Google search engine

“የሚፎካከረን ቅ/ጊዮርጊስ ብቻ ነው”፤ ሻምፒዮና የምንሆነው ደግሞ እኛ ነን”
እንየው ካሳሁን /ፋሲል ከነማ/

በመሸሻ ወልዴ


የፋሲል ከነማው የቀኝ መስመር /የኮሪደር ስፍራው/ ተጨዋች እንየው ካሳሁን በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ለክለቡ እየተሰለፈ በእንቅስቃሴ ደረጃ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ በኩል ጥሩ ብቃቱን በሜዳ ላይ እያሳየ ሲሆን በተለይ ደግሞ ለቡድኑ የፊት መስመር የአጥቂ ስፍራ ተጨዋቾች በሚያቀብላቸው የተሳኩ ኳሶችም አድናቆትን በማትረፍ ላይ ይገኛል፡፡


ፋሲል ከነማ በቤትኪንጉ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና እስካሁን ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ትናንት የተደረጉትን ጨዋታዎች ውጤት ሳይጨምር ሶስቱን አሸንፎ እና በአንዱ ተሸንፎ 9 ነጥብን በመያዝ ቅ/ጊዮርጊስን ተከትሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን የእዚሁ ቡድን ተጨዋች እንየው ካሳሁን ቡድናቸው ወላይታ ድቻን 4-2 ካሸነፈበት ግጥሚያ በኋላ “አሁን ላይ ምንም እንኳን በእዚህ ደረጃ ላይ እንገኝ እንጂ በቅርቡ በመሪነት ደረጃ ላይ መቀመጣችን የማይቀር ነው፤ ከዛም ውጪ ዘንድሮ ሻምፒዮና የምንሆነውም እኛ ነን” ሲልም ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሹን ሰጥቷል፡፡


ከፋሲል ከነማው ተጨዋች እንየው ካሳሁን ጋር በተለያዩ ተጨማሪ ጥያቄዎች ዙሪያም ያደረግነው ቆይታም ይሄንን ይመስላል፤ ተከታተሉት፡፡


ሊግ፡- የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አጀማመራችሁ ምርጥ ነው ማለት ይቻላል?


እንየው፡- አዎን፤ መጀመሪያ ወደ ዘንድሮው ውድድር የገባነው ከቱኒዚያው ክለብ ጋር ለነበረብንና በጎል ልዩነትም ለወደቅንበት የኢንተርናሽናል ጨዋታ ተሳትፎአችን ጥሩ ዝግጅትን አድርገን ነበር፤ ከዛም በኋላ የሊጉን ውድድር ስንጀምር ዋንኛው ዓላማችን ዋንጫውን ማንሳት ነውና ቅ/ጊዮርጊስን በማሸነፍ ነው ጥሩ ጅማሬን አድርገን የነበርነው፤ ቀጥሎም ባልጠበቅነው እና ሁላችንንም ግራ ባጋባን መልኩም በቡና ሽንፈትን አስተናገድንና ራሳችንን ወደምንፈትሽበት ሁኔታዎች ለማምራት ቻልን፤ በኋላምሁለቱን ተከታታይ ግጥሚያዎቻችንን በማሸነፍ እና እየተሻሻልንም በመሄድ የአሁን ሰዓት ላይ አጀማመራችንን በማሳመር ላይም ነው የምንገኘው፡፡


ሊግ፡- ፋሲል ከነማ ባለፉት ሁለት ዓመታቶች ምርጥ ቡድኑን አሳይቷል፤ ይሄን ዘንድሮስ ያስቀጥላል?


እንየው፡- ለእዛ ምንም አይነት ጥርጥር የለንም፤ ከፕሪ-ሲዝን ዝግጅታችን አንስቶ በሁሉም ተጨዋቾች ውስጥ አንድ እና አንድ ዓላማችን የሊጉን ዋንጫ ማግኘት ነውና ለእዛም ነው በመዘጋጀት ላይ የምንገኘው፤ ዋንጫ ለማንሳት የሚጫወት ቡድን ደግሞ የግድ ምርጥ ቡድን ሊኖረው ይገባዋልና ያንን ጥንካሬያችንን እናስቀጥለዋለን፡፡


ሊግ፡- በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈትን ለማስተናገዳችሁ በምክንያትነት ደረጃ የምትጠቅሰው ምኑን ነው? ሽንፈቱ አስቆጫችሁ?


