Google search engine

“የሰሜን አሜሪካው ውድድር ኢትዮጵያዊነት የሚቀነቀንበት ፕሮግራም ነው”አቶ ተድላ በላይነህ የሚኒሶታ ኒያላ ስፖርት ክለብ ፕሬዝዳንትና የESFNA የቦርድ አባል

“የሰሜን አሜሪካው ውድድር ኢትዮጵያዊነት የሚቀነቀንበት ፕሮግራም ነው”

አቶ ተድላ በላይነህ የሚኒሶታ ኒያላ ስፖርት ክለብ ፕሬዝዳንትና የESFNA የቦርድ አባል

በዓለምሰገድ ሰይፉ

ለ36 አመታት በፅናት በመስራትና ኢትዮጵያኖችን በማቀራረብ ረገድ የላቀ ሚና የተጫወተው የሰሜን አሜሪካው ፌዴሬሽን ESFNA ዘንድሮ በአትላንታ ደማቅ የሆነ ድግስ አዘጋጅቷል፡፡ በሃገራችን ከመጣው አዲስ ለውጥ ጋር ተያይዞ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያውያኖች ውድድር የሚያዘጋጀው ESFNA በዚህ ውድድር ላይ ሊታደሙ የሚችሉና በስተመጨረሻው ሰአት ሰርፕራይዝ የሚያደርጉ እንግዶችም እንዳሉት ሰምተናል፡፡ በእዚህና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚኒሶታ ክለብ ፕሬዝዳንትና የESFNA የቦርድ አባል አቶ ተድላ በላይነህ ከሊግ ስፖርት ማኔጂንግ ኤዲተር አለምሰገድ ሰይፉ ጋር አጭር ቆይታ አላቸው፡፡ በነገራችን ላይ ከሊግ ስፖርት ጋዜጣችን በተጓዳኝ በwww.leaguesport.net ትኩስ መረጃዎችን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡  

ሊግ፡- አንተ የምትመራው የሚኒሶታ ኒያላ ስፖርት ክለብ ከተቋቋመ ምን ያህል ጊዜ አስቆጠረ? በምንስ አቋም ላይ ይገኛል?

አቶ ተድላ፡- የሚኒሶታ ኒያላ ስፖርት ክለብ ከተቋቋመ ረጅም አመታትን አስቆጥሯል፡፡ ይህም ማለት እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1988 ዓ.ም ነው የተመሰረተው፡፡ በአንደኛው ዲቪዝዮን ለአራት ጊዜያት ያህል ለዋንጫ ፍልሚያ ደርሶ ዋንጫ ለማንሳት ባይታደልም ክለቡ በከፍተኛ ደረጃ የሚከበርና የሚፈራ ቲም ነበር፡፡ ነገር ግን ባለፉት 12 አመታት በተጨዋቾች እጥረትና በተለያዩ ምክንያት እንቅፋት ሆኖብን ወደ ሁለተኛ ዲቪዝዮን ወርደን ከ12 አመት በኋላ ዳላስ ላይ በተደረገው ውድድር የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ወደ አንደኛ ዲቪዝዮን ማለፍ ችለናል፡፡

ሊግ፡- ክለቡ ከተቋቋመ ረጅም አመት ከማስቆጠሩ በዘለለ የተሻለ ውጤት ተብሎ ሊገለፅ የሚችለው የትኛው ነው?

አቶ ተድላ፡- በ1990ዎቹ አካባቢ በጣም ጠንካራ ተጨዋቾች ስለነበሩ ቡድናችን የተሻለ አቅም ነበረው፡፡ ለምሳሌ ያክል እነ ጠንክር አስናቀ፣ ራምዜ፣ ነብዩ፣ጌታቸውና ሌሎች በርካታ የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ስለነበሩ ይህ ስብስብ በጣም አስፈሪ ነበር፡፡

ሊግ፡- ቡድኑን ጠንካራ መሰረት ለማስያዝ በምታደርጉት ጥረት የገጠማችሁ ፈተና እንዴት ይገለፃል?

