋት እንዳለብንም ካላቸው ልምድ በመነሳት የሚያስተካክሉንም ናቸውና በጣም ይገርሙናል፤ በእዚህ ሊመሰገኑም ይገባል፡፡
ሊግ፡- እንደ እነሱ ለብዙ ዓመታት መጫወት አያስመኝም?
አሚን፡- በጣም እንጂ እነሱ እኮ ለእዚህ ሁሉጊዜ እየተጫወቱ ያሉት ጠንክረው ስለሰሩ ነው፤ ከእነሱ ጋር መጫወትም በራሱ እድለኝነት ነው፡፡
ሊግ፡- ሚካኤል ደስታ ጣሊያን ጉዳትን አስተናግዶ ነበር?
አሚን፡- አዎን፤ አሁን ታክሞ ተመልሷል፤ የሁለተኛው ዙር ላይም ልምምድ ይጀምራል፤ እሱ ሲጎዳ የቡድናችን መሪና ካፒቴንም ስለነበር ያጎደለን ነገር አለ፤ አሁን በመመለሱ ግን ቀጣዩ ዙር ላይ ይጠቅመናል፤ ፈጣሪም እንኳን ወደ መልካም ጤንነቱም አበቃው እላለው፡፡