በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/
የሸገር ደርቢ ታላቅና ተጠባቂ ጨዋታ
ቅ/ጊዮርጊስ vs ኢትዮጵያ ቡና
ነገ በ10፡00 ሰዓት
የቅ/ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ደጋፊዎች፣ እንደዚሁም ደግሞ የሁለቱም ቡድን ተጨዋቾችና የስፖርቱ ተመልካቾች በጉጉት የሚጠብቁት የሸገር ደርቢ ጨዋታ ነገ እሁድ ከ10 ሰአት ጀምሮ በርካታ የእግር ኳሱ አፍቃሪዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል፡፡
ቅ/ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና በሚያከናውኑት የነገው የሸገር ደርቢ ጨዋታም ከሌላው ጊዜ በበለጠ በርካታ የእግር ኳሱ አፍቃሪዎች ግጥሚያውን ይከታተሉታል ተብሎ በመጠበቅ ላይ ሲሆን የጨዋታው ባለሜዳም ቅ/ጊዮርጊስ መሆኑም ታውቋል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ክለቦች በፕሪምየር ሊጉ የውድድር ታሪክ ከ1991 ዓ/ም ጀምሮ በደርቢው ፍልሚያ የሁለት ዙር ጨዋታዎችን በማከናወን ሲገናኙ በእስከዛሬው የእርስ በርስ ግንኙነታቸው አብዛኛዎቹን ጨዋታዎች በማሸነፍ ቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነቱን የወሰደ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ስንመለከት የአቻ ውጤት የተመዘገበበት ውጤት ቁጥሩ ከሌላው ጊዜ ግንኙነታቸው አኳያ ከፍ ያለ ሆኖም ተመዝግቧል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ክለቦች ከእዚህ ቀደም የፊንፊኔ ደርቢ የሚል ስያሜን በኋላ ላይ ደግሞ የሸገር ደርቢ የሚል መጠሪያ የያዘውን ጨዋታዎቻቸውን ከማከናወናቸው በፊት በሁለቱም ቡድን ደጋፊዎችም ሆነ ተጨዋቾች በኩል ለግጥሚያው የሚሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር አንዳቸው አንዳቸውን አሸንፈው ለመውጣት እና ከጨዋታው በኋላም ቀኑን በፌሽታ እና በደስታ አጣጥመው ለመዋል ከፍተኛ ዝግጅትን የሚያደርጉበት ሁኔታን የተመለከትን ሲሆን የደርቢው ጨዋታ ከቅርብ ዓመታቶች ወዲህ በሜዳ ላይ ሲደረግ ግን የሁለቱም ቡድን ተጨዋቾች በደጋፊዎቻቸው እንደሚሰጣቸው የአማረ እና ድንቅ ድጋፍ የተመልካቹን የኳስ ስሜት የሚያረካ እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ባለመሆኑ ደርቢው በሜዳ ላይ ከሚታየው እንቅስቃሴ አንፃር አጓጊነቱ ያን ያህል የሚያስነግርለት አይደለምና በዚህ በኩል መሻሻል እንዳለበትም በሁሉም ዘንድ እየተነገረም ይገኛል፡፡
የቅ/ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ክለቦች የነገው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ላይስ በግጥሚያው ምን ያሳዩን ይሆናል? በደርቢው ጨዋታ ዙሪያና ተያያዥ የሆኑ ጥያቄዎችን ከሁለቱ ቡድን ተጨዋቾች መካከል ከቅ/ጊዮርጊስ ተከላካዩን አስቻለው ታመነን እና አጥቂውን አቤል ያለውን ከኢትዮጵያ ቡና ወገን ደግሞ አማካዮቹን አማኑኤል ዩሃንስንና ሳምሶን ጥላሁንን አናግረናቸው ምላሻቸውን ሰጥተውናል፤ እንደሚከተለውም ይቀርባል፡፡