እንየው፡- በጣም፤ በእግር ኳስ ጨዋታ ሽንፈት የሚያጋጥም ነው፤ ቡና ያደረሰብን ሽንፈት ግን ፈፅሞ ያልጠበቅነው ስለነበርም ያን ዕለት ያስቆጨን፤ በእለቱ ጨዋታ ለውጤት ማጣታችንም በዋነኝነት ልጠቅሰው የምፈልገው እኛ ለሌሎች ቡድኖች ትኩረት እንደምንሰጠው ሁሉ በእዛን ዕለት ጨዋታ ለቡናዎች በቂ ትኩረትን ልንሰጣቸው ያለመቻላችን ነው፤ ያ እኛን ያዘናጋን ይመስለኛል፤ በጣም ተቀዛቅዘን ነበር ግጥሚያውን ያደረግነው፤ በመጨረሻም ጨዋታው ዋጋ ሊያስከፍለን ችሏል፡፡


ሊግ፡- በወላይታ ድቻ ብትፈተኑም ጨዋታውን ማሸነፍ ችላችኋል፤ ስለ ጨዋታው ምን ትላለህ?


እንየው፡- ከወላይታ ድቻ ጋር የነበረን ጨዋታ በጣም ጠንካራ እና ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ነበር፤ አንዳችን አንዳችንን ለማሸነፍ የተጫወትንበት ግጥሚያም ነበር፤ ወላይታ ጥሩ ቡድን እንዳለው በእንቅስቃሴ ደረጃም አስመልክቶናል፤ በእዛን ዕለት ጨዋታ እነሱ ረጅም ኳሶችን በመጠቀም ሲፈትኑን ነበር፤ በእዛ ደረጃም ግብን አስቆጥረዋልና ይሄን ፈታኝ ጨዋታ በአሸናፊነት ስለተወጣን በጣም ደስ ብሎኛል፡፡


ሊግ፡- ፋሲል ከነማ በጨዋታው ጅማሬ ወላይታ ድቻን 2-0 ከመራ በኋላ 25 ደቂቃዎች ባልሞሉበት ሰዓታቶች ውስጥ 2 ተከታታይ ግብ ተቆጥሮበት አቻ ለመሆን ችሎ ነበር፤ ያን ጊዜ ምን አይነት ስሜት ነበር ሊፈጠርባችሁ የቻለው?


እንየው፡- ማንኛውም ቡድን በጎል ልዩነቶች የመራውን ጨዋታ በደቂቃ ልዩነቶች ውስጥ ግብ ተቆጥሮበት አቻ ሲሆን በጣም ነው የሚደናገጠው፤ እኛንም የገጠመን ይሄ ነበር፤ በኋላ ላይ ግን ከድንጋጤያችን በፍጥነት ለማገገም ስለቻልንና በጨዋታው ላይም የነበሩብንን ክፍተቶች በመቅረፍና ብርቱ እንቅስቃሴንም ለማድረግ ስለቻልን የጨዋታው አሸናፊ ለመሆን ችለናል፡፡


ሊግ፡- ፋሲል ከነማን በአግባቡ እየጠቀምኩት ነው ብለህ ታስባለህ?


እንየው፡- በፍፁም፤ እንደዛ ለማለት በበርካታ የክለቡ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፌ ከእኔ የሚጠበቁትን ጥቅሞችና ግልጋሎቶችን ልሰጥ ነው የሚገባኝ፤ ይሄን ግን ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ላይ ወደ ቡድኑ ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ በጉዳት ከሜዳ ስለራቅኩና በኮሮናው የተነሳም የሊጉ ውድድር ተቋርጦ ስለነበር ክለቤን በምፈልገው መልኩ እያገለገልኩት አይደለም፡፡


ሊግ፡- ዘንድሮ እና ከእዚህ በኋላስ?


እንየው፡- አሁንማ በሙሉ ጤንነት እና በጥሩ ብቃት ላይ ነው የምገኘው፤ ከዛ ውጪም የሊጉ አጀማመሬ ተስፋ ሰጪና እያበረታታኝ ስለሆነም ዘንድሮ በሚኖረኝ የቡድኑ ቆይታዬ ክለቤ ዋንጫ እስከሚያነሳበት ጨዋታ ድረስም ነው ከእኔ የሚጠበቀውን ምርጥ ጥቅምን ልሰጠው የተዘጋጀሁት፡፡


ሊግ፡- ባለፉት ተከታታይ ግጥሚያዎች ለፋሲል ከነማ በቋሚነት በመሰለፍ መጫወት ጀምረሃል፤ ይሄን ቦታህን ታስከብራለህ?