አቶ ተድላ፡- እውነት ነው ቡድኑን መሰረት ለማስያዝ የነበረው ፈተና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በዛ ላይ ሁሉ ነገር የሚሰራው በበጎ ፈቃደኝነት ነው፡፡ የክለቡ ፕሬዝዳንት፣ የስራ አስኪያጅ፣ አሰልጣኝና ተጨዋቾች ለሚሰጡት ግልጋሎት የሚከፈላቸው ምንም ነገር የለም፡፡ በአንፃሩ ፌዴሬሽኑ የሚሸፍናቸው ወጪዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የስቴድየም፣ የትራስፖርትና የሆቴል ወጪዎችን ይሸፍናል፡፡ ከዛ በተረፈ ሁሉም ተጨዋች ወጪያቸውን የሚችሉት በራሳቸው ነው፡፡ ይህንንም ለመሸፈን ተጨዋቾች ከራሳቸው ከሚያወጡት በተጨማሪ ስፖንሰሮች በማፈላለግ ነው የምንሰራው፡፡ ይህን ነገር ከውጪ ስታየው ቀላል ይመስላል፡፡ ነገር ግን ስራው በጣም ፈታኝ እንደሆነ ብናውቅም የምናፈቅረው ስፖርት በመሆኑና ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻችንን በአመት አንድ ጊዜ የሚያገናኝ ፕሮግራም በመሆኑም ሁሌም በጉጉት ነው የምንጠብቀው፡፡

ሊግ፡- ዘንድሮ አትላንታ ላይ በሚደረገው ውድድር ቡድናችሁ ምን ድረስ ለመጓዝ አስቧል?

አቶ ተድላ፡- በውጤት ደረጃ ካየኸው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውድድር ስትገባ ትንሽ ያስቸግራል፡፡ አሁን በአትላንታ በሚደረገው ውድድር ላይ ራሱ የሚገጥሙን ቡድኖች በአለም ዋንጫ ላይ የሞት ምድብ የሚባለው አይነት ነው፡፡ በአንደኛ ዲቪዝዮን 1ኛ የወጣው የሲያትል ባሮን ነው የምንገጥመው፡፡ በመቀጠል ሜሪላንድ ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ የዲሲው  የቅዱስ ሚካኤል ቡድን ነው፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንክረን እየሰራን እንገኛለን፡፡ በዛ ላይ ወጣቱ አሰልጣኛችን ቴዲ ሞላ ቡድኑን በደንብ እያዘጋጀው ይገኛል፡፡

ሊግ፡- በየአመቱ በሰሜን አሜሪካ የምታደርጉት ውድድር ኢትዮጵያኖችን ከማቀራረቡ ባሻገር ስፖርቱን በማገዝ ረገድ ያለው ሚና እንዴት ይገለፃል?

አቶ ተድላ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳኸው፡፡ ሁላችሁም እንደምታውቁት ይህ ፌዴሬሽን የተቋቋመው በስደተኞች ነው፡፡ በመሆኑም የውድድሩ ዋነኛ አላማ ኢትዮጵያኖችን እንዴት ማቀራረብ እንችላለን? የሚለው ሃሳብ ሲነሳ ብቸኛ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው የዚህ አይነቱን ስፖርታዊ ቶርናመንት ማዘጋጀት ነበር፡፡ እናም በፈረንጆች አቆጣጠር በ1984 በአራት ቲሞች ይህ ፌዴሬሽን እውን ሊሆን ችሏል፡፡ ካልተሳሳትኩ ይህ ውድድር የተጀመረው ሂውስተን ላይ ነው፡፡ በአራት ቡድኖች የተጀመረው ውድድር በሂደት አድጎ በአሁን ሰአት 32 ተሳታፊ ቡድኖች በዚህ ቶርናመንት ላይ ይሳተፋሉ፡፡

ከዚህ አንፃር ካየኸው በየአመቱ የሚደረገው ውድድር ከፍተኛ ወጪ ነው የሚጠይቀው፡፡ ይህም ማለት እያንዳንዱ ቡድን 25 ተጨዋቾች ይኖሩታል፡፡ በአጠቃላይ ሲሰላ ወደ ስምንት መቶ ይደርሳል፡፡ በዛ ላይ የእነዚህ ተጨዋቾች፣ ቤተሰቦችና ጓደኞች ሲጨመር በጣም በርካታ ነው፡፡ በአስተዋፅኦ ደረጃ ላነሳኸው ጥያቄ ውድድሩ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ መጫወት የሚችሉ ልጆችን አፍርቷል ማለት ባልችልም በዚህ ረገድ ለሃገራችን ፉትቦል ተጨዋች ማበርከት የምንችልበት ጊዜ የተቃረበ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በርካታ ጥሩ ብቃት ያላቸው ልጆች አሉ፡፡ በአሜሪካ በሜጀር ሊግ ላይም የሚሳተፉ ስላሉ ወደፊት የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድን የሚያገለግሉ ተሰላፊዎችን እንደምናፈራ ተስፋ አለኝ፡፡

