Google search engine

…የማያርፈው አርፏል…

 

በዮሴፍ ከፈለኝ
ትክክለኛ አገላለጽ ነው ….የህጻናት ይሁን የወጣቶች የሴቶች ይሁን የወንዶች በትንሽ ይሁን በትልቁ ጨዋታ ከተካሄደ መሸሻ ወልዴአይጠፋም….በዚህ ባህሪው ተደጋጋሚ ጊዜ ገጠመኞችን አይቻለሁ ሰርግ ይሁን ለቅሶ ልደት ይሁን ድግስ እግርኳስ ካለ በመሼ ልብ ውስጥ ቦታ የላቸውም ..ለእግርኳስ ቦታ የሰጠ ልብ አለው..
ከማንም የስፖርት ቤተሰብ ጋር ሙግት አይወድም ዜና ሲሰራ መላተም አይፈልግም..አለመግባባትን በርቀት ሲሸሽ ኖሮ ላይመለስ ሄዷል መሸሻ ወልዴ.. በርካታ የስፖርት ቤተሰብ መሼን የሚያስታውሰው የፕሮፋይል ይዘት ባለው ቃለምልልሱ ነው ማገዝ እንጂ ሀርድ ቶክ አይወድም…
በርካታ መረጃዎች እሱ ጋር አይጠፉም ቤቱ የመግባት ዕድል አግኝቻለሁ ከ8 ከረጢት የማያንስ ጋዜጣና ፎቶ ቤቱ ተከማችተዋል..ኤግዚቢሽን የማሳየት ፍላጎት ኖሮን አውርተንበታል..ግን የማንመልሰው ጊዜ ቀደመን.. ተንቀሳቃሽ ላይብረሪ የተባለውም ለዚህ ነው..ከመሼ ጋር ያለው ዕድሜ ተኮር ቀልዳችን ትዝታ ሆኖ አልፏል..ሰው ወዳጁ በሰው ተወዳጁ መሼ ሰው እያለው በሰው ተከቦ ችግሩን ሳይታወቅ ህመሙን ሳንረዳ አምልጦናል…
በተደጋጋሚ ጊዜ እንዲታከም እንዲታይ ስንወተውተው ተሽሎኛል ጤነኛ ነኝ አይተውኝ ችግር የለም ብለውኛል እያለ ሲመልስ ኖሯል… ደጋግሞ ይዋሽ እንደነበር ካመለጠን በኋላ ገብቶኛል…አሁን እሱን መመለስ አንችልም እኛ ወደ እሱ ብንሄድ እንጂ …ቤተሰቡን ሁለት ወንድሞቹንና አክስቱን መንከባከብ በመሼ ወዳጆች መዳፍ ላይ አርፏል። በመዳፋችን እንጠቀም እሱ እንዳይረሳ የሚያደርግ ስራ እንስራ የሚለው መልዕክቴ ነው … የመሼ ዕልፈት እስከተሰማበት ሰዓት ድረስ ሊግና ሀትሪክ የስፖርት ጋዜጦች ላይ ሲሰራ ቆይቷል….በሁለቱም ቢሮዎች የኔና የመሼ ሳቅን የሚፈጥሩ ቀልዶች ይታወቃሉ….ዛሬ መሼና ቀልዶቹ ትዝታ ሆነዋል…እሱ የሌለበት ቢሮ ስንገባ እንዴት እንለምደው ይሆን..? ካሁኑ ጨንቆኛል… የመሼና የዮሴፍ ኢንተርቪዎች ዛሬ ዜና አይደሉም …ነገም የውይይት ርዕስ አይሆኑም እንዴት ግን ይጨንቃል…ጌታን ለመንኩት አቅም ሁነን ብዬ.. በመጨረሻም ባልደረባችን ኑራ ኢማም እንዳለችውና ርዕስ እንዳደረኩት ለስፖርት ቤተሰቡ የምለው የማያርፈው አርፏል…

…. መሼ ጎዴ ነፍስህ በሰላም ትረፍ…….