እንየው፡- አዎን፤ ለእዛም በሜዳ ላይ ጉዳት አያጋጥመኝ እንጂ በቋሚነት ቦታዬን አስከብሮ ለመሰለፉ እና ለመጫወቱ ምንም አይነት ጥርጥር የለኝም፤ የውድድር ዘመኑንም ከጓደኞቼ ጋር እና ከቡድኔ ጋር ሆኜም በጥሩ ብቃቴ ለማጠናቀቅና ችሎታዬንም በተግባር ለማሳየትም ዝግጁ ነኝ፡፡


ሊግ፡- ፋሲል ከነማ የሊጉ ምርጥ ቡድን ነው?


እንየው፡- ባይሆን ነው የሚገርመው፤ የእዚህ ቡድን ምርጥነትም በሜዳ ላይ ብቻ ሳይሆን በፋሲሊቲም ጭምር ነው፤ እንደ ምርጥነቱም ለዋንጫ ጠንክሮ የሚሰራ ክለብ ከመሆኑ አኳያም የሊጉ ዋንጫ የሚገባው ቡድንም ነው፡፡


ሊግ፡- በፋሲል ከነማ ቆይታህ ደስተኛ ነህ? እንደ እግር ኳስ ተጨዋችነትህ ምን ነገርንስ ከወዲሁ እያለምክ ነው?


እንየው፡- ፋሲል ከነማን የተቀላቀልኩት ምንም እንኳን ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ላይ ቢሆንም ከቡድኑ ጋር በነበረኝ የእስካሁን ቆይታ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ከዛ ውጪም እንደ አንድ ተጨዋች አሁን ላይ በማለም ላይ ያለሁት ከምጫወትለት ቡድን ጋር ሻምፒዮና መሆንና በአፍሪካ ክለቦች የውድድር መድረክ ላይም ተሳትፎ ማድረግ እንደዚሁም ደግሞ በኳሱም ከበፊት አንስቶም የእኔ ዋንኛው ጥረትና ዓላማዬም በከፍተኛ ቡድን ደረጃ ደርሶ መጫወትም ነውና እነዚህን ማሳካት እፈልጋለውኝ፡፡


ሊግ፡- ከባህር ዳር ከተማ ጋር ስለሚኖራችሁ የዛሬው ጨዋታ ምን ትላለህ?


እንየው፡- ይሄን ጨዋታ እኛ አሸንፈን እነሱ ደግሞ ከሽንፈት መልስ በመምጣት የምናደርገው ነው፤ ከዛ ውጪ ውጤቱም ለሁለታችንም ለእኛ መሪነቱን እንድንጨብጥ የሚያደርገን እነሱን ደግሞ ወደ ደረጃው ፉክክር ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርጋቸው ስለሆነ ጥሩ ፉክክር ይኖራል ብዬ አስባለው፤ የጨዋታውም አሸናፊ እኛ እንሆናለን፡፡


ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ለፋሲል ከነማ የቱ ቡድን የዋንጫው ተፎካካሪው ይሆናል? የእዚህ ዓመትን ዋንጫስ ማን ወደላይ ከፍ አድርጎ ያነሳል?
እንየው፡- የውድድር ዘመኑ ቆይታችን ላይ ቡድናችንን ለዋንጫው የሚፎካከረው ክለብ ቅ/ጊዮርጊስ ነው፤ በመጨረሻ ግን እኛ ሻምፒዮና እንሆናለን፡፡


ሊግ፡- ከሀገር ውስጥ የየቱ ተጨዋች አድናቂ ነህ?
እንየው፡- የሳላህዲን ሰይድ፡፡


ሊግ፡- ከውጪ የምደግፈው ቡድንስ?


እንየው፡- ማንቸስተር ዩናይትድን፡፡


ሊግ፡- ማንቸስተር ዩናይትድ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ያነሳል?


እንየው፡- የቡድኑ አቋም ይዋዥቃል፤ ይሄ ነው የምትለውም አይደለም፤ ያን ስመለከት ማንችስተርን ለዋንጫው ፉክክር በመጫወት ደረጃ ውስጥ ይገባል ብዬ እንጂ የምጠብቀው ዋንጫ ያነሳል ብዬ አይደለም፡፡


ሊግ፡- በመጨረሻ በምን እናጠቃል?


እንየው፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነቱ ጉዞዬ አሁን ላይ ከዓመት ዓመት ጥሩ መሻሻልን በማሳየት ፈጠን ያለ እድገትን እያሳየው ነው፤ ይሄ ለመሆን መቻሉም አስደስቶኛል፤ በኳሱም እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረሴም ያሰለጠኑኝ አሰልጣኞች እና ቤተሰቦቼ እንደዚሁም ወንድሜና የቅርብ ጓደኞቼም አሉበትና ሁሉንም በፈጣሪ ስም ላመሰግናቸው

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P