“በተላበስነው የአሸናፊነት መንፈስ ቅ/ጊዮርጊስን ድል እናደርጋለን”
አማኑኤል ዮሃንስ /ኢትዮጵያ ቡና/
ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲን ከሸገር ደርቢው ጨዋታ በፊት ድል ስለማድረጋቸውና በስታዲየም ውስጥ ስለነበረው ድባብ
“የሸገር ደርቢውን ጨዋታ ከማድረጋችን በፊት ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲን ልናሸንፋቸው የቻልንበት ዋናው ምክንያት ባለፈው ግጥሚያችን አዳማ ከነማን በመርታታችንና ወደአሸናፊነቱም መንፈስ ስለተመለስን ይህን የሜዳችን ላይ ጨዋታን ማሸነፍ መቻል ወደዋንጫው ለሚኖረን ግስጋሴ የሚረዳን ስለሆነ ግጥሚያውን በስኬት ለማጠናቀቅ የቁርጠኝነት ስሜትን ይዘን ስለገባን የግጥሚያው አሸናፊ ልንሆን ችለናል፤ በስቴድየም ላይ ስለነበረው ድባብ ደግሞ መናገር የምፈልገው ደጋፊዎቻችን ሙሉውን 90 ደቂቃ ከእኛ ጋር ነበሩ፤ ጥሩ ድጋፋቸውንም ሲሰጡን ታይተዋልና ይሄ ሊቀጥል የሚገባው ነው”፡፡
ኢትዮጵያ ቡና የሰሞኑ ተከታታይ ጨዋታውን ድል እያደረገ የሚገኘው የፍፁም ቅጣት ምት ጎል እያስቆጠረ ስለመሆኑና በጨዋታ ላይ በሚገኙ ኳሶች ጎሎችን እያስቆጠረ አለመሆኑ
“በሊጉ የሰሞኑ ጨዋታዎቻችን ላይ እንደ ቡድኑ ተጨዋችነቴ መናገር የምፈልገው ክለባችን በጨዋታ የሚገኙ እድሎች ላይ ጎል በማስቆጠሩ በኩል ድክመት አለብን፤ ያገኘናቸውንም የግብ አጋጣሚዎች ያለመጠቀማችን እንደደካማ ጎንም እናየዋለን፤ ሰሞኑንም ልምምድን ስንሰራ የነበረው በእዚህ ችግራችን ላይም ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን የፍፁም ቅጣት ምት /ፔናሊቲም/ ለማግኘት የማጥቃት እንቅስቃሴያችን ላይ ትኩረት አድርገን በመስራታችን ያ ሊጠቅመንና በእዚያም እድል ተጠቅመን ጎሎችን እንድናስቆጥርም አድርጎናል፤ ከዚህ በኋላ የሚኖሩ ግጥሚያዎች ላይ ደግሞ የበለጠ ጠንክረን ሰርተን በመምጣት በጨዋታ ላይ የሚገኙ ተጨማሪ ጎሎችንም የምናስቆጥርበት ስልትም ስለሚኖረን በጣም ጠንካራና የተሻለ የሆነውን ቡድንም ይዘን እንደምንመጣ እርግጠኞች ነን”፡፡
ከቅ/ጊዮርጊስ የምታደርጉት ታላቁ የሸገር ደርቢ ጨዋታ እሁድ ይደረጋል፤ ይህን ጨዋታ እንዴት ነው የምትጠብቀው? ማንስ የጨዋታው አሸናፊ ይሆናል?
“ኢትዮጵያ ቡናና ቅ/ጊዮርጊስ የሚያደርጉት የሸገር ደርቢው ጨዋታ በስታዲየም ውስጥ ከሚታየው ድባብ አንፃር ሁሌም ለየት የሚልና የሚያምር ቢሆንም በሜዳ ላይ ከሚታየው የጨዋታ እንቅስቃሴ አንፃር ግን ለግጥሚያው እኔ የተለየ ግምትን አልሰጠውም፤ ያም ሆኖ ግን ይህን የደርቢ ጨዋታ ሁሌም ክለባችን የሚጠብቀው በተደጋጋሚ ጊዜ ያለበት ደካማ ጎኑ ላይ በመስራት እንጂ ተጋጣሚውን በመፍራት አይደለም፤ ኢትዮጵያ ቡና ሁሌም ተጋጣሚዎቹን የሚያከብር በመሆኑም አሁን ካለን እና ከተላበስነው የአሸናፊነት መንፈስ አንፃር የነገውን ጨዋታም አሸንፈን ነው ከሜዳ የምንወጣው”፡፡
የሁለቱ ክለቦች የሸገር ደርቢ ጨዋታ ላይ ስላለህ ትውስታ
“ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር የሚኖረን የሸገር ደርቢ ጨዋታዎች ሁሌም ብዙ ትውስታዎች ያሉት ቢሆንም የመጀመሪያ ቀን ላይ የምታደርገው ግጥሚያ ግን መቼም ቢሆን ከአዕምሮህ አይጠፋም፤ የእኔንም የመጀመሪያዬን የደርቢ ጨዋታ በፍፁም አልረሳውም፤ ያኔ ስቴድየሙ ሙሉ ሆኖ ድባቡ ያምር ነበር፤ የሁለታችንም ክለብ ደጋፊዎች ቡድኖቻቸውን በጥሩ ሁኔታ በማበረታታት ግጥሚያው የተጠናቀቀበትን ሁኔታ አስታውሳለሁ”፡፡
የቅ/ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡናን የሸገር ደርቢ ጨዋታ ከስፖርታዊ ጨዋነት መከበር አንፃር አስተያየትህን ብትሰጥበት እና የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሜዳ ላይ የጨዋታ እንቅስቃሴ ያንን ያህል ጥሩና ማራኪ ፉትቦል የሚታይበት ስላለመሆኑ
“የእሁዱን የደርቢ ጨዋታ አስመልክቶ ግጥሚያው በሰላም እንዲጠናቀቅ በሜዳ ላይ ለሚኖረው የስፖርታዊ ጨዋነት መከበር ትልቁን አስተዋፅኦና ድርሻ ልንወስድ የሚገባን የሁለታችንም ቡድኖች ተጨዋቾች ነን፤ በጨዋታው ላይ ማንኛውም ደጋፊ ስሜታዊ ሆኖ የሚታየው እኛ ተጨዋቾች በሜዳ ላይ በምናሳየው ባህሪይ ነው፤ ስለዚህ እንደተጨዋችነታችን ደጋፊውን የሚያነሳሳ ነገር ባናደርግ እና ኳሱን ብቻ በመጫወት ተመልካቹ የሚፈልገውን ጥሩ ነገር በሜዳ ላይ አሳይተን ብንወጣ ጥሩ ነው፡፡ በእዚህ በኩል በቡና ወገን እንደካፒቴንነቴ ለተጨዋቾቻችን ይህንን መልዕክት አስተላልፋለሁ፡፡ የሁለታችን የደርቢ ጨዋታን አስመልክቶ ብዙ ጊዜ ግጥሚያው ጥሩ ፉክክር የማይደረግበት ሁኔታ የእውነት ነው፤ ለዛ በምክንያትነት የሚቀመጠውም ጨዋታው ውጥረት ስለሚበዛበት እና አንዱም በአንዱ መሸነፍን አጥብቆ ስለሚጠላ ነውና ተመልካቹ በኳሱ ረክቶ የሚወጣበት ሁኔታ እየታየ አይደለም፤ የነገው ጨዋታ ላይ ግን የስፖርት ቤተሰቡም ሆነ ደጋፊዎቻችን በጨዋታችን የሚደሰቱበት እንቅስቃሴን ለማሳየት የምንችለውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን”፡፡
ቅ/ጊዮርጊስ ካለው ወቅታዊ አቋም አንፃር በደርቢው ጨዋታ የምትፈሩት ነገር አለ?
“ይቅርታ አድርግልኝና በእኔ በኩል ምንም የምፈራው ነገር የለም፤ የቡድናችንም ተጨዋቾች አይፈሩም”
በሸገር ደርቢው ጨዋታ ከአንተ ምን ይጠበቅ?
“የእግር ኳስ ጨዋታ የቡድን ስራ እንደሆነ ባምንም የደርቢው ጨዋታ ላይ እንደቡና ተጨዋችነቴ በሜዳ ላይ ማድረግ ያለብኝን ነገር ሁሉ አደርጋለሁ፤ ከቅ/ጊዮርጊስ በምናደርገው የነገ ጨዋታ ወደ ሜዳ የምንገባው ግጥሚያውን ለማሸነፍ ነው፤ በእዚህ ሚና ውስጥም እንደ ተጨዋችነቴ ክለቤ አሸናፊ ሊሆን እንዲችል የሚጠበቅብኝን ነገር ሁሉ አደርጋለሁ”፡፡
ከቅ/ጊዮርጊስ የሚደረግ ጨዋታን ማሸነፍ መቻል የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ለማንሳት ወሳኝ ነው ትላለህ?
“እንደ ራሴ አመለካከት የሻምፒዮና ቡድን ሁሌም ውጤታማ የሚሆነው ከፊት ለፊቱ ያሉበትን እያንዳንዳቸውን ጨዋታዎች ሲያሸንፍ እንጂ ቅዱስ ጊዮርጊስን ብቻ ስለረታ አይደለም፤ የነገው የደርቢ ጨዋታችንን ከማድረጋችንም በፊት እናስብ የነበረው ወልዋሎን እንዴት አድርገን እናሸንፋለን ብለን ነበር ወደ ሜዳ የገባነውና ስናስብ የነበረው፤ ይሄን ጨዋታም አሸንፈናል፤ አሁን ደግሞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለብንን ጨዋታ በማሸነፍ አጠቃላይ ውጤቱን ወደፊት በጋራ አብረንም ነው የምናየውና ለሌሎቹም ግጥሚያዎች እየተዘጋጀን ነው የሚገኘው”፡፡