 

የጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አጭር የህይወት ታሪክ

ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ከእናቱ ከወ/ሮ ጌጤ ገ/ስላሴ እና ከአባቱ ሀምሳ አለቃ ወልዴ ደምበል ሚያዚያ 29/1965 ዓ.ም በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ መርካቶ ሰባተኛ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ተወለደ እድሜውም ለትምህርት ሲደርስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የፊደል ገበታ ትምህርትን በየኔታ መምራ ወ/ገብርኤል ከተማረ በኋላ የአንደኛ ደረጃውን በዳግማዊ ቴዎድሮስ ከ1ኛ እስከ 6ኛ የተማረ ሲሆን በመቀጠል ደግሞ ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍልን በቀድሞው ወሰንሰገድ በአሁኑ የካቲት 23 ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትሏል ከዛም በመቀጠል ለትምህርት ባለው ፍላጎት በ1986 ዓ.ም በቴክኒክና ሙያ ከተግባረእድ በመካኒካል ዘርፍ ተምሮ በዲፕሎማ ተመርቋል በተጨማሪም በጋዜጠኝነት በበርካታ አጫጭር ስልጠናዎች ሰርተፍኬት አግኝቷል ለሙያው ባደረበት ፍቅር የተነሳ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ እያለ የጋዜጠኝነት ስራውን በፅሁፍ መልክ መስራት እንደጀመረ የህይወት ታሪኩ ይናራልም ያወሳልም ።
በ1987 ዓ/ም ጀምሮ በደንብ ሙያውን ተቀላቅሎ ህይወቱ እስካለፈበት ቀን ድረስ ስራው እና ሙያውን በፍቅር ተወጥቷል አሻራውንም አስቀምጧል በዚሁም ለአብነት ያህል ካታንጋ ፣ሻምፒዮን ፣ማራቶን ፣፣ግሎባል ፣ካምቦሎጆ ይድነቃቸው አዲስ ስፖርት ፣ቤስት ሊግ ፣እና ሀትሪክ በተሰኙት የህትመት ውጤቶች ላይ ላቅ ያለ ስራውን አበርክቷል በሬድዮ በዛሚ 90.7፣ሀበሻ ሊግ ፣በኤፍ ኤም 96.3 (ፕላኔት ስፖርት ) ላይም ሰርቷል የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ውስጥ ለረጅም ጊዜ በአባልነት እንዲሁም በስራ አስፈፃሚነት በማገልገል ላይ ነበር አድዋ አፍሪካ አለም አቀፍ ቶርመንት በተሰኘው ድርጅትም መስራች እና የቦርድ አመራር በመሆን አገልግሏል በመርካቶ የጤና ስፖርት ማህበር ውስጥ አባል ነበር ፡፡
ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ በበጎ አድራጎት ስራዎች ተሳታፊ ለተቸገሩ ፈጥኖ ደራሽ የነበረ እና በስራዎቹ አንቱታን ብሎም ምስጋናን ያተረፈ ባለሙያ ነበር ከሙያ ባልደረባዎቹም ጋር መልካም ግንኙነት ነበረው በስራውዎቹ ደግሞ በ ከአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሁለት ጊዜ የእውቅና ሽልማት የተበረከተለት ሲሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ጨምሮ ጋዜጠኞች የሙያ ማህበራት የቀድሞ ተጫዋቾች ደጋፊዎች በአጠቃላይ የስፖርቱ ቤተሰቦች የተሳተፉበት የምስጋና መርሀ ግብር ሀሙስ ጳጉሜ 4/2013 ዓ.ም ተደርጎለት ነበር፡፡
ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ በተወለደ በ50 ዓመቱ እሁድ ጥር 21/2015 ዓ.ም በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ ስርዓት ቀብሩም ወደጃ ዘመዶችና የሞያ አጋሮቹ በተገኙበት በቀጨኔ ደብረሰላም ተፈፅሟል።

ለቤተሰቦቹም ለስራ ባልደረቦቹ መጽናናት ይስጥልን

 

… የስራ ባልደረቦቹ ስለ መሸሻ ወልዴ ምን አሉ…?

“መሸሻ ወልዴ ለየትኛውም ውድድር ልዩ ትኩረት ከመስጠቱ ባሻገር ወጣት እና ጀማሪ ጋዜጠኞችን የሚረዳበት ስብዕናው እና ፍላጎቱ ሌላው ብዙዎች ሊያውቁት የሚገባው በጎ ተግባር መሆኑን እኔም እመሠክራለው ። በሌላ በኩል እንዳለው ምጡቅ የታሪክ እውቀት የያዛቸውን ምስሎች እና ዶክመንቶች ወደ ገንዘብ አስገኚ ፈጠራዎች አለመቀየሩ ሁላችንንም አንገታችንን ያስደፋል። በሚዲያ ካፕ ህልፈቱ እስኪሠማ ድረስ ስፖርት ዞን ወክሎ የተጫወተውን ወንድማችንን መሸሻ ወልዴ ን ፈጣሪ ከ ደጋጎቹ ጎን ያሳርፍልን”
ጋዜጠኛ አሉላ ፍሬው / ከዓባይ ቲቪ/

“ጋዜጠኛ መሽሻ ወልዴ ለስፖርት ጋዜጠኝነት ሆኖ የተፈጠረ ፣ ጨዋታ ባለበት የማይጠፋ ፣ ሰምቶ ሳይሆን ተመልክቶ የሚዘግብ ቅን ባለ ውለታዬ የሙያ አጋሬ ነው።
የሃገር ውስጥ ዘገባ ከባድ ከሆነበት ያኔ ከ2 አስርት አመታት በፊት ጀምሮ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን በእግሩ እያቋረጠ ጭምር ከሰፈር ጨዋታዎች እስከ ተጠባቂ ታላላቅ የሃገሪቱ ጨዋታዎች ያለ አድልዎ የዘገበ ታላቅ ሰው። ሄሎ መሽሎ ብለው ለሚደውሉለት የሙያ አጋሮቹ ስለ ስፖርተኞች ታሪክም ሆነ አድራሻ ሳይሰስት ፤ ሳይደክም የሚያገለግለን የመረጃ ቋት ነበር።
ፈጣሪ ከደጋጎቹ ጎን ያስቀምጥህ                                                                                                        ጋዜጠኛ ዮናስ ሞላ / ከአዲስ ቲቪ/

“መሸሻን የማውቀው ጋዜጠኛ ከሆንኩ በኋላ ነው።ጋዜጠኝነት የሰጠኝ ጥሩ ወዳጄ ነበር።የልቡን የማያወራ በውስጡ ብዙ የሚያስቀር ምስኪን ሰው ነበር። ለሀገር ውስጥ እግርኳስ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ስፖርት የለፋ እና የደከመ ሰው ነበር መሸሻ።መሸሻን ማየው እንደ አንድ ተቋም ነው።እንደመረጃ ተቋም።ሰው አይደለም ያጣነው ተቋም ነው።ብዙ ታሪኮችን እና መነሻ የሚሆኑ ሃሳቦችን ይዞ አልፏል። ነብስህ በሰላም ትረፍ።
ጋዜጠኛ መኳንንት በርሄ /ከስፖርት ዞን/

” የእውነት ለመናገር እንደ መሸሻ ወልዴ እግርኳስና ሙያውን የሚወድ ሁሉን በእኩል የሚያይ ትንሽ ትልቁን አክባሪ ለአገራችን እግርኳስ ዕድገት ራሱን አሳልፎ የሰጠ ሰው ማግኘት ከባድ ነው እግርኳስ ይሁን እንጂ የትኛውንም ጨዋታና ውድድር ተመልክቶ በልዩነት ያየውን ተጨዋች ያስተዋወቀም እንደርሱ አይነት ያለ አይመስለኝም ብቻ በድንገተኛ የስጋ ዕረፍቱ ልባችን ቢሰበርም… ለሰራው ስራ የሚመጥን ባይሆንም በመልካም ሰዎች አስተባባሪነት ለሰራው ስራ ምስጋናና ዕውቅና ሲያገኝ የፕሮግራሙ አንድ አካል ሆኜ የደስታ ስሜቱን በመጋራቴና እሱም በህይወት እያለ ይህንን በማየቱ መጽናኛ ሆኖልኛል..መሹ ነፍስህ በሰላም ትረፍ…”
ጋዜጠኛ ምስግና መብራቱ /ከኢቢኤስ ቲቪ/

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P