ከምንም በላይ ግን ለእኛ ፌዴሬሽን እንደትልቅ እገዛ ብለን የምናስበው ከአሁን በፊት በሃገር ውስጥ ለብሄራዊ ቡድንና በተለያዩ ክለቦች ግልጋሎት ሰጥተው የተረሱ ሰዎችን በመጋበዝ እነርሱን ከማስተዋወቅ ባሻገር ታሪካቸው እንዳይረሳ ለማድረግ በትጋት እየሰራን ነው፡፡

ሊግ፡- በድጋሚ ለማስታወስ ያህል በዘንድሮው በአትላንታው ውድድር ላይ የሚጋበዙት እንግዶችን ቢገልፁልኝ?

አቶ ተድላ፡- አቶ ሃይለማሪያም ሻሾ፣ መሃመድ ከድርና ጊላ ሚካኤል ናቸው፡፡ ይህ ግለሰብ በሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሻምፒዮን ሲሆን የቡድኑ ግብ ጠባቂ የነበረ ነው፡፡ እነዚህን ሶስት ሰዎች በዘንድሮው የአትላንታ ውድድር በእንግድነት እናመጣለን፡፡ የዚህ ፋይዳ ደግሞ ያለፈውን ትውልድ ከአዲሱ ትውልድ ጋር ለማስተዋወቅና ለማቀራረብ ነው፡፡

ሊግ፡- የዘንድሮው የአትላንታው ዝግጅት በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?

አቶ ተድላ፡- አለምሰገድ ለኢንተርቪው ከመገናኘታችን በፊትም ስደውልልህ ይህን ጉዳይ አንስተህልኝ ነበር፡፡ የአትላንታው ዝግጅት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነው፡፡ ነገር ግን በስራ ሂደት ሊፈጠር የሚችል ነገር አጋጥሞናል፡፡ ይህም በ2014 ሳኖዜ ላይ የስቴድየም ኪራይ ችግር አጋጥሞን ነበር፡፡ አሁንም ምንድነው የሆነው መጀመሪያ የተገኘው ስቴድየም ትልቅ የነበረ ሲሆን ኮንትራቱም በደንብ ጠርቶ ለፊርማ የተዘጋጀ አልነበረም፡፡ በዛ ምክንያት የስቴድየሙ ኪራይ ሊቀንስ ይችላል የሚል እምነት ነበረን፡፡ ነገር ግን ያሰብነው ባለመሆኑ ምክንያት ያንን ሰርዘን ሌላ ስቴድየም መፈለግ ነበረብን፡፡ አንተም እንደምታውቀው አንድን ኮንትራት ሰርዘህ ወደሌላ ስትሄድ ትንሽ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ምንም እንኳን ሂደቱ ጊዜ ቢወስድም ይህ በየአመቱ በተሻለ ሁኔታ የሚካሄድ ቶርናመንት መስተጓጎል የለበትም በሚል መነሻነት የዋሽንግተን ዲሲ ቲምን ጠይቀን ሜሪላንዶች “እናዘጋጃለን” ብለው እድሉ ተሰጣቸው፡፡ በነገራችን ላይ ሁሉን ነገር የምንሰራው በጣም ግልፅና ዲሞክራቲክ በሆነ መንገድ ነው፡፡ በመሆኑም ሁለቱም ቲምች አዲስ አግሪመንት አቅርበው በድጋሚ አሁንም አትላንታ አሸነፈ፤ እናም የተወሰነ መጓተት  የፈጠረው የስቴድየሙ ኪራይ ነበር፡፡ በተረፈ አሁን ሁሉ ነገር መሰረት የያዘ በመሆኑ አትላንታ የሚገኘው ኮሚዩኒቲና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለዝግጅቱ ስኬት በከፍተኛ ደረጃ እየተረባረበ ነው፡፡

ሊግ፡- በመሃል ይህ ነገር መፈጠሩ የፕሮግራማችሁን ስኬጁል አላበላሸባችሁም?

አቶ ተድላ፡- ምንም የፈጠረብን ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ይህ ለ35 አመታት የቆየ ፌዴሬሽን በስራ ሂደት ብዙ ነገሮችን የተማረ በመሆኑ የዚህ አይነቱ ክፍተት ሲፈጠር እንዴት መፈታት እንዳለበት ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ ያው እንደምታውቀው ፕሮግራሙ ቅዳሜ ተከፍቶ እሁድ ይዘጋል፡፡ አርብ ደግሞ የኢትዮጵያ ቀን ነው፡፡

ሊግ፡- ውድድሩ ከሚጠይቀው ከፍተኛ ወጪ አንፃር በጀቱን ለማሟላት የተደረገው እንቅስቃሴ ስኬታማ ነበር ማለት ይቻላል?

አቶ ተድላ፡- ይሄንን ውድድር ብዙ ጊዜ የምናካሂደው አንድም በፌደሬሽኑ አቅም ከዛም ግፋ ሲል ስፖንሰሮችን በማፈላለግ ነው፡፡ ሲያትል ላይ ኡበር ስፖንሰር አድርጎናል፡፡ በዳላስ ውድድር ላይም ሰቨን ኢለቨን የሚባል ኩባንያ ስፖንሰር አድርጎናል፡፡  ከዚህ በተረፈ እዛ የሚገኙ ኢትዮጵያኖች እና የቢዝነስ ተቋማት መዋጮ ያደርጋሉ፡፡ በአብዛኛው ግን ይህ ፌዴሬሽን ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው፤ እናም ከአመት አመት ራሱን የቻለ በጀት ስላለ በዚህ ረገድ ያፈርንበት ሁኔታ ተፈጥሮ አያውቅም፡፡

ሊግ፡- በአትላንታው ውድድር ላይ ስንት ቡድኖች ይሳተፋሉ? ማረጋገጫስ ሰጥተዋል?

አቶ ተድላ፡- ከሌላው ጊዜ ምንም የተለየ ነገር የለውም፤ በዚህ ውድድር ላይ ከአመት አመት የሚሳተፉ ቡድኖች 31 ክለቦች አሉ፡፡ 32ኛው ደግሞ ቅዱስ ሚካኤል የሴቶች ቡድን ነው፡፡ እዚህ ላይ የእነርሱ ተፎካካሪ ቲም ባይኖርም እነርሱ ግን መጥተው ይሳተፋሉ፡፡ በአጠቃላይ በውድድሩ የሚሳተፈው 32 ቡድን ነው፤ ከዛሬ 8 አመት በፊት የሚኒሶታ የሴት ቡድን ለውድድሩ ሄዶ ነበር፡፡ ከእግር ኳስ በተጨማሪ ዋነኛ አላማና ግባችን ኢትዮጵያኖችን ማቀራረብም በመሆኑ ሴቶችንም ለማሳተፍ ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው፡፡

ሊግ፡- የእናንተ ፌዴሬሽን ከሌሎች የሚለየው ውድድር ከማሰናዳት ባሻገር በበጎ አድራጎት ላይ የተሳተፉ ድርጅቶችን ታግዛላችሁ፤ ዘንድሮስ?

አቶ ተድላ፡- የፌዴሬሽኑን አላማ ያልተረዱት አንዳንድ ወገኖች ኳስ ብቻ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ እውነታው ግን እንደዛ አይደለም ኳሱ ተካሂዶ ስፖርተኞች መገናኘታቸው እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ከዛ በተጓዳኝ ግን ሁላችንም መርሳት የሌለብን ነጥብ ኢትዮጵያውያን እንደመሆናችን መጠን የሃገራችን ጉዳይ ይመለከተናል፡፡ በመሆኑም በተለያዩ ጊዜ ወገኖቻችን ላይ በደረሱት ጉዳቶች ድጋፍ ያደረግንበት ሁኔታ አለ፡፡

ከዛ በተረፈ እዛው በአሜሪካ ለተለያዩ ወገኖቻችን ስኮላር ሺፕ እንሠጣለን፡፡ የተለያዩ የመጣጥፍና ስነ-ፅሁፍ ውድድር አካሂደን ለአሸናፊዎች እውቅና እንሰጣለን፡፡ ከምንም በላይ ግን ይህን ፌዴሬሽን ከሌሎች የሚለየው አንጋፋነቱ ነው፡፡ 35 አመታት ያህል በፅናት ቆሞ ይሄን የመሰለ ድንቅ ውድድር በየአመቱ ማሰናዳት መቻል ትልቅ ነገር ነው፡፡ ይህ ማለት ግን በነበረው የረጅም አመት ጉዞ መሰናከል አልገጠመውም ማለት አይደለም፡፡ በተለያየ ጊዜ ብዙ ችግሮች አጋጥመውንና “በቃ ይሄ ፌደሬሽን አበቃለት” በሚባልበት ጊዜ የአምላክ እገዛም ታክሎበት ይኸው እነሆ 35ተኛ አመት ላይ ደርሰናል፡፡ ወደፊት ደግሞ ከእዚህ እጥፍ በሆነ እድሜ ከነጥንካሬው እንደሚቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡   

ሊግ፡- የአትላንታውን ውድድር ለየት የሚያደርገው በሃገራችን ከመጣው ለውጥ ማግስት የሚደረግ ከመሆኑ አንፃር ምን አዲስ ነገር እንጠብቅ?

አቶ ተድላ፡- ቀደም ብዬ እንደገለፅኩልህ የክብር እንግዶቹ ማንነት ታውቋል፡፡ ከዛ ውጪ ያሉ ነገሮች እንዳሉ ባውቅም በስተመጨረሻ ላይ ሰርፕራይዝ የሚደረጉ በመሆናቸው ለመናገር እቸገራለሁ፡፡ ይህን የምልህ ሚስጢር ላደርግብህ ፈልጌ ሳይሆን ይሄን ሰርፕራይዝ እኛ ራሳችን የቦርድ አባላቱ የማናውቀው ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡ በተለይ በውድድሩ መክፈቻና መዝጊያ ፕሮግራም ላይ የሆነ ሰርፕራይዝ የሚኖር ይመስለኛል፡፡ በተለይ ከለውጡ በኋላ ባለፈው  ጊዜ ዳላስ ላይ በተደረገው ውድድር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በቀረበልን ጥያቄ መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትራችን አቶ አብይ ውድድሩ ላይ ለመገኘት ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡

ሆኖም ከነበረው ጊዜ እጥረት አንፃር፣ ከሴኩሪቲ፣ ከስቴድየሙ ማነስና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ጠይቀናል፡፡ እናም በዘንድሮው ውድድር ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ይገኛሉ የሚለው ተስፋችን በጣም ትልቅ ነው፡፡ ዶክተር አብይ ይህን ጋዜጣ የሚያነቡ ከሆነ እሳቸውን ለመቀበል በራችን በትልቁ ክፍት ነው፡፡ መጨረሻ ላይም ሰርፕራይዝ እንሆናለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሊግ፡- ፌዴሬሽናችሁ ተፅዕኖ ፈጣሪነቱን ተጠቅሞ ወደፊት ምን ለማድረግ አስቧል?

አቶ ተድላ፡- እኛ ሁሌም ራሳችንን በሚገባ እንፈትሻለን፡፡ በየአመቱ የሚሳተፉት 32ቱ ቲምች ሁለት ሁለት ተወካዮቻቸውን ይልካሉ፡፡ አንደኛው ተለዋጭ ሲሆን የተቀረው ደግሞ ዋና ተወካይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ስራ አስኪያጁን ጨምሮ ወደ 90 የሚጠጋ ሰው ቁጭ ብሎ ሃሳብ የሚያፈልቅበትና ይህ አንጋፋ ፌዴሬሽን በቀጣዮቹ 35 አመታት በምን ቁመና ላይ ነው የሚደርሰው? የሚለውን ሃሳብ በሚገባ እንፈትሻለን፡፡ ለዚህም ስኬት ወጣቶችን ማሳተፍና ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚሉት ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው፡፡ ለምሳሌ ከአሁን በፊት ዘ-ልማዲዊ የነበረውን የትኬት አሻሻጭ እነዚህ ወጣቶች ከመጡ በኋላ አሰራሩን አዘምነውታል፡፡ በእዚህም ምክንያት ተመልካቹ ከፈለገ ኦን-ላይን፣ አልያም የሳምንቱን ጨዋታ ፓኬጅ መግዛት የሚችልበትን መንገድ ከፍተናል፡፡

ሊግ፡- በስተመጨረሻ የሚሉት ነገር ካለ በሩ ክፍት ነው…

አቶ ተድላ፡- ምንም እንኳን ያለነው ከአገር ውጪ ቢሆንም ሁሌም ቢሆን ቤተሰባችንን፣ ህዝባችንን እና ሃገራችንን ከማሰብ ወደኋላ ብለን አናውቅም፡፡ አቅም ፈቅዶልን አንጋፋ የተባሉትን ሁሉንም ማምጣት ብንችል ደስ ባለን ነበር፡፡ እንደዛ ሆኖ ግን ለኢትዮጵያ ስፖርት ደም የሰጡና ለሃገራቸው ነፃነት መውጣት በፅናት የታገሉ ግለሰቦችን በተለያየ ጊዜ እንግዳ በማድረግ ጋብዘናቸዋል፡፡

በዚህም ምክንያት በሰሜን አሜሪካና ካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያኖች የእነዚህን ሰዎች ማንነት ጠንቅቅው እንዲገነዘቡ ለማስቻል የምንችለውን ያህል ጥረት አድርገናል፡፡ እንደምሳሌም ባለፈው ዳላስ ላይ በተደረገው ውድድር አየለ ማሞና እስክንድር ነጋ ተጋባዥ ነበሩ፡፡ ከዛ በፊት በነበሩ ተሳትፎዎች ደግሞ ሲያትል ላይ ካስ ፊደሉን፣አቶ አስቻለው ማሞ ዲሲም የመጡበት ጊዜ አለ፡፡ በ2015 አቶ ተስፋዬ ፈጠነ፣ በ2014 በዛ ያሉ እንግዶች ነበሩን አቶ ሰለሞን ሽፈራውና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ተጋብዘዋል፡፡ እነዚህን እንደምሳሌነት አነሳሁልህ እንጂ በርካት ያሉ የክብር እንግዶችን ጋብዘናል፡፡ እነዚህ ለሃገር ውለታ የሰሩ ሰዎችን እኛ በእድሜ ገፋ ያልን ሰዎች ልናውቃቸው ብንችልም አዲሱ ትውልድ ስለእነዚህ ግለሰቦች ማንነት ጠንቅቆ እንዲረዳና የተበታተኑትን ኢትዮጵያዊያን በእዚህ ስፖርት ሳብያ አሰባስበን ወደ አንድ ቦታ ማምጣት የሚለው ነጥብ ነው፡፡ በዛ ላይ ይህ ፌዴሬሽናችን በዘር፣ በፆታ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት በማናቸውም ነገሮች ልዩነት ሳይፈጥር ስለ   ኢትዮጵያዊነት ብቻ የሚቀነቀንበት ውድድር ነው፡፡ ይሄም አንድነታችንና ህብረ ብሄራዊነታችን መቀጠል መቻል አለበት፡፡ እንደሚቀጥልም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሊግ፡- አቶ ተድላ እጅግ በተጣበበው ፕሮግራም ላይ ሠአት ወስደው ከእኛ ጋር ቆይታ በማድረግዎ ላቅ ያለ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ?

አቶ ተድላ፡- እኔም ለተሠጠኝ እድል አመሠግናለሁ፡፡

በመሸሻ ወልዴ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮናን መቐለ 70 እንደርታ ሲመራ ደደቢት ደግሞ የመጨረሻውን ስፍራ ይዞ ይገኛል፤ የፕሪምየር ሊጉ ውድድር ሊጠናቀቅ የ7 ሳምንታት ጨዋታዎች በቀሩበት የአሁን ሰዓት ላይም እስካሁን በተደረጉት ጨዋታዎች የውድድሩ ሻምፒዮናም ሆነ ወራጅ ክለቦቹ ስላልታወቁ ቀጣይ ጨዋታዎቹ አጓጊም ሆነዋል፤ የሊጉ የ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬና ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች ቀጥለው የሚደረጉ ሲሆን ከእነዚህ ተወዳዳሪ ክለቦች መካከል በሊጉ ቡድኖቻቸው እየተጓዙ ስለሚገኙበት መንገድ እና የውድድር ዘመናቸውንም በምን ውጤት እንደሚያጠናቀቁ እንደዚሁም ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን ለጅማ አባጅፋሩ አክሊሉ ዋለልኝ እና ለደቡብ ፖሊሱ ሄኖክ አየለ ጥያቄዎችን አቅርበንላቸው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P