Google search engine

“የሲዳማ ቡና መዘናጋት እኛን ለድል አብቅቶናል” “አቡበከር ናስርን ሁሌም ነው የማደንቀው፤ እሱ ሀበሻ  አይመስለኝም” እንዳልካቸው መስፍን /አርባምንጭ ከተማ/

 

አርባምንጭ ከተማ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የእዚህ ሳምንት ጨዋታ ሲዳማ ቡናን 2-1  ረትቶ ጣፋጭ ድልን አስመዝግቧል። አርባምንጭ ተጋጣሚውን ሲረታ ሁለቱንም የድል ግቦች  ኤሪክ ካፓይቶ  ያስቆጠረ ሲሆን ለእዚህ ቡድንም  ጥሩ እንቅስቃሴን እያሳዩ ካሉት ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነውን እንዳልካቸው መስፍንን  አነጋግረነዋል።

የአርባምንጭ ከተማው አማካይ ሊጉ ላይ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን እያስመለከተን ሲሆን ከታላቅ ወንድሙ ሙሉዓለም መስፍን /ዴኮ/ ጋርም በተቃራኒነት ከአንዴም ሁለት ጊዜ የተጫወቱበትን ሁኔታ ልንመለከት ችለናል።

የአርባምንጩን እንዳልካቸው መስፍን  ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ አናግሮት የሰጠው ምላሽ በሚከተለው መልኩ ቀርቧል። ተከታተሉት።

 

ስለ ትውልድ እና እድገቱ

“በአርባምንጭ  ጬንጫ በምትባል አካባቢ  ነው ተወልጄ ያደግኩት”።

እግር ኳስ ተጨዋች የመሆን ፍላጎት ነበረህ?

“አዎን፤ አርአያዬም ወንድሜ ሙሉዓለም መስፍን /ዴኮ/ም ነበር፤ እሱ ሲጫወት እያየሁትም ነው ያደግኩት”።

የእግር ኳስ ተጨዋች ባትሆን ኖሮ

“ሁሌም  አህምሮዬ ላይ ያለው ኳስ  ተጨዋች ስለመሆን  ብቻ ስለነበር ሌላ ነገርን ፈፅሞ አስቤ አላውቅም፤ የእልሜንም ነው አሁን እያሳካው ያለሁት”።

በቤተሰባችሁ ከአንተ እና ሙሉዓለም ውጪ ሌላ ስፖርተኛ አለ?

“አለ፤ የእኔም ታላቅ ነው። አሁን ላይ ግን መጫወቱን አቁሟል”።

የእግር ኳስ ተጨዋች በመሆንህ ደስተኛ ነህ?

“በጣም እንጂ! ኳስ ሁሌም ደስተኛ የሚያደርግህም ስፖርት ነውና”።

አሁን ለምትገኝበት ደረጃ እበቃለሁ ብለህ ጠብቀህ ነበር?

“አዎን፤ ሁሌም ነው የማስበው ሰውም ጥሩ ደረጃ ላይ እንደምደርስ ይነግሩኝም ነበር። ያኔ እኔም እርግጠኛ የሆንኩበት ሁኔታዎች ስለነበሩ በርትቼ ሰርቼ ለእዚህ ለምገኝበት ደረጃ ልበቃ ቻልኩ”።

የልጅነት ዕድሜህ ላይ አሁን በምትጫወትበት የአማካይ  ስፍራ ላይ ነው ትጫወት የነበረው

“አይደለም፤ ያኔ  አጥቂ  ነበርኩ።  ወደ መሀል የመጣሁበትን አጋጣሚም አላስታውስም። በዚህ ስፍራ እንድጫወት ያደረገኝ ግን ቴዎድሮስ የሚባል አሰልጣኜ ነበር”።

የኳስ ጨዋታ ጅማሬህ ከየት የሚነሳ ነው?

“በሰፈር ደረጃ ከተጫወትኩ በኋላ በሀይስኩል ስማር ነው በደንብ አድርጌ  መጫወት የጀመርኩት። ከዛም እዛ ጬንጫ ወረዳ  ውስጥ አሞ ጬንጫ የሚባል ቡድን ነበርና ለክለቡ ተጫወትኩ።  ከዛም ወደ አርባምንጭ ዋናው ቡድን ዘንድሮ በመግባት ይኸው እየተጫወትኩ ነው”።

ቤተሰቦችህ በልጅነት ዕድሜህ  ኳሱን ስትጫወት ይፈቅዱልህ ነበር?

“አዎ፤  ሁሉም  ያበረታቱኛል። ለአንድም ቀን ወንድሞቼና እህቶቼን ጨምሮም  አትጫወት ብለው ከልክለውኝ አያውቁምም ነበር”።

ታላቅ ወንድምህ ሙሉዓለም ከኳሱ ውጪ በትምህርቱም ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሶ ተመርቋል፤ አንተስ?

“እኔ እስከ 12ተኛ ክፍል ደረጃ ብማርም ውጤት የለኝም።  አሁን ላይ  ግን ትምህርቴን በርቀት ደረጃ በመማር  አካውንቲንግን እየተማርኩ ነው”።

በእግር ኳስ ተጨዋችነት የት ደረጃ ላይ መገኘት ግብህ ነው?

“የእኔ ዓላማ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመመረጥ እና መለያውን በማጥለቅ ሀገሬን ማገልገል እና ለውጤትም ማብቃት  ነው፤ ከዛ ባለፈም ከሀገር ወጥቶ በመጫወት ኢትዮጵያን ማስጠራትም እፈልጋለሁ”።

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ቡድናችሁ እያደረገ ስላለው የውድድር ጉዞ ምን ትላለህ?

“ሊጉን በእዚህ ዓመት ብንቀላቀልም እያመጣነው ያለው ውጤት ግን አይገባንም። ከዚህ በላይ ውጤት ሊኖረን ይገባን ነበር። አሁን ላይ ግን እየበረታን እና እየተሻሻልን  ነው”።

ከቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ መውረድ ያሰጋችኋል? ያስፈራችኋል?

“ኸረ በፍፁም! የምን ስጋት ነው? አስበነውም አናውቅም”።

ሲዳማ ቡናን ስለረቱበት ጨዋታ

“ጫና ቢኖርብንም ግጥሚያው ጥሩ ነበር። ፈጣሪ ይመስገን ልናሸንፋቸው ችለናል”።

ድሉ ይገባቸው እንደሆነ

“ከእነሱ እንሻል ስለነበርን ነው ያሸነፍነው። ስለዚህም ውጤቱ ለእኛ ይገባናል”።

ስለ ተጋጣሚያቸው ሲዳማ ቡና

“በጨዋታው ጥሩ ይሆኑና  የሚዘናጉት ነገር ነበር። እኛ ደግሞ ያንን ክፍተታቸውን በመጠቀም ልናሸንፋቸው ችለናል”።

ከወንድምህ ሙሉዓለም ጋር በተቃራኒነት የመጫወቱን ዕድል አግኝተሃል፤ ስሜቱ ምን ይመስላል?

“በጣም ይከብዳል፤ ደስ ይላልም፤  ጨንቆኝም ነበር። ብቻ ይሄን ዕድል ስላገኘው ፈጣሪ ይመስገን”።

ሁለት ጊዜ ጥፋት ሰርቶብህም ነበር?

“አዎ፤ ወዲያው ግን  አይዞህ ነው ያለኝ”።

በአንድ ማሊያ ከእሱ ጋር ስለመጫወትን አታልምም?

“አለኝ እንጂ!  እርግጠኛ ነኝ አንድ ቀን የሚሳካም ይመስለኛል”።

ከባህርማዶ ተጨዋቾች የምታደንቀው?

“የክርስቲያኖ ሮናልዶ አድናቂ ነኝ”።

የእረፍት ጊዜህን በምን ታሳልፋለህ?

“ከቤተሰቦቼ ጋር ነው”።

ስለ አሰልጣኛቸው መሳይ ተፈሪ

“እሱ ይለያል። ሁሌም  አሸንፉ አሸንፉ ነው የሚለን። መሸነፍንና  አቻን አይፈልግም። ከማሸነፍ ውጪ ሌሎች ውጤቶች አያስደስተውም”።

ቤትኪንጉን ስትመለከት በጣም እያደነቅከው ያለው ተጨዋች ማን ነው?

“ይሄማ አያጠያይቅም የቡናዋ አቡኪ ለእኔ አንደኛ  ናት። እሱ ሀበሻ ተጨዋችም አይመስለኝም። ሁሌም ነው የማያት፤ ሁሌም ነው የማደንቃት”።

በእግር ኳስ ሜዳው ላይ ማሻሻል ስላለበት ነገር

“ክፍተቶች አሉብኝ። በተለይ ሹት ላይ ከዛ ውጪ ደግሞ ያለ ኳስ ባለኝ እንቅስቃሴም ላይ የሚጎድለኝ ነገር አለና ይህን በማረም የሀገሪቷ ትልቅ ተጨዋች መሆንን እፈልጋለሁ”።

ስናጠቃል

“በእግር ኳሱ አሁን ላይ ጅማሬ ላይ ነኝ። ብዙ የሚቀሩኝ ነገሮችም አሉ። እስካሁን ለመጣሁበት መንገድ ግን እዚህ ደረጃ ላይ እንድደርስ መጀመሪያ ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ። ከዛ ደግሞ በትጥቅም ሆነ በሌላ እንክብካቤያቸው በጣም የሚለዩብኝን ሁሉንም ቤተሰቦቼን፣  የቡድናችንን አሰልጣኞች  እና የተወለድኩበትን የጬንጫ የስፖርት አፍቃሪዎችንና ነዋሪዎችን እንደዚሁም ደግሞ የቡድኔን ጓደኞችንም አመሰግናለሁ”።

 

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P