test
Google search engine

የሸገር ደርቢ ታላቅና ተጠባቂ ጨዋታ | አስቻለው ታመነ /ቅ/ጊዮርጊስ/

 

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/

የሸገር ደርቢ ታላቅና ተጠባቂ ጨዋታ
ቅ/ጊዮርጊስ vs ኢትዮጵያ ቡና

ነገ በ10፡00 ሰዓት
የቅ/ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ደጋፊዎች፣ እንደዚሁም ደግሞ የሁለቱም ቡድን ተጨዋቾችና የስፖርቱ ተመልካቾች በጉጉት የሚጠብቁት የሸገር ደርቢ ጨዋታ ነገ እሁድ ከ10 ሰአት ጀምሮ በርካታ የእግር ኳሱ አፍቃሪዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል፡፡
ቅ/ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና በሚያከናውኑት የነገው የሸገር ደርቢ ጨዋታም ከሌላው ጊዜ በበለጠ በርካታ የእግር ኳሱ አፍቃሪዎች ግጥሚያውን ይከታተሉታል ተብሎ በመጠበቅ ላይ ሲሆን የጨዋታው ባለሜዳም ቅ/ጊዮርጊስ መሆኑም ታውቋል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ክለቦች በፕሪምየር ሊጉ የውድድር ታሪክ ከ1991 ዓ/ም ጀምሮ በደርቢው ፍልሚያ የሁለት ዙር ጨዋታዎችን በማከናወን ሲገናኙ በእስከዛሬው የእርስ በርስ ግንኙነታቸው አብዛኛዎቹን ጨዋታዎች በማሸነፍ ቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነቱን የወሰደ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ስንመለከት የአቻ ውጤት የተመዘገበበት ውጤት ቁጥሩ ከሌላው ጊዜ ግንኙነታቸው አኳያ ከፍ ያለ ሆኖም ተመዝግቧል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ክለቦች ከእዚህ ቀደም የፊንፊኔ ደርቢ የሚል ስያሜን በኋላ ላይ ደግሞ የሸገር ደርቢ የሚል መጠሪያ የያዘውን ጨዋታዎቻቸውን ከማከናወናቸው በፊት በሁለቱም ቡድን ደጋፊዎችም ሆነ ተጨዋቾች በኩል ለግጥሚያው የሚሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር አንዳቸው አንዳቸውን አሸንፈው ለመውጣት እና ከጨዋታው በኋላም ቀኑን በፌሽታ እና በደስታ አጣጥመው ለመዋል ከፍተኛ ዝግጅትን የሚያደርጉበት ሁኔታን የተመለከትን ሲሆን የደርቢው ጨዋታ ከቅርብ ዓመታቶች ወዲህ በሜዳ ላይ ሲደረግ ግን የሁለቱም ቡድን ተጨዋቾች በደጋፊዎቻቸው እንደሚሰጣቸው የአማረ እና ድንቅ ድጋፍ የተመልካቹን የኳስ ስሜት የሚያረካ እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ባለመሆኑ ደርቢው በሜዳ ላይ ከሚታየው እንቅስቃሴ አንፃር አጓጊነቱ ያን ያህል የሚያስነግርለት አይደለምና በዚህ በኩል መሻሻል እንዳለበትም በሁሉም ዘንድ እየተነገረም ይገኛል፡፡
የቅ/ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ክለቦች የነገው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ላይስ በግጥሚያው ምን ያሳዩን ይሆናል? በደርቢው ጨዋታ ዙሪያና ተያያዥ የሆኑ ጥያቄዎችን ከሁለቱ ቡድን ተጨዋቾች መካከል ከቅ/ጊዮርጊስ ተከላካዩን አስቻለው ታመነን እና አጥቂውን አቤል ያለውን ከኢትዮጵያ ቡና ወገን ደግሞ አማካዮቹን አማኑኤል ዩሃንስንና ሳምሶን ጥላሁንን አናግረናቸው ምላሻቸውን ሰጥተውናል፤ እንደሚከተለውም ይቀርባል፡፡
