test
Google search engine

“የማይፈራና በስነ-ልቦናው ያልተጎዳ ቡድን ስላለን በአፍሪካ ዋንጫው ክስተት እንሆናለን” መስፍን ታፈሰ /ሐዋሳ ከተማ/

 

ወጣቱ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች መስፍን ታፈሰ ለሁለት ጊዜው የፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮና ሐዋሳ ከተማ መጫወት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለኢትዮጵያ ተስፋና ዋናው ብሔራዊ ቡድንም  ተመርጦ የተጫወተበት አጋጣሚ ያለ ሲሆን አሁንም ለቡድኑ ተመርጦ ሀገሩን በስኬት ለማገልገል ዝግጅቱን እንደቀጠለ ይገኛል፡፡

የሐዋሳ ከተማ እና የዋልያዎቹ  የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች ብሔራዊ ቡድናችን በጥር ወር ላይ ስለሚያደርገውም የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ዙሪያውም ይህንን ብሏል “የአሁኑ ብሔራዊ ቡድን የማይፈራ ነው፤ በስነ- ልቦናውም ያልተጎዳ ነው፤ ከእዚህ መነሻነት በካሜሮን የምናደርገውን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎአችንን አሁን ላይ ስመለከተው የውድድሩ ክስተት እንደምንሆን ነው፤ ለዛም እርግጠኛ ነኝ” የሚል ምላሽንም ሰጥቷል፡፡

ለዋልያዎቹ  አጥቂ   ሊግ ስፖርት በእዚህና  በክለባቸው ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎአቸው  ዙሪያም  በጋዜጠኛዋ  መሸሻ ወልዴ አማካኝነት አናግራው  ተጨዋቹ የሰጣት ምላሽም  በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፡፡

በዋልያዎቹ የተጨዋቾች ስብስብ ውስጥ ስለመገኘቱ

“ለብሔራዊ ቡድን መጠራትና መጫወት ሁሌም ቢሆን ከፍተኛ ደስታን ይሰጥሃል፤ እኔም እነዚህን እድሎች ካለፉት ጥቂት ዓመታቶች አንስቶ  በተደጋጋሚ ጊዜ እያገኘዋቸውም ነውና የእዚሁ ቡድን አባል በመሆኔ የራስ መተማመኔን ጨምሮልኛል፤  አሁንም የእዚሁ ቡድኑ አባል ነኝ፤ ወደፊት ጥሩም ጉዞ ይኖረኛል”፡፡

የዋልያዎቹን የተጨዋቾች ስብስብ በየግጥሚያዎቹ ስትመለከተውና በአፍሪካ ዋንጫው ስለምናመጣው ውጤት

“ከዚህ ቀደም ያለን  ቡድን  በስነ-ልቦናው  በመጎዳት ጨዋታውን የሚያደርግ ነበር፤ ከዚህ ተሸንፎ ይጓዝም ነበር ፤ ከቅርብ ጊዜ በኋላ  የመጣው ቡድን ግን  ማንንም የማይፈራ ብሎም ደግሞ በስነ-ልቦናውም ያልተጎዳ ሆኖ በውድድር ላይ የሚቀርብ እንደዚሁም በተጋጣሚዎቹም እየተፈራና ለእኛም ትላልቅ ሀገራቶች ሁሉ ግምት እየሰጡን ያለ ስለሆነም ጥሩ ለውጦችን ተመልክቼበታለው፤ ከእዚህ መነሻነትም በአፍሪካ ዋንጫው  ተሳትፎአችን ላይ ጥሩ ውጤት እናመጣለን፤ የውድድሩም  ክስተት እንሆናለን”፡፡

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ክለባቸው ስላለው የዘንድሮ የውድድር ጅማሬ

“የያዝነው ዓመት የሊግ አጀማመራችን  በጣም ጥሩ ነው፤ ካደረግናቸው ሶስት ጨዋታዎች ውስጥ አንዱን በመሀል ብንሸነፍም ሁለቱን በድል ልንወጣ ችለናል፤ ቶሎ ብለንም ወደ አሸናፊነት መንፈሱ ተመልሰናል፤ ከዛ ውጪም መልካም የሚባል የጨዋታ እንቅስቃሴንም በሜዳ ላይ እያሳየን ስለሆነም በዛ ተደስተን ይገኛል”፡፡

ከውድድሩ ጅማሬ አንፃር ስላላቸው ጥንካሬና ክፍተት ጎን

“ስለ ደካማ ወይንም ደግሞ ክፍተት ጎናችን አሁን ላይ አለ ብዬ አላስብም፤ ምክንያቱም ሊጉ ገና ጅማሬ ላይ ስለሆነና ቡድኖችም አንዳቸው አንዳቸውን በማጥናት ላይ የሚገኙበት ክለባቸውንም በደምብ አድርገው እያጠኑበት ያለ ጊዜም በመሆኑ ነው፤ ወደ ጥንካሬያችን ሳመራ ግን አምና ያለን ህብረትና አንድነት አሁንም ከቡድናቸን ጋር አብሮን ያለ ነው፤ ያንንም ነው እያስቀጠልንም የሚገኘውና ለዛም ነው በውጤት ደረጃ ቡድናችንን በጥሩ ሁኔታ እየተጓዘ የሚገኘው”፡፡

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ካደረጋችኋቸው ሶስት ጨዋታዎች የቁጭት ስሜትን የፈጠረባችሁ

“ከወላይታ ድቻ ጋር ያደረግነውና የተሸነፍንበትን ጨዋታ ነው የተቆጨንበት፤ ሽንፈት አንድ አንዴ በእግር ኳስ ውስጥ ያጋጥማል፤ በዛን ዕለት ጨዋታ እኛ በጣም ጥሩ ነበርን፤ ነገር ግን እነሱ ቀድመው አገቡብንና ዘገቡን፤ ብዙ ጎል የማስቆጠር እድሎችን ፈጥረን ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ልናመክናቸው ችለናልና፤ እንደዚህ አይነት ሽንፈቶች ስለሚያጋጥሙ ተቀብለነው ወደ ቀጣይ ስራችን አምርተናል”፡፡

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሲቋረጥ የመጨረሻ ጨዋታችሁን ሲዳማ ቡናን በማሸነፍ ነበር ያጠናቀቃችሁት፤ የእዛን እለት እሳት ለብሳችሁ፤ እሳት ጎርሳችሁ የገባችሁበት የተለየው ስሜት ምን ነበር….?

“በዛ መልኩ ለመጫወታችን ምንም አይነት ሚስጥርም ሆነ ምክንያት የለም፤ የሁለታችን ጨዋታ ሁሌም ቢሆን የደርቢ ስሜት ስላለውና በዛ ላይ ደግሞ ግጥሚያውን ረተን ወደ አሸናፊነት መንፈሱም በፍጥነት መመለስ ስለነበረብንና በዛም ላይ ስለተነጋገርንበት ነው ግጥሚያውን በእልህ ተጫውተን ያሸነፍነው”፡፡

ስለ ተጋጣሚያችሁ ሲዳማ ቡናና በዛን ዕለት ግጥሚያውን ለማሸነፍ ስለነበራችሁ ልዩነት

“ሲዳማ ቡናዎች የግብ እድልን በመፍጠሩ በኩል ከእኛ ይሻሉ ነበር፤ ግን እድሉን አልተጠቀሙበትም፤ እኛ ደግሞ በከፍተኛ ሞራል በመጫወት ስሜትና  ያገኘነውንም  እድል በመጠቀም በኩል ጥሩ ስለነበርንም ነው እነሱን ካሸነፍንባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ ሊሆንልን የቻለው”፡፡

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ከተቋረጠበት ዳግም ሊቀጥል ተዘጋጅቷል፤ ውድድሩ ነገም ይጀመራል፤ ከዚህ በኋላ የሚኖረው የቡድናችሁ ጉዞ የት ድረስ ነው…..?

“ሐዋሳ ከተማ በደርቢው ፍልሚያ ሲዳማ ቡናን አሸንፎ ጣፋጩን ድል ከተጎናፀፈ በኋላ በቀጣዮቹም ጨዋታዎች ይሄንን የያዘውን የአሸናፊነት መንፈስ ለማስቀጠል ነው በሚገባ እየተዘጋጀን የሚገኘው፤ ክለባችን በሊጉ የጅማሬ ጨዋታዎች አሁን እያስመዘገበ ባለው ውጤት ፈፅሞ አይኮፈስምና ድሉን የምናስቀጥለው ነው”፡፡

በሐዋሳ ከተማ ውስጥ ዘንድሮ ስለተመለከተው የተለየ ነገር

“ለእኔ ለየት ያለብኝ አምና ውድድራችንን ስንጀምር በሽንፈት ነበር የጀመርነው፤ ዘንድሮ ደግሞ በውጤታማነት ነው ሊጉን እያስጓዝን የሚገኘው”፡፡

ስለ አዲሱ የቡድናቸው አሰልጣኝ እና ስለ ዘንድሮ የተጨዋቾች ስብስባቸው

“ስኳዳችንን በሚመለከት ብዙዎቹ አምና የነበሩት ናቸው፤ ጥቂቶች ብቻም ናቸው እኛን የተቀላቀሉት፤  በአብዛኛው በወጣቶች የተገነባ ጥሩ ስብስብም ነው ያለን፤ ህብረታችንና አብሮነታችንም እንዳለ ስለሆነም በሊጉ ጥሩ የሚባል ውጤትን እናስመዘግባለን፡፡ ወደ አሰልጣኛችን ዘርዓይ ሙሉ ስመጣ ክለቡን በአዲስ ሀላፊነት ሊያገለግል ወደ ክለቡ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ እንደተመለከትኩት ለተጨዋቾች ያለው ነገር ጥሩ ነው፤ አቅምህን አውጥተህ እንድትጫወት ያደርግሃል፤ በወጣት ተጨዋቾች ላይም እምነት አለው፤  ከዛም በተጨማሪ በአጨዋወት ደረጃም የክለቡን እንቅስቃሴ ለማሳደግ እየጣረ የሚገኝም ነውና ጥሩ ነገርን እያየሁበት ነው”፡፡

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአችሁ የሁለት ጊዜ ሻምፒዮናው ክለባችሁ ዘንድሮስ ምንን አልሟል…?

“ይሄን ክለባችንን በሚመለከት በ1996 እና በ1999 የሊጉን ዋንጫ ለሁለት ጊዜ ማንሳቱን ሰምተናል፤ ያኔ እኛ አብዛኛዎቹ ተጨዋቾች አልነበርንም፤ ከዛ በኋላ ግን ይሄ ቡድን ያን ታሪክ መድገም አቅቶታል፤ ስለዚህም የአሁኑ ጊዜ የቡድኑ ተጨዋቾች የእዚህን ቡድን ስምና ዝና እንደዚሁም ደግሞ ስኬት ዳግም መመለስ ከእኛ የሚጠበቅ ትልቅ የቤት ስራ ስለሆነ ለየጨዋታዎቹ ጠንክረን ልንቀርብ ይገባል፤ በቤትኪንግ የእዚህ ዓመት ተሳትፎ ሁሉም ቡድን ውድድሩን ሲጀምር ዋንጫን ለማንሳት ነው፤ አዳዲስ አሰልጣኞች ሲመጡ ደግሞ ዋንጫ ማንሳት እንደ ግዴታ ባይቆጠርባቸውም እኛ የቡድኑ ተጨዋቾች ግን እንደ ፈጣሪ ፈቃድ ዋንጫውን ለማንሳት  ነው የምንጫወተው”፡፡

በሐዋሳ ከተማ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ጅማሬህ በምፈልገው መልኩ ለክለቡ ጥሩ እየተንቀሳቀስኩ ነው ትላለህ…?

“እንደ ቡድኑ አጨዋወትና ለእኔ እንደተሰጠኝ የጨዋታ ሚና አዎን ጥሩ እየተንቀሳቀስኩ ነው፤ በሐዋሳ ከተማ አጨዋወት ውስጥ እኔ ቡድኑን እያገለገልኩ የምገኘው ወደዳር ወጥቼ እንዳጠቃና ቡድኑ ኳስ ሲያጣ ደግሞ በጥልቀት መለስ ብዬም በመከላከሉ ላይ ቡድኑን እንዳግዝም ነው፤ በዚህ አጨዋወት ውስጥ ጎል ማስቆጠሩ ላይ ብዙ ሊጋብዘኝ ባይችልም እኔ ግን ጎል ከማስቆጠር ወደ ኋላ እንደማልል እርግጠኛ ነኝ”፡፡

ስለ ቡድናቸው አጥቂ ብሩክ በየነ

“ብሩክ በክለባችን ውስጥ በጥሩ ብቃቱ ከምናደንቀው ተጨዋቾች መካከል አንዱ ነው፤ ጎል የማስቆጠር ኳሊቲው ይገርማል፤ ጥሩ አጣማሪዬም ነው፤ ዘንድሮ ለክለቡ የተሻለ ነገርን ይሰራል፤ እንደ ግልና እንደ ቡድንም ተቀናጅተን በመጫወት ክለቡን ለጥሩ ደረጃም የምናበቃው ይመስለኛል”፡፡

እስካሁን ለረጅም ዓመታት ኳስን እየተጫወቱ ስላሉት ሁለቱ የቡድናቸው ሲኒየር ተጨዋቾች አዲስ ዓለም ተስፋዬና ዳንኤል ደርቤ

“የእነዚህ ሁለት ተጨዋቾቻችንና ቡድኑንም በአምበልነት እየመሩት ስላሉት ልጆቻችን ከወዲሁ  ማለት የምፈልገው ከእኛ ጋር አብረው መኖራቸው በጣም እየጠቀመን ነው፤ ልምዳቸውን እያካፈሉን ይገኛል፤  እነሱ  ቤቱን በደንብ  ያውቁታል፤  የሚነግሩንን  ምክርም እንሰማለን፤ በዚሁ ጠንክረን ሰርተን በመምጣትም ፈጣሪ ጤናውን ይስጠን እንጂ እንደ እነሱ ለረጅም ዓመታት እግር ኳስን ለመጫወት እንሞክራለን፤ በእዚህ አጋጣሚም ለሚሰጡን ምክር ላመሰግናቸው እፈልጋለው”፡፡

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ አብዛኛው ተጨዋቾች የሐዋሳ ዩንቨርስቲ ሜዳን ስለማማረራቸው

“ይሄ እኮ ሀቅ ነው፤ በማይመች እና ተጨዋቾችን ለጉዳት በሚዳርግና እየዳረገ ባለም ሜዳ  ላይ ነው እየተጫወትን የሚገኘው፤ እንደዛም

ሆኖ ግን  ተጨዋቾች ሜዳው ባይመቻቸውም አቅማቸውን አውጥተው ለመጫወት ሲሞክሩ ይታያሉና ጥሩ ባይሆኑ እንኳን እነሱ ላይ መፍረድ በጣም ከባድ ነው”፡፡

የሜዳው ችግር ምን እንደሆነ

“በጣም ደርቋል፤ ታኬታ አድርገህ ስለምትጫወትበትም ለጉዳት ይዳርግሃል፤ ስለዚህም ለእዚህ ሜዳ አዘጋጁ አካል ትኩረት ሰጥቶት ተመልካቹ ጥሩ እግር ኳስን ቢመለከትበት መልካም ይመስለኛል”፡፡

ስለ ቀጣዩ የእግር ኳስ ጉዞው ምን እያሰበ እንደሆነ

“በሐዋሳ ከተማ ክለብ ውስጥ አሁን ላይ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን እያሳየው እገኛለው፤ ከዚህ በኋላ በሚኖረኝ የኳስ ህይወቴ ደግሞ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ውጪ ወጥቼ ከዛም ባሻገር ለሀገሬ ብሔራዊ ቡድንም በመጫወት  ትልቅ ተጨዋች የመሆን እልም አለኝና ያን ማሳካት ቀዳሚው ግቤ ነው”፡፡

በእግር ኳስ ማሻሻል የሚፈልገው

“አሁን ላይ ገና ሙሉ ተጨዋች አይደለሁም፤ የሚቀረኝ ነገር አለ፤ ያንንም ከራሴ ጋር እያወራሁበትም  ነው የሚገኘው፤ በክፍተቴ ላይ ሰርቼ በመምጣትም የሀገሪቱ ምርጥ ተጨዋች መባልን እፈልጋለው”፡፡

የእረፍት ጊዜውን ስለሚያሳልፍበት መንገድ

“በአብዛኛው ቤት ውስጥ ነው፤ ሌላው ደግሞ ወደምናርፍበት ሆቴል ሳመራ ወይ ለመተኛት አለያም ደግሞ ለመመገብ በምንፈልግበት ጊዜ እዛው ሄጄ አሳልፋለው”፡፡

በመጨረሻ….

“ፈጣሪ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

P