“ቡናዎችን የግብ ክልላችን ጋር ሳናደርስ እናሸንፋችኋለን”
አስቻለው ታመነ /ቅ/ጊዮርጊስ/
የቅ/ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡናን የሸገር ደርቢ ጨዋታ እንዴት እየጠበቅከው ነው?
በጨዋታውስ ምን ውጤት ታስመዘግባላችሁ?
“የኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚኖረን የነገው ጨዋታ የሃገሪቱ ትልቅ ደርቢ ከመሆኑ ባሻገር ይሄን ግጥሚያ የምናደርገው የቡድናችን አቋም እና ውጤትም ጥሩ ባልሆነበት ወቅት ስለሆነ ግጥሚያውን የምንጠብቀው በከፍተኛ ጉጉት ነው፤ ይህን ጨዋታም ለማሸነፍ ተዘጋጅተናል፤ ከቡና ጋር የሚኖረን የነገው ጨዋታም ሁለታችንም ሰሞኑን ባደረግናቸው የተስተካካይ ጨዋታዎች ድል አድርገን የምንገናኝበትም ስለሆነ ከፍተኛ ፉክክርም እንደሚታይበት እርግጠኛም ነኝ”፡፡
የቅ/ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና የደርቢ ጨዋታ በጉጉት ተጠብቆ ደጋፊውና የስፖርት ቤተሰቡ ጥሩ ጨዋታን በሜዳ ላይ እየተመለከተ አለመሆኑ
“ይሄ እውነት ነው፤ ብዙ ጊዜ የደርቢው ጨዋታ ላይ የሁለታችንም ቡድን ተጨዋቾች በሜዳ ላይ ህዝቡ የሚፈልገውን እና ከእኛ የሚጠበቀውን ነገር አናሳየውም፤ ይሄ ሊሆን የቻለው ግጥሚያውን ለማሸነፍ ካለን ጉጉት እና ደጋፊዎቻችንንም አሸንፈን ለማስደሰት በሚል ከፍተኛ ምኞትም ስላለን ነው፤ ለእዚህም ነው ጥሩ ጨዋታን የማናሳየው፤ የነገው የደርቢ ጨዋታ ላይ ግን እንደከዚህ ቀደሙ ግጥሚያው ፈፅሞ አሰልቺ አይሆንም፤ በሁለታችንም መካከል መሸናነፍ የሚኖርበት ግጥሚያም ነው የሚሆነው፤ በዚህ የደርቢ ጨዋታም አሁን ላይ እኛ ጋር ካለው ጥሩ መሻሻል እና ጥሩ ነገርንም ለመስራት ከምናከናውነው ዝግጅት አንፃር በተጋጣሚያችን ላይ የኳስ ብልጫን ወስደን እና ጥሩ ጨዋታን ተጫውተን ተመልካቹን በጨዋታ እንቅስቃሴ ለማስደሰትና ግጥሚያውን በማሸነፍም ደጋፊዎቻችንን ለማስደሰት በዝግጅት ላይ ነው የምንገኘው”፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ጋር በሚኖራችሁ የሸገር ደርቢው ጨዋታ እነሱ ካላቸው አቋም በመነሳት የሚያሰጋችሁ ነገር አለ?
“የኢትዮጵያ ቡናን በምንገጥምበት የነገው የደርቢ ጨዋታችን ላይ አሁን እየሰራን ካለው የታክቲክ ልምምድ አኳያ እነሱ ለእኛ ምንም አይነት ስጋት አይሆኑብንም፤ ቡና ባለፉት ሁለት ጨዋታዎቹ ግጥሚያውን አሸንፎ የወጣው በፍፁም ቅጣት ምቶች ጎል ነው፤ ስለዚህም የእነሱን ወደ ተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል ጋር የሚደርሱበትንም ሆነ የፍፁም ቅጣት ምትም በማግኘት ግብ ሊያስቆጥሩ የሚችሉበትንም ሁኔታ በደንብ እያወቅንና እየተገነዘብንም ስለሆነ የደርቢው ጨዋታ ላይ የእነሱ አጥቂዎችም ሆኑ ሌሎች ተጨዋቾቻቸው በፍፁም የጎል ክልላችን ጋር እንዳይደርሱ እና የፍፁም ቅጣት ምትም እንዳያገኙ እናደርጋቸዋለንና በዚሁ በመጠቀም ጨዋታውን እኛ በምናስቆጥረው ግብ አሸንፈን እንወጣለን”፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ጋር በሚኖራችሁ የነገው የደርቢ ጨዋታ ከአንተ ምን ይጠበቅ?
“የሸገር ደርቢው ጨዋታ ላይ ለክለቤ ሁሌም ቢሆን እንደቡድን በጋራ በመንቀሳቀስ እጠቅመዋለው እንጂ በግሌ ብቻ የተለየ ነገርን ፈፅሞ አደርጋለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም፤ ቡድናችን ብዙ ጊዜ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ስኬታማ ሆኖ የሚታየው እንደቡድን ስለሚንቀሳቀስ ነው፤ በእዚያ ውስጥ ሆኜ ግን ከራሴ የሚጠበቅብኝን ግልጋሎት ለቡድኔ እሰጣለው፤ በእነዚህ መካከል የኋላ የተከላካይ መስመሩን የምመራው እኔ ስለሆንኩም ከቡና ጋር በሚኖረው የደርቢ ጨዋታ ላይ እነሱ ፔናሊቲ እንዳያገኙ የሚቻለኝን ሁሉ ጥረት በማድረግ ቡድኔ የጨዋታው አሸናፊ እንዲሆንም አድርጋለው”፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና የቅ/ጊዮርጊስ የሸገር ደርቢ ጨዋታ ላይ ግጥሚያው በሰላም እንዲጠናቀቅ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር በተያያዘ ምን መደረግ አለበት ትላለህ?
“የሸገር ደርቢው ጨዋታ ላይ ብቻ ሳይሆን በሃገራችን የሚከናወኑ የተለያዩ የእግር ኳስ ውድድሮችን በተመለከተ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር በተያያዘ በሚዲያም ሆነ በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ ብዙ ተብሏል፤ እንዲህ ተነግሮ ችግሩ እስካሁን ድረስ ሊቀረፍ አልቻለም፤ ይሄ መሆኑ ደግሞ የሃገሪቱን እግር ኳስ በጣም ሊጎዳው ችሏልና በእዚህ ላይ ችግሩን ከማቅለል አንፃር ብዙ ስራ ሊሰራ የገባል፤ የሸገር ደርቢውን የነገ ጨዋታ በተመለከተ የሁለታችንም ክለብ ደጋፊዎች ጨዋታው በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ የተነጋገሩበት ነገር እንዳለ በተለያዩ ድረ ገፆች ላይ የተመለከትንበት ሁኔታ ስላለ ይሄ እሰየው ያስብላል፤ የተነጋገሩበት ነገርም ዜና ብቻ ሆኖ መቅረትም የለበትምና የነገውን ጨዋታ ማንም አሸነፈ የተሸነፈው ቡድን ውጤቱን በፀጋ ተቀብሎ ከሜዳ መውጣት አለበትና ጨዋታው በስፖርታዊ ጨዋነት እንዲጠናቀቅ ምኞቴ ነው”፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚኖረው የነገው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ለክለቡ በጣም ወሳኝ ነው?
“ለቅ/ጊዮርጊስ ወሳኝ የሚሆኑት ግጥሚያዎች ዓመቱን ሙሉ የሚከናወኑት ናቸው፤ ለእዛም ነው ሁሌም ለጨዋታዎቹ እኩል ግምትን ሰጥቶ ባለድል የሚሆነው ፤ የነገውን ግጥሚያ በተመለከተ ደግሞ ለመናገር የምፈልገው ሁለቱ ክለቦች ካላቸው ብዙ ደጋፊ አንፃር የተቀናቃኝነት ስሜት ስላለና አንዱ በአንዱም መሸነፍን አጥብቆም ስለሚጠላ ጨዋታው በወሳኝነቱ አቻ የማይገኝለት ነው፤ ይህ ጨዋታ በተለይ እኛ ካሸነፍን ወደዋንጫ ወደ ምንጓዝበትም መንገድ ይበልጥ ያመጣናልና ጠንክሮ የሚመጣብንን ቡና ለማሸነፍ በሙሉ ዝግጅት ላይ እንገኛለን